ዓመታዊው የቅድስት ሥላሴ ክብረ በዓል በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በድምቀት ተከበረ

ጥር 7 ቀን 2013 ዓ.ም የአዲስ አበባና ጉራጌ አህጉረ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ፣ አረጋዊው አባት ብፁዕ አቡነ ጢሞቲዎስ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ካህናት አስተዳደር ዋና ክፍል ኃላፊ መልአከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ ሰይፈ፣ የአራዳና ጉለሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ መ/አሚን አባ ላዕከ ማርያም፣ የካቴድራሉ አስተዳዳሪ ሊቀ ሥልጣናት አባ ሲራክ እንዲሁም የደብሩ ማኅበረ ካህናትና እጅግ በርካታ ኦርቶዶክሳዊ ምእመናን በተገኙበት የእግዚአብሔርን ክብር በሚገዳደር መልኩ በሰናዖር ሜዳ ላይ የተሠራውን ሕንጻ ሰናዖር እግዚአብሔር ያፈረሰበትንና መግባቢያ ቋንቋቸውንም የደባለቀበትን ዕለት በሚዘከርበት ሁኔታ በድምቀት ተከብሯል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የዕለቱን ታሪክ የተመለከተ ሰፊ ትምህርት የተሰጠ ሲሆን በእኛም ዘመን የእግዚአብሔርን ክብር የሚጋፋ የትኛውም ዓይነት ክፉ ተግባር እንዳናከናውን ደግሞም በሕይወታችን ያለውን የኃጢአት ክምር በንስሐ እናፈርሰ ዘንድ መልእክት ተላልፏል፡፡

በመቀጠልም ካቴድራሉ በ1924 ዓ.ም ተመስርቶ በ1936 ዓ.ም መንፈሳዊ አገልግሎት መጀመሩና ለረጅም ጊዜያት ማለትም ለሰባ ሰባት ዓመታት ያክል አገልግሎት በመስጠቱ የተነሣ በከፍተኛ ጉዳት ውስጥ እንደሚገኝ ተገልፆ በአሁኑ ስዓት ግን ይህንን ታሪካዊና መንፈሳዊ ቅርስ ለመታደግና የዕድሳት ሥራ ለመሥራት ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገርና ልዩ ልዩ ኮሚቴዎች እንደ ተዋቀረና በእንቅስቃሴ ላይም እንደሚገኝ በቀረበው ሪፖርት ላይ ተደምጧል፡፡

በመጨረሻም የአዲስ አበባና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የዕለቱ ትምህርት በሰፊው ተሰጥቷልና ይበቃናል፣ የሰማነውን በሕይወት እናኑረው፣
ይህ ትልቅ ካቴድራል ከመንፈሳዊ ቦታነቱም ባሻገር የቤተ ክርስቲያናችንን ብሎም የሀገራችንን ታሪክ ጠገብነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፣ ስለሆነም የተጀመረው የዕድሳት እንቅስቃሴ የሕንጻውን ታሪካዊ ማንነት በጠበቀ መልኩ መታደስ ይኖርበታል፣ ለዚህም መልካም ተግባር ሀገረ ስብከታችን በአስፈላጊው ነገር ሁሉ ከእናንተ ጋር ነው በማለት አረጋግጠዋል።
የጥምቀት በዓልም ኦርቶዶክሳዊ ጨዋነት በተላበሰ መልኩ እንዲከበር ለሕዝበ ክርስቲያኑ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ምንጭ ፦አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ድረ-ገጽ

ወርሐዊ የአጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ ክብረ በዓል ባማረ ሁኔታ ተከበረ

                           በወጣት ኢዮብ በላቸው 

ዛሬ ሰኔ 7 ቀን 2012 ዓ.ም በተከበረው ወርሐዊ የአጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ ክብረ በዓል ባማረ ሁኔታ ተከብሮ ውሏል። በዓሉ ባማረ ሁኔታ እንዲከበር የካቴድራሉ ሰ/ት/ቤት አባላት ፣ የአካባቢ ወጣቶች፣ የሃሌ ሉያ ከፍተኛ ክሊኒክ የጤና ባለሙያዎችና የካቴድራሉ የጤና አጠባበቅ ኮሚቴ በጋር በመሆን ጠንካራ የማስተባበር ሥራ በመሥራታቸው በዓሉ እጅግ ባማረ ሁኔታ ተከብሯል።

ለሕዝቡ ደህንነት ሲባል ሕዝበ ክርስቲያኑ በሙቀት መለኪያ ማሽን በመለካት፣ በአካባቢው ወጣቶች የእጅ ሳኒታይዘር እየተደረገላቸውና የአፍና የአፍንጫ ጭንብል ማድረጋቸውን በመቆጣጠር ምዕመናን በተዘጋጀላቸው ወንበር ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲቆሙ በማድረግ የካቴድራሉ የሰ/ት/ቤት አባላት ፣ የአካባቢ ወጣቶች፣ የሃሌ ሉያ ከፍተኛ ክሊኒክ የጤና ባለሙያዎችና የካቴድራሉ የጤና አጠባበቅ ኮሚቴ ከፍተኛ አገልግሎት ሰጥተዋል።

በተለይም ከዚህ በፊት በግቢው ውስጥ ይፈጠር የነበረውን የመኪና መጨናነቅ ቦታ በመለየት፣ መግቢያና መውጫው ምዕመናኑ በአግባቡ እንዲገለገሉ አድርገዋል ።

በትላንትናው ዕለት ሰኔ 6/2012 ዓ.ም በካቴድራሉ አስተዳደር አማካኝነት የተለያዩ የኮረና በሽታ ቅድመ መከላከያ የሚያገለግሉ 3 የሙቀት መለኪያ፣ 54 ሌትር ሳኒታይዘር፣ 30 የአካባቢው ወጣቶች የሚያስተናግዱበት መለያ ልብስ ተገዝቶ ለአገልግሎት መዘጋጀቱና የጸረ ተዋህስያን ኬሚካል በሃሌሉያ ከፍተኛ ክሊኒክ የጤና ባለሙያዎች አማካኝነት በካቴድራሉ ቅጽረ ግቢ መርጨቱ መዘገባችን ይታወሳል።

በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቅጽረ ግቢ ጸረ ተዋህስያን ኬሚካል ተረጨ

በነገው ዕለት ለሚከበረው ወርሃዊው የአጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ ክብረ በዓል ምክንያት በማድረግ በካቴድራሉ
አስተዳደር አማካኝነት የተለያዩ የኮረና በሽታ ቅድመ መከላከያ የሚያገለግሉ 3 የሙቀት መለኪያ፣ 54 ሌትር
ሳኒታይዘር፣ 30 የአካባቢው ወጣቶች የሚያስተናግዱበት መለያ ልብስ ተገዝቶ ለአገልግሎት የተዘጋጀ ሴሆን
የጸረ ተዋህስያን ኬሚካል መርጨት መርሐ ግብሩም በሃሌሉያ ከፍተኛ ክሊኒክ የጤና ባለሙያዎች አማካኝነት እንዲከናወን ተደርጓል።

መልካም በዓል ያድርግልን።

አስከፊ በሽታውም አብርሃሙ ሥላሴ ከኢትዮጵያ ሀገራችንንና ከዓለማችን ያርቁልን።

         

በወቅታዊ ጉዳይ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተሰጠ መግለጫ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡፡ አሜን
በመላው ዓለም የተስፋፋውን የኮሮና ወረርሽኝ ለመግታት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተሰጠ መግለጫ
በሀገራችን ኢትዮጵያ በገጠር፣ በከተማና በመላው ዓለም ለምትገኙ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን በሙሉ!
ወቅታዊ የሰው ልጅ ሥጋት በመሆን በመላው ዓለም በፍጥነት በተስፋፋው የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ዓለም አቀፍ ሥጋት ስለተከሰተ መንግሥታት ሀገርን ከጥፋት፣ ሕዝብን ከሞት ለመጠበቅ አዋጆችን እያወጡ ይገኛሉ፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት ለመታደግ እምነትና ቀኖናን ጠብቆ ሃይማኖታዊ መመሪያ የመስጠት ሐዋርያዊ ኃላፊነት አለባት፡፡
ስለዚህ ቋሚ ሲኖዶስ የጉዳዩን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት መሠረተ እምነትንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ጠብቆ ለሁሉም ካህናትና ለሕዝበ እግዚአብሔር ደኅንነት ሲባል የሚከተሉትን መመሪያዎች አስተላልፏል፡-

 1. በሰሙነ ሕማማት እንደምናደርገው የእርስ በርስ መሳሳም ቀርቶ ራስን ዝቅ በማድረግ፣ እጅ በመንሳት ወይም በእማሄ ሰላምታ በማቅረብ እንዲፈጸም፣
 2. ወረርሽኙ በሰዎች መሰባሰብ የሚስፋፋ ስለሆነ ማናቸውም መንፈሳዊ ጉባኤያት፣ የትምህርት ክፍለ ጊዜያት፣ ወደ ገዳማትና አድባራት የሚደረጉ ጉዞዎች እና ምዕመናን የሚሳተፉባቸው ታላላቅ መርሐ ግብሮች ለጊዜው እንዲቋረጡ፣
 3. ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲገባም ሆነ አሰፈላጊ በሆነበት ጊዜ ሁሉ እጆቻንን በመታጠብና ዘርዘር ብሎ በመቆም ሥርዓተ አምልኮ እንዲፈጸም፣
 4. ዓመታዊ የንግሥ ክብረ በዓላት በቅዳሴና በማኅሌት ታስበው ክብረ በዓላቱ በሌላ ጊዜ እንዲከበሩ፣
 5. የጉንፋን ምልክት ያለባቸው ለሌሎች እንዳያስተላልፉ በቤታቸው በጥንቃቄ ተለይተው በጸሎትና በሕክምና እንዲቆዩ፣ ከቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ አገልግሎትም በልዩ ሁኔታ እንዲያገኙ፣
 6. በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ የተቋቋመው ግብረ ኃይል የተስፋ ልዑክ በመሆን እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ተደራጅቶ ተልዕኮውን በአስቸኳይ እንዲጀምር
 7. ሥርዓተ ቅዳሴን በተመለከተ፡-
  • በቤተ መቅደስ ቀዳስያን በሆኑት ልዑካን ብቻ ሥርዓተ ቅዳሴው እንዲፈጸምና ሌሎች አገልጋዮች በቅድስቱ ዘርዘር ብለው በመቆም እንዲያገለግሉ፣
  • በዕለቱ ለሚቆርቡ ምዕመናን ለአረጋውያን፣ ለወጣቶችና ለሕፃናት የፈረቃ ተራ በማዘጋጀት ቆራቢዎች ብቻ ወደ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ገብተው ዘርዘር ብለው በመቆም እንዲያስቀድሱ፣
  • ሌሎች ምእመናን በአጸደ ቤተክርስቲያን ቢያንስ ሁለት የትልቅ ሰው እርምጃ ያህል በመራራቅ ቆመው እንዲያስቀድሱ፣
  • የቅዳሴ ጠበል በየግል መጠቀሚያ ምእመናን በየቆሙበት ቦታ በጥንቃቄ እንዲሰጥ፣
  • ሌሎች ከቅዳሴ ጋር የተያያዙ ዝርዝር የአፈፃፀም ጉዳዮችን ግብረ ኃይሉ አዘጋጅቶ በቅዱስ ሲኖዶስ በማጸደቅ ለአህጉረ ስብከት በሚልከው መመሪያ መሠረት ተግባራዊ እንዲደረግ፤
 8. ከሥርዓተ ቅዳሴ በተጨማሪ እንደ ስብሐተ ነግሕ፣ ሰዓታት፣ ቁመተ ማኅሌት፣ ጥምቀተ ክርስትና፣ ጸሎተ ፍትሐት፣ የመሳሰሉ አገልግሎቶች ለሥርዓቱ በሚያስፈልገው ቁጥር ብቻ እና በውሱን ሊቃውንት በተራ እንዲፈፀም፣
 9. ወረርሽኙ ከዓለም እንዲጠፋ ካህናት ብቻ በቤተ መቅደስ፣ በዐውደ ምኅረትና በአጸደ ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ጸሎተ እጣን በማድረስ ማዕጠንት እንዲፈጽሙ፣
 10. በማኅበራዊ ግንኙነት በደስታ፣ በሐዘን፣ በእድር፣ በሥርዓተ ቀብር አፈፃፀምና በመሳሰሉት መሰባሰቦች በሽታው እንዳይሠራጭ አገልግሎቱ በውስን የሰው ቁጥር በጥንቃቄ እንዲፈፀም፤
 11. ምዕመናን ራሳቸውን እየጠበቁ በቫይረሱ የተጠቁና አገግመው የወጡ ወገኖችን፣ እንዲሁም በውጭ ሀገር ዜጎች ላይ ከሃይማኖትና ከምግባር የወጣ መገለልና ጥቃት እንዳይደርስባቸው በክርስቲያናዊ ፍቅርና በኢትጵያዊ ጨዋነት እንክብካቤ እንዲደረግላቸው፣
 12. ለነዳያን እና ለተቸገሩ ወገኖች አስፈላጊው ማኅበራዊ እና ቁሳዊ እገዛ በሁሉም አጥቢያዎች እንዲደረግ፣
 13. ቤተ ክርስቲያንን ከማይወክሉና ቀኖናዊ ካልሆኑ አሳሳች መረጃዎች በመቆጠብ ሊቃውንት፣ ካህናት፣ መምህራን፣ ሰባክያን፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ከቅዱስ ሲኖዶስ የሚሰጡ መመሪያዎችን በየአጥቢያችሁና አስፈላጊ በሆኑ ቦታዎች ሁሉ እንድትፈጽሙ እና እንድታስፈጽሙ ተወስኗል፡፡
  በአጠቃላይ በበሽታው እስካሁን ለተያዙት፣ በጊዜያዊ ማቆያ ለሚገኙት በሙሉ እግዚአብሔር አምላካችን ምህረቱን እንዲሰጥልን እንጸልያለን፤
  በመላው ዓለም ዜጎቻቸውን በበሽታው ለተነጠቁ ሁሉ መጽናናቱን እንዲሰጥልን ያረፉትንም እንዲምርልን እግዚአብሔርን በጸሎት እንጠይቃለን፤
  በመላው ዓለም የምትገኙ ወገኖቻችን የራሳችሁና የሌሎች ሕይወት ከወረርሽኙ እንዲጠበቅ እንዲሁም የበሽታው ሥርጭት እንዲቆም መንፈሳዊና ማኅበራዊ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ እያሳሰብን የተሰጡት መመሪያዎች ወረርሽኙ እስኪጠፋ ድረስ የጸኑ እንዲሆኑ በጥብቅ እናስታውቃለን፡፡
  ልዑል እግዚአብሔር በቸርነቱና በይቅርታው ብዛት ዓለማችንን ከጥፋት የሰውን ልጅ ሁሉ ከመከራ ሞት ይጠብቅልን፡፡ አሜን፡፡
  ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
  አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
  መጋቢት 14 ቀን 2012 ዓ/ም አዲስ አበባ

በዓለ አስተርእዮ

አስተርእዮ፡– ቃሉ ግእዝ ነው፡፡ አስተርእዮ ማለትም መገለጥ፣ መታየት ማለት ነው፡፡

በግሪክ ቋንቋ ኤጲፋንያ ይባላል ኤጲፋንያ ማለት መገለጥ፤ መታየት ማለት ነው፡፡ አሁን ያለንበት ዘመን ዘመነ አስተርእዮ ይባላል የመገለጥ፣ የመታየት ዘመን ማለት ነው፡፡

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ነሥቶ ሰው ሆኖ የተገለጠበት ዘመን ስለሆነ እና እንዲሁም በጥምቀቱ አንድነቱን ሦስትነቱን የገለጠበት ዘመን በመሆኑ ዘመነ አስተርእዮ፡- የመገለጥ፣ የመታየት ዘመን ተብሏል፡፡

በተለይ የአሁኑን የጥምቀት በዓል ልዩ የሚያደርገው በዓሉ በዩኔስኮ /UNESCO/ መመዝገቡ ነው፡፡ ይህም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊት፣ ሐዋርያዊት፣ ታሪካዊት፣ ብሔራዊት፣ ዓለማቀፋዊት መሆኗን የሚገልጽ በመሆኑ ለቤተ ክርስቲያናችን ትልቅ ክብር ነው፡፡ የሰላም አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች እንደሚከተለው ተገልጸዋል፡፡

 • አንድነቱንሦስትነቱንለመግለጽነው፡ /በማቴዎስ ወንጌል ም. 3፡13-17/ እንደተጻፈው ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ ሲጠመቅ እግዚአብሔር አብ “ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር” /የምወደው ልጄ እርሱ ነው/ ሲል ከሰማይ ተናግሯል፡፡

እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በርግብ አምሳል በራሱ ላይ ተቀምጧል፡፡ በዚህም አንድነቱን ሦስትነቱን ገልጧል፡፡

 • የተነገረውን ትንቢት ለመፈጸም ነው፡- ከትንቢቶቹ አንዱን ለአብነት ያህል እንጠቅሳለን “ባሕርኒ ርዕየት ወጐየት ወዮርዳኖስኒ ገብአ ድኅሬሁ አድባር አንፈርአጹ ከመ ሐራጊት” /ባሕርም አየች ሸሸችም ዮርዳኖስም ወደኋላው ተመለሰ ተራሮችም እንደ ጊደሮች ዘለሉ/፡፡ /መዝ. 113፡3/
 • የዕዳ ደብዳቤአችንን ለመቅደድ ነው፡- የክፋት እና የተንኮል ምንጭ የሆነው ጠላታችን ዲያብሎስ አዳምና ሔዋንን መከራውን እንዳቀልላችሁ ስመ ግብርናታችሁን ጽፋችሁ ስጡኝ አላቸው፡፡ ይህም ማለት የእኔ አገልጋይ መሆናችሁን የሚገልጽ ጽሑፍ ስጡኝ ማለት ነው እነርሱም በእውነት መከራውን የሚያቀልላቸው መስሏቸው ጽፈው ሰጡት፡፡ ጽሑፉም “አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ሔዋን አመቱ ለዲያብሎስ” የሚል ነው፡፡ ይህም ማለት አዳም የዲያብሎስ አገልጋይ ነው ሔዋን የዲያብሎስ አገልጋይ ናት ማለት ነው፡፡ ይህንንም በሁለት የድንጋይ ሠሌዳ ላይ ጽፈው ሰጡት አንዱን በዮርዳኖስ፣ አንዱን በሲኦል ጣለው፡፡ በዮርዳኖስ የጣለውን የዕዳ ደብዳቤአችንን ጥር 11 ቀን የሰላም አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ በጥምቀቱ ደምስሶልናል አጥፍቶልናል፡፡

በሲኦል የጣለውንም ደግሞ በዕለተ ዓርብ በስቅለቱ በሞቱ ደምስሶልናል አጥፍቶልናል “በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው እርሱንም በመስቀል ጠርቆ አስወግዶታል” /ቆላስ 2፡14/

ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ኤፍሬምም ይህንን መሠረት በማድረግ በደረሰው የእመቤታችን ምስጋና ላይ “ወሰጠጠ መጽሐፈ ዕዳሆሙ ለአዳም ወለሔዋን” /የአዳም እና የሔዋንን የዕዳ ደብዳቤ ቀደደ፤ ደመሰሰ፣ አጠፋ/ ሲል ተናግሯል፡፡

 • ጥምቀትንለእኛለመባረክነው፡ ለእኛ አብነት ለመሆንና ከአምስቱ አዕማደ ምስጢር በአንዱ በምስጢረ ጥምቀት ልጅነትን እንድናገኝ ለማድረግ ነው፡፡

“በዮርዳኖስ ውኃ በተጠመቀ ጊዜ ይህ ምሥጢር ዳግመኛ ተገለጠ፤ ጥምቀትን ሽቶ አይደለም፤ ሽቶ አልተጠመቀም፤ አምላክ በሥጋ ተገልጦ ጥንተ ልደትን ዳግመኛ ይሰጠን ዘንድ ነው እንጂ” (ሃይ. አበው ምዕ. 87፥15)

 • ትሕትናንለእኛለማስተማርነው፡ይህም በአገልጋዩ በቅ/ዮሐንስ እጅ መጠመቁ ነው፡፡

አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን በ30 ዘመኑ ተጠመቀ? ቢሉ አዳም በተፈጠረ በ30 ዘመኑ ልጅነቱን አስወስዷል አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም ይህንን ልጅነት ለመመለስ በተመሳሳይ ዘመን በ30 ዘመኑ ተጠምቋል፡፡

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን በውኃ ተጠመቀ? እኛም በውኃ እንድንጠመቅ ለምን አዘዘ?

የሰላም ንጉሥ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በውኃ የተጠመቀበት፣ እኛም በውኃ እንድንጠመቅ ያዘዘበት ምክንያት ብዙ ነው፡፡ ለአብነት ያህል ውኃን ድሃውም ሀብታሙም በቀላሉ ያገኘዋል ለድሃውም ለሃብታሙም እኩል ነው በዚህ መሠረት ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁላችንም መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ ስለሚፈልግ በውኃ እንድንጠመቅ አዘዘ፡፡ እርሱም በውኃ ተጠመቀ፡፡

ያለ ጥምቀት መዳን የለም “ያመነ የተጠመቀ ይድናል ያላመነ ያልተጠመቀ ግን ይፈረድበታል፡፡ /ማር. 16፡16/

“አማን አማን እብለከ ዘኢተወልደ ዳግመ እማይ ወእመንፈስ ቅዱስ ኢይክል በዊአ ውስተ መንግሥተ እግዚአብሔር” /እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ካልተወለደ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ይገባ ዘንድ አይችልም/ /ዮሐ. 3፡5/ ሲል የእውነት አምላክ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስ በነገረው መሠረት ያለ ጥምቀት የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ አይቻልም፡፡

ወንዶች በተወለዱ በ40 ቀን ሴቶች በተወለዱ በ80 ቀን የሚጠመቁበት ምክንያት፡- እንደሚከተለው ተገልጻ;ል፡፡

1ኛ. አዳም በተፈጠረ በ40 ቀኑ ሔዋን በተፈጠረች በ80 ቀኗ ቅድስት ሥላሴ ብርሃን አልብሰው ብርሃን አጎናጽፈው ገነት አስገብተዋቸዋል፡፡ ይህን መሠረት በማድረግ ዛሬ ወንዶች በተወለዱ በ40 ቀናቸው ሴቶች በተወለዱ በ80 ቀናቸው ይጠመቃሉ /መጽ. ኩፋ 4፥9-13/

2ኛ. በብሉይ ኪዳን ወንድ ልጅ በተወለደ በ40 ቀኑ ሴት ልጅ በተወለደች በ80 ቀኗ ወደ እግዚአብሔር ቤት ይገቡ ነበር /ዘሌዋ. 12፡ 1-5/ ይህንም መሠረት በማድረግ ዛሬ ወንዶች በተወለዱ በ40 ቀናቸው ሴቶች በተወለዱ በ80 ቀናቸው ይጠመቃሉ፡፡

መንታ ወንድና ሴት ልጆች ከተወለዱ ወንዱ ልጅ አርባ ቀን ሲሞላው በሞግዚት ሄዶ ይጠመቃል፡፡ ሴቷ ልጅ ደግሞ ሰማንያ ቀን ሲሞላት በእናቷ ሄዳ ትጠመቃለች፡፡ (ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 3)

በ40፣ በ80 ቀን የምንጠመቅበት ውኃ፡- በግእዝ ማየ ገቦ ይባላል ማይ ውኃ፤ ገቦ ጎን ነው ማየ ገቦ፡- አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ ሲሰቀል ከጎኑ የፈሰሰው ውኃ ነው፡፡ (ዮሐ. 19፥34) በቄሱ ጸሎት ውኃው ወደ ማየ ገቦነት ይለወጣል፡፡ በዚህ ተጠምቀን ከሥላሴ ተወልደናል፤ ልጅነትን አግኝተናል፤ ክርስቲያንም ተብለናል፤ ክርስቲያን የሚለውን ስም ያገኘነው በጥምቀት ነው፡፡ ክርስቲያን ማለት ትርጉሙ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም የተጠመቀ ማለት ነው፡፡ እንዲሁም በክርስቶስ ክርስቲያን ተብለናል፡፡ በዚህ መሠረት የክርስቲያኖችን ሥራ ሠርተን መገኘት አለብን የክርስቲያኖች ሥራ፤ ሕገ እግዚአብሔርን፣ ትእዛዘ እግዚአብሔርን መጠበቅ ነው “ብትወዱኝስ ትእዛዜን ጠብቁ” /ዮሐ. 14፡15/ ብሎ አምላካችን በቅዱስ ወንጌል በተናገረው መሠረት ትእዛዙን መጠበቅ አለብን የክርስቲያኖች ሥራ ይህ ነው፡፡ ትእዛዙን ካልጠበቅን ወዳጆቹ አይደለንም ብትወዱኝስ ትእዛዜን ጠብቁ ብሏልና በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ እንድናገኝ ትእዛዙን እንጠብቅ፡፡

            ሕጉን ትእዛዙን ጠብቀን በማየ ንስሓ ታጥበን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ተቀብለን በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት እንዲሁም በቅዱሳን አማላጅነት መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ ልዑል እግዚአብሔር ወሰን በሌለው ቸርነቱ ይርዳን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ምንጭ፡- https://addisababa.eotc.org.et/am/

በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ለአስተዳደር ሠራተኞች የአስተዳደር ሥልጠና ተሰጠ

ኅዳር 16/03/2012 ዓ.ም በካቴድራሉ አስተዳደር ጽ/ቤት ለውጥ /Change management በሚል ርዕስ የአንድ ቀን ሥልጠና ተሰቷል፡፡
ሥልናውን የሰጡት በዚሁ ሙያ ላይ የረጅም ጊዜ አገልግሎት ያላቸው የሰበካ ጉባኤ አባል የሆኑት አቶ ደረጃ ተክሌ ናቸው፡፡

አስተዳደራዊ ለውጥ ቤተ ክርስቴያን ያስፈልጋል፤ ቀደም ሲል የነበሩ የቤተ ክርስቲያን አባቶችና መሪዎች ለሀገሪቱ እና ለቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን በስፋት ያብራሩት አቶ ደረጃ እንደ አባቶቻችን ለሀገራችንና ለቤተ ክርስቲያናችን ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ እና ለሰው ልጅ ሁሉ ስለአንድነት ዘወትር ማስተማር እንደሚገባ፤ አንድነቱም ከራሳችን ነው መጀመር ያለበት እኛ አንድ ሳንሆን ሌላውን አንድ ማድረግ አንችልም፤ የትኛውንም ችግር ያለ አንድነት ሊፈታ አይችልም ብለዋል፡፡

በዘርና በፖለቲክ መለያት አግባብ አይደልም፤ በተለይም በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ሁሉም ሰው የእግዚአብሔር ፍጡር ሆኖ ሳለ በዘርና በፖለቲካ ተለያይቶ ማየት እጅግ ያሳፍራል ብለዋል፡፡
ከቴድራሉ ዓለም አቀፍ እንደመሆኑ መጠን በእስትራቴጂክ ፕላን እና በእቅድ መመራት ይኖርበታል ፤አሰራራችን በሻሻልን እና በለወጥን ቁጥር ካቴድራሉንና የካቴድራሉ ማኅበረ ሰብ እንዲሁም ተገልጋዩን ማኅበረ ላይ ጥሩ ተነሳሽነትን ይፈጥራል ብለዋል፡፡
ካቴድራሉ የቱሪስት መስህብ ቢሆንም ለቱሪስት የተመቻቸ ሁኔታ ባለመኖሩ የሚጠበቅበትን ያህል አይደልም፤ ደረጃውን የጠበቀ ቤተ መጻህፍትም የለውም፤በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶበት ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡
የካቴድራሉ አስተዳደር ሠራተኞችም በበኩላቸው ሥልጠና አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው በቀጣይ ይህን መሰል ሥልጠና በየሥራ ዘርፉ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ ሃሳባቸውን ገልፀዋል፡፡

የዚህ ዓይነት ሥልጠና ቀደም ሲል በካቴድራሉ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ለመምህንና ለልዩ ልዩ ሠረተኞች እንደተሰጠ ይታወሳል፡፡

በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በክቡር ቢተወደድ ባሕሩ አብርሐም G+2 የአብነት ት/ቤት የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ

ኅዳር 11/2012 ዓ.ም ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ብጹዕ አቡነ መልከጼዴቅ የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ኃላፊና የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ብጹዕ አቡነ እንድርያስ፣ክቡር ቢተወደድ ባሕሩ አብርሐም እና ቤተ ሰዎቻቸው ፣የካቴድራሉ አስተዳር ሠራተኞች እና ልማት ኮሚቴ አባላት፣የካቴድራሉ ማኅበረ ካህናት፣የካቴድራሉ ሰንበት ት/ቤት አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል፡፡

ይህ መሠረት ድንጋይ የተቀመጠበት የአብነት ት/ቤት ቀደም ሲል እውቁ የመጽሐፍ መምህር የነበሩት መጋቤ ሚስጢር ልሣኑ ብሩ ለዘመናት መጽሐፍ ሲያስተምሩበት የነበረና ብዙ ሊቃውንት የተማሩበት ቦታ ነው፡፡

በካቴድራሉ 6 የአብነት መምህራን ቢኖሩም የሚያሰተምሩበት ምቹ የሆነ ቦታ ባለመኖሩ ለዘመናት ሲቸገሩ መኖራቸው ሊቃውንቱ፣የሊቃውንቱ ደቀ መዛሙርትና የካቴድራሉ ማኅበረ ካህናት የሚያወቁት ሀቅ ነው፡፡ እነሆ ዛሬ የሊቃውንቱን ጸሎት በሥላሴ ፊት ደርሶ በአንድ በጎ አድራጊ ባለፀጋ በቢተወደድ ባሕሩ አብርሐም በካቴድራሉ ግቢ ውስጥ ሊሠራ ለታሰበው ዘመናዊ G+2 የአብነት ት/ቤት በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የመሠረት ድንጋይ ተጥሏል፡፡

የአብነት ት/ቤቱ እንዲሠራ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ለልዩ ሀገረ ስብከታቸው ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በሰጡት አባታዊ መመሪያ መሠረት ነው የመሠረት ድንጋዩ የተጣለው፡፡

ቅዱስነታቸው በመርሃ ግብር ግቡ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት ይህን የመሰለ ሊቃውንት የሚያፈራ የአብነት ት/ቤት መሥራት ቤተ ክርስቲያኒቱ ለምትሰጠው ሁለንተናዊ አገልግሎት የላቀ አስተዋፅኦ ስላለው ሌሎች በጎ አድራጊዎችም እንደ ቢተወደድ ባሕሩ አብርሐም በቤተ ክርስቲያን የማይጠፋ አሻራቸው ሊያስቀምጡ ይገባል ብለዋል፡፡

የአብነት ት/ቤቱ እጅግ ዘመናዊ የሆነ ሁለገብ G+2 ሕንፃ ሲሆን ከ15 እስከ 16 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅ ክቡር ቢተወደድ ባሕሩ አብርሐም ተናግረዋል፡፡
ሙሉ ሪፖርቱን እንደ ደረሰን እናቀርባለን፡፡

የካቴድራሉ ዋና አስተዳዳሪ ሊቀ ሥልጣናት አባ ገ/ዋህድ ገ/ኪዳን ያቀረቡትን ሙሉ ሪፖርት እንደሚከተለው ቀርቧል፡

ኅዳር 11 ቀን 2012 ዓ.ም

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡


ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እና የጉራጌ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የተከበሩ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና አስኪያጅ መ/ር አባ ሞገስ ኃ/ማርያም፣ የተከበራችሁ የጠቅላይ ቤተ ክሕነት፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ የአራዳና ጉለሌ ቤተ ክሕነት ክ/ከተማ የመምሪያ ኃላፊዎች፣ ክቡር ቢትወደድ ባህሩ አብርሃም፣ ክቡራን የካቴድራሉ የሰበካ ጉባዔ እና የልማት ኮሚቴ አባላት፣ የአስተዳደር ኃላፊዎች፣ ማኅበረ ካሕናት፣ የሰንበት ት/ቤት አባላትና ልዩ ልዩ ሠራተኞች ፣ የተከበራችሁ እንግዶች፣ ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን በዛሬዋ ዕለት በዚህ ታላቅ ካቴድራል በበጎ አድራጊው ክቡር ቢትወደድ ባህሩ አብርሃም አማካይነት ሊሠራ ለታሰበው የአብነት ትምህርት ቤት ሕንፃ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ለማስቀመጥና አባታዊ ቡራኬና መመሪያ ለመስጠት ስለተገኙልን በካቴድራሉ ሰበካ ጉባዔ ጽ/ቤት ስም ከፍተኛ ምስጋናናችንን እናቀርባለን፡፡
“ግበር ለገብርከ በከመ ምሕረትከ ወምህረኒ ኵነኔከ ገብርከ አነ አለብወኒ ወአእምር ስምዓከ ጊዜ ገቢር ለእግዚአብሔር ” መዝ ፻፲፰÷፻፳፬-፻፳፮ “ለባሪያህ እንደ ምሕረትህ አድርግ ሥርዓትህን አስተምረኝ እኔ ባርያህ ነኝ እንዳስተውል አድርገኝ ምስክርህንም አውቃለሁ ለእግዚአብሔር የሥራ ጊዜ አለው” መዝ ፻፲፰÷፻፳፬-፻፳፮


በዛሬው ዕለት የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት ለብዙ ዓመታት በካቴድራሉ ቅጽረ ግቢ ውስጥ የአብነት ትምህርት ቤት ሕንፃ ግንባታ ለማስገንባት በከፍተኛ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ ባለበት ጊዜ መዝሙረኛው ቅዱስ ዳዊት “ለእግዚአብሔር የሥራ ጊዜ አለው” እንዳለው በተለያዩ አድባራትና ገዳማት በተለይም በጉራጌ ሀገረ ስብከትና በተለያዩ ሀገረ ስብከት በገንዘባቸው በከተማና በገጠር ያሉ ታላላቅ አብያተ ክርስቲያናትን በማሳነጽና የአብነት ትምህርት ቤት ሕንጻዎችን በማስገንባት እንዲሁም በገንዘባቸው መምህራንን በመቅጠር ብዙ ደቀመዛሙርትን ለቤተ ክርስቲያኒቱ በማፍራት ላይ የሚገኙት የቤተ ክርስቲያኒቷ የቁርጥ ቀን ልጅ የሆኑት ክቡር ቢትወደድ ባህሩ አብርሃም “እግዚአብሔር ሆይ ከታናሽነቴ ጀምረህ መታመኛዬ ነህና ከማሕፀን ጀምሮ በአንተ ተደገፍሁ ከእናቴም ሆድ ጀምሮ አንተ መሸሸጊያዬ ነህ ሁልጊዜም ዝማሬዬ ለአንተ ነው” መዝ ፸÷፭-፯ የሚለውን የመጽሐፍ ቃል መሠረት በማድረግ ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት በማሰብ በዚሁ ታላቅ ካቴድራል አሁን በህይወተ ሥጋ የሌሉ የወንድማቸውን የክቡር በኩረ ትጉሃን ከበደ ተካልኝን አርዓያ በመከተል በካቴድራሉ ቅጽረ ግቢ ውስጥ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የሙዝየም አገልግሎት የሚሰጥ ሕንፃ ገንብተው ለካቴድራሉ እንዳስረከቡት ሁሉ እርሳቸውም ለቤተ ክርስቲያኗ እጅግ አስፈላጊ የሆነውን እና የካቴድራሉ ሰበካ ጉባዔና ልማት ኮሚቴ ሲጨነቅበት የነበረውን የአብነት ት/ቤት ሕንፃ ግንባታ በአጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ መልካም ፈቃድ በራሳቸው ሙሉ ወጪ B+G+2 ለማሳነጽ ቃል በገቡልን መሠረት እና ቅዱስነትዎም ይህንን በጎ ተግባር በመደገፍ በሀገረ ስብከቱ በኩል ፈቃድ እንዲሰጥ በሰጡት መመሪያ መሠረት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በኩል የአብነት ት/ቤቱ እንዲሠራ በመፈቀዱ እነሆ በዛሬዋ ዕለት በቅዱስነትዎ የአብነት ት/ቤት ሕንፃ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ለማኖር በካቴድራሉ ስለተገኙልን ቅዱስነትዎን በሰበካ ጉባዔው ጽ/ቤት ስም እጅግ እጅግ አድርገን እናመሰግናለን፡፡

የቅዱስነትዎ ቡራኬ ይድረሰን፡፡

Discover Ethiopia (Kedst selase cathedral church)

Holy Trinity Cathedral, known in Amharic as Kidist Selassie, is the highest-ranking Ethiopian Orthodox Tewahedo cathedral in Addis Ababa, Ethiopia. It was built to commemorate Ethiopia’s liberation from Italian occupation and is the second most important place of worship in Ethiopia, after the Church of Our Lady Mary of Zion in Axum.

The cathedral bears the title ‘Menbere Tsebaot’, or ‘Pure Altar’. The church compound is the burial place for those who fought against the Italian Occupation, or those who accompanied the Emperor into exile from 1936 to 1941. Emperor Haile Selassie, I and his consort the Empress Menen Asfaw are buried in the north transept of the cathedral. Other members of the Imperial Family are buried in the crypt below the church. The High Altar of the cathedral is dedicated to ‘Against Alem Kidist Selassie’ (Sovereigns of the World the Holy Trinity). The other two altars in the Holy of Holies on either side of the High Altar are dedicated to St. John the Baptist and to ‘Kidane Meheret’ (Our Lady Covenant of Mercy). In the south transept of the cathedral is a recently added chapel of St. Michael, which houses the Tabot or Ark of St. Michael the Archangel, which was returned to Ethiopia in February 2002 after being discovered in Edinburgh. This relic was taken by British forces from the mountain citadel of Magdalla in 1868 during their campaign against Emperor Tewodros II.

The cathedral complex also includes the ‘Bale Wold’ (Feast of God the Son) Church, which is also known as the Church of the Four Heavenly Creatures. This church served as the original Holy Trinity Monastery Church before the building of the Cathedral and dates back to the reign of Emperor Menelik II. Other facilities include a primary and a secondary school, a monastery and the Holy Trinity Theological College, a museum and monuments housing the remains of those massacred in Addis Ababa by the Italians in 1937 in response to an assassination attempt against the Fascist Viceroy of Italian East Africa. In addition, is the monument and tomb of the officials of the imperial government who were executed by the Communist Derg regime. Holy Trinity Cathedral is the official seat of the Orthodox Archdiocese of Addis Ababa. The Patriarchs of the Ethiopian Orthodox Tewahedo Church are enthroned at Holy Trinity Cathedral and all Bishops are consecrated there as well.

The tombs of Emperor Haile Selassie I and Empress Menen Asfaw, as well as other members of the Imperial Family, are inside Holy Trinity Cathedral. The late Patriarchs, Abune Tekle Haimanot and Abune Paulos of the Ethiopian Orthodox Tewahedo Church, are buried in the churchyard, as is the famous British suffragette and anti-fascist activist Sylvia Pankhurst. The late Prime Minister Meles Zenawi and other prominent Ethiopians are also buried there.

ዓመታዊው የዓጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ ክብረ በዓል በድምቀት ተከበረ

ከፎቶ ማህደር

በየዓመቱ ሐምሌ 7 ቀን በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የሚከበረው ዓመታዊው የሥላሴ ክብረ በዓል በዚህ ዓመትም በመንበረ ጸባዖት ቅድሰት ሥላሴ ካቴድራል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኩሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ ብፁአን ሊቃነ ጳጳሳት እንዲሁም በብዙ ሽህ የሚቆጠሩ ምዕመናን በተገኙበት እጅግ ደማቅ በሆነ ሁኔታ በዓሉ ተከብሮ ውልዋል፡፡

በዚሁ ዕለት አጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ በአብርሃም ቤት ተገኝተው ቤቱን የባረኩበት፣ የአንድነታቸውንና ሦስትነታቸው ሚስጢር የተገለፀበት ታላቅ በዓል ነው። በዓሉ መከበር የጀመረው ከዋዜማው ከሐምሌ 6 ጀምሮ ሲሆን የካቴድራሉ ካህናትና መዘምራን ከዋዜማው ከቀኑ 3 ሰዓት ጀምሮ ለ30 ሰዓታት ያህል ሌሊትና ቀኑን ሙሉ ያለ ማቋረጥ ስብሃተ እግዚአብሔር ሲያቀርቡ ውለው አድረዋል፡፡

ይህ መንፈሳዊ አገልግሎት ማለትም ስርዓተ ማህሌተ፣ ስርዓተ ቅዳሴ እንዲሁም ሰዓታትና ሰርክ ፀሎት በአጠቃለይ የስርዓተ አምልኮ አፈፃፀም በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ልዩ በመሆኑ የእምነቱ ተከታዮች ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም እጀግ የሚስደንቅ በዓል ነው፡፡

የበአሉን ታሪክ አጠር አድርገን እንደሚከተለው አቅርበነዋል
እግዚአብሔርን የሚፈራና ቸር ጻድቅ የሆነ ስሙ አብርሃም የተባለ ምድያም በሚባል አገር አንድ ሰው ይኖር ነበር የሚስቱም ስም ሣራ ይባላል።እነዚህም ቅዱሳን በሥላሴ ሕግ ተጠብቀው ስደተኛውንና እንግዳውን እየተቀበሉ ያስተናግዱ ነበር።እንግዳ ሳይዙ ወይም ሣይኖር የሰናፍጭ ቅንጣት ስንኳ ያህል ምግብ ምንም ምን አይቀምሱም ነበር።
የበጎ ነገር ጠላት የሆነ ሰይጣንም ይህን በተመለከተ ጊዜ ከጭፍሮቹ አንዱን እንዲህ ሲል ላከው። እንግዶች ሁሉ ወደ አብርሃም ቤት እንዳይሄዱ ሄደህ በምድያም ጎዳና ተቀምጠህ ዕውነቱን በሐሰት ለውጠህ ተናገር።
እነሆ ደምህ በመሬት ላይ እስኪወርድ ድረስ እራስክን በድንጋይ ፈጥፍጠው አለው።ሰይጣኑም ይህን ትእዛዝ ከተቀበለ በኋላ ወደ ምድያም ወረደና ደሙ በምድር ላይ እስኪፈስ ድረስ ራሱን በድንጋይ ገምሶ በጎዳና ዳር ተቀመጠ። በጎዳና የሚያልፉ መንገደኞች ሰዎችም ወደ እርሱ በደረሱ ጊዜ እናንት መንገደኞች ከወዴት መጥታችኋል ወዴትስ ትሄዳላችሁ ሲል ጠየቃቸው።
መንገደኞቹም እኛስ ወደ ደገኛው ወደ አብርሃም ቤት እንሄዳለን አሉት።በውኑ አብርሃም ደግነቱ በክፋት እንደተለወጠና ክፉ ሰው እንደሆነ አልሰማችሁምን።እነሆ እንግዳ ከመጥላቱ የተነሣ ደሜ ከመሬት ላይ እንደ ውሃ እስኪፈስ ድረስ የፈነከተኝን እራሴን መጥታችሁ ተመልከቱ ይልቁንስ በኔ የደረሰ እንዳይደርስባችሁ አትሂዱ አላቸው።እንግዶቹም ያ ቸርና መልካም ሰው የነበረ አብርሃም ምን ነክቶት ክፉ ሰው ሊሆን ቻለ በማለት እርስ በራሳቸው ተወያዩ።ይህንንም ከተባባሉ በኋላ ተመልሰው ወደ ሀገራቸው ሄዱ።በዚችም ዕለት አብርሃም ከቤቱ ወጥቶ በጎዳና እንግዳ ፈልጎ አጣ።ከዚያም ወደ ቤቱ ተመልሶ ገባና ምንም ምን ሳይቀምስ ተኛ።
በማግስቱም አምስት ሰዎች ወደ አብርሃም ቤት ሲሄዱ ያ ተንኰለኛ ሰይጣን አገኛቸውና እንደቀድሞው እናንተ ሰዎች ወዴት ትሄዳላችሁ ሲል ጠየቃቸው።
እነሱም ወደ አብርሃም ቤት እንሄዳለን አሉት።ሰይጣኑም መልሶ ወንድሞቼ ሆይ አብርሃም እራሴን ፈንክቶኝ ከማህል ራሴ የሚወርደውን ደሜን ኑ ተመልከቱ አላቸው።እነሆ አሁንም እንደኔ እንዳትሆኑ በሰላም ወደ ሀገራችሁ ተመለሱ አላቸው።በዚህን ጊዜ እነዚያ እንግዶች እርስ በራሳቸው አብርሃም ከሚገድለንስ ወደ ሀገራችን ብንመለስ ይሻላል ተባባሉ።
ዳግመኛም እንደ ልማዱ አብርሃም ወደ ጎዳና ወጥቶ ፀሐይ እስኪጠልቅ ድረስ ሲጠብቅ ውሎ ምንም እንግዳ ሳያገኝ ቀረ።ከዚያም ወደ ቤት ተመልሶ ምንም ምን ሳይቀምስ ተኝቶ አደረ።
በሦስተኛውም ቀን አጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ የአብርሃምን የልቡን ቆራጥነትና የሰይጣንን ተንኰል ተመልክተው ወደ አብርሃም ቤት ሄዱ።በዚህ ጊዜ የሰይጣን ምክሩን ሁሉ ተሻረ ይዘውም ወደ መጨረሻይቱ የሲኦል ረግረግ ጣሉት።እሊህ ሥላሴም በእንግዳ ደንብ በአብርሃም በቤቱ ደጃፍ ተቀመጡ። አብርሃምም በደጁ እንደተቀመጡ በተመለከተ ጊዜ ወደ ቤቱ ሮጦ ገብቶ ለሚስቱ እንዲህ ሲል ነገራት።
እኅቴ ሣራ ሆይ እነሆ የከበሩ አረጋውያን ሦስት እንግዶች መጥተውልናል።
እንግዲህ አንቺ ፈጥነሽ እንጀራና ወጡን ጥሩውን ጠላና መልካሙን ጠጅ አዘጋጂ እኔም የወይፈን ፍሪዳ አርዳለሁ አላት።ሣራ ሚስቱም እሺ ጌታየ እንዳልከኝ አደርጋለሁ አለች።ዳግመኛም ዕርጎውን ማሩን እንድታዘጋጅና ለእግራቸው መታጠቢያም ውሀ በምንቸት ታሞቅላቸው ዘንድ አዘዛት።ከዚያም በኋላ ለእያንዳንዳቸው ለየራሳቸው ፤ ሦስት ታላላቅ ዳቦ ትጋግር ዘንድ አዘዛት።
አብርሃምም ይህን ከተናገረ በኋላ ወይፈኑን አርዶ ሥጋውን በየብልቱ አወጣው።ከዚያም የታረደውን የወይፈን ሥጋ በትከሻው ተሸክሞ ወደ ቤቱ ይዞ ከገባ በኋላ ለሚስቱ ሰጣትና እኔ እግራቸውን እስካጥብ ድረስ ይህን ሥጋ ቅባቱን በዛ አድርገሽ በጨውና በቅመም አጣፍጠሽ ስሪው አላት።እሷም እሺ በጄ አለችው። አብርሃምም ከቤቱ መድረክ በስተውጭ ሥላሴን ባገኛቸው ቦታ ላይ ልብሱን አነጠፈና ጌቶቼ እግራችሁን አጥባችሁ ዘንድ ወደ ወንድማችሁ ቤት ዝለቁ ግቡ አላቸው።
ከዚህ በኋላ ተነሥተው ወደ ድንኳኑ ወይም አዳራሹ ገቡና ባነጠፈላቸው ምንጣፍ ላይ ተቀመጡ። በዚህን ጊዜ የአብን እግር ማጠብ ጀመረና አብን ካጠበ በኋላ ወልድና መንፈስ ቅዱስም ታጥበው አገኛቸው ያለመለየት አንድ ናቸውና።በዚህ ጊዜ ማዕዱን በገበታ ሠርቶ ወይኑንም በማድጋ ቀድቶ አቀረበላቸውና እስኪጠግቡ ድረስ በሉ ጠጡ።ማዕዱ ከተነሣ በኋላ ለእንግዶቹ እራት የታረደውን ወይፈን በቤቱ በራፍ ፊት ለፊት ከውጭ በኩል ቆሞ አየው።አብርሃምም ይህን ወይፈን ባየ ጊዜ ፈጽሞ ፈራ ተንቀጠቀጠ።በዚህ ጊዜ ሥላሴ አብርሃም ሆይ ሰይጣን እንዳይቀናብህ ጠንቅቀህ ዕወቅ።እንግዳ በመጣልህ ጊዜ በብሩህ ልቡና እና በንቁህ ኅሊና ሆነህ ተቀበለው።ነገር ግን እንግዳ ካልመጣ እራትህን በጊዜው ብላ መጠጥህንም ጠጣ እንጂ ጦምህን አትደር አሉት።ይህንንም ተናግረው እኒህ በአምሣልና በህልውና ትክክል የሆኑ ሥላሴ ወደ ሰማይ ዐረጉ።
የምድያም ሰዎችም ስለዚህ ለምግብ ከተዘጋጀ በኋላ ሥላሴ ስላስነሡት ወይፈን እንዲሁም በሥላሴ ዘንድ በተደረጉት ድንቅ ድንቅ ሥራዎች ሁሉ ፈጽመው ተደነቁ።

የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የ2011 ዓ.ም የፋሲካ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለ300 ችግረኞች እርዳታ ሰጠ!!

 “እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ” 2ኛ ቆሮ.9÷7

በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ምግባረ ሠናይ ክፍል መሪነት እና አስተባባሪነት ለ300 አረጋወያን ዘላቂና ለተወሱኑ ወራት ሊያቆይ የሚችል ለእያንዳንዳቸው በአይነት15 ኪሎ ፍርኖ ዱቄት፣3 ሌትር ዘይት እና 3 ኪሎ ስኳር ተሰቷል፡፡

ካቴድራሉ 15 አረጋወያን በመደበኛነት የሚጦራቸው ያሉት ሲሆን ከዚሁ በተጨማሪ ምእመናንን በማስተባበር ሁልጊዜ በየዓመቱ የትንሣኤን በዓል ምክንያት በማድረግ ከአራዳ ክፍል ከተማ ወረዳ 9 ችግረኛ መሆናቸውን ተገልፆ ዝርዝራቸው በደብዳቤ የተላኩና እንደዚሁም ችግረኛ መሆናቸውን በአጥቢው በተዋቀረው ኮሚቴ ተጠንቶ ዝርዝራቸው ለቀረቡ ችግረኞች እርዳታው ይሰጣል፡፡

ዝርዝር መረጃውን በሚቀጥሉት ሳምንታት እናቀርባለን፡፡

ማሳሰቢያ

 የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ምግባረ ሠናይ አረጋውያን መርጃ መዕከል ይምጡና ይጎብኙ!!
አድራሻ፡-4 ኪሎ ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ገቢ ውስጥ ከሙዝዬሙ ጀርባ
ስ.ቁ. :-0912 66 26 88/011-1-23-35-18
ኢ-ሜል ፡- eotcht@gmail.com
ድረ-ገጽ፡- www.trinity.eotc.org.et
ዘወትር ከሰኞ- እሁድ በካቴድራሉ የእለት ገንዘብ መቀብያ እየመጡ ለካቴድራሉ አረጋውያን ብለው መክፈል ይችላሉ ወይም በኢትያጵያ ንግድ ባንክ የቁጠባ ሒሳብ ቁጥር ፡- 1000010560318 ይክፈሉ፡፡