ቅ/ሥ/ካቴድራል

ቤተክርስቲያን

የቤተክርስቲያን ቅድመ ታሪክ በአጭሩ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በርካታ ቋሚና ተንቀሳቃሽ የሆኑ ሃይማኖታዊ ትውፊትና ታሪካዊ ቅርሶችን ጠብቃ የያዘች ናት፡፡ ይህም ማለት በሕንጻ ግንባታና ከድንጋይ ተፈልፍለው የታነፁ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፡ ገዳማትና ታሪካዊ ሐውልቶች፣ የሥነ ጽሑፍ፣ የዕደ ጥበብ፣ የተለያዩ ንዋየ ቅዱሳትና የሌሎችም ቅርሶች ባለቤት መሆኗ ግልጽ ነው፡፡እነዚህ ደግሞ በዓለም አስደናቂ ከሆኑት ነገሮች መካከል በታሪካዊነታቸው ተመዝግበው የሚገኙ ናቸው፡፡

የቅድስት ሥላሴ ካቴድራልም ከእነዚሁ አስደናቂ ታሪኮች አንዱ አካል ነው፡፡ ካቴድራሉም በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ዓለም ዓቀፋዊ ይዘት ያለውና አንጋፋ ካቴድራል ነው፡፡

ከታሪካዊነቱም በተጨማሪ፡-

 • ዓለም አቀፋዊ የኃይማኖት ስብሰባዎች ይካሄድበታል፣
 • የፓትርያሪኮችና ጳጳሳት በዓለ ሲመት ይከናወንበታል፣
 • ብሔራዊ የመታሰቢያ በዓላትና ሥርዓተ ፀሎት ይካሄድበታል፡፡

የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ታሪክ

የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አመሠራረት

የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የተመሠረተው ታኅሣሥ 15 ቀን 1924 ዓ.ም. እንደሆነ ታሪካዊ ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ፡፡ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ የክርስትናው እምነት እንዲስፋፋና እንዲጠናከር የሀገራቸውም ዕድገትና ሥልጣኔ ከፍ ካለ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ከነበራቸው ቀና አመለካከትና ፅኑዕ ፍላጎት በመነሳትና የውጭውንም ዓለም ሥልጣኔ መልካም አርአያነት አብነት በማድረግ ይህን ዓለም አቀፍ ይዘት ያለውን ካቴድራል ለመመሥረት/ለመሥራት በቅተዋል፡፡

በዚህም ጊዜ አያሌ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና መኳንንት በዚሁ የመሠረት ድንጋይ የማኖር ከፍተኛ ሥነ ሥርዓት ላይ የታደሙ ከመሆኑም በላይ 113ኛው የእስክንድርያ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ዮሐንስ 19ኛ የሥነ ሥርዓቱ ተሳታፊ በመሆን ቡራኬ ሰጥተው የመሠረት ድንጋዩም በግርማልነታቸው ተጥሏል፡፡

የሕንፃ ግንባታው ስለመጀመሩ፡-

የሕንፃ ሥራው በንጉሠ ነገሥቱ ከፍ ያለ አጽንዖት ተሰጥቶበት እየተፋጠነ የበርና የመስኮት መግጠም ሥራ ብቻ ሲቀር የፋሽሽት ኢጣሊያ የግፍ ወረራ በመከሠቱ ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም. ድረስ ለአምስት ዓመታት የሕንፃ ግንባታው ተቋርጦ ቆይቷል፡፡ ቢሆንም በሥላሴ ኃይልና ቸርነት ግርማዊ ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ በድል አድራጊነት ወደ ውድ ሀገራቸው በተመለሱ በ2ኛው ዓመት በ1935 ዓ.ም. ሥራው እንደገና ቀጥሎ ተፋጥኖ በመሠራቱና ፍጻሜ በማግኘቱ ጥር 7 ቀን 1936 ዓ.ም. ሥራው እንደገና ቀጥሎ ተፋጥኖ በመሠራቱና ፍጻሜ በማግኘቱ ጥር 7 ቀን 1936 ዓ.ም. ቅዳሴ ቤቱ ከፍ ባለ ሥነ ሥርዓትና በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል፡፡

የቤተክርስቲያኑ ስም ለውጥ

በ1939 ዓ.ም. መካነ ሥላሴ መባሉ ቀርቶ ሥራው የተራቀቀ አስገራሚ ሆኖ በመኘቱ በሰማያዊት ኢየሩሳሌም አምሳል መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ተብሎ ሲሰየም አስተዳዳሪውም ሊቀ ሥልጣናት እንዲባል ተወሰነ፡፡

የመጀመሪያውም ተሻሚ መምህር መልእክቱ በኋላ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ናቸው፡፡ ይህ ዘመናዊ ካቴድራል ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት የተሻለ በመሆኑ ሕዝቡ በብዛት መጉረፍ ጀመረ፡፡ በዚህም ምክንያት በጣም ሰፊ ነው የተባለው ቤተክርስቲያን በድጋሚ ሊጠብ ቻለ፡፡ የሕዝቡ ቅሬታ ከመሰማቱ በፊት የቤተክርስቲያኑ አስተዳደር የንጉሠ ነገሥቱን ትዕዛዝ በመቀበል የሕንፃው ቁመትና ስፋት እንዲጨመር፣ ጌጣጌጡም የተሻለ ዘመናዊ እንዲሆን በዩኒዬን ኢንጂነሪንግ አጥኝነት በሥራ ሚኒስቴር ተቆጣጣሪነት በ1957 ዓ.ም. ሥራው ለሁለተኛ ጊዜ ተጀመረ፡፡
ሥራው ከልዩ ልዩ ዓለማት በመጡ የሕንፃ ጠበብትና በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ተቆጣጣሪነት 36 ሜትር በ12ዐዐ ካሬ ሜትር የወለሉ ስፋት፣ ከምሥራት ወደ ምዕራብ 36 ሜትር ከሰሜን ወደደቡብ 26 ሜትር፣ ቁመቱ 35 ሜትር ሆኖ ለ3 ዓመታት ያህል በጥራት ሲሰራ ከቆየ በኋላ በ196ዐ ዓ.ም. ተጠናቆ ጥር 7 ቀን በደማቅ ሥነ ሥርዓት ቅዳሴ ቤቱ ተከበረ፡፡

አዲሱ ሥራ ብዙ ውስጣዊ መሻሻሎችን ያካተተ ሆኖ ተገንብቷል፡፡ ይኸውም የንዋየ ቅድሳት፣ የአልባሳት፣ የመጻሕፍት አና ልዩ ልዩ ቅርሶች ማስቀመጫ በምሥራቅ በኩል ባለው ምድር ቤት የተዘጋጀ ሲሆን በምዕራብ አቅጣጫ ባለው ምድር ቤት ደግሞ የዕቃ ግምጃ ቤት፣ የማጥመቂያ ክፍሎች በዘመናዊ መልክ ተዘጋጅቶውለታል፡፡

ወደ ላይ ሲወጣ ደግሞ በፎቕ መልክ የተሠራው ቅኔ ማኅሌት የሕንፃውን ጠበብት በሚያስመሰግን ሁኔታ ተሰርቷል፡፡ በዚህ ድርብ ሥር የቤተክርስቲያኑ መሥራች ታላቁ ንጉሠ ነገሥት ግርማዊ ቀዳማዊ ዓፄ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ለልዩ ልዩ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ቋሚ መታሰቢያ እንዲሆን በጦር ሜዳ ለወደቁና ለሕያዋኑ ጦር ውለታቸውን ለመግለጥና በሕገ መንግሥቱ በ15ኛው ክፍል የተመለከተውን አይተው ይህንኑ ለመፈጸም፡፡

 • 1ኛ. ከ1927-1933 ዓ.ም. ያለውን የጦር ሠራዊት ሰንደቅ ዓላማ፣
 • 2ኛ. የክብር ዘበኛ ሰንደቅ ዓለማ፣
 • 3ኛ. ከ1927-1933 ዓ.ም. በጦር ሜዳ ለወደቁ ጀግኖች ሰንደቅ ዓላማ ሲሆኑ በኋላ በሀገሪቱ የተመሠረተውን ጠንካራ የአየር ሃይል፣ የባህር ኃይልና የምድር ጦር ሠራዊትን ለማክበር የተሰቀለውን ሰንደቅ ዓላማ በ4ቱም ባንዲራዎች ላይ የሥላሴ ኒሻን ያለው ተተክሎ እንዲውለበለብ በመፍቀዳቸው ሰንደቅ ዓላማዎቹ በመዘክርነት ይኖራሉ፡፡

በዚህ ካቴድራል ውስጥ አያሌ ሥዕሎች ስለነፃነት የተደረጉ ታሪካዊ ሂደቶችን በማመላከት በተለያዩ ክፍሎች ተሥለው ለትውልድ የታሪክ አሻራነታቸውን በማስተላለፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ ቅኔ ማኅሌቱ ለዘወትር ግልጋሎት የሚሰጥ ሲሆን በዓላት በሚከበሩበት ጊዜ ስለሚጠብ ከሕንፃው ሰሜን አቅጣጫ ባለው ሰፊ ክፍል በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ሊቃውንት ከተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ስለሚመጡ ሥርዓተ ማህሌቱ በተጠቀሰው ቦታ ሲካሄድ ያድራል፡፡

ከቅኔ ማህሌቱ ታች ያለው ቦታ በብዙ ሺህ የሚቆጠር ሕዝብ ይይዛል፡፡ ከቅድስቱ መግቢያ በስተቀኝ የንጉሠ ነገሥቱ ዙፋን በግራ በኩል የእቴጌ መነን ዙፋን በከበረ እንጨትና በአማረ ጌጣጌጥ ተሰርተው በታሪክነት ተቀምጠዋል፡፡ በግራ በኩል ሰሜን አቅጣጫ የንጉሡና የእቴጌይቱ መቃብር በከበረ ድንጋይ ተገንብቷል፡፡ ቃላቱ ንጉሠ ነገሥት እንደቀደምት አባቶቻቸው ነገሥታት አንድነትንና ሦስትነትን ለማስተማር በሥላሴ ስም ይህን ካቴድራል ሲያሰሩ ከራሳቸው ጀምሮ ንጉሣውያን ቤተሰብ ሁሉ ማረፊያው በዚሁ ቅዱስ ቦታ እንዲሆን በመመኘትም ጭምር መሆኑ አይካድም፡፡ መቅደሱ ሦስት መንበሮች ያሉት ሲሆን መካከለኛው በአጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ ስም የተሰየመ ሆኖ ከወርቅ፣ ከብር፣ ከዝሆን ጥርስና ከወይራ እንጨት የተሠራ ነው፡፡
በመንበሩ ላይ ልዩ ልዩ ስዕሎች፣ ንጉሣዊ ዘውድ፣ መላእክት፣ ምሴተ ሐሙስ፣ የሰሎሞን ኒሻን፣ የንግሥት ሳባ ኒሻንና የጰራቅሊጦስ ሥዕል እንዲሁም የጌታችንና የመድነኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የወርቅ ሥዕል የወይን፣ የስንዴ ቅርፅን አካቶ በመያዝ የቤተክርስቲያናችንን እምነትንና ታሪካዊነት በሰፊው ይገልጻል፡፡ የአርባዕቱ እንስሳ ቅርጽም በ4ቱ ማዕዘን አለ፡፡

ከዋናው ቤተመቅደስ በስተቀኝ በቅድስት ማርያም የተሰየመው መንበር በስተደቡብ ይገኛል፡፡ ስያሜውም የሥላሴን ሦስትነት ለማወቅ ነው፡፡
ከዋናው መቅደስ በስተግራ በቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ የተሰየመው መንበር በስተሰሜን ይገኛል፡፡ በቅዱስ ዮሐንስ የተሰየመበት ምክንያት አንድነት ሦስትነት የታወቀው ከጥምቀት በኋላ መሆኑን ለማዘከር ነው፡፡

አገር ጐብኝዎች

በካቴድራሉ ግራና ቀኝ የማስታወቂያ ግድግዳዎች ላይ እጅግ ማራኪ የሆኑ ስለ ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን ታሪክ የሚያስረዱ ሥዕላት ይገኛሉ፡፡ እንዲሁም በግድግዳ ላየ የተሳሉ ታሪካዊ መንፈሳዊ ሥዕሎችም ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ሥዕሎች በኢትዮጵያዊ ታዋቂ ሠዓሊ በአገኘሁ እንግዳ የተሣሉ ናቸው፡፡

መቃብሮች

የጃንሆይና የባለቤታቸው የእቴጌ መነን መቃብሮች በካቴድራሉ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ መቃብሮቹ ሦስት ታሪካዊ ነገሮችን ያንፀባርቃሉ እነርሱም፡-

 • የአክሱም ሀውልትን፣
 • አንድ የላሊበላ ውቅር ቤተክርስቲያን፣
 • የይሁዳ አንበሳ፣

ዙፋኖች

 • በካቴድራሉ ቅድስት ውስጥ የጀንሆይና የእቴጌ መነን ዙፋኖች ይገኛሉ፡፡

እስከ አሁን የተሾሙ የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አስተዳዳሪዎች (ከ1935 -2004)

 1. ሊቀ ሥልጣናት አባ መልእክቱ /ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ/1935-1938/
 2. ሊቀ ሥልጣናት አባ ቄርሎስ ተስፋዬ /አቡነ ቄርሎስ/ /1949-1954/
 3. ሊቀ ሥልጣናት አባ ሀ/ማርያም ወርቅነህ /አቡነ መልከፄዲቅ/1954-1966/
 4. ሊቀ ሥልጣናት አባ መዓዛ ቅዱሳን /1966-1967/
 5. ሊቀ ሥልጣናት ዶ/ር አባ ሀ/ሥላሴ ተስፋ /አቡነ ጤሞቲዎስ//1968-1969/
 6. ሊቀ ሥልጣናት አባ ኤልያስ አበበ /አቡነ ኒቆዲሞስ/ /1969-1971/
 7. ሊቀ ሥልጣናት ገብረማርያም ፈለቀ /አቡነ ፊሊጶስ/ /1971-1973/
 8. ሊቀ ሥልጣናት አባ ገ/ሥላሴ ኃ/ማርያም /አቡነ አረጋዊ/1973-1979/
 9. ሊቀ ሥልጣናት ተክለሚካኤል ዓባይ /አቡነ ሚካኤል/ከ1979-1980/
 10. ሊቀ ሥልጣናት አባ ዳንኤል ባሳዝነው/1980-1984/
 11. ሊቀ ሥልጣናት አባ ገብረ ማርያም አጽብሐ /ቆሞስ/1986-1989/
 12. ሊቀ ሥልጣናት አባ አምኃሥላሴ አሳየኸኝ / አቡነ ኢጲፋንዮስ/1989-1990/
 13. ሊቀ ሥልጣናት አባ ሐረገወይን ገብረ ሥላሴ /አቡነ ሠላማ/1991-1996/
 14. ሊቀ ሥልጣናት አባ ገብረ ክርስቶስ ስብሐት /ቆሞስ/1996-1998/
 15. ሊቀ ሥልጣናት አባ ጥዑመ ልሳን ኪዳነማርያም /ቆሞስ/1998-2004/
 16. ሊቀ ሥልጣናት አባ ገ/ሥላሴ በላይ/ቆሞስ/ ከ2004-2006 ዓ.ም
 17. ሊቀ ሥልጣናት አባ ኪሮስ ፀጋዬ /ቆሞስ/ ከ2006-2008 ዓ.ም
 18. ሊቀ ሥልጣናት አባ ገ/ዋህድ ገ/ኪዳን 2010 ዓ.ም ጀምሮ

ዓ.ም ጀምሮ