በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ብሔርን መሠረት አድርጎ የቀረበው ውንጀላ እና በብሔራቸው ምክንያት ቀርቦባቸው የነበረውን የይነሱልን ጥያቄ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አጣሪ ኮሚቴ ተመዶቦ አጣርቶ ያቀረበውን ሙሉ ሪፖረት ይፋ ተደረገ

መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በኢትዮጵያ ከሚገኙ ገዳማትና አድባራት ቀዳሚ ሥፍራ ይዞ የሚገኝ ታላቅ የቱሪስት መስህብ ካቴድራል ነው፡፡ካቴድራሉ አጠቃላይ 300 ልዩ ልዩ ሠራተኞች ሲኖሩት ልማታዊ ከሚባሉ ገዳማትና አድባራትም የመጀመሪያው ሥፍራ ይዞ ይገኛል፡፡

ይህን ያልተዋጠላቸው ፖለቲካዊ ተልዕኮ የተሰጣቸው የሰንበት ት/ቤት አባላት ነን የሚሉ የነውጥ ኃይሎችና በጣት የሚቆጠሩ የካቴድራሉ ሠራተኞች ጋር በመሆን ከቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮና ቀኖና ውጭ የቤተ ክርስቲያኒቱን መዋቅር በመጣስ መሰል ተልዕኮ ከተሰጣቸው ጥቂት ጳጰሳትና መሰሎቻቸው ጋር ኔትዎርክ በመዘርጋት ቀለማችሁ አላማረንም በማለት የውሸት ክስ በመክሰስና በቤተ ሰዎቻቸው ሚዲያ ላይ ስም በማጥፋትና የውሸት ቃለ ጉበኤ ከማዘጋጃት ጀምሮ ብዙ ትርምስ ሲፈጥሩ ከቆዩ በኋላ የዘር ጥላቻ ከሳቸውን ወደ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ወስደውት እንደነበር ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ የአጥቢያ ጉዳይ የሚታየው በወረዳ በል ካለም ደግሞ በሀገረ ስብከት ደረጃ ሲሆን ይህን ሁሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ተጥሶ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ከፍተኛ እውቀትና የቤተ ክርስቲያን ልጅነት ያላቸው የኮሚቴ አባላት ጉዳዩን እንዲያጣሩት ተደርጎ ቤተ ክርስቲያኒቱን ብቻ ማዕከል አደርገው ፍጹም የክርስትና ሕይወት በተሞላበትና ከፍተኛ ሙያዊ ብቃት ታክሎበት ከ584 በላይ ዶክሜንት፣ 22 ገጽ ያለው የጽሑፍ ሪፖረት ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ቀርባል፡፡የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ አባላትም በጉዳዩ ላይ በጣም እንዳዘኑና ቤተ ክርስቲያን ወዴት እየሄደች ነው የሚል ሐሳብ እንደተናገሩ እስታውሳለን፡፡

የዚሁ ትልቅ መነሻም የካቴድራሉ ሰንበት ት/ቤት ነን የሚሉ ግን ያልሆነ ጥቂት ጎረምሶች ከ300,000 ብር በላይ ከካቴድራሉ በመዝረፋቸውና ለድብቅ ፖለቲካ ዓላማቸው ብለው ካቴድራሉ የማያወቀው የባንክ አካውንት በመክፈታቸው የተነሳ ነበር፡፡
ከዚህ ቀጥሎ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አጣሪ ኮሚቴ ተጣርቶ ያቀረበውን ሙሉ ሪፖረት እንደሚከተለው ይቀርባል ፡፡

መልካም ንባብ

ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን
ቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት
አዲስ አበባ

ጉዳዩ፡- በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የተፈጠረውን አለመግባባት አስመልክቶ ያደረግነው የማጣራት ሪፖርት ማቅረብን ይመለከታል፡፡
መግቢያ፡-
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የተፈጠረውን አለመግባባት አስመልክቶ ግንቦት 21 ቀን 2011 ዓ/ም ባደረገው መደበኛ ስብሰባ በጉዳዩ ላይ ሠፊ ውይይት ከተደረገ በኋላ ዝርዝር ጉዳዩ ተጣርቶ እንዲቀርብ ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት ከቅዱስ ሶኖዶስ ጽ/ቤት በቁጥር 276/34/2011 በ22/09/2011 ዓ/ም በተጻፈ ደብዳቤ ዝርዝር ጉዳዩን አጣርተን ሪፖርት እንድናቀርብ በታዘዘው መሠረት የቀረበ ሪፖርት ሲሆን፤ በትዕዛዙም መሠረት ግራ ቀኙ የጉዳዩ ባለቤቶች በተገኙበት በግልጽ የውይይት መድረክ የማጣራት ሥራውን አከናውነን እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡

1.የማጣራት ሥራውን ያከናወንበት መንገድ
1.የምደባ ደብዳቤው እንደደረሰን ከአመልካቾች የቀረበውን አቤቱታና ከካቴድራሉ የቀረበውን ምላሽ ዝርዝር ዶክሜንት ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ተረክበናል፡፡

2.ለማጣራት ከተመደብነው ልዑካን መካከል አንዱ የሆኑት መጋቤ ጥበብ ምናሴ ወ/ሃና ለቅድመ ውይይት ሊገኙ ባለመቻላቸው ለቅርብ አለቃቸው ለብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ በመንገር በስልክ አመራር እንዲሰጡልን አስደርገናል፡፡
3.ግራ ቀኙ የጉዳዩን ባለቤቶች ለማጣራት ሥራው እራሳቸውን አዘጋጅተው እንዲቀርቡ ቀኑን ወስነን አስቀድመን ጥሪ አስተላልፈናል፡፡

4.በግራ ቀኙ መካከል በውይይት ወቅት ግጭት እንዳይከሰት በመስጋት ከአራት ኪሎ አካባቢ ፖሊስ ጽ/ቤት አካባቢውን የሚቆጣጠሩ 2 የፖሊስ አባላት አስመድበናል፡፡

5.አሁን ካለው የሚስጥር መጠበቅ ችግር ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ከአጣሪዎች ጀምሮ ሁሉም የውይይቱ ተሳታፊዎች ማንኛውም ዓይነት የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን በተዘጋገው ቦታ አስቀምጠው ባዶ እጃቸውን እንዲገቡ በማስደረግ የማጣራት ሥራው ጤናማና ሰላማዊ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት አድርገናል፡፡

6.የማጣራት ሥራው የበለጠ ተዓማኖነት እንዲኖረው በማሰብ ከኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ መገናኛ ብዙኃን ድርጅት አንድ ካሜራ ማን በማስመደብ ሙሉ የማጣራት ሥራው በቪዲዮ እንዲቀረጽ አድርገናል፡፡

7.ምንም እንኳ ከላይ አንደገለጽነው በተያዘው ቀን ቀጠሮ መሠረት ሁላችን አጣሪዎችና ግራ ቀኙ ባለጉዳዩ በሰዓቱ በቦታው ብንገኝም አንደኛው አጣሪ መ/ጥበብ ምናሴ ወ/ሃና ሊገኙ ባለመቻላቸው የተወሰነ ጊዜ ከጠበቅናቸው በኋላ የምደባውን ደብዳቤ ለፈረሙት ለብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ጉዳዩን በስልክ ያስረዳን ሲሆን ጉዳዩ አስቸኳይ ስለሆነ ሁለታችሁ ማጣራቱን ቀጥሉ በማለት በሰጡት የቃል አባታዊ አመራር መሠረት፤
1ኛ. በአፈ መምህር አባ ገ/ሥላሴ ጌትነት፤
2ኛ. በሊቀ ኅሩያን ሰርጸ አበበ አማካኝነት የማጣራት ሥራው ተከናውኗል፡፡

2.በማጣራት ሥራው የተሳተፉ አካላት በተመለከተ፤
1.በከሳሽ የቀረቡት የካቴድራሉ የቢሮ ሠራተኞችና አገልጋዮች እንዲሁም የሰንበት ት/ቤት አባላት፤
2.ተከሳሽ የሆኑት የካቴድራሉ አስተዳደር ሠራተኞ በሙሉ በማጣራት ሥራው ላይ በግራ ቀኙ ስምምነት እንዲገኙ አድርገናል፡፡

3.የማጣራት ሒደቱም በመጀመሪያ በጽሑፍ የቀረበው አቤቱታ በንባብ ከተሰማ በኋላ ተጨማሪ የቃል አቤቱታም ካለ እንዲጨምሩ ለከሳሾች ዕድል በመስጠትና ለእያንዳንዱ የፅሑፍም ሆነ የቃል አቤቱታ ከሳሾች ያላቸውን የሰነድና የሰው ማስረጃ እንዲሠሙ ዕድል በመስጠት ዝርዝር አቤቱታቸውን እንዲያብራሩ ተደርጓል፡፡

4.በመቀጠል ለቀረበው አቤቱታ ተከሳሽ የሆኑት የካቴድራሉ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎ በማስረጃ አስደግፈው መልስ እንዲሰጡበት አድርገናል፡፡

5.ያለምንም አድልዎና ገደብ ግራ ቀኙ ያላቸውን ማስረጃ እንዲያቀርቡ ተደርጓል፡፡
በመሆኑም ከላይ በተዘረዘረው መሠረት በከሳሾች የቀረበውን አቤቱታና የተከሳሾችን መልስ ካቀረቡት መረጃና መ፣ስረጃ ጋር አቀናጅተን እንደሚከተለው በዝርዝር አቅርበናል፡፡
3.የቀረበው የማጣራት ሪፖርት በቅደም ተከተል፤
1.በካቴድራሉ ቀደም ሲል በልዩ ልዩ የሥራ መደብ ሠራተኛ ይቀጠርና ይመደብ የነበረው በኢትዮጵያዊነት መሥፈርት የነበረ ቢሆንም አሁን ግን የሚመደበው የአንድ ብሔር ብቻ ነው፤ በማለት የቀረበውን አቤቱታ እነማን እንደሆኑ በከሳሾች እንዲያብራቡ እድል ተሰጥቷቸው፤
1.1ዲ/ን ብሩህ ሁኔ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በዝውውር ወደ ካቴድራል ተመድበው ቢመጡም ብሔራቸውን መሠረት ተደርጎ አንቀበልም ብለው መልሰው ነገር ግን በብሔር መ/ገነት ይትባረክ በርሄን በአዲስ በጀት ቀጥረዋል በማለት ከሳሾች ያስረዱ ሲሆን፤
ተከሳሾች በሰጡት መልስ ዲ/ን ብሩህ ሁኔ አስቀድሞ በደጅ ጠኚነት ለተወሰነ ጊዜ በካቴድራሉ የነበረ መሆኑን ጠቅሰው ነገር ግን በወቅቱ የነበረበትን የሥነ ምግባር ችግርና የሙያ እውቀት/ውስንነት ስለምናውቅ ነው ለሀገረ ስብከቱ ሌላ ሙያ ያለው ማንኛውም መነኩሴ ይመደብልን ብለን ምላሽ የሰጠነው እንጂ ብሔርን መሠረት አድርገን አይደለም፡፡ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሳሾች እንደገለጹት መ/ገነት ይትባረክ በርሄን ልንቀበላቸው የቻልነው በብሔር ሳይሆን ግለሰቡ ይኖሩ የነበሩት በምስራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሲሆን ከ1986 ዓ/ም ጀምሮ ለ24 ዓመት በልዩ ልዩ የሥራ ኃላፊነት ሲያገለግሉ ቆይተው ወቅቱ ባመጣው ግጭት ምክንያት በተለያዩ ጊዜያት ፈተና ሲደርስባቸው ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ከብፁዕ አቡነ ሰላማ በቁጥር 2/1509/556/10 በ09/09/2012 ዓ/ም በአድራሻ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የተጻፈ መሸኛ ደብዳቤ ይዘው መጥተው አቤቱታ በማቅረብ በሙያቸው ተመድበው እንዲሩ ቅዱስነታቸው ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በሰጡት አባታዊ መመሪያ መሠረት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትም በቁጥር 1246/9/2011 በ05/02/2011 ዓ/ም በተጻፈ ደብዳቤ የቅዱስ አባታችን መመሪያ መሆኑን በመጥቀስ በአንድ ሰው ተደርቦ ተይዞ በነበረው የዕቅድና ልማት ክፍል የሥራ መደብ መድበን እንድናሠራ በታዘዘው መሠረት ተቀብለን የመደብናቸው እንጂ እንደ ክስ አቀራረቡ በአድሎና በብሔር አለመሆኑን የሰነድ ማስረጃ በማቅረብ አስረድተዋል፡፡

እኛም አጣሪዎች የምስራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት የጻፏቸውን ደብዳቤዎች በማየት ያረጋገጥን ሲሆን ዲ/ን ብሩህ ሁኔን ለካቴድራሉ የሚመጥን ሙያ የለውም በማለት የመለሱት መሆኑን ተረጋግጧል፡፡ ለማስረጃም 3 ገጽ ፎቶ ኮፒ ተያይዟል፡፡

2.ከሳሾች ውጤታማ የካቴድራሉ ሠራተኞች በማንነታቸው ብቻ ዝቅተኛ ቦታ በመመደብ በአንጻሩ ምንም ችሎታ የሌላቸውን ግለሰቦች በተደራራቢ የሥራ መደብ ሁለትና ሦስት ደመወዝ እንዲያገኙ ተደርጓል በማለት ያቀረቡትን እነማን እንደሆኑ እንዲያብራሩ ተጠይቀው፤ ሁለትና ሦስት ደመወዝ የሚበላ አለመኖሩን በቀረበው የሰነድ ማስረጃ ተረጋግጧል ::

3.የካቴድራሉ ሠራተኛ ለአባይ ግድብ የ1 ወር ደመወዙን በ2003 ዓ/ም ከፍሎ የጨረሰ ቢሆንም በወቅቱ ባንክ መግባት ሲገባው ለ5 ዓመት በግለሰብ እጅ ቆይቶ በ2008 ዓ/ም ባንክ እንደገባ ተደርጎ ለሠራተኛው ሰርተፍኬ ተሰጥቷ ተብሎ ለቀረበው ክስ የካቴድራሉ ሒሳብ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ሣራ ገ/ሥላሴ በሰጡት መልስ፡- ከሳሾች ያለ ማስረጃ እንዲሁ በጥቻ ያቀረቡት ክስ መሆኑን ገልፀው ነገር ግን ትክክለኛ እውነታው የተባለው የግድቡ ገንዘብ በዚያው በጀት ዓት ማለትም ሰኔ 20 ቀን 2003 ዓ/ም በሕዳሴው ግድብ አካውንት ቁጥር ገቢ ያደረጉበትን ደረሰኝ በማቅረብ ያስረዱ ከመሆናቸውም በተጨማሪ እንዳውም ሠራተኛው ያወጣው የ2 ወር መዋጮ ብቻ ሲሆን የ10ሩን ወር መዋጮ ሠራተኛው እንዳይጎዳ ከካቴድራሉ ካዝና በመክፈል ለሠራተኛው ግን ሙሉ የ12 ወሩን መዋጮ ነው በቦንድ ሠርተፍኬት የተሰጠው ካሉ በኋላ የቦንድ ሰርተፍኬቱ ሊዘገኝ የቻለው ግን በራሱ በመንግስሥት አሠራር እንጂ በካቴድራሉ አስተዳደር አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡ ለማስረጃነትም በ2003 ዓ/ም ባንክ ገቢ ያደረጉበትን ደረሰኝ 1 ገጽ ፎቶ ኮፒ ተያይዞ ቀርቧል፡፡

4.የሀብት ቆጠራና የመሬት ልኬት በሚል ሽፋን ለግለሰቦች አለአግባብ ገንዘብ ተከፍሏል ተብሎ የቀረበው ክስ በተመለከተ የካቴድራሉ ሒሳብ ክፍል በሰጡት መልስ፡- ገንዘቡ የተከፈለው ቤተ ክርስቲያኒቱ ለረጅም ዘመናት ስትገለገልበት የነበረው የሲንግል ኢንትሪ የሒሳብ አያያዝ ወደ ደብል ኢንትሪ የሒሳብ አያያዝ እንዲቀየር ከሀገረ ስብከቱ በተሰጠው መመሪያ መሠረት አስፈላጊውን ስልጠና ከወሰድን በኋላ የደብል ኢንትሪ ሒሳብ አያያዝ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረቶች እንዲቆጠሩ ስለሚያስገድድ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በተላለፈው መመሪያ የንብረት ቆጠራውን የመሬት ልኬታውን ላከናወኑት ባለሙያዎች የተከፈለ መሆኑን የሰነድ ማስረጃ በማቅረብ አስረድተዋል፡፡

5.ሃያ ሁለት ማዞሪያ ካቴድራሉ በስጦታ ባገኘው ቦታ ላይ ካቴድራሉ እያስገነባው ያለው ሕንፃ ከሀገረ ስብከቱ እውቅናና ፈቃድ ውጪ በሕገ ወጥ መንገድ የአስተዳደሩ የሥራ ኃላፊዎች እርስ በርሳቸው ሿሚና ተሿሚ በመሆን የቅድሚያ ኪራይ ክፍያ ገንዘብ ሲሰበስቡ ለሀገ ስብከቱ በደረሰው ጥቆማ መሠረት ታግዶ ይገኛል በማለት ለቀረበው ክስ የካቴድራሉ የሥራ ኃላፊዎች በሰጡት መልስ፡-
22.ማዞሪያ ካቴድራሉ በስጦታ ባገኘው ቦታ ላይ የሚሠራው G+6 ፎቅ ሁለገብ ሕንፃ ያለ መሆኑንና ሥራው ሲከናወን የቆየው በካቴድራሉ ከውጭ ቀሪ ተቀማጭ ገንዘብ የነበረ ቢሆንም ገንዘቡ በማለቁና የሕንፃ ሥራ ተቋራጩ ለሠራበት ክፍያ በተደጋጋሚ ጠይቆ የምንከፍለው በማጣታችን በፍ/ቤት እንደሚከሰን ማስጠንቀቂያ ስለሰጠን በሌሎች አድባራት እንደሚደረገው ሁሉ ለሕንጻው ሥራ ማስፈጸሚያ የሚሆን ገንዘብ ማግኘት እንችል ዘንድ የቅድመ ኪራይ ክፍያ ገንዘብ ከተከራዮች ላይ እንድንሰበስብ እንዲፈቀድልን ለብፁዕ ወቅዱስ አባታችን አቤቱታ አቅርበን ቅዱስነታቸውም የ3 ዓመት ቅድመ ክፍያ እንድንሰበስብ ለሀገረ ስብከቱ በሰጡት አባታዊ መመሪያ መሠረት ሀገረ ስብከቱ በቁጥር 1307/9/08 በቀን 11/08/2008 ዓ/ም በተጻፈ ደብዳቤ የሦስት ዓመት ቅድመ ኪራይ ክፍያ ሰብስበን የግንባታው ሥራ እንዲቀጥል በፈቀደልን መሠረት ወዲያው በዘፈቀደ እንሰብስብ ሳንል የአካባቢውን ዋጋ አጥንተው የሚያቀርቡ ኮሚቴ በሰበካ ጉባዔ ውሣኔ በመመደብና ተጠንቶ በቀረበው ሪፖርት ላይ የጭማሪ ማሻሻያ በማድረግ፤
5.1 ለምድር ቤት በካሬ 531.00 ብር
5.2 ለሚዛኒኑ በካሬ 531.00 ብር
5.3 ለ1ኛ ወለል በካሬ 450.00 ብር
5.4 ለ2ኛ ወለል በካሬ 350.00 ብር
5.5 ለ3ኛ ወለል በካሬ 300.00 ብር
5.6 ከ4ኛ እስከ 6ኛ ወለል በካሬ 230.00 ብር የቅድመ ኪራይ ክፍያ ገንዘብ እንዲሰበሰብ በሰበካ ጉባዔ በመወሰንና ውሳኔውንም የሚያስፈጽሙ በካቴድራሉ አስተዳዳሪ የሚመራ ኮሚቴ በመሰየም ወደ አፈጻጸም የተገባ እንጂ ከሳሾች እንዳሉት ከሀገረ ስብከቱ እውቅናና ፈቃድ ውጭ የተሠራ አለመሆኑን ገልፀው እንዲያውም የዋጋ ጥናቱን ኮሚቴ በመምረጥና ገምግሞ በማጽደቅ አብረው የሰበካ ጉባዔ አባል ሆነው የወሰኑት መ/ር ሃይማኖት ቻለና መ/ር ኃ/ገብርኤል እንዳለ እውነታውን እያወቁ ዛሬ እንደማያውቁ ሆነው ከሳሽ ሆነው መቅረባቸው በእጅጉ የሚያሳዝን መሆኑን ገልጸው ዝርዝር የሰነድ ማስረጃ በማቅረብ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ለማስረጃም ያህልም ሀገረ ስብከቱ የፈቀደበትና በኮሚቴ የዋጋ ጥናት ተደርጎ የተወሰነበትን ቃለ ጉባዔ በድምሩ 8 ገጽ ፎቶ ኮፒ አያይዘን አቅርበናል፡፡

6.የካቴድራሉ ማኅተም ቤተ ክህነቱ ባወጣው የአሠራር ደንብ መሠረት መዝገብ ቤት እንዲቀመጥ ቢታዘዝም አስተዳዳሪውና ጸሐፊው በመመሳጠር ማኅተሙ እንዳይገባ አድርገው ሌላ ሥራ እየተሠራበት ነው ተብሎ ለቀረበው ክስ የካቴድራሉ ዋና ፀሐፊ በሰጠው መልስ በአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት በሙሉ የጽ/ቤቱን ማኅተም የሚይዘው ዋና ፀሐፊው መሆኑን በሁሉም ዘንድ የሚታወቅ ነው፡፡ ማኅተም ወደ መዝገብ ቤት ገቢ ይሁን የሚል መመሪያ አዘል ደብዳቤ እስካሁን ከሀገረ ስብከቱ አልደረሰንም ከእኔ በፊት በነበረው አሠራር መሠረት ነው እየሠራሁ ያለሁት ከሀገረ ስብከቱ ደብዳቤ ከደረሰኝ ገቢ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ በማለት ምላሽ የሰጡ ሲሆን ሌላ ሥራ እየተሠራበት ነው የተባለውን በተመለከተ ከሳሾች እንዲያብራሩ ተጠይቀው ወ/ሮ ጤናዬ መኮንን ሲያስረዱ የሐውል ሥራ ገቢ የፋክቱር ደረሰኝ ማህተም ያረፈበትን ሰነድ አቅርበው ያብራሩ ሲሆን አጣሪ ኮሚቴው እንዴት በፋክቱር ደረሰኝ ገቢ ይሰበሰባል የሚል ጥያቄ ለካቴድራሉ አስተዳደር ጥያቄ አቅርበን አሠራሩ ከተጀመረ የቆየ መሆኑን በፋክቱር ደረሰኝ ሊሰበሰብ የቻለበት ምክንያት ሲያስረዱ ሐውልቱ የሚሠራው ሙያው ባላቸው የግንባታ ባለሙያዎ ሲሆን ከሚገኘው ገቢ ላይም 50% ለባለሙያው 50% ለካቴድራሉ ነው ገቢ የሚሆነው እናም ካሁን በፊት ሁሉንም ገቢ በሞዴል 64 ገቢ ከአደረግን በኋላ በዓመቱ መጨረሻ ሀገረ ስብከቱ ፐርሰንት ለመሰብሰብ ሲመጣ የሐውልት ሥራ ገቢው 50% የባለሙያው ክፍያ በወጭ ይያዝልን በማለት ስንጠይቃቸው እንቢ ብለው በጥቅል ገቢው ላይ ላይ ፐርሰንት ስላልከፈሉን በጉዳዩ ላይ የካቴድራሉ አስተዳደር ሰበካ ጉባዔ ተወያይቶ በጊዜያዊነት መለያ ቁጥር ተሰጥቶትና ማኅተም አርፎበት በፋክቱር ደረሰኝ ገቢ ከሆነ በኋላ ሥራው ሲጠናቀቅ 50% የባለሙያ ክፍያ ተቀንሶ ቀሪው 50% የካቴድራሉ ድርሻ በሞዴል 64 ገቢ ይሁን በማለት በወሰነው መሠረት እየተፈጸመ ለብዙ ዓመታት የቆየ አሠራር እንጂ አሁን በአለነው አስተዳዳሪና ጸሐፊ የተጀመረ አሠራር አለመሆኑን በመግለጽ ለአብነት ያህል በከሳሾ በኩል ቀርቦ የነበረውን የፋክቱር ደረሰኝ የሐውልት ሥራ ገቢ 50% የካቴድራሉን ደርሻ በወቅቱ ገቢ የሆነበትን የባንክ እስቴትመንት በሰነድ ማስረጃነት አቅርበው አስረድተዋል፡፡ እኛም ለማስረጃነት ከሣሽና ተከሳሽ ያቀረቡትን ማስረጃ 7 ገጽ ፎቶ ኮፒ አያይዘን አቅርበናል፡፡

7.በ2010 ዓ/ም በቀድሞው ሊቀ ሥልጣናት አባ ገ/ሥላሴ በላይ የተሰበሰበ ወርቅና ዳይመንድ በአሁኑ ሊቀ ሥልጣናት አባ ገ/ዋሕድ ገ/ኪዳን የቃል ትዕዛዝ በሕጋዊ ደረሰኝ ገቢና ወጭ ሳይደረግ ንብረት ክፍሉ ሳያውቀው የት እንደደረሰ አይታወቅም ተብሎ የቀረበው ክስ በተመለከተ የካቴድራሉ አስተዳዳሪ ሊቀ ሥልጣንት አባ ገብረ ዋህድ ገብረ ኪዳን በሰጡት መልስ እኔ አስቀድሞ ወርቅም ይሁን ዳይመንድ ይኑር አይኑር አላውቅም፡፡ ነገር ግን እኔ በአስተዳዳሪነት ተመድቤ እንደመጣሁ ወርኃዊ የሙዳይ ምጽዋት ሊቆር ተሰብስበን እያለ የሙዳይ ምጽዋቱ መክፈቻ ቁልፍ የሚቀመጥበት አነስተኛ ሳጥን ሲከፈት የሆነ ወርቅ መሰል ነገር በማየታችን ምንድነው ብዬ ስጠይቅ በስዕለት የገባ ነው አሉኝ እና ለምን ከዚህ ተቀመጠ ብዬ ስጠይቅ ወርቅ ነሆኑ ስላልተፈተሸ ንብረት ክፍሉ ወርቅ ብዬ ገቢ አላደርገውም በኋላ ባይሆን ያስጠይቀኛል ብሎ እንቢ ስላለ ለጊዜው በአደራ ተቀምጦ ነው የሚል መልስ እንደቀረበልኝ ወዲያው ጉዳዩን ለጉባዔ በማቅረብ እንዳሁን ቀደሙ ሁሉ በኮሚቴ ወደ ወርቅ ቤት ተወስዶ ምንነቱን በማስፈተሸ በወቅቱ ባለው ዋጋ ወደ ገንዘብ ተቀይሮ ገቢ እንዲሆን በተደረሰው ስምምነት መሠረት የተመረጡት ኮሚቴዎች የነበሩትን ወርቅ መሰል ቀለበቶችና ሀበል ወስደው አስመርምረው በነበረው ዋጋ መሠረት ጠቅላላ ዋጋው ብር 18,340 ገቢ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ከዚህ ውጭ ዳይመንድ መኖሩን አላውቅም በማለት መልስ የሰጡ ሲሆን እኛም አጣሪዎች ከሳሾን ዳይመንድ መሆኑን በምን አወቃችሁ የሚል ማጣሪያ ጥያቄ አቅርበንላቸው ሲመልሱ ቀለበቱ ላይ ዳይመንድ የሚመስል የፈርጥ ምልክት ስላለው ነው እንጂ ዳይመንድ መሆኑን ፈትሸን አላረጋገጥንም በማለት መልስ የሰጡ ሲሆን በኮሚቴነት ተመርጠው ሸጠዋል የተባሉት እንዲያስረዱን ጠይቀን የሚያውቁት ዳይመንድ እንዳልነበረና አስፈትሸን በመሸጥ በወቅቱ ገንዘቡን ለካቴድራሉ ገቢ አድርገናል፡፡ በማለት የገቢ ደረሰኙን አቅርበው አስረድተዋል፡፡ ይሁን እንጂ በነበረው ጥያቄና መልስ ወቅት ዳይመንድ መሰሉ ማዕድንና አንድ የወርቅ ሐብል በፊት የነበረ የት እንደደረሰ አናውቅም የሚል ምላሽ ከንብረት ክፍሉ በቀረበው ሐሳብ ላይ መተማመን ሳይችል ቀርቷል፡፡ እኛም ለማስረጃነት ገቢ የሆነበትን ገጽ ፎቶ ኮፒ የሰነድ ማስረጃ አያይዘን አቅርበናል፡፡

8.በባለወልድ አካባቢ የተሠራው ሁለገብ ሕንፃ የመጀመሪያ ዋጋው 7,000,000 ብር ሲሆን 18,000,000 ብር ወጪ ሆኖ የተከፈለ መሆኑንና ሥራው አልቆ ርክክብ ያለተፈተመ መሆኑን አስመልክቶ ለቀረበው ክስ የካቴድራሉ አስታደር የሥራ ኃላፊዎች በሰጡት መልስ በመጀመሪያ ሲሠራ የታሰበው ሕንፃ ዲዛይን G+1 እንደነበረና የግንባታውም ዋጋ 7,000,000 ብር እንደነበረ ነገር ግን ቦታውን ከመቆጠብ አንፃር የዲዛይን ማሻሻያ በማድረግ ከG+1 ወደ G+4 እንዲያድግ በመደረጉ የመጣ የዋጋ ለውጥ መሆኑን፤ ርክክብ ያልተደረገውም የሥራው አፈጻጻም በልማት ኮሚቴው ተገምግሞ እንዲቀርብ በታዘዘው መሠረት ገና ያላቁ ሥራዎ መኖራቸውን ዘርዝር ሪፖርት በማቅረቡ ምክንያት ሲሆን ሥራዎቹ እንዲጠናቀቁ ለኮንትራክተሩ ደብዳቤ የጻፍን ቢሆንም ኮንትራክተሩ ጉድለቱን ከማረም ይልቅ ሥራውን ሳይጨርስ የመጨረሻ ክፍያ ይከፈለኝ በማለት በፍርድ ቤት ከሶን በክርክር ላይ እንገኛለን በማለት የሰነድ ማስረጃ በማቅረብ ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡
262 ገጽ ኮፒ አያይዘን አቅርበናል::

9.የበዓለወልድ ቤተ ክርስቲያ መጠለያ ግንባታ ርክክብን መዘግየት አስመልክቶ ለቀረበው አቤቱታም ቢሆን በውሉ መሠረት ሥራው ባለማለቁ እንጂ ለመረከብ ቸልተኞ ሆነን አይደለም በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

10.የአብነት ት/ቤት እንሠራለን በሚል ሽፋን የካቴድራሉን ታሪካዊ አቀማመጥ ሊጎዳ በሚችል መልኩ የካቴድራሉ ቅርጽና ማስቀደሻ እንዲሁም መጠለያ ብሎም ረጅም ዘመን ያስቆጠሩ ዛፎችን በመቁረጥ ለግል ባለሀብቶች የፉካ /መቃብር/ ባለ 5 ፎቅ እንዲገነቡ ለመስጠት የአፈር ምርመራ ላይ የሚገኙ ስለሆነ ይህ ግንባታ የካቴድራሉን ቅርስና የመጠለያ ቦታ ሊጎዳ ስለሚችል እንዳይፈቀድ ቢታገድ ተብሎ በቀረበው አቤቱታ ላይ የካቴድራሉ የሥራ ኃላፊዎች በሰጡት መልስ ካቴድራሉን ጥንታዊና ታሪካዊ ቦታ እንደመሆኑ መጠን በርካታ የአብነት መ/ራን ያሉት ሲሆን አንድም የአብነት ት/ቤት ባለመኖሩ ዘወትር ያዝኑ እንደነበርና በየጊዜው ለመሥራት እየታቀደ በበጀት እጥረት ሳይሠራ እንደቆየ ነገር ግን የእግዚአብሔር ፈቃድ ሲደርስ ቢትወደድ ባሕሩ አብርሃም የተባሉ ባለሀብት ለሥሜ መጠሪያ የሚሆንና ለታሪክ የሚቀመጥ የበረከት ሥራ መሥራት እፈልጋለሁ ቢቻል ቢቻል የአብነት ት/ቤት ቢሆን የሚል ጥያቄ ለካቴድራሉ ሲያቀርቡ ምኞታችን ተሳካ በማለት የአብነት ት/ቤት ቢሆን የሚል ጥያቄ ለካቴድራሉ ሲያቀርቡ ምኞታችን ተሳካ በማለት የአብነት ት/ቤት መሥራት እንደሚችሉ በመንገር ነገር ግን ቦታው ጥንታዊ እንደመሆኑ መጠን ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ሳያውቁትና ሳይፈቅዱ መሥራት እንደማይቻል እርሳቸውም እሺ በማለት ኅዳር 1 ቀን 2011 ዓ/ም በተጻፈ ማመልከቻ ለቅዱስ አባታችን ጥያቄ አቅርበው ቅዱስነታቸውም በጥያቄያቸው መሠረት በተገቢው መንገድ ይፈጸም በማለት የአብነት ት/ቤት መሥራት እንደሚችሉ በመንገር ነገር ግን ቦታው ጥንታዊ እንደመሆኑ መጠን ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ሳያውቁትና ሳይፈቅዱ መሥራት እንደማይቻል እርሳቸውም እሺ በማለት ኅዳር 1 ቀን 2011 ዓ/ም በተጻፈ ማመልከቻ ለቅዱስ አባታችን ጥያቄ አቅርበው ቅዱስነታቸውም በጥያቄአቸው መሠረት የካቴድራሉ ሰበካ ጉባዔ ተሰብቦ የቦታ መረጣ ውይይት ያደረገ ሲሆን አስቀድሞም መጋቤ ምስጢር ልሳነወርቅ ብር ጉባዔ ዘርግተው ሲያስተምሩበት የነበረው ጉባዔ ቤት ቤቱ ፈርሶ መሠረቱ አሁንም ድረስ ለምልክት ያለ በመሆኑ ታሪክን ከመመለስ አንጻርና አካባቢውንም ትልልቅ ባለሥልጣናት ሲሞቱ እንቀበርበት እያሉ ዘወትር ስለሚያስቸግሩ ቦታው በመቃብር ከሚያዝ የአብነት ት/ቤት ቢሠራበት ተተኪ ትውልድ ማፍራት ይሻላል በማለት ቦታውን አብነት ት/ቤት እንዲሠራበት የፈቀድን ሲሆን የአብነት ት/ቤቱ ዲዛይን ሲሠራ ለምዕመናን ማስቀደሻ የሚሆን መጠለያ ያካተተከ G+1 የአብነት ት/ቤት ዲዛይን ሥራው ተጠናቆና የሕንፃ ሥራ ተቋራጩም ከባለሀብቱ ጋር ተዋውሎ የቀብድ ክፍያ መቀበሉንና ቀጥሎም በቦታው ላይ የነበረው የኤሌክትሪክ ፖል እንዲነሣ ካደረግን በኋላ በቦታው ላይ ያሉት ባህር ዛፍና የተለያየ መጠን ያላቸው ጽዶች መነሳት ያለባቸው በመሆኑ የአስተዳደር ሠራተኞ በቃለ ጉባዔ በመወሰን እንዲሁም ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በደብዳቤ በማሳወቅ እንዲቆረጡ አድርገን ሥራው በመቀጠል ላይ እያለ የአሁኑ ከሳሾች ለአብነት ት/ቤት የተፈቀደውን ለመቃብር ፉካ ነው በማለት ከፍተኛ የሆነ የአድማ ቅስቀሳ በማድረጋቸው ለጊዜው ነገሩ እስኪረጋጋ ሥራው የቆመ መሆኑን ገልፀው በከሳሾች በኩል ለባለሀብት መቃብር ፉካ ነው ተብሎ የቀረበው ከእውነት የራቀ መሆኑንና አስቀድሞም የካቴድራሉ አብነት ት/ቤት የነበረበት ቦታ መሆኑን ሥራው ተጀምሮ ዛፎችም ከተቆረጡ በኋላ የአብነት ት/ቤቱ ሳይሠራ ይቅር ተብሎ እየቀረበ ያለው የከሳሾች ክሽ ከፍጹም ጥላቻ የመነጨ መሆኑንና ቦታው ባዶ ከመሆኑም በላይ የባለሥልጣናቱ ቀብር እየሰፋ ከጥጉ የደረሰ በመሆኑ ከትንሽ ጊዜ በኋላ ለአብነት ት/ቤት የከለልነው ነባር የጉባዔ ቤቱን ቦታ የመቃብር ሐውልት ሲሠራበት የታሪክ ተወቃሾች እንዳንሆን የተከበረው ቅዱስ ሲኖዶስ የተጀመረው የአብነት ት/ቤት ግንባታ ቀጥሎ የቀድሞው ታሪክ እንዲመለስ ያደርግ ዘንድ በካቴድራሉ ስም እንጠይቃለን በማለት ማሳሰቢያ ያቀረቡ ሲሆን እኛም አጣሪዎ ከቀረበው ማመልከቻና ይግንባታ ፈቃድ መጠየቂያ ደብዳቤ መረዳት እንደቻልነው ግንባታው ለአብነት ት/ቤት እንጂ ለመቃብር ፉካ አለመሆኑን ከሰነድ ማስረጃዎች ያረጋገጥን ሲሆን ለማስረጃ ያህልም ባለሀብቱ ለቅዱስ አባታችን አመልተው አባታዊ አመራር ያሰጡበትን፤ የካቴድራሉ ሰበካ ጉባዔ በቃለ ጉባዔ የወሰነበት፤ ስለ ዛፎቹ መቆረጥ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ያሳወቁበት ደብዳቤና ለክፍለ ከተማው የግንባታ ፈቃድ የተጻፉትን ደብዳቤዎች 13 ገጽ ፎቶ ኮፒ በአስረጂነት አያይዘን አቅርበናል፡፡

11.የካቴድራሉ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት መምህርት ለሆኑት ለወ/ሮ ኖላዊት መካ የኮንትራት ሠራተኛ እንደሆነች እየታወቀ ለባንክ ብድር እንዲጠቅማት ቋሚ ሠራተኛ ነች በማለት ደብዳቤ ጽፈዋል ተብሎ የቀረበው አቤቱታ በተመለከተ የካቴድራሉ አስተዳዳሪ በሰጡት መልስ የአመልካቿ ባለቤት የሆኑት አቶ አማረ ጠጁ የባንክ ሠራተኛ መሆናቸውንና ባላቸው የባንክ ብድር የማግኘት መብት መሠረት የቤት መግዣ ብድር ለማግኘት ባለቤታቸው በካቴድራሉ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት በመምህርነት በኮንትራት ውላቸው እየታደሰ ሲሩ ለቆዩት የድጋፍ ደብዳቤ እንድንጽፍላቸው በጠየቁን መሠረት ከመተባበር አንጻር የተጻፈ ደብዳቤ እንጂ እዳዋን ባትከፍል ካቴድራሉ ይከፍላል ተብሎ መገለፁ የጥላቻ ንግግር እንጂ የካቴድራሉ አቋም አይደለም በማለት መልስ ሰጥተዋል፡፡ እኛም ተጻፈ የተባለውን ደብዳቤ እስከነ ዝርዝር ማስረጃው 10 ገጽ ፎቶ ኮፒ አያይዘን አቅርበናል፡፡

12.የጥምቀት በዓልን ምክንያት በማድረግ በቤተ ክርስቲያኑ ስም ገንዘብ ለማሰባሰብ ስምና አድራሻ የሌለው ወረቀት የተበተነ በመሆኑ የሚገኘው ገንዘብ ለምን እንደሚውል ይመርመር ተብሎ ለቀረበው ጥያቄ የካቴድራሉ የሥራ ኃላፊዎች በሰጡት መልስ የ2011 ዓ/ም የጥምቀት በዓል ተረኞ በመሆናችን ለአገልጋዮች ሊቃውንት ቤተ ክርስቲያንና ለሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የሚሆን ጥንግ ድርብ፣ መቋሚያ፣እጀ ጠባብ ሱሪ፣ ለሴት መዘምራን ቀሚስ፣ የመዘምራን ጫማ፣ የመዘምራን አክሊል፣ ጸናጽልና ሌሎች መገልገያዎች በአዲስ ለማሠረት ታስቦ የቤቱን በጀት ከመጠበቅ አንጻር አንዳንድ ባለተስፋዎችን አነጋግሮ በአይነት እየገዙ እንዲያመጡ የሚያስተባብር ኮሚቴ በማዋቀር የተሠራ ሥራ እንጂ አንደ ክስ አቀራረቡ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ታስቦ የተሠራ አለመሆኑንና ከሳሾ ለክስ ማዳበሪያ ያቀረቡት መሆኑን በመግለጽ የሰነድ ማስረጃዎችን በማቅረብ አስረድተዋል፡፡ እኛም ለማስረጃ ያህል ከሁለቱም ወገን የቀረበውን 3 ገጽ ፎቶ ኮፒ የጽሑፍ ማስረጃ አያይዘን አቅርበናል፡፡

13.ነባሩ ሰበካ ጉባዔ የሥራ ዘመኑ በማብቃቱ በ2010 ዓ/ም በአዲስ መልክ ከተመረጠ በኋላ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት አባላት የስብሰባ ጥሪ ስለማይደረግላቸው ኃላፊነታቸውን እንዳይወጡ ተደርጓል፡፡ በማለት ለቀረበው አቤቱታ የካቴድራሉ አስተዳሪ በሰጡት መልስ፡- በመጀመሪያ ደረጃ የሰበካ ጉባዔ አባላቱ ምርጫ የተደረገው እኔ ገና ወደ ካቴድራሉ በኃላፊነት በተመደብኩ በ21ኛ ቀኔ በመሆኑ ለቦታው አዲስ ነበርኩ ነገር ግን አስቀድሞ ተይዞ የነበረ ፕሮግራም በመሆኑ ከሀገረ ስብከትና ለክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ተወካዮች በነበሩበት ምርጫው ተካሂዷል፤ አባላቱ እንዳይሰበሰቡ ተደርጓል ለተባለው ከእኔ ይልቅ እነርሱ በአካል ስላሉ መልስ ይስጡበት በማለት እድሉን ሰጥተዋቸው ሁሉንም ሥራዎች በስብሰባ እየተገኙ እየተወያዩና በቃለ ጉባዔ እየወሰኑ እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል፡፡

13.1 ለምሳሌ የስበት ት/ቤት ተወካይ ታግደዋል ለተባለው የተሰጠው ምላሽ እውነት ነው ወጣት ኃይለ ገብርኤል እንዳለ የተባለው የሰንበት ት/ቤት ተወካይ በተደጋጋሚ የካቴድራሉን አስተዳዳሪና ም/ሊ/መንበር በስብሰባ ላይ በመዝለፍለፋቸው፤ ከካቴድራሉ እውቅናና ፈቃድ ውጪ በሕገ ወጥ መንገድ በሰንበት ት/ቤቱ ስም የባንክ አካውንት ተከፋይ ሲያንቀሳቅሱ በመገኘታቸው፤ ያልሆነውን ሆነ ያልተደረገውን ተደረገ እያሉ ለስንበት ት/ቤት ወጣቶች ያልተገባ መረጃ በመስጠት እየበጠበጡ ስላስገሩንና በሌሎች ጥፋታቸው ከሰበካ ጉባዔ አባልነታቸው የታገዱ ሲሆን በምትካቸው እርሳቸው ሲመረጡ ተጠባባቂ የነበሩት ተተክተው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በሰ/ት/ቤቱ አባላት መካከል በፈጠሩት ችግር ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያና ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ተወካዮች በተገኙበት ጉዳያቸው ተጣርቶ ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው በመምሪያው ኃላፊ በመ/ር ዕቆ ባሕርይ ተከስተ ፊርማ ከሰንበት ት/ቤት አመራርነት ከታገዱ በኋላ በሌላቸው ሥልጣን ከሰ/ት/ቤቱ የባንክ ሒሳብ ላይ በፊርማቸው ወጪ አድርገው በመገኘታቸው ጉዳዩ በማጣራት ላይ ይገኛል፡፡ ዋናው ለዚህ ክስ መሠረቱም ጥቅማቸው ስለተነካባቸው በበቀለኝነት ስሜት ይህን ሁሉ ችግር እየፈጠሩ ያሉ እኒሁ ግለሰብ ናቸው በማለት ዝርዝር የሰነድ ማስረጃ አቅርበው አስረድተዋል፡፡ እኛም አጣሪዎች የታገዱባቸውን ደብዳቤዎችና ከታገዱ በኋላ በፊርማቸው ከባንክ ውጪ ያደረጉበትን የባንክ እስቴትመንት ለማስረጃ ያህል አያይዘን አቅርበናል፡፡

13.2 የካቴድራሉ አስተዳደር በአንድ ብሔር ብቻ ተይዞ የካቴድራሉን ገንዘብና ንብረት እየዘረፉት ነው ተብሎ የቀረበው አቤቱታ በተመለከተ፤ የካቴድራሉ የሥራ ኃላፊዎች በሰጡት መልስ በተለያዩ ጊዜያት ከሀገረ ስብከቱ የሥራ ዝውውር ምደባ የመጣን እንጂ በከሳሾ እንደተባለው አሁን ባሉት አስተዳዳሪ የተሰባሰብን አይደለንም በማለት የምደባ የሥራ ዘመናቸውን በመግለጽ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

14.የካህናት የጡረታ መዋጮን አስመልክቶ ለአስተዳዳሪው ጥያቄ ብናቀርብም የት እንደሚገባ አላወቅም ብለዋል በማለት የቀረበውን አቤቱታ በሚመለከት
የካቴድራሉ አስተዳዳሪ በሰጡት መልስ፡- ጥያቄው የት ነው የሚገባ ሳይሆን የጡረታ መዋጮ አይቆረጥብን የሚል ሲሆን ከሀገረ ስብከቱ የመጣን መመሪያ እና ማስቀረት አልችልም ብዬ ነው የመለስኩላቸው፡፡ ነገር ግን ካላቸው ጥላቻ የተነሳ ነገሩን አዛውረው ነው ጥያቄ ያደረጉት እንጂ እኔው ራሴ ተቀናሹን ገንዘብ ወደ ሀገረ ስብከቱ የጡረታ ሒሳብ ቁጥር ገቢ እንዲሆን በደብዳቤ እየፈረምኩ ስፈጽም የቆየሁበት 3 ገጽ የሰነድ ማስረጃ አቅርበው አስረድተዋል፡፡ እኛም ለማስረጃነት አያይዘን አቅርበነዋል፡፡

15.ኅዳር 28 ቀን 2011 ዓ/ም የቄሰ ገበዝና የሊቀ ዲያቆናት ምርጫ በተጠራው ስብሰባ ላይ አስተዳዳሪው እዚህ ብዙ ወሬኛ አለ፤ ሰላም የነበረው ካቴድራል እየታመሰ ያለው በተወሰኑ ወሬኞች ነው፤ በማለት በሠራተኛው ላይ ዛቻና ጫና ፈጽመዋል፤ ለተባለው ክስ
አስተዳዳሪው በሰጡት መልስ፤ ስብሰባው ከመደረጉ አስቀድሞ ብጥብጥ እንዲነሣ ለማድረግ ከ20 በላይ ሠራተኞች እንዲነሱ አስተዳዳሪው ደብዳቤ ጽፈዋል በማለት ተቀስቅሶ ስለነበርን ከተሰብሳቢዎች ለቀረበው የሥጋት ጥያቄ መልስ ስሰጥ የተነገረ ቃል ነው፤ ሙሉ ቃሉም ይህ ካቴድራል የሰላም ቦታ ነበር ነገር ግን አንዳንድ አገልጋዮ በዝውውር ከመጡ ወዲህ ለምሳሌ ዲ/ን ሀብታሙ ፀጋ በዝውውር ከመጣ ጀምሮ የዘርና የብሔር ቅስቀሳ በማድረግና አገልጋዮችን በቡድን በምክፈል በሚሠራው ሥራ ነው፤ ይህ ሁሉ ችግር እየተፈጠረ ያለው እኛ ማንም እዲነሳ የፃፍነው ደብዳቤ የለም በማለት የማረጋጋት ቃላት ተናግሬያለሁ፤ ካሉ በኋላ አሁንም ድረስ ካቴድራሉ እየተበጠበጠ ያለው በጥቂት ግለሰቦች ነው እንጂ ሌላው አገልጋይ በሙሉ ሰላማዊ ነው፤ በማለት መልሳቸውን ሰጥተዋል፡፡
16. ታህሳስ 7 ቀን 2011 ዓ/ምተደረገ ስለተባለው ‹‹ሚ በዝኍ›› ቅኔ በተመለከተ ተደረገ የተባለው ቅኔ ሙሉ ንባቡን በጽሑፍ አያይዘን ያቀረብን ስለሆነ የተከበረው ቅዱስ ሲኖዶስ ቅኔውን መርምሮ የመለሰውን ውሳኔ ይሰጥበት፤

17.ከአንድ አካባቢ ተሰብስበው ታላቁ ካቴድራል የነበረውን ዓለም አቀፋዊ ዕውቅና ዝቅ እንዲል ከማድረጋቸውም በላይ ለሠራተኛው ደመወዝ ሲጨመር በዘርና በብሔር ክፍና ዝቅ በማድረግ አድሎአዊ አሠራር ይፈጽማሉ ተብሎ ለቀረበው ክስ፤ በመጀመሪያ ማን ነው? የደመወዝ ጭማሪ አድሎ የተፈጸመበት ሠራተኛ በማለት ላቀረብነው የማጣሪያ ጥያቄ
ከሳሾች ሲያብራሩ ለምሳሌ ለመ/ር ሐዋዝ ገ/ሊባኖስ ደመወዝ ሲጨመር ለሊቀ ብርሃናት ሐዋዝ ተበጀ አልተጨመረላቸውም በማለት ያብራሩ ሲሆን እኛም አጣሪዎች ለምን አልተጨመረላቸውም በማለት አስተዳደሩ ጠይቀን በሰጡት መልስ፤ ክሱ መሠረት ቢስ ነው በማለት በስም ለተጠቀሱት ሠራተኛ ደመወዝ የተጨመረበትን ነሐሴ 28 ቀን 2010 ዓ/ም የተያዘ ቃለ ጉባዔ አቅርበው ክሱ ሐሰት መሆኑን በማረጋገጥ መልስ ሰጥተዋል፡፡

18.ከላይ በዝርዝር የቀረቡትን ቅሬታዎች አቤቱታ በማቅረባችን አስተዳዳሪው ከ20 በላይ ሠራተኞች እንድንዛወር ለበላይ ጠባቂዎቻቸው ደብዳቤ በመጻፍ በማሴር ላይ ናቸው በማለት የቀረበውን አቤቱታ በተመለከተ አስተዳደሩ በሰጡት መልስ ከ20 በላይ ሠራተኞች ተብሎ የቀረበውን አቤቱታ በተመለከተ አስተዳደሩ በሰጡት መልስ ከ20 በላይ ሠራተኘቾ ተብሎ የቀረበው ሀሰት ነው፤ ነገር ግን ከተፈጠረው አለመግባባት ወዲህ5 የሚሆኑ ሠራተኞች በተደጋጋሚ ክስ ላይ ነን በሚል ሽፋን በምድብ ሥራቸው ላይ ሊገኙ ባለመቻላቸው የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ የገንዘብ መቀጮ ቅጣት ብንወስንም ከበላይ አካል የተጻፈን ደብዳቤ እንደ ሽፋን በመጠቀም በተደጋጋሚ ከሥራ እየቀሩ ሥራው እየተበደለ ስለሆነ 5ቱ ሠራተኞ ወደ ሌላ ቦታ እንዲዛወሩ ማሳሰቢያ አቅርቤያለሁ፤ ይህም ለሥራውና ለሰላሙ ሲባል ነው በማለት የጻፉትን ደብዳቤ 2 ገጽ ፎቶ ኮፒ አቅርበው አሳይተዋል፤ እኛም ከሪፖርቱ ጋር አያይዘን አቅርበነዋል፡፡

19.በአቤቱታው ተራ ቁጥር 1.16 ላይ የተገለፅው በዚሁ ሪፖርት ተራ ቁጥር 1.1. ላይ ተብራርቶ የቀረበወ በመሆኑ በድጋሚ መጻፉ አግባብ ስላልሆነ አልፈነዋል፡፡

20.ካቴድራሉ ለሰ/ትቤቱ የፈቀደውን ዓመታዊ በጀት ቀንሶብናል በማለት ለቀረበው ጥያቄ የካቴድራሉ ሒሳብ ክፍል በሰጡት መልስ እውነት ነው የጸደቀ በጀት ነበራቸው ነገር ግን በጀቱን ከተቀደለት ዓላማ ውጪ ለማዋል ያቀረቡት ጥያቄ አግባብ ባለመሆኑ ሲከለከሉ በቅዳቸው መሠረት ላቀረቡት ጥያቄ ግን በዓመት ከብር 50,000 (ከሃምሳ ሺህ ብር) በላይ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል በማለት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

21.ብር 1,500,000 (አንድ ሚሊዮን አምስት መቶ ሺህ ብር) ያፈጀ ሳይት ፕላን አጥንት አቅርበን ሊቀበሉን አልቻሉም ተብሎ ለቀረበው ጥያቄ፤
አስተዳደሩ በሰጡት መልስ፡- በመጀመሪያ የገንዘቡ ተመን ከየት እንደመጣ አናውቅም፡፡ ነገር ግን ሳይት ፕላን አጥንተን አምጥተናል ብለው ሲጠይቁ በቅድሚያ ላንድ እስኬፑ መጠናት እንዳለበት ገልፀንላቸው በዚህ ሊስማሙ ባለመቻላቸው ነው ወደ ትግበራ ያልተገባው፤ በቀጣይ በባሉመያዎች ተገምግሞ ሲታመንት ይተገበራል በማለት ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡

22. የካቴድራሉ ካህናት፤ ዲያቆናትና ምእመናን በተገኙበት የተደረገው የሰበካ ጉባዔ ምርጫ በድምጽ ብልጫ ያሸነፉትን ሰዎች ያለአግባብ በቢሮ ውስጥ ቀንሰው በማስቀረት ያልተመረጡትን አስገብተዋል ተብሎ ለቀረበው ጥያቄ፤
የካቴድራሉ አስተዳደር በሰጡት መልስ፤ ምርጫው ከተካሄደ በኋላ እራሳቸው አስመራጭ ኮሚቴዎች ባደረጉት ማጣራት ሁለት መራጮች በድምጽ ብልጫ ቢያልፉም እድሜያቸው ከ60 ዓት በላይ በመሆኑ ቃለ አዋዲው ስለሚከለክላቸው በደንቡ መሠረት ተጠባባቂዎ እንዲተኩ ተደርጓል፡፡ ይህም የተደረገው የተመራጮች ሕጋዊ መታወቂያ ቀርቦ በአስመራጭ ኮሚቴው ታይቶና በአስመራጭ ኮሚቴ የውሳኔ ቃለ ጉባዔ እንጂ በክሱ ላይ እንደተገለፅው በካቴድራሉ አስተዳደር ባለመሆኑ ክሱ መሠረት ቢስ ነው በማለት የሰነድ ማስረጃ አቅርበው አስረድተዋል፤ እኛም ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ምርጫ የተካሄደበትን 9 ገጽ ቃለ ጉባዔ ፎቶ ኮፒ አያይዘን አቅርበናል፡፡

23.ተራ ቁጥር 2.4 ስቀድሞ በተራ ቁጥር 8 ላይ በዝርዝር ከተገለፀው ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ ታልፏል፡፡
24. የሰ/ት/ቤት ኢንተርኔት መስመር መቋረጥን በተመለከተ ለቀረበው አቤቱታ የካቴድራሉ IT ባለሙያ በሰጠው መልስ መስመሩ ሊቋረጥ የቻለው መስመሩን የሚያገናኘው እስዊች በመቃጠሉ ሲሆን ዕቃው እንደተገዛ አገልግሎቱ የሚቀጥል መሆኑን በመግለፅ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

25. የሰ/ትቤቱን ተወካይ መታገድ በተመለከተ ከላይ በዝርዝር የተገለፀ በመሆኑ ታልፏል፡፡
26. የካቴድራሉ አስተዳደር የሰ/ት/ቤቱን አባላት በልዩ ልዩ መንገድ በማለል ሰ/ት/ቤቱ ከሁለት እንዲከፈል አድርገውታል ተብሎ ለቀረበው፤
አስተዳደሩ በሰጠው መልስ፤ የሰ/ት/ቤቱ ከሁለት እንዲከፈል ያደረገው እራሱ ወጣት ኃ/ገብርኤል እንዳለ እንጂ እኛ አይደለንም አሁን ከእርሱ መታገድ ወዲህ ግን የአመራር ለውጥ ተደርጎ ሰ/ት/ቤቱ መደበኛ አገልግሎቱን እየሰጠ ይገኛል፡፡ በማለት መልስ ሰጥተዋል፡፡

27.በእነ እቡረ እድ ኤልያስ አብርሃና መ/ር እንቁ ባሕርይ ተከስተ አስተባባሪነት ሠፊ ዝግጅት ሲደረግበት የነበረወ የ75ኛው ዓመት በዓላችን የካቴድራሉ አስተዳደር እንዲደናቀፍ አድርጎብናል በማለት ለቀረበው ጥያቄ፤
የካቴድራሉ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች በሰጡት መልስ እኛ አላደናቀፍንም እራሳቸው በፈጠሩት ብጥብጥ የተነሳ ለሁለት ቀን ከተከበረ በኋላ መቆሙን ብቻ እናውቃለን በማለት ማብራሪያ ጥተዋል፡፡

28.ለ75ኛው ዓመታዊ በዓልና ለጥምቀት በዓል ሊሠራልን የነበረው ጥንግ ድርብና ሌሎ መገልገያዎች በአስተዳዳሪው ምክንያት ሳይሠራልን እንዲቀር አድርገዋል በማለት ለቀረበው ጥያቄ፤
አስተዳዳሪው በሰጡት መልስ ክሱ መሠረተ ቢስ ነው፤ ሥራውን እንዲራ የተመረጠው ባለሙያ የሥራ ውል የወሰደው ከ5 ወር በፊት ቢሆንም በውሉ መሠረት ከበዓሉ በፊት ማድረስ ባለመቻሉ በዓሉ ከአለፈ በኋላ ካቴድራሉ ከፍሎ የነበረውን የቅድሚያ ክፍያ ከብር 5,000.00 (አምስት ሺህ ብር) መቀጮ ጋር በሕግ በማስመሰል ወደ ካቴድራሉ ገቢ አድርገናል፡፡ በመሆኑም በባለሙያው ችግር እንጂ በእኛ ችግር አይደለም በማለት መልስ ሰጥተዋል፡፡

29.የታላቁን ካቴድራል እድሳት በተመለከተ ጉዳዩ እስከ ቋሚ ሲኖዶስ ድረስ እንዲታደስ ውሣኔ የተሰጠበት ቢሆንም ሕንፃው ባለመታደሱ አስተዳደሩ ተጠያቂ ነው ተብሎ ለቀረበው ጥያቄ፤
የካቴድራሉ አስተዳዳሪ በሰጡት መልስ ካቴድራሉ እድሳት የሚያስፈልገው መሆኑ አጠያያቂ ይደለም፤ ይሁን እንጂ እድሳቱን አስመልክቶ እንዴት መታደስ እንዳለበት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ባለሙያዎች እንዲጠና አድርገን አጠቃላይ ለእድሳቱ የሚያስፈልገው ወጭ ከብር 40,000,000 (ከአርባ ሚሊዮን ብር) በላይ መሆኑን በጥናቱ ተረጋግጦ የቀረበ ሲሆን ካቴድራሉ በቅርስነት የተመዘገበ በመሆኑ እድሳቱ እንዲፈቀድልንና የበጀት ድጎማም እንዲደረግልን ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በደብዳቤ ጠይቀን ጥናቱ በድጋሚ ይሠራል ብለውን በመጠባበቅ ላይ የምንገኝ እንጂ ከሳሾች እንዳሉት ለካቴድራሉ የማንጨነቅ ግዴለሽ ሆነን እንዲሁም ዝም ብለን የተቀመጥን አይደለንም፡፡ በተጨማሪም የዕድሳቱን ወጭ በተመለከተ የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቤተ ሰቦችን አነጋገርን የእድሳቱን ግማሽ ዋጋ ለመቻል ቃል የገቡልን ሲሆን የእድሳቱን ጥናት ማጠቃለያ እየተጠባበቅን እንገኛለን በማለት መልስ ሰጥተዋል፡፡

በአጠቃላይ በጽሑፍ የቀረቡት አቤቱታዎችና በካቴድራሉ አስተዳደር በኩል የተሰጡ መልሶች ከላይ በዝርዝር የቀረበው ሲሆን አቤቱታ አቅራቢዎች በቃል ያቀረቡትን ተጨማሪ ጥያቄና መልስ እንደሚከተለው በአጭሩ አቅርበናል፡፡

በቃል የቀረቡ ተጨማሪ ጥያቄዎችና መልሶቸው፤
1.የውስጥ ዝውውር ሲፈጸም ሠራተኛው የተሻለ ቦታ የሚያገኘው በብሔር እንጂ በሙያ አይደለም ለዚህም ማስረጃው ከሙካሽ ቤቱ ጀምሮ እስከ እለት ገንዘብ ሰብሳቢ ድረስ በቅርብ የተፈጸመው ዝውውር ማስረጃ ነው በማለት ለቀረበው ጥያቄ
የካቴድራሉ አስተዳደር በሰጡት መልስ ፤ የካቴድራሉ የዕለት ገንዘብ ሰብሳቢ የነበሩት አቶ ሲራክ ወ/ሥላሴ በጡረታ ሲገለሉ የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት የተፈጸመ የውስጥ ሽግሽግ ምደባ ሲሆን ምደባው የተደረገውም ኅዳር 27 ቀን 2011 ዓ/ም በሰበካ ጉባዔው ውሣኔ ሰጭነት እንጂ አስተዳደሩ ብቻውን አይደለም፤ በተደረገው የውስጥ ዝውውር ምደባም ቅሬታ ያቀረበ አመልካች የለም፡፡ በምደባው የተሳተፉት ሠራተኞች ብሔርን መሠረት ያደረገ ነው ይበሉ እንጂ እኛ እንደ ከሳሾች ወርደን የብሔር መልስ መስጠት ስለማንፈልግ ነው እንጂ እነማን እንዶኑ ይነገር ቢባል ከሳሾች ያፍራሉ፤ በማለት የውስጥ ዝውውር ምደባ የተወሰነበትን 2 ገጽ ቃለ ጉባዔ አቅርበው አስረድተዋል፡፡

2.ሐምሌ 5 ቀን 2009 ዓ/ም ከሙዳየ ምፅዋት ቆጠራ የተገኘው ገቢ ብር 1,439,172.56 (አንድ ሚሊዮን አራት መቶ ሠላሳ ዘጠኝ ሺህ አንድ መቶ ሰባ ሁለት ብር ከሃምሳ ስድስት ሳንቲም) ቢሆንም አንድ ሚሊዮን ተቀንሶ ገቢ ተደርጓል፤ ለዚህም ብር 439,172.56 (አራት መቶ ሰላሳ ዘጠኝ ሺህ አንድ መቶ ሰባ ሁለት ብር ከሃምሳ ስድስት ሳንቲም) ብቻ ገቢ የሆነበት ደረሰኝ አለን በማለት ደረሰኙን አያይዘው ከሳሾች ያቀረቡ ሲሆን ለቀረበው ጥያቄ የካቴድራሉ ሒሳብ ክፍል በሰጡት መልስ በመጀመሪያ ጥያቄው የቀረበው በመረጃ እጥረት ወደ ከረንት አካውንት የገባውን ደረሰኝ ብቻ ይዘው ነው እንጂ ወደ ቁጠባ ሒሳብ በእለቱ የገባውን የ1,000,000 ብር ደረሰኝ ይኸው በማለት ገቢ የሆነበትን ደረሰኝ አቅርበው አስረድተዋል፡፡ እኛም አጣሪዎች የሁለቱም የገቢ ደረሰኝ የያዘ 7 ገጽ ፎቶ ኮፒ የሰነድ ማስረጃ አያይዘን አቅርበናል፡፡

3.ለሐውልት ሠራተኛ ባለሙያ ለሆነው አቶ ታደሰ ብርሃኑ ስም ሐውልት የሠሩበት የዕጅ ዋጋ 54,150 ብር አለአግባብ ሁለት ጊዜ ወጭ ሆኖ አንደኛው ወጭ ተበልቷል፡፡ በማለት ለቀረበው ጥያቄ የካቴድራሉ ሒሳብ ክፍል ኃላፊ በሰጡት መልስ የውጭ ማዘዣው ደብዳቤ የመጀመሪያው ጠፍቶ ለሒሳብ ማወራረጃ በድጋሜ ተፅፎ ይሆናል እንጂ የካቴድራሉ የሒሳብ ሰነድና የባንክ እስቴትመንት የሚያረጋግጠው አንድ ጊዜ ብቻ ወጪ እንደሆነ ነው በማለት ወጭ የሆነበትን የባንክ እስቴትመንት አቅርበው ያስረዱ ሲሆን እኛም አጣሪዎች በድጋሜ ወጭ የሆነበትን ማግኘት አልቻልንም፡፡ ይሁን እንጂ ወጭ ሆኖበታል የተባለውን ደብዳቤ አንድ ጊዜ ብቻ ወጭ የሆነበትን እስቴትመንት ለማስረጃነት 7 ገጽ ፎቶ ኮፒ አያይዘን አቅርበናል፡፡

4.የካቴድራሉ ገንዘብና ንብረት ለማባከን ከእቅድ ውጪ እየተገዛ ይከማቻል በማለት ላቀረቡት የቃል ጥያቄ እንዲያብራሩ ተጠይቀው ያለ ዕቅድ የቧንቧ መሥመርና ተያያዥ ማቴርያሎች በከፍተኛ ወጪ መገዛታቸውንና ንብረት ክፍል የተቀመጠን ቆርቆሮ የካቴድራሉ አስተዳዳሪ በስልጣናቸው ለግላቸው ወስደውታል በማለት ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ የካቴራሉ የሥራ ኃላፊዎች በሰጡት መልስ በመጀመሪያ ደረጃ የቧንቧ መስመሩና ተያያዥ ሊገዙ የቻሉት የዘንድሮው በዓል ጥምቀት ተረኛ ካቴድራሉ ስለነበረ ለጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት የሚያስፈልጉ ማቴርያሎች በሙሉ ተገዝተው እንዲሟሉ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ በቁጥር 2127/290/2011 በቀን 26/03/2011 ዓ/ም በተጻፈ ደብዳቤ በታዘዝነው መሠረት ከዋው መ/ቤት ለበዓሉ አከባበር የተዋቀረው ኮሚቴ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት የተገዛ እንጂ እንደ ከሳሾች አባባል ገንዘብ ለማባከን የተገዛ አለመሆኑን የሒሳብ ክፍል ኃላፊው ያስረዱ ሲሆን ቆርቆሮ ተወስዷል የተባለውን በተመለከተ ንብረት ክፍሉ ተጠይቆ ውሸት ነው የተባለው ቆርቆሮ አሁንም በንብረት ክፍሉ ይገኛል በማለት ምላሻቸውን የሰጡ ሲሆን በዓለ ጥምቀትን አስመልክቶ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ የተጻፈውንና ኮሚቴው ቃለ ጉባዔ ይዞ የገዛበትን የሚያስረዱ 8 ገጽ የሰነድ ማስረጃዎች በአስረጂነት ተያይዘው ቀርበዋል፡፡

5.ከክስ በኋላ የተጻፉ ማስጠንቀቂያዎችና የገንዘብ ቅጣቶችን አስመልክቶ ከከሳሾች ለቀረበው ጥያቄ ተከሳሾች በሰጡት መልስ በከሳሾ ላይ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ሊጻፍ የቻለው ክስ ካቀረብን ማን ይነካናል በማለትና ከዋናው መ/ቤት ደብዳቤ ተጽፎልናል በሚል ሽፋን በተደጋጋሚ ከምድብ ሥራቸው ላይ ስለማይገኙ ከቅርብ ተቆጣጣሪያቸው መጋቢት 23 ቀን 2011 ዓ/ም በቀረበው ሪፖርት መነሻነት የካቴድራሉ ሰበካ ጉባዔ በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት የፅሑፍ ማስጠንቀቂያና ያልሠሩበት ቀን ተሰልቶ ከደመወዛቸው ላይ እንዲቀነስ የተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፤ለማስረጃ ያህልም ግራ ቀኙ ያቀረቡትን የሰነድ ማስረጃ 12 ገጽ ፎቶ ኮፒ አያይዘን አቅርበናል፡፡

6.የዲ/ን ሀብታሙ ፀጋ ማስጠንቀቂያዎችና ቀጥሎም የተፃፈውን ዝውውር አስመልክቶ ለቀረበው የቃል ጥያቄ የካቴድራሉ የሥራ ኃላፊዎች በሰጡት መልስ
ዲ/ን ሀብታሙ ፀጋ ፡- በመጀመሪያ ደረጃ በካቴድራሉ በዲ/ን መሐሪ በርሄ የሥራ መደብ ተመድበው ሲመጡ በወቅቱ የነበረው የካቴራሉ አስተዳደር በካቴድራሉ ሊያስመድብ የሚችል የቤተ ክርስቲያን ሙያና ስነ ምግባር የሌላቸው መሆኑን በመግለፅ ለሀገረ ስብከቱ ምላሽ ቢሰጥም ሀገረ ስብከቱ የወቅቱን የካቴድራሉ አስተዳዳሪ የሊቀ ሥልጣናት አባ ገ/ሥላሴ በላይ የወር ደመወዝ በማገዱ ነገር ለማብረድ ሲባል ካቴድራሉ የተቀበላቸው መሆኑንና ተመድበው ከመጡበት እለት ጀምሮ እውቀታቸውና ሥነ ምግባራቸውን ከማሻሻል ይልቅ ያተደረገውን ተደረገ ያልሆነውም ሆነ እያሉ ሰላም በማወካቸውና በምድብ ሥራቸው ላይ በተደጋጋሚ ስለማይገኙ፤
1. በ25/04/2009 ዓ/ም የፅሑፍ ማስጠንቀቂያ
2. በ25/08/2010 ዓ/ም ከሥራ በመቅረት የገንዘብ ቅጣት፣
3. በ08/04/2011 ዓ/ም ወደ ሌላ ቦታ እንዲዛወሩ የተጻፈበት፣
4. በ22/06/2011 ዓ/ም ከሥራና ከደመወዝ የታገዱበት፣
5. በ26/07/2011 ዓ/ም ወደ ቃሊቲ መ/ብ/ርሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ተዛወረው የተመደቡት የሰነድ ማስረጃ በማቅረብ ምንም እንኳን ዝውውሩ የተፈጸመው አቤቱታው ከቀረበ በኋላ ቢሆንም ባላቸው የሥነ ምግባር ችግር እንዲዛወሩልን የጠየቅነው ግን ጥር 16 ቀን 2011 ዓ/ም ተፅፎ የቀረበው አቤቱታ ከመቅረቡ ከአንድ ወር በፊት ታህሳስ 8 ቀን 2011 ዓ/ም በተጻፈ ደብዳቤ በመሆኑ ክሱን በሽፋንነት መቅረቡ አግባብ አይደለም በማለት መልስ የሰጡ ሲሆን ከሳሾ ያልተገባ ቁጥጥር ይደረግብናል በማለት ያቀረቡትን ቅሬታ በተመለከተ በሰጡት ምላሽ የሥራ ቁጥጥሩን ልናጠናክር የቻልነው ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በቁጥር 671/482/2011 በቀን 10/7/2011 ዓ/ም በተጻፈ ደብዳቤ ጥብቅ ቁጥጥር እንድናደርግ በተላለፈልን መመሪያ መሠረት ነው፤ በማለት የማጠቃለያ መልሳቸውን ሰጥተዋል፤ እኛም የግራ ቀኙን የሰነድ ማስረጃ 24 ገጽ አያይዘን አቅርበናል፡፡

የማጣራት ሥራው ከላይ በዝርዝር የቀረበውን ሲመስል ከቀረበው ዝርዝር ሀሳብ እና አስረጅ የሰነድ ማስረጃ በመነሳት ለእያንዳንዱ ክስ ተከታዩን አስተያየት አቅርበናል፤
የአጣሪዎች ማጠቃለያ አስተያየት

1.የሠራተኛ ቅጥርና ምደባው ብሔርን መሠረት ያደረገ ነው ተብሎ የቀረበው አቤቱታ በተመለከተ ቅጥሩም ሆነ ምደባው የሚፈጸመው በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እንደመሆኑ መጠን የካቴድራሉን የሥራ ኃላፊዎች የማይመለከት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ሆን ተብሎ የአንድ ብሔር ሰዎችን ለመመደብ ታስቦ የተደረገ አለመሆኑን ለማረጋገጥ ችለናል፤

2.የውስጥ የሥራ መደብ ሽግሽግን አስመልክቶ በብሔር ላያ የተመሠረት ነው ተብሎ የቀረበው አቤቱታም ቢሆን የዕለት ገንዘብ ሰብሳቢው ጡረታ በመውጣቱ የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት የተደረገ የውስጥ ሽግሽግ እንጂ ሆን ተብሎ አንዱን ጎድቶ ሌላውን ለመጥቀም የተደረገ አለመሆኑን ከሰበካ ጉባዔው የቃለ ጉባዔ ውሣኔና የመድረክ ማጣራቱን ለማረጋገጥ ችለናል፤
3.የካቴድራሉ ሠራተኞች ለአባይ ግድብ ያዋጡትን ገንዘብ አስመልክቶ የቀረበው አቤቱታ በተመለከተ ትክክለኛውን መረጃ ባለማወቅ የቦንድ ሰርተፍኬቱን ብቻ በማየት የቀረበ አቤቱታ መሆኑን ለማረጋገጥ ችለናል፤

4. ለሀብት ቆጠራና ለመሬት ልኬት ለባለሙያ የተከፈለውን ገንዘብ አስመልክቶ የቀረበውን አቤቱታ በተመለከተ፡- የደብል ኢንትሪ የሂሳብ አያያዥ መመሪያ ያለውን አስገዳጅነት ካላመረዳትና እንዴት እንደተከፈለ በቂ ማስረጃ ሳይኖር እንዲሁም የቀረበ አቤቱታ መሆኑን አረጋግጠናል፤

5.ሃያ ሁለት ማዞሪያ ያለውን የካቴድራሉን ሕንፃ ግንባታ አስመልክቶ ሀገረ ስብከቱ ሳያውቅ ተብሎ በአቤቱታው ላይ የተጠቀሰውን በተመለከተ የቀረቡት የሰነድ ማስረጃዎ እንዲያስረዱት በቅዱስ አባታችን አባታዊ መመሪያ ሰጭነት ሀገረ ስብከቱም የቅድመ ኪራይ ክፍያ እንዲሰበሰብ በደብዳቤ ከተፈቀደ በኋላና የዋጋ ተመን አጥንቶ የሚያቀርብ ኮሚቴ ተሰይሞ የአካባቢው ዋጋ ተጠንቶ በቀረበው ሪፖርት መሠረት የተፈጸመ እንጂ ከሀገረ ስብከቱ እውቅና ውጪ የተባለው አግባብነት የሌለው ሲሆን በማጣራቱ ወቅት ሦስት ግለሰቦች እኛን በአግባቡ አላሳተፉንም በማለት ቅሬታ ያቀረቡልን ስለሆነ በቀጣይ ለትክክለኛ ፍትህ ይረዳ ዘንድ የሀገረ ስብከቱ ተወካይ በተገኙበት አፈጻጸሙ ቢቀጥል የተሻለ መሆኑን ለማሳሰብ እንወዳለን፤

6.የካቴድራሉን ማኅተም አቀማመጥ በተመለከተ እንደ አዲሰ አበባ ሀገረ ስብከት አድባራትና ገዳማት ነባራዊ ሁኔታ ሲታይ አብዛኛው የጽ/ቤቱ ማኅተም የሚቀመጠው የደብሩ ዋና ፀሐፊ እጅ ቢሆንም በ2009 ዓ/ም ለ4ኛ ጊዜ ተሻሽሎ በወጣው ቃለ ዓዋዲ አንቀጽ 17/5/ ላይ ማኅተሙ ተመልተክናል፡፡ በመዝገብ ቤት ይቀመጣል በማለት በተደነገገው በመዝገብ ቤት መቀመጥ ሲገባው በጸሐፊው እጅ መቀመጡ አግባብት የሌለው መሆኑን ተመልክተናል፡፡ ይህ እንዲህ እንዳለ የሐውልት ሥራ ገቢን አስመልክቶ የቀረበውን አቤቱታ በተመለከተ ሀገረ ስብከቱና ካቴድራሉ ተወያይተው ዘለቄታዊ መፍትሄ ቢሰጡት የተሻለ መሆኑን ለማሳሰብ እንወዳለን፤

7. ጠፋ ስለተባለው ወርቅና ዳይመንድ በተመለከተ በንብረት ክፍሉና በሳጥን ቁልፍ ያዡ መካከል መካካድ ስላለ በቀጣይ ሀገረ ስብከቱ ጥልቅ ክትትል አድርጎ የማስተካከያ እርምት እንዲሰጥበት አመራር ቢሰጠው የተሻለ መሆኑን ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡

8.የባለ ወልድ ሁለገብ ሕንፃና የመጠለያ ግንባታን አስመልክቶ የቀረበውን በተመለከተ የግንባታ ዋጋው ሊጨምር የቻለው ሕንፃው አስቀድሞ ከነበረው የG+1 ዲዛይን ወደ G+4 በማደጉ የተፈጠረ የዋጋ ልዩነት እንጂ በአስተዳደር ሰራተኞች ችግር አለመሆኑን በሰነድ ማስረጃ የተረጋገጠ ሲሆን የዘገየውን እርክክብ በተመለከተ የፍርድ ቤቱ ክርክር እዳለቀ ቀሪ ሥራዎ ተጠናቀው ርክክቡ በፍጥነት እንዲፈጸም ለካቴድራሉ አስተዳደር መመሪያ ቢተላለፍ፤
9.የአብነት ት/ቤቱን አስመልከቶ የቀረበውን አቤቱታ በተመለከተ ለመቃብር ፉካ ተብሎ የቀረበው ማስረጃ የሌለው ሲሆን ዝርዝር የግንባታ አፈጻጸሙንና የዛፍ አቆራረጡን በተመለከተ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤትም ሆነ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አስቀድመው ጉዳዩን እንዳወቁት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት አመራርና ድጋፍ ሰጥተውት ቢሆን ኖሮ ችግሩ ላይከሰት ይችል የነበረ ሲሆን በቀጣይ ሊሆን የሚገባውን በተመለከተ ቦታው አስቀድሞም መ/ምስጢር ልሳነወርቅ ብሩ ጉባዔ ቤት ተክለው ሲያስተምሩበት የነበረ ከመሆኑም አንፃርና የከፍተኛ ባለሥልጣናቱና የአርበኞች ቀብር ቦታውን ሊወረው ከመሆኑም በላይ የአብነት ት/ቤት ከሚሰጠው ጠቀሜታ አንጻር ታይቶ ቅዱስ ሲኖዶሱ አመራር ቢሰጥበት የተሻለ መሆኑን እያሳሰብን የካቴድራሉ አስተዳደር ጽ/ቤቱም በቀጣይ ከቦታው ታሪካዊነት አንጻር እንዲህ አይነት ጉዳዮች ሲከሰቱ ብቻውን ከመተግበር ይልቅ የበላይ አካልን ዘወትር እያማከረ መሥራት እንዳለበት ዛፎቹ ከመቆረጣቸውም በፊት ለሀገረ ስብከቱ የተጻፈው ደብዳቤ ምላሽ እስኪሰጠው መጠበቅ የነበረበት መሆኑን ተገልጾ በቀጣይ እንዳይደገም ጥብቅ አመራረ ቢሰጠው፤

10. የካቴደራሉ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት መምህርት ለሆኑት ለወ/ሮ ኖላዊት መካ የተጻፈውን የቋሚነት የድጋፍ ደብዳቤ በተመለከተ ሠራተኛዋ ምንም እንኳን በመጀመሪያ ደረጃ በኮንትራት የሥራ ውል የተቀጠሩ ቢሆንም በ2010 ዓ/ም በተፈጸመው የውል ማደሻ ፎርም ላይ ኮንትራት የሚል የጊዜ ገደብ የሌለው ቢሆንም እንዲ ዓይነቱ ጥንቃቄ የጎደለው አሠራር የአሠራርክፍተት ያለበት መሆኑን ለማየት ችለናል፡፡

11. የሰበካ ጉባዔ ተማራጭ አባላት ለውጥንና የስብሰባ ተሳትፎን አስመልክቶ የቀረበውን በተመለከተ አባላቱ የተለወጡት በቃለ ዓዋዲው አንቀጽ 10 ንዑስ ቁጥር 2/ለ/5 መሠረት እድሜያቸው ከ60 ዓት በላይ የሆናቸው መመረጥ አይችሉም በሚለው ድንጋጌ መሠረት በአስመራጭ ኮሚቴው ውሳኔ የተለወጡ እንጂ እንደ ክስ አቀራረቡ በአስተዳደሩ የተለወጡ አለመሆኑን የተመለከትን ሲሆን የሰበካ ጉባዔ አባላቱ በስብሰባ እየተገኙ አይወስኑም የተባለውን እራሳቸው የሰበካ ጉባዔ አባላቱ ሀሰት መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

12.የሰንበት ት/ቤቱ ተወካይ መታገድን በተመለከተ ለቀረበው አቤቱታ ከምንም በላይ በጀመሩት አግባብ በሰላምና በአንድነት ተስማምቶ መሥራቱ አማራጭ የሌለው ቢሆንም እንኳን ከሰነድ ማስረጃዎች ለመረዳት እንደቻልነው ግለሰቡ ሊታገድ የቻለው ደረጃ በደረጃ ምክር ከተሰጠ በኋላ እንደሆነ ቃለ ጉባዔ 7 ገጽ ከበላይ አካል የተጻፉት ደብዳቤዎች ስለሚያስረዱ እግዱ ከእውነት የራቀ ነው ለማለት አይቻልም፡፡

13. የሠራተኛ ደመወዝ ጭማሪ አስመልከቶ አድሎ ተፈጽሟል ተብሎ የቀረበው አቤቱታ በተመለከተ፤

ሀ. በመጀመሪያ ደረጃ ደመወዝ የሚጨመረው ወይም አግባብነቱ ተመርምሮ የሚጸድቀው በሀገረ ስብከቱ እንጂ በካቴድራሉ አስተዳደር አለመሆኑን፤

ለ. ሁለት ደመወዝ የሚያገኙ አሉ የተባለው ሁለት ደመወዝ የሚበላ የሌለ መሆኑን የተረጋገጠ ሲሆን ተደርበው ለሚሠሩ የሙያ ሥራዎ ግን መጠነኛ አበል የሚከፈል መሆኑን፤

ሐ. በሊቀ ብርሃናት ሐዋዝ ተበጀ ላይ የደመወዝ ጭማሪ ታልፈዋል ተብሎ የቀረበው ጭማሪ የተደረገበት ቃለ ጉባዔ ቀርቦ ጭማሪ መደረጉ የተረጋገጠ በመሆኑን አቤቱታው በማስረጃ የተደገፈ አለመሆኑን አይተናል፡፡

14. የካቴድራሉ አስተዳደር አለአግባብ 20 ሠራተኞች እንድንቀይር ለበላይ አካል ደብዳቤ ጽፏል፤ ስለተባለው አቤቱታ በተመለከተ ምንም እንኳን የሠራተኛ ይቀየርልኝ ጥያቄው ደብዳቤ የተጻፈው አቤቱታ ከመቅረቡ በፊት ሳይሆን አቤቱታው ከመቅረቡ በፊት ሳይሆን አቤቱታው ጥር 16 ቀን 2011 ዓ/ም ከቀረበ በኋላ የካቲት 25 ቀን 2011 ዓ/ም መሆኑ በሰነድ ያረጋገጥን ሲሆን በደብዳቤው ላይም እንዲዛወሩ የተጠየቁት 20 ሳይሆን 5 ሠራተኞ መሆናቸውን አረጋግጠናል፡፡

15.የካቴድራሉ ሰንበት ት/ቤት አባላት ከሁለት ግሩፕ መከፈላቸውን አስመልክቶ ለቀረበው አቤቱታ በተመለከተ በርግጥም የሰንበት ት/ቤቱ ተወካይ የነበረው ወጣት ኃ/ገብርኤል እንዳለ እስከ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ ድረስ ጉዳዩ ቀርቦና ተጣርቶ ሲታገድ እርሱን የሚመስሉ ተባባሪዎች ግሩፕ ፈጥረው በመውጣታቸው ሰንበት ት/ቤቱ ለሁለት እንደተከፈለ ስለሚያሳይ በቀጣይ የሰላምና የውይይት መድረክ ተፈጥሮና ልዩነት ተወግዶ ወደ አንድነት እንዲመጡ ቢደረግ የተሸለ መሆኑን እናሳስባለን፡፡

16. ለበዓለ ጥምቀትና ለ75ኛው ዓመታዊ ክብረ በዓል ሊሠራ የነበረው ጥንግ ድርብና ሌሎች መገልገያዎችን አስመልክቶ የቀረበውን አቤቱታ በተመለከተ፤ ካቴድራሉ ሥራው እንዲሠራ ከባለሙያው ጋር ተዋውሎና ቅድመ ክፍያም 73,000 ብር የከፈለ ቢሆንም ውሉን የወሰደው ባለሙያ በተባለው ጊዜ ገደብ ሠርቶ ሊያስረክብ ባለመቻሉ በዓሉ ካለፈ በኋላ ካቴድራሉ ውሉን በመሰረዝ የከፈለው ገንዘብ ከ5,000 ብር መቀጫ ጋር እንዲመለስ ስለተደረገ ችግሩ የባለሙያው እንጂ የካቴራሉ አስተዳደር አለመሆኑን አረጋግጠናል፡፡
17.የታሪካዊውን ካቴድራል እድሳት አስመልክቶ የቀረበውን አቤቱታ በተመለከተ ምንም እንኳ ካቴድራሉ እድሳቱን አስመልክቶ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የእድሳት ጥናት ባለሙያዎ ያስጠናና ጥናቱንም እድሳቱን ለሚፈቅደው ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ያቀረበ ቢሆንም በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተሰጠው የድጋሜ ይጠና አመራር ተፋጥኖ ወደ እድሳት እንዲገባ በማድረግ በኩል ካቴድራሉ ዘገምተኝነት የታየበት በመሆኑ በቀጣይ ጥብቅ ክትትል በማድረግ የዕድሳት ሥራው በፍጥነት እንዲጀመር ቅዱስ ሲኖዶዱ አመራር ቢሰጥበት፤

18.ሐምሌ 5 ቀን 2009 ዓ/ም ከሙዳየ ምፅዋት ቆጠራ የተገኘው ገቢ ላይ 1000,000 (አንድ ሚሊዮን ብር) ገቢ ሳይሆን ቀርቷል፤ ተብሎ ከከሳሾች በቃል የቀረበውን አቤቱታ በተመለከተ ከላይ የተጠቀሰው ገንዘብ በዕለቱ በሞዴል 64 ናምራ ቁጥር 00311312 ሐምሌ 5 ቀን 2009 ዓ/ም ገቢ መሆኑ እስከ ባንክ ደረሰኙ ድረስ ማስረጃ የቀረበ ስለሆነ አቤቱታው በመረጃ እጥረት የቀረበ መሆኑን አረጋግጠናል፤
19. ለሐውልት ሥራ ባለሙያ ሁለት ጊዜ ተከፍሏል ተብሎ የቀረበውን አቤቱታ በተመለከተ ባደረግነው የሰነድ ማጣራት የካቴድራሉ የባንክ ስሊፕ እንደሚያስረዳው አንድ ጊዜ ብቻ የተከፈለ መሆኑን ለማየት ችለናል፡፡

20.የዲ/ን ሀብታሙ ፀጋ ማስጠንቀቂያና ዝውውርን አስመልክቶ የቀረበውን አቤቱታ በተመለከለተ ከላይ በሪፖርቱ በዝርዝር እንደተገለጸው ከቀድሞው የካቴድራሉ አስተዳዳሪ ጀምሮ ደረጃ በደረጃ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያና የገንዘብ ቅጣት ውሳኔ ሲሰጠው ቆይቶ በመጨረሻም አቤቱታ ከመቅረቡ በፊት የካቴድራሉ አስተዳደር በቀን 08/04/2011 ዓ/ም ወደ ሌላ ቦታ እንዲዛወር ለሀገረ ስብከቱ በጻፉት ማሳሰቢያ መሠረት በሀገረ ስብከቱ አዘዋዋሪነት በመጀመሪያ ደረጃ በጽርሐ ጽዮን ጎላ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በምክትል ተቆጣጣሪነት ከተመደቡ በኋላ ወዲውኑ ያለበቂ ምክንያት ወደ ቃሊቲ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በጀቱ ተቀንሶ በዲቁና የሥራ መደብ ተዛውረው ተመድበው እያሉ አሁንም ያለምንም በቂ ምክንያት በአሁኑ ሰዓት በብሥራተ ገብርኤል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በዲቁና ሙያ ተመድበው በማገልገል ላይ መሆናቸውን ከማህደረ ጉዳያቸው ያረገጋገጥን ሲሆን ይን እንጂ በግለሰቡ ላይ በተከታታይ የተፈጸመባቸው ዝውውር ፍትሃዊነት የጎደለው በመሆኑ በመጀመሪያው የዝውውር ምደባ መሠረት በም/ተቆጣጣሪነት የሥራ መደብ እንዲሠሩ ቢደረግ የተሸለ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
21. የሒሳብ አሠራርና ከንብረት አያያዝ ጋር ተያይዞ የቀረቡትን አቤቱታ በተመለከተ በቀጣይ ዘለቄታዊ መፍትሄ መስጠት ይቻል ዘን ካቴድራሉ ኦዲት እንዲደረግ አመራር ቢሰጥት የተሸለ መሆኑን ለማሳሰብ እንወደለን፡፡

በመጨረሻም የተከበረው ቅዱስ ሲኖዶስ ከላይ በዝርዝር ያቀረብነውን የማጣራት ሪፖርት በጽሞና ተመልክቶ ተገቢነው ያለውን ውሳኔ እንዲሰጥበት በታላቅ አክብሮት እየጠየቅን ይህ በእንዲህ አንዳለ ከጽሑፍ ሪፖርቱ በተጨማሪ ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት እስከ ምሽቱ 3፡00 ሰዓት ድረስ ዝርዝር የማጣራት ሂደቱን በሙሉ ቪዲዮ የተቀረጸ ስለሆነ የቪዲዮ ማስረጃውንም እንደ ግብአት መጠቀም እንደሚችል እየገለጽን በግራ ቀኙ የቀረበውን ልዩ ልዩ የሰነድ ማስረጃ 584 ገጽ አያይዘን ያቀረብን መሆናችንን እንገልጻለን፡፡

ሪፖርት አቅራቢዎች
1. አፈ መምህር አባ ገ/ሥላሴ ጌትነት
2. ሊቀ ኅሩያን ሰርጸ አበበ