በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የአንድነት ጉባኤ መርሃ ግብር ተካሄደ

0005

የካቲት 14 እና 15 2007 ዓ.ም ብፁአን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና ሊቃውንት ቤተ ክርስቲያን በተገኙበት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ  ልዕኮ ዋና ክፍል አስተባባሪነት የአንድነት ጉባኤው ተጀምሯል፡፡ በዚሁ የአንድነት ጉባኤ መርሃ ግብር ላይ የተለያዩ መምህራን ወቅቱን አስመልክተው ለምዕመናን ትምህርተ ወንጌል የሰጡ ሲሆን እንደዚሁም ወቅቱን የተመለከቱ የተለያዩ  መዝሙሮች በተለያዩ ዘማሪያን ቀርበዋል፡፡
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልዕኮ ዋና ክፍል አስተባባሪነት የተጀመረው ይህ የገዳማት እና   አድባራት የአንድነት ጉባዔ የተጀመረው የካቲት 14 ቀን 2007 ዓ.ም በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል  ሲሆን የዚሁ ዓይነት ጉባዔም በሁሉም የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት ሊካሄድ እንደሚችል ታውቋል፡፡ የአንድነት ጉባዔው ምደባ  ከሶስት አድባራት እስከ አስር አድባራት የሚያጠቃልል  እንደሆነም ነው የተገለፀው፡፡
የዚህ ዓይነት የአንድነት ጉባኤ ቀደም ሲል ሲካሄድ የነበረ ቢሆንም ለተወሰነ ጊዜ የአንድነት ጉባዔው ተቋርጦ የነበረ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ ይሁን እንጂ የአንድነት ጉባዔው ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት፤ ምዕመናንን ወደ ንስሐ ለማቅረብና በሃይማኖታቸው ጸንተው እንዲኖሩ ለማድረግ የአንድነቱ ጉባኤ መቀጠል ጠቀሜታው እጅግ የጎላ በመሆኑ የክፍላተ ከተማ  የስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊዎች እና የሀገረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌል ዋና ክፍል ባደረጉት የጋራ ምክክርና ውይይት ቀደም ሲል ተጀምሮ የነበረው የአንድነት ጉባዔ በማህበረ ካህናትም ሆነ በማህበረ ምዕመናን ዘንድ እጅግ ተወዳጅ የነበረ መሆኑን በማውሳት ለወደፊቱም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል በማለት ስምምነት ላይ የተደረሰ በመሆኑ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትም በጉዳዩ ላይ ትኩረት በመስጠት ለሁሉም አድባራት ባስተላለፈው መመሪያ መሠረት  የአንድነት ጉባዔው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን  ጾም ምክንያት በማድረግ ጉባዔው በሰባቱም ክፍላተ ከተሞች ተጠናክሮ እንዲቀጥል በመደረግ ላይ ነው፡፡ የአንድነቱ ጉባዔ የሚካሄድባቸው ቀናት በየሳምንቱ ቅዳሜ እና እሁድ እየተከተለ ሲሆን በተለይም በርካታ ምዕመናን የሚገኙባቸውን ወርሃ በዓላት እና ዓመት በዓላትን ምክንያት በማድረግ ነው፡፡
 የስብከተ ወንጌል አገልግሎት እንዲሰጡ የሚጋበዙ መምህራነ ወንጌል በገዳማት  እና  አድባራት ጽ/ቤት ጠያቂነት ከጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ በየገዳማቱ  እና  አድባራቱ  ተመድበው የሚያገለግሉ ሰባክያነ ወንጌል እና በትሩፋት የሚያገለግሉ የወንጌል አገልጋዮች ናቸው፡፡ መነሻውን ከመንበረ ፀበኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ያደረገው ይህ ዐቢይ የአንድነት ጉባኤ በተለያዩ ገዳማት  እና  አድባራት  የሚከናወን ሲሆን መጋቢት 26 እና 27/2007 ዓ.ም በቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም ካቴድራል እንደሚካሄድ ለማወቅ ተችሏል፡፡

{flike}{plusone}