የብፁዕ አቡነ አረጋዊ ሥርዓተ ቀብር በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጸመ

d4250

የብፁዕ አቡነ አረጋዊ የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የበላይ ሓላፊ ሥርዓተ ቀብር ዛሬ ጥር 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ሲያገለግሉበት በነበረው በዚሁ ታላቅ ካቴድራል ቅዱስ ፓትርያርኩ፤ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነትና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የመምሪያ ሓላፊዎች፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን በተገኙበት ተፈጸሟል፡፡
ከጸሎተ ፍትሐቱ በኋላ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በሰጡት ቃለ ምእዳን “ብፁዕ አቡነ አረጋዊ ሕይወታቸውን ሁሉ ለእግዚአብሔር የሰጡ፤ እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ፤ ሲያከብሩ የኖሩ፤ ሃይማኖትን ጠብቀው ያስጠበቁ አባት ነበሩ” ብለዋል፡፡

በሥርዓተ ቀብራቸው የተነበበው የብፁዕነታቸው የሕይወት ታሪክ እንደሚከተለው እናቀርባለን፡-
ዜና ሕይወቱ ወሞቱ ለብፁዕ  አቡነ አረጋዊ ሊቀ ጳጳስ
1. ብፁዕ አቡነ አረጋዊ በ1901 ዓ.ም ተወልደው እድሜአቸው ለትምህርት ሲደርስ ትምህርት ቤት ገብተው ንባብና ዳዊት ተምረው እንዲሁም እስከ ፀዋትወ ዜማ ያለውን የቤተ ክርስቲያናችንን ትምህርት አጠናቅቀው ከብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ግብጻዊ ዲቁና እና መዓረገ ክህነት ተቀብለዋል፡፡ ወደ ዋልድባ አብረንታት ገዳም ሔደው ከ1933 እስከ 1942 ዓ.ም ድረስ ለዘጠኝ ዓመታት ያህል ሥርዓተ ገዳሙን ከአጠኑ በኋላ በዚሁ ታላቅ ገዳም መዓረገ ምንኩስናን ተቀብለው በደብረ ዓባይ ገዳም የደብረ ዓባይ መዝገበ ቅዳሴ ዜማን ተምረው ለመምህርነት በቅተዋል፡፡
2. በ1943 ዓ.ም በብፁዕ አቡነ ባስልዮስ ትእዛዝ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማትን እንዲያገለግሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተልከው ለ4 ዓመታት ያህል ካገለገሉ በኋላ በቅዱስ ፓትርያርኩ ፈቃድ ወደ ግብፅ ሔደው ለ16 ዓመታት ያህል የዓረብኛ ቋንቋና ነገረ መለኮትን ተምረዋል፡፡
3. ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በሱዳን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን በኃላፊነት ለማገልገል ተልከው ለ6 ዓመታት ያህል አስተዳዳሪ ሁነው ሠርተዋል፡፡ በዚሁም ኃላፊነት ሳሉ በ1968 ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ሁነው በተሾሙ ጊዜ በሱዳን የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያንን ወክለው በመምጣት ለበዓሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡
4. በ1972 ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በቅዱስ ፓትርያርኩ ፈቃድ የመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሊቀ ሥልጣናት ተብለው በማስተዳደር ላይ እያሉ በ1983 ዓ.ም በሱዳን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ሆነው ተሾመዋል፡፡
5. ከመጋቢት 1985 ዓ.ም ጀምሮ የኢሉባቦርና ጋምቤላ አኅጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ለአንድ ዓመት ያህል ሠርተዋል፡፡
6. ከየካቲት 1986 ዓ.ም ጀምሮ የምስካዬ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳምና ት/ቤት የበላይ ኃላፊ ሆነው ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡
7. ከሐምሌ 1986 ዓ.ም ጀምሮ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ሠርተዋል፡፡
8. ከግንቦት 1992 ዓ.ም ጀምሮ ወደ አዲስ አበባ ተዛውረው የመንበረ ጸበዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የበላይ ኃላፊ ሆነው እንዲሠሩ ተደርጓል፡፡
በመጨረሻም በዚሁ ሥራ ላይ ሳሉ ባደረባቸው ድንገተኛ ሕመም ምክንያት በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ጥር 1 ቀን 2007 ዓ.ም በተወለዱ በ106 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ ተለይተዋል፡፡ በቀብራቸውም ሥነ ሥርዓት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በተገኙበት፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ባሉበት፣ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ካህናት ተገኝተው በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት ጸሎተ ፍትሐቱ ከተፈጸመ በኋላ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የብፁዕነታቸው የቀብር ሥነ ሥርዓት ተፈጽሟል፡፡

{flike}{plusone}