የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተ መዘክር (ሙዚየም)

አደረጃጀትና ይዘት በአጭሩ

ቀደም ባሉት ጊዜያት ካቴድራሉ በሙዚየምነት ሲጠቀምበት የነበረው ከካቴድራሉ ቤተ መቅደስ አንደር ግራውንድ (ምድር ቤት) የሚገኘውን የዕቃ ግምጃቤት እንደ ነበረ ቀደምት ታሪኩን እናስታውሳለን፡፡ ይህ ደግሞ ከምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን መጠበቅና ሥርዓት አንፃር ቦታው ለጉብኝቱ ሂደት አመች አልነበረም፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ባላቸው ፅኑዕ እምነት፣ ለቱሪዝም ዕድገትና መስፋፋት በነበራቸው ከፍ ያለ ራዕይና ከውጭው ዓለም ተሞክሮ በመነሣት ባደረባቸው መንፈሳዊ ቅንዓት በመነሳሳት በተከበሩ በከCረ ምዕመናን ከበደ ተካልኝ በግል ገንዘባቸው ተሠርቶ በበጎ አድራጎት ለሥላሴ ከተሰጠው ዘመናዊ የሙዚየም ሕንፃ ቅርሶቹ ተዛውረው ከተደራጁ በኋላ ጥር 6 ቀን 1998 ዓ.ም. በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም፣ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚዳንትና የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዚዳንት ቡራኬ ተመርቆ ከተከፈተበት ጊዜ ጀምሮ ከቱሪዝም መዳረሻዎችና መስህቦች አንዱ ክፍል ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡

በዚህም ደረጃውን በጠበቀ ዘመናዊ ሙዚየም ውስጥ በጥሩ አደረጃጀትና ጥበቃ ተይዘው በመጎብኘት ላይ ያሉ በርካታ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ቅርሶች ይገኛሉ፡፡ እነዚህም ውድና ማራኪ የሆኑ ቅርሶች በዋጋ ሊተመኑና በምንም ሁኔታ ሊተኩ የማይችሉ ናቸው የተሰጡትም ከቀድሞ ነገሥታት፣ ከእቴጌዎቹ፣ ከብፁዓን አባቶች፣ ከቤተ መንግሥት ልዑላንና ልዕልቶች፣ ከቀድሞ ከመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ከበጎ አድራጊ ክርስቲያኖችና ከ5ቱ አኅት ዐቢያተ ክርስቲያናትም ጭምር ሲሆን ደኅንነታቸውም ለረጅም ዘመናት በሚባ ተጠብቆላቸው ከዚህ ትውልድ ደርሰዋል፡፡

የተሠሩትም ከወርቅ፣ ከብር፣ ከነሐስና ከመሳሰሉት ማዕድናት ሲሆን የወርቅና የብር ቅቦችንም ያጠቃልላል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ከጥልፍ (ሙካሽ) ሥራ የተዘጋጁ የቤተ መቅደስ አልባሳት፣ ድባብ ጥላዎችና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ይልቁንም በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ በተለያዩ ጸሐፍትና አርእስት በግእዝ ቋንቋ የተጻፉ በርካታ ሃይማኖታዊ የብራና ቅዱሳት መጻሕፍትም የዚሁ ሙዚየም ታዳሚዎች ናቸው፡፡

ከእነዚህም ቅዱሳት መጻሕፍት መካከል በ6ኛው መ/ክፍለ ዘመን በቅ/ያሬድ በ8 የዜማ ምልክቶችና በ3 የዜማ ቅኝቶች ከተደረሱት አምስቱ የዜማ መጻሕፍት ውስጥ አንዱና ከ5ዐዐ ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆረጠው ድጓ ተብሎ የሚታወቀው መጽሐፍ በይዘቱም ሆነ በጣዕመ ዜማው በእጅጉ ከሚመስጡትና ከሚያስደንቁት ዋነኛው ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንም ከእነዚህ ከ3ቱ ቅኝቶች ውጭ የሆኑ የዜማ ስልቶች የሏትም አትጠቀምም፡፡ ቅኝቶቹም ዘመን የማይሽራቸው ጊዜ የማይገድባቸውና የማይሰለቹ ሰማያዊ ስጦታዎች ናቸው፡፡

በተጨማሪም ሀገራችን ኢትዮጵያ ከመንፈሳዊው ምንጭ የተቀዳ የራሷ የሆነ ፊደል፣ አኃዝ (ቁጥር)፣ ቀናትና አዝማናት መቁጠሪያ (ካላንደር) ያላት በመሆኗ ከሌላው የዓለም ክፍል ይልቅ በዚህ መንፈሳዊና ሥጋዊ ጥበቧ የተለየች ያደርጋታል፡፡

የሙዚየሙ ዋና ዓላማ

 • 1.    ሃይማኖታዊና ታሪካዊ የሆኑትን የቤተክርስቲያን ቅርሶች በሙዚየም ውስጥ በማደራጀት በልዩ ጥበቃና እንክብካቤ ይዞ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር ጐብኝዎች በማስጐብኘት የቤተክርስቲያኒቱን ታሪካዊ ገጽታ በዓለም ደረጃ እንዲታወቅ ማድረግ፣

እነዚህኑ አስደናቂ ታሪኮችንና ሃይማኖታዊ ቅርሶችን በጥንቃቄ ጠብቆ በመያዝ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ነው፡፡

ከእነዚህም መካከል ለአብነት ያህል በየክፍላቸው መድበን እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡

1ኛ. ከታሪካዊ ቅርሶች

 • የነገሠታቱ የቤተ ክርስቲያን ውስጥ የክብር ዙፋኖች፣
 • የነገሥታቱ የአርበኝነት አልባሳት፣
 • በሞዛይክ ቅርፅ የተዘጋጀ የአፄ ኃይለ ሥላሴ ምስል (ፖርትሬት) እና ሌሎችም፣

2ኛ. ከሃይማኖታዊ ቅርሶች

 • በተለያየ ዲዛይን የተሠሩ መስቀሎች፣
 • ልዩ ልዩ ጽዋዎችና ጻሕሎች ከነእርፈ መስቀሎታቸው፣
 • የተለያዩ ወርቀ ዘቦና የብር ጥልፍ (ሙካሽ) ሥራ ካባዎችና ድባብ ጥላዎች፣
 • የተለያዩ የብራና ቅዱሳት መጻሕፍት ገበታቸው በወርቅና በብር የተለበጡ ጭምር፣
 • ከዕንቀ፣ ከብርና ከሞዛይክ የተሠሩ ቅዱሳት ሥዕላት፣ ሥነ-ስቅለትና የመሳሰሉት ይገኛሉ፣

የሰጭዎቹም ዘርዝር

 • ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና ከሌሎችም አባቶች፣
 • ከዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ፣
 • ከቀ አፄ ኃይለ ሥላሴ፣
 • ከንግሥት ዘውዲቱ፣
 • ከእቴጌ ጣይቱ፣
 • ከእቴጌ መነን፣
 • ከልዑላትና ከልዕልቶቹ፣
 • ከቀድሞ ቤተ መነግሥት ባለሥልጣናት፣
 • ከበጎ አድራጊ ክርስቲያኖች፣
 • ከአኀት አብያተ ክርስቲያናትና ከሌላም

እነዚህም ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ቅርሶች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ይልቁንም ባለሀብቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚገባ ጠብቆና ተንከባክቦ ለቱሪዝም ሴክተሩ እንቅስቃሴ ቢጠቀምባቸው በብዙ መልኩ ከፍ ያለ ሀገራዊ ፋይዳ ይኖራቸዋል እንላለን፡፡ሙሉውን መረጃ ለማግኘት መጥታችሁ ትጐበኙ ዘንድ ቤተ ክርስቲያናችን በአክብሮት ትጋብዛችኋለች፡፡