በዓላትን ማክበር ያለብን ያጡትንና የተቸገሩትን በማሰብ/በመርዳት መሆን እንዳለበት ተገለፀ

001

የትንሣኤን በዓል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን ሞትን በመስቀል ላይ ከተቀበለ በኋላ በሦስተኛው ቀን መግነዝ ፍቱልኝ፣ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል ከሙታን ተለይቶ የተነሣበት ዕለት ነው፡፡

የትንሣኤውም ዓላማ የሰው ልጅ በመቃብር ፈርሶ በስብሶ አለመቅረቱን ለማስረዳት፣ ክርስቲያኖች ከሞት በኋላ ተስፋ ትንሣኤ እንዳለን ለማጠየቅና ከወደቅንበት ኃጢአት በንስሐ መነሣት እንዳለብን ለማስተማር መሆኑን መገንዘብ ይገባናል፡፡

በቤተክርስቲያናችንም እነዚህ ታላላቅ ዓላማዎች ያሉት የትንሣኤ በዓል በደመቀ ሁኔታ እንደሚከበር ይታወቃል፡፡ ምክንያቱም ጠላቶቻችን ሞትና ሰይጣን ድል የተነሡበት፣ የሰው ልጅም ከሰይጣን ባርነት ነጻ የወጣበት፣ በአዳምና በሔዋን ምክንያት በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የነበረው የጥል ግድግዳ የፈረሰበት፣ የድል፣ የነጻነትና የሰላም ዕለት ስለሆነ ነው፡፡ ስለዚህም በቤተክርስቲያናችን የትንሣኤ ሰላምታ የተለየ ነው፡፡ ይኸውም፡-

ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን. . . በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን አሰሮ ለሰይጣን. . . አጋዐዞ ለአዳም ሰላም . . . እም ይእዜሰ ኮነ . . . ፍስሐ ወሰላም የሚል ነው፡፡

እንግዲህ ይህንን በዓል በየዓመቱ ስናከብር ዓላማውን ዘንግተን በዓሉን የምግብና የመጠጥ ብቻ እንዳናደርገው መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ በልዩ ልዩ መንገድ በፈቃዱ የሰይጣን ባሪያ የሆነ፣ ከክርስቲያናዊ ምግባርና ትሩፋት የራቀ ሁሉ ራሱን እንዲመረምርና ለመልካም ሥራ እንዲነሣ የሚያደርግ በዓል መሆኑን ተረድተን ራሳችንን ልናስተካክል ያስፈልጋል፡፡ በዓለም በሥጋ ሥራ በመመላለስ የምንኖር ከዚህ ሥራችን በልቦና ትንሣኤ ተነሥተን የንስሐ ፍሬ የምናፈራበት እንዲሆን ልንተጋ ይገባናል፡፡ ክርስትናችን በስም ብቻ ተወስኖ በዓለም በሥጋ ሥራ የምንኖር ደግሞ ራሳችንን በመመርመር በንስሐ ታጥበንና ታጥነን ትንሣኤውን ቅዱስ ሥጋውን፣ ክቡር ደሙን በመቀበል እናክብረው፡፡

ሁልጊዜም በዓሉን ከነዳያን ጋር እየተካፈልን የምንኖር መልካም ልማድ ያለን የትሩፋት ሥራችንን እያሳደግን፣ በሃይማኖትና በምግባርም እየበረታን ልንሔድ ያስፈልጋል፡፡ ክርስትና ሠላሳ፣ ስድሳና መቶ ፍሬ የምናፈራበት የዕድገት ጉዞ እንጂ በምንሠራት ጥቂት የትሩፋት ሥራ ብቻ ረሥተን የምንቆምበት አይደለምና በትሩፋት ላይ ትሩፋት፣ በጸጋ ላይ ጸጋ እየጨመርን መሔድ ይገባናል፡፡

{flike}{plusone}

ትንሣኤውን በማሰብ ነዳያንን የምናስፈስከውም የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና ማኅበራትም ሁልጊዜ በሬ እያረዱ ፋሲካውን ማክበር ብቻ ሳይሆን፤ ነዳያኑንና ወጥተው ለመለመን አፍረው በየቤቱ የተቀመጡ ወገኖቻችንን ጭምር በማስታወስ እንዲሁም በልማት የሚያሳትፍ ሥራ ወደመሥራት በማደግ ችግረኞቹን በዘላቂ ልማት ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ ይገባናል፡፡ ከዚህም ሌላ ነዳያኑን በዚህ ዓለም በሥጋ ስላጡ በነፍሳቸው በመንፈሳዊ ሕይወት እውቀት አግኝተዋል ማለት ስላልሆነ፤ በነፍሳቸው የእግዚአብሔር መንግሥት ወራሾች እንዲሆኑ መንፈሳዊውንም ምግብ ልንመግባቸው ያስፈልጋል፡፡

በአጠቃላይ በዓሉን በምናከብርባቸው ዕለታት ሁሉ ነገረ መስቀሉን በማሰብ፣ መልካም ሥራን በመሥራትና በትሩፋት ላይ ትሩፋት በመጨመር፣ በንስሐ እንዲሁም በንጽሕና ቅዱስ ሥጋውን፣ ክቡር ደሙን በመቀበል ይሁን፡፡

000

በዚሁም መነሻነት ነው የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጽ/ቤት የትንሳኤን በዓል ምክያት በመድረግ ከ850 በላይ የሚሆኑ ነዳያንን ለመርዳትና ለመመገብ የካቴድራሉ ሰንበት ት/ቤት ከካቴድራሉ ምግባር ሠናይ ክፍል ጋር በማስተባበርና በማቀናጀት የትንሣኤን በዓል ምክንያት በማድረግ የሰንበት ት/ቤቱን አባላት፣በሰንበት ት/ቤቱ በመማር ላይ የሚገኙትን የተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን እንዲሁም የአጥቢያውን ምእመናን በማስተባበር ገንዘብ እና አልባሳት በማሰባሰብ ነዳያንን የሚረዳው፡፡ በዚህም ዓመት ግንቦት 4ቀን 2005 ዓ.ም የሰንበት ት/ቤቱን አባላት፣ የ4 ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ጉባኤ የተማሪዎች፣ የ4 ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ጉባኤ ተማሪዎችን፣ የዳግማዊ ምኒልክ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ግቢ ጉባኤ ተማሪዎችን፣ የሲ.ፒ.ዩ ኮሌጅ ግቢ ጉባኤ ተማሪዎችን እንዲሁም በካቴድራሉ አጥቢያ የሚገኙ ምዕመናንን እና በጎአድራጊ ግለሰቦችን በማስተባበር ገንዘብ እና አልባሳት በማሰባሰብ፣

1. በካቴድራሉ ምግባረ ሠናይ ክፍል ለሚጦሩ 12 አረጋዊያን ቤታቸው በመገኘት፣

2. ከ600 በላይ የሚሆኑ ነዳያንን በሰንበት ት/ቤቱ አዳራሽ በመሰብሰብ፣

3. በምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም እና በእንጦጦ ሐመረ ኖህ ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን አካባቢ በመኪና በመዘዋወር ከ300 በላይ የሚሆኑ የእለት ጉርስ የሚሹ እና የሚለብሱት የሌላቸው ችግረኛ ነዳያን ወገኖቻችን እንዲረዱ የተደረገው፡፡

ተርቤ አብልታችሁኛል፥ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና… ኑ ያዘጋጀሁላችሁን መንግሥት ውረሱ ማቴ. ፳፭፥፴፬ – ፴፭

በመሆኑም የካቴድራሉ አስተዳደር ክፍሎችን በመወከል ተገቢ መልካም የሥራ ትብብር ላደረጉ ሁሉ በልዑል እግዚአብሔር ስም ምስጋናውን ያቀርባል፡፡

እንዲሁም በየዓመቱ ትብብራቸውን ለማይለየን ምዕመናን ከፍ ያለ ምስጋና ለማቅረብ እንወዳለን፡፡ ወደፊትም እገዛችሁ እንዳይለየን በአጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ ስም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

                        ማሳሰቢያ

የካቴድራሉ አረጋውያን መርጂያ  አገልግሎት ከዛሬ 45 ዓመታት በፊት ከዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት ጀምሮ በንጉሱ አማካኝነት በካቴድራሉ በጎ አድራጎት /ምግባረ ሠናይ ክፍል ሥር በቃለ ዓዋዲ መሠረት የተቋቋመ ሲሆን ቀደም ሲል በብዙ መልኩ የተደራጀ እንደነበር የሚነገር ሲሆን አሁንም በካቴድራሉ አስተዳደር አማካኝነት እንደቀድሞ ለማጠናከር ከፍተኛ የሆነ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ በመሆኑም በዘላቂነተ የአረጋውያኑ ችግር በመጠኑ ለመቅረፍ አቅማችሁ የፈቀደውን/የቻላችሁትን ያህል እርዳታ እንድታድርጉ እናሳስባለን፡፡ አረጋውያኑ ከሚያስፈልጓቸው መሠረታዊ ነገሮች መካከል፡-

1. ምግብ፣

2. መጠለያ፣

3. ንጽህና፣

4. ልብስና

5. ሞግዚት ሲሆኑ የቦታው ጉዳይ በተመለከተ አሁን አረጋውያኑ ያሉበት ቤትና አጠገቡ ያለውን ቦታ ከካቴድራሉ ጽ/ቤት ጋር በመነጋገርና በማስፈቀድ በዘመናዊ መልኩ ቤቱ መሥራት ከመቻሉም በላይ አቅም በፈቀደ መጠን ተጨማሪ ረዳት አልባ አረጋውያንና ሕፃናት መርዳት ይቻላል፡፡

የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን አሜን፡

{flike}{plusone}