የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖ 2ኛ ዓመት በዓለ ሲመት ተከበረ

0019

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት 2ኛ ዓመት የፕትርክና በዓለ ሲመት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የካቲት 24 ቀን 2007 ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ የሃይማኖት መሪዎች፤ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት፤ አምባሳደሮች፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያ ኃላፊዎች፤ የድርጅት ኃላፊዎች፤ የኮሌጅ ኃላፊዎች፤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፤ ሠራተኞች፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ካህናት፤ ምዕመናንና ምዕመናት በተገኙበት በታላቅ መንፈሳዊ ድምቀት ተከብሯል፡፡
ቅዱስነታቸው በበዓሉ ላይ በሰጡት ቃለ ምእዳን “የእግዚአብሔር መንግሥት ማእከል የሆነችው ቤተ ክርስቲያን ጌታችን በሐዋርያት እንድትጠበቅ አድርጓል፡፡ ሐዋርያትም በበኩላቸው በተኳቸው ጳጳሳት እና ቀሳውስት ጠባቂነት ቤተ ክርስቲያን እንድትመራና እንድትጠበቅ አድርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ሐዋርያዊት፤ አንዲትና ቅድስት እንደመሆኗ መጠን ከመጀመሪያው አንስቶ መንፈሳዊውን ጥበቃ በጳጳሳትና በቀሳውስት ስታከናውን ኖራለች፡፡ አሁንም እያከናወነች ነው፤ ወደፊትም በዚሁ ትቀጥላለች” ብለዋል፡፡
ቅዱስነታቸው አያይዘውም ጳጳሳትና ቀሳውስት የተሰጣቸውን የጠባቂነት ሚና አስመልክቶም “ይሁንና በዘመናችን እየተነሳ ያለው መሠረታዊ ጥያቄ የእግዚአብሔር መንግሥት ተጠሪ የሆኑት ጠባቂዎች ሓላፊነታቸውን በሚፈለገው ሁኔታ እየተወጡ ነው ወይ? የሚለው ጥያቄ በአሁኑ ጊዜ ዓለም አቀፋዊና የወቅቱ ጥያቄ ሆኖ ይገኛል፡፡ የእግዚአብሔር መንጋ የሆኑት ክርስቲያኖችን በባሕር ማእበል ሞገድ እንደሚናጥ መርከብ በጥርጣሬ እየተናጡ አጉል መንገድ ላይ እንዲቀሩ እያደረገ ነው፡፡ ከመንጋው ተነጥሎ እንደሚቅበዘበዝ በግ ባለማመን ማእበል እያንጓለሉት ነው፡፡ በጠባቂነት የተሾምን ሁሉ ከተጠያቂነት ለመዳን በዛሬው እለት የበዓለ ሲመተ ክህነትን ለማክበርና ማሰብ በተሰባሰብንበት ቀን የመንጋ ጥበቃ ሥራችን የት ላይ እንዳለ ማሰላሰል አለብን፡፡ መንጋው እየበዛ ነው ወይስ እየቀነሰ፤ ጤናማ ነው ወይስ በሽተኛ? የሚለውን ጥያቄ አንስተን ተጨባጭ መልስ ልንሰጥ ይገባል” በማለት ተናግረዋል፡፡
ከተወቃሽነት ለመዳን መደረግ ስለሚገባው አገልግሎት ሲገልጹም “የተመረጥንበት የጥበቃ ሓላፊነት በትክክል ካልሰራንበት በመንጋውም፤ በታሪክም፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ በእግዚአብሔር ፊት ወቀሳ እንደማይቀርልን ተገንዝበን ከተጠያቂነትና ከተወቃሽነት ለመዳን የጥበቃ ሥራችንን በርትተን መሥራት ይገባናል፡፡ የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ ተብለናልና” ብለዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ የወላይታ ኮንታ ደውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በበኩላቸው 56ኛውን በዓለ ሲመተ ፕትርክና እና 2ኛውን የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በዓለ ሲመተ ፕትርክናን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልእክት “እግዚአብሔር ለቅዱሳን ያለው ፍቅር በርቀት የሚመዘንና የሚለካ አይደለም፡፡ እነሱ በአጠገቡ ሆነው የእሱን ሥራዎች እንዲሠሩ ፈቅዶላቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በምድር ላይ መጋቢዎች፤ እንዲሁም አስታራቂዎች አድርጓቸዋል፡፡ “ለአባቶቻችን ያዘዘውን ለሚመጣው ትውልድ ለልጆቻቸው ያስታውቋቸውም ዘንድ አልሰወሩም” እንዲል ቅዱስ ዳዊት ዛሬ በዚህ ዐውደ ምሕረት ላይ እንደምንመለከተው ቅዱስነትዎ ከአባቶችዎ የተረከቡትን ሓላፊነት በታማኝነት ለመጠበቅ ቃል የገቡበትን እለት ለማስታወስ ነው” ብለዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የስብከት ወንጌል መምሪያ የበላይ ጠባቂና የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ  በቅዱስ ፓትርያሪኩ ትምህርት እንዲሰጡ የተጋበዙ ሲሆን ቅኔውንና ትምህርቱን አዋህደውና አዋዝተው ሰማዕያኑን እጅግ በአስደነቀ መልኩ አቅርበዋል፡፡

በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያሪክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፤ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም፤ ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጥተው የበዓሉ ፍፃሜ ሁኗል።
{flike}{plusone}