የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ት/ቤት

በ1955 ዓ.ም. መስከረም 14 ቀን በማታ ፕሮግራም ሥራውን የጀመረው የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ት/ቤት በወቅቱ የተቀበላቸው ተማሪዎች 8 ብቻ ሲሆኑ እነዚህን መነኮሳትና ዲያቆናት ነበሩ፡፡ በ1956 ዓ.ም. ከ1ኛ እስከ 4ኛ ባሉ ቁጥራቸው 39 የሚደርሱ ተማሪዎችን ይዞ የመደበኛ ትምህርት ጀመረ፡፡ በዚያን ጊዜ የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ት/ቤት “የኢትዮትያ ኦርቶዶክስ ሐዋርያዊ ድርጅት” በመባል ይታወቅም ነበር፡፡

ት/ቤቱን ለመክፈት ያስፈለገበት ዓላማም የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ዘመናዊ ትምህርት እንዲያገኙ ታስቦበት ሲሆን ለዚህም ተግባራዊነት የጥንቱ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ት/ቤት የ1ኛና 2ኛ ደረጃ ት/ቤት መዘጋቱ ለት/ቤቱ በዚያን ወቅት መጀመር ተጽዕኖ እንደነበረው ይነገራል፡፡ የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዘመናዊ ት/ቤት ሊቋቋም የተጠና ዓላማ ይዞ ነበር፡፡

ይኽም ዓላማ ካህናትን ዘመናዊ ትምህርት ለማስተማር ነው፡፡ በወቅቱ ለነበሩ መነኮሳትና ዲያቆናት የዘመናዊ ትምህርት እንዲማሩ ማድረግ በቀላሉ የተከናወነ ሳይሆን በወቅቱ የነበሩ የካቴድራሉ የበላይ አስተዳዳሪዎች ጥብቅ ቁጥጥርና እርምጃ እያደረጉ የቤተክርስቲያኑ አገልጋዮች ት/ቤት ገብተው እንዲማሩ በማድረጋቸው ነበር፡፡

ምንም እንኳ ት/ቤቱ በተጀመረበት ወቅትና ከዚያ ቀጥሎ ባሉት ዓመታት በት/ቤቱ በየዓመቱ ይማሩና ያስተምሩ የነበሩ መምህራን የመማሪያ ክፍሎች ብዛትና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ሠራተኞችና ክፍሎች በስርዓቱ መረጃ ባለመያዙ ምክንያት በዚሁ ጽሑፍ ውስጥ ለማቅረብ የተሞከረው የተገኘው መረጃ ብቻ ነው፡፡

ተ.ቁ ዓ.ም. የተማሪ ቁጥር የመምህራን ቁጥር
1 1955 8 የማታ ተማሪ ብቻ አልታወቀም
2 1956 39 መደበኛ ተማሪ አልታወቀም
3 1958 3ዐዐ ተማሪዎች አልታወቀም
4 1964 425 ተማሪዎች 15
5 1965 78ዐ ተማሪዎች 20
48 2003 2354 ተማሪዎች 34

ቀደም ሲል ለቀሳውስት መነኮሳትና ዲያቆናት ዘመናዊ ትምህርት እንዲያገኙ ታስቦ የተቋቋመው የካቴድራሉ ት/ቤት አገልግሎቱን ወደ ሌላው የህብረተሰብ ክፍል እንዲዳረስ አድርጓል፡፡ የቤተክርስቲያኗ አንዱ ዓላማ ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት ሲሆን ልጆቻቸው እንዲማሩላቸው ይጠይቁ የነበሩ ችግረኛ የህብረተሰብ ክፍሎች ያለክፍያ እንዲማሩ ሲደረግ በአካባቢ የነበሩ ጫማ ጠራጊዎች፣ መጽሔትና ጋዜጣ ሻጮች የትምህርት ዕድሉን እንዲያገኙ ተደርጓል።

ቀደም ሲል በት/ቤቱ ይሰጥ የነበረው ሥርዓተ ትምህርት

  • የቤተ ከርስቲያን ታሪክ
  • የመጽሐፍ ቅዱስ
  • የኃይማኖት ትርጓሜ
  • ቅኔና ዜማ

ከዘመናዊ ሥርዓተ ትምህርቶች ጋር ይሰጥ ስለነበረ ት/ቤቱ ታዋቂነትና ዝና ያገኘው በጣም በፈጠነ ሁኔታ ነበር፡፡ ለዚህም በዋነኝነት ሲጠቀስ የሚችለው ተማሪዎች በትምህርት ችሎታቸው በትህትናቸውና በሥርዓት አክባሪነታቸው ተለይተው ስለሚታወቁና ይኸም የህብረተሰቡን ትኩረት መቆጣጠር በመቻሉ ነበር፡፡

የተማሪዎች ቁጥር ሲጨምርና ት/ቤቱም ሲያድግ ተማሪዎች መጠነኛ ክፍያ እንዲከፍሉና የተሻለ የትምህርት አገለግሎት እንዲያገኙ ከህብረተሰቡ ጥያቄው በመቅረቡ በ1962 ዓ.ም. መጠነኛ ክፍያ-አምስት ብር-እንዲከፈል ተወስኖ ከዚያ ጀምሮ ትምህርት በክፍያ ሆነ፡፡
ት/ቤቱን ፈላጊው ሕብረተሰብ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥሩ እየጨመረ በመሄዱና ማስተናገድ ከሚችለው በላይ በመሆኑ የተማሪ ቅበላ የሚከናወነው በየዓመቱ ኮሚቴ እየተቋቋመ ኮሚቴው በሚያወጣው የመቀበያ መስፈርት አማካይነት ነበረ፡፡

ት/ቤቱ መጀመሪያ ሲቆረቆር ይዞት የነበረው ቦታ አሁን የካቴድራሉ ጽ/ቤት ጀርባ በነበሩ ክፍሎተ ነበር፡፡ የተማሪ ቁጥር እያደገ ሲሄድ ደግሞ አሁን 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ያለበትን ቦታ ይዞ እስከ 1968 ዓ.ም. ድረስ 12ኛ ክፍል ደረጃ አድርሶና 12ኛ ክፍል በዚሁ ት/ቤት አንድ ጊዜ የብሔራዊ ፈተና አስፈትኖ በወቅቱ በተደረገበት ተጽዕኖ ደረጃው ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ባለው ደረጃ በቻ እንዲሆን ተደረገ፡፡

የ1966 ዓ.ም. አብዮትን ተከትሎ የመጣው ሥርዓት በት/ቤቱ ዕድገት ላይ ተጽዕኖ ቢኖረውም በእርሾነት እንዲቆይና ለዛሬው ደረጃ እንዲደርስ የካቴድራሉ አስተዳዳሪዎችና ሠራተኞች ከፍተኛ ጥረትና መስዋዕትነት መክፈላቸው የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ይኸም በመሆኑ ዛሬ የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ት/ቤት በሦስት የትምህርት ዕርከኖች ወይም ደረጃዎች ተደራጅቶ በርካታ ወጣቶችን እያስተማረ ይገኛል፡፡ እነዚህም ት/ቤቶች፡-

  • 1.    አፀደ ህፃናት
  • 2.    የ1ኛ ደጃ ት/ቤት
  • 3.    የ2ኛ ደረጃ እና መሰናዶ ት/ቤቶች ናቸው፡፡

በ2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎችን እንደገና ማስተናገድ የጀመረው በ1ኛ ደረጃው ት/ቤት በ1996 ዓ.ም 9ኛ ክፍል በመክፈት ነበር፡፡
በ1997 ዓ.ም. አዲስ ያሰራውን ህንፃ ለ2ኛ ደረጃና ኮሌጅ መሰናዶ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተናገደ ይገኛል፡፡

በመሆኑም ት/ቤቱ በአሁኑ ጊዜ ከመዋዕለ ሕጻናት እስከ ኮሌጅ መሰናዶ ድረስ ከ2,000 ያላነሱ ተማሪዎችን እየተቀበለ ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት በመስጠት ላይገኛል፡፡ከትምህርቱ ጥራትም የተነሳ ተማሪዎች በሁሉም ብሔራዊ ፈተናዎች ከፍተኛ ውጤት እያመጡ ከደረጃ ወደ ደረጃ እያለፉ ስለመጡ የመንበረ ጸበዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ት/ቤት በተገልጋዩ ህብረተሰብ ዘንድ በአዲሰ አበባ ከሚገኙ እውቅ ት/ቤቶች አንዱ ለመሆን በቅቷል፡፡በዚህም ምክንያት ት/ቤቱ በአሁኑ ጊዜ ለህብረተሰቡ እየሰጠ ያለው ት/ት ካቴድራሉን ብቻ ሳይሆን የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክርስቲያንም የሚያኮራና የሚያስመሰግን ት/ቤት ሆኗል፡፡