በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ መሰናዶ ት/ቤት የውሃ ማጣሪያ ማሽን ተገጥሞ ሥራ ላይ ዋለ

0001

የውሃ ማጣሪያ ማሽኑ እስፕላሽ ኢንተርናሽናል ከሚባል ግብረ ሰናይ ድርጅት በእርዳታ የተገኘ ሲሆን ለዚሁ ሥራ ከ120,000.00 ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበት የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሚሊዮን ገልጸዋል፡፡

ማሽኑ የተለያዩ ጀርሞችና ቆሻሻን በሚገባ ከመከላከሉም በላይ የምንጠጣው ውሃ ጥሩ ጣዕም እንዲኖረው እንደሚያደርግም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

በዚሁ የምረቃ ፕሮግራም ላይ የተገኙት ክቡር ሊቀ ሥልጣናት አባ ገ/ሥላሴ የካቴድራሉ ዋና አስተዳዳሪ በበኩላቸው ባስተላለፉት መልእክት እግዚአብሔር ውሃውን ንጹህ አድርጎ የፈጠረ ሲሆን ነገር ግን የሰው ልጅ በተለያየ ሰው ሰራሽ ነገሮች ውሃ እንደሚበከል ገልጸው ሆኖም ግን እግዚአብሔር ለሰው ልጅ በሰጠው ጸጋ ሳይንሱንና ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ይህንን የመሰለ የውሃ ማጣሪያ ተሰርቶ አገልግሎት ላይ በመዋሉ የሚያስደስት መሆኑን ገልጸዋል ፡፡

በመሆኑም ማሽኑ በሰው ሰራሽ ነገሮች እንዳይበላሽ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግበት እንደሚገባ አባታዊ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡ አያይዘውም ይህንን የመሰለ እርዳታ ላደገው ለእስፕላሽ ኢንተርናሽናል ድርጅትና ሃላፊዎች በካቴድራሉ ስም ከፍተኛ የሆነ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ በቀጣይም በተለያዩ የመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ የድርጅቱ ትብብር እንደማይለያቸው እምነታው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከሊቀ ሥልጣናት በመቀጠል ንግግር ያደረጉት የካቴድራሉ ዋና ፀሃፊ ክቡር ሊቀ ስዩማን ወንደወሰን ቱሉ ሲሆኑ የካቴድራሉ አስተዳደር ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ሳይውልና ሳያድር ስራው እንዲሰራ ከመፍቀዱም በላይ በድርጅቱ በኩል የተጠየቀውን የተወሰነ ወጪ በካቴድራሉ ወጪ ተደርጎ በአስቸኳይ ሥራው እንዲሰራ በማድረግ ካቴድራሉ ከፍተኛ የሆነ የሥራ ትብብር ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

ከክቡር ዋና ፀሃፊው በመቀጠል ንግግር ያደረጉት ወ/ት ቤተልሔም የሴቭ ሄቨን ድርጅት የአገር ውስጥ ተጠሪ ናቸው ወ/ት ቤተልሔም እንደገለጹት በካቴድራሉ ት/ቤት 96 ተማሪዎችን ድርጅታቸው እየረዳቸው እንደሚያስተምሩ ገልጸው የውሃ ማጣሪያ ማሽን እርዳታ ያደረገው የድርጅት ኃላፊዎች ት/ቤቱን እንዲያዩት በመጋበዝ እርዳታው በእሳቸው ጋባዥነት ሊገኝ እንደቻለ ገልጸዋል፡፡ ንጹህ ውሃ ለሰው ልጅ ሊሰጠው የሚችለውን አገልግሎት በሰፊው አብራርተዋል፡፡

በመጨረሻም በክቡር ሊቀ ሥልጣናት አባ ገ/ሥላሴ በላይ የካቴድራሉ ዋና አስተዳዳሪ አማካኝነት የውሃ ማጣሪያ ማሽኑ ተባርኮና ተመርቆ የበአሉ ፍጻሜ ሆኗል፡፡

{flike}{plusone}