5.3

ዓመታዊው የዓጋዓዝተ ዓለም ሥላሴ ክብረ በዓል በድምቀት ተከበረ

                        እንኳን ለአብርሃሙ ሥላሴ ዓመታዊ ክብረ በዓል በሰላም በጤና በሕይወት አደረሳችሁ፡፡

                          በመ/ር ዘሩ እና በመ/ር ዳዊት

5.3

‹‹እመ እግዚአብሔር ኢሐነፀ ቤተ ከንቶ ይፃምው እለ የሃንፁ›› ‹‹እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ ግንበኞቹ በከንቱ ይደክማሉ›› መዝ 126፡1 ይህን የታላቁን ነቢይ ቃል ለመነሻነት የተመረጠው ዛሬ በቤተ ክርስቲያናችን የሚከበረው የአጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ በዓለ ንግሥን ምክንያት ለመግለፅ ነው፡፡ ታላቁ ነቢይ ቅዱስ ዳዊት ምንም እንኳ ይህን ኃይለ ቃል ከጊዜ በኋላ የፃፈው ቢሆንም የዚህን ጽሑፍ ሐሳብ የሚያንፀባርቀው ቀደም ሲል በዘመነ ህገ ልቡና የተፈፀመ ነበረ በዘፍ1ዐ፡32 ላይ ‹‹የኖኀ የልጆቹ ነገዶች እንደየ ትውልዳቸው በየህዝባቸው እነዚህ ናቸው፤ አህዛብም ከጥፋት ውኃ በኋላ በምድር ላይ ከነዚህ ተከፋፈሉ››፡፡ ይልና በተለይ በዘፍ 11፡1 ጀምሮ ያለውን ስንመለከት ደግሞ ‹‹ምድርም ሁሉ በአንድ ቋንቋ ንግግር ነበረች›› ብሎ የሰናኦርን ግንብ መገንባትና መፍረስን ያትታል፡፡ በአጭሩ የዚህ ኃይለ ቃል ጭብጥ ሐሳብ፡- የሰው ልጆች እግዚአብሔርን ለመቃወም ሲሉ ታላቅ ግንብ እንደገነቡና እግዚአብሔር ደግሞ ይህን ታላቅ ግንብ እንደ አፈራረሰባቸው ነው የሚያብራራው፡፡ ይህን ግንብ ለመገንባት 43 ዓመት ፈጅቶባቸዋል፡፡

ይህ ግንብ በአሁኑ ዘመን በነዱባይ ከተገነቡት ታላላቅ ሰማይ ጠቀስ ህንፃዎች እንደሚበልጥ የቤተ ክርስቲያኒቱ መምህራን ይናገራሉ፡፡ ይህንን ህንፃ ሲገነቡ የነበሩ ሰዎች ቀደም ሲል እንደተገለፀው ለትምክህትና እግዚአብሔርን ለመቃወም ስለሆነ እግዚአብሔር ደግሞ ትምክህትንና ራሱ እግዚአብሔርን የሚቃወም ሰው አይወድም ዘዳግ 5÷ 10 አስመ አነ አምላክ ቀናኢ እኔ እግዚአብሔር ቀናተኛ አምላክ ነኝ ሲል በሙሴ አፍ እንዳስተማረ የሚቃወሙትን የቃወማቸዋል ፡፡

እግዚአብሔር በአምላክነቱ ቀናኢ ነው፡፡ ስለዚህ እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች የሚሠሩት ሥራ (ህንፃ) ስኬታማ አይሆንምና ብትንትኑ ወጣ፤ ፈራረሰ፡፡ መ/ቅዱሱ እንደ ነገረን አንድ የነበረ የሰዎች ቋንቋ በሰዎቹ ቁጥር ልክ ሆነ፡፡ ይህም የኃጢአት ውጤት ነው፡፡ አዳም ከመበደሉ በፊት ሰው ከእንስሳትና አራዊት ከጠቅላላ ፍጥረታት ሁሉ በቋንቋ ይግባባ እንደ ነበረ አበው ያስተምራሉ አዳም ሐጢአት ከሠራ በኋላ ግን ከፍጥረታት ጋር መግባባት ተሳነው፡፡ አሁን ደግሞ በነዚህ ኃጢአት ምክንያት ሰውና ሰው መግባባት አቃታቸው፡፡ ሰው ኃጢአት ሲሰራ ከራሱ ከልቡናው ጋር ይጣላል፤ መግባባት ያቅተዋል፡፡ ሰዎች የሚሠሯአቸው ሥራዎች በስኬት እንዲጠናቀቁ ካስፈለገ እግዚአብሔር እንዲጨመርበት ማድረግ ነው፤ እግዚአብሔር ካልተጨመረበት ግን ነቢዩ እንደነገረን ልፋቱ ከንቱ ድካም ነው የሚሆነው፡፡ ይህ ታሪክ በዘመነ ህገ ልቡና የተፈፀመ ሲሆን ሌላ ተጨማሪም ቤተክርስቲያናችን ከዚሁ ጋር አብራ የምታከብረው ታላቁ የሐዲሱ ኪዳን የልደት በዓል ነው፡፡ ሐዋሪያው ቅዱስ ዮሐንስ በ1 ዮሐ 3÷8 ‹‹በእንተ ዝንቱ አስተርአየ ወልደ እግዚአብሔር ከመ ይሥዓር ግብሮ ለጋኔን›› ‹‹ስለዚህ የዲያብሎስን ሥራ ያፈርስ ዘንድ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ›› ብሎ እንደ ነገረን የእግዚአብሔር ልጅ ዲያብሎስ ለ55ዐዐ ዘመን የገነባው የሐጢአትን ግንብ ለማፍረስ ሰው የሆነበት ወቅት ነው፡፡ ይህ ወቅት ሠራዊተ ዲያብሎስ ያዘኑበት የተዋረዱበት ሲሆን የሰው ልጆችና መላእክት ደግሞ ያመሰገኑበትና የዘመሩበት ጊዜ (ወቅት) ነው፡፡ ታላቁ ሊቀ ቅዱስ ቄርሎስ ‹‹ዮም አሐደ መርኤተ ኮኑ መላእክት ወሰብእ ከመይሰብሕዎ ለክርስቶስ በቃለ አሚን›› ‹‹እነሆ ዛሬ መላእክትና ሰዎች በእምነት ቃል ኢየሱስ ክርስቶስን ለማመስገን አንድ መንጋ ወይም አንድ ማኀበር ሆኑ›› ሲል ይገልፀዋል ታላቁ የኢትዮጵያውያን መመኪያ የሆነ ሊቁ ቅዱስ ያሬድም በጣዕመ ዜማ ይህን ያብራራዋል፡፡

5.5

ይህ የሚያመለክተው ሰዎች ለ55ዐዐ ዘመን በዲያብሎስ ሥር ተገዝተው(በዲያብሎስ ግዛት )ስለነበሩ በዚሁ በጌታ ልደት ከዚህ አስቀያሚ ከሆነው የዲያብሎስ ግዛት ነፃ መውጣታቸውን ያረጋገጡበት ቀን ስለሆነ ለአምላካቸው፣ ለመድኃኒታቸው ታላቅ ምስጋናን አቅርበዋል፡፡ መላእክትም ደግሞ በሰው ሞት አዝነውና ተክዘው ነበር አሁን ግን ሰው ድህነተ፤ ሥጋ ድህነተ ነፍስን ስላገኘ ደስ ብሏቸው አመስግነዋል ዘምረዋል፡፡ መላእክት ሰዎች በሥጋቸውም ይሁን በነፍሳቸው እንዳይጎዱ ወደ ፈጣሪ የሚለምኑ፣ የሚማፀኑ ናቸው፡፡ በዘካ 1፡12 ‹‹የእግዚአብሔርም መልአክ መልሶ አቤቱ የሠራዊት ጌታ ሆይ እነዚህን ሰባ ዓመት የተቆጣሃቸው ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች የማትምራቸው እስከ መቼ ነው›› አለ ይላል ይህ የመላእክትን ምልጃ የሚያመላክት ነው፡፡ ስለዚህ መላእክት ለሰው ድህንነት በየጊዜው ይፀልያሉ፤ ይማልዳሉ፡፡ ሰው ሲድን ደግሞ ደስ ብሏቸው ይዘምራሉ ያመሰግናሉ ይህን ቅዱስ ሉቃስ በወንጌሉ በሉቃ2÷12 ድንገትም የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋራ ነበሩ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ፤ሰላምም በምድር ለስውም በጎ ፈቃድ ወይም እርቅ ተጀመረ አሉ ሲል የመዘገበልን ፡፡ አሁን ታላቁ ኢትዮጵያዊ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በዝማሬው ‹‹ዮም መላእክት ይየብቡ ወሊቃነ መላእክት ይዜምሩ ኃይላት ይየብቡ እስመ መድኀን መጽአ ውስተ ዓለም ለቢሶ ሥጋነ›› ‹እነሆ መላእክት ሊቃነ መላእክት ለአምላካቸው ለፈጣሪያቸው፣ ምስጋናን ያቀርባሉ ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስ መድኃኒት ለመሆን የሰውን ሥጋ ለብሶ ወደ ዓለም መጥቷልና በተጨማሪም ለኛ ስለ ተወለደልን ሥልጣን ያላቸው መላእክት ይቀድሱታል፤ ሱራፌልም እግዚአብሔርን ይባርካሉ፤ ኪሩቤልም ውዳሴን ያቀርባሉ፤ ዛሬ ከኛ የጥንቱ መርገም ተወግዷል፤ ዛሬ ሐጢአታችን ተተወልን ወዘተ….. በማለት ያመሰገኑትን ምስጋና ይቀጥላል፡፡ በነዚህ ሁለቱ ታሪኮች ተመሳሳይ የሆኑ ድርጊቶችን እግዚአብሔር አከናውኗል፡፡

1. ሰው የገነባው ግንብን ማፍረስ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች አእምሮን የሰጣቸው መልካም ነገርን እንዲሰሩበትና መልካም ነገርን እንዲያስቡበት እንጂ ለመጥፎ አልነበረም እነሱ ግን ይህንን አእምሮ ለመጥፎ ነገር ያውሉታል ሰዎች በአእምሮአቸው መጥፎ ሥራ ቢሰሩ የሚጎዱ ራሳቸው ፤ጥሩ ሥራ ቢሠሩ የሚጠቀሙ ራሳቸው ነቸው፡፡

2. ዲያብሎስ ለ55ዐዐ ዘመን የገነባውን የኃጢአት ግንብን ማፍረስ ነው፡፡ ከነዚህ ከሁለቱ ታሪኮች የምንማረው ፡-

1. የሰው ልጅ ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ምንም፣ ምንም ነገር መሥራት እንደማይችል ነው ሰው ግንብን ቢገነባ፣ መኪና ቢገዛ፣ ቢነግድ ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ሊሆን እንደማይችል መገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡

2. አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዲያብሎስ ለ55ዐዐ ዘመን በብዙ ውጣውረድ የገነባውን የኃጢአት ግንብ በልደቱ (ሰው ሆኖ) ንዶታል፡፡ ነገር ግን ይህ የተናደውን ግንብ እንደገና ኃጢአትን በመስራት እንዳንገነባው ወይም እንዳንጠግነው ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ዲያብሎስ ይህንን የፈረሰውን የኃጢአት ግንብ ለማስጠገን እየወጣና እየወረደ ነው ያለው ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ በ1ኛ መልእክቱ 5÷8 በመጠን ነሩ ነቁም ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና ሲል የሚገልፀው፡፡ ስለዚህ በጥንቃቄ እንድንኖር እጅግ አስፈላጊ ነው ይህንንም እንድናደርግ አምላካችን እግዚአብሔር ይርዳን፡፡ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ እስራኤል ዘተሰሃለነ ወገብረ መድኃኒተ ለሕዝበ ዚአሁ፡፡ ስለዚህ በዓለ ቅድስት ሥላሴ ጥር 7 ቀን ምን ተደረገ? ከጥፋት ውሃ በኋላ የኖኅ ልጆች ወልደው ተዋልደው ብዙዎች ሆኑ ባቢሎን የነበሩት በሰናዖር ምድር ሰፊ ሜዳ አግኝተው ሳንሞት ስም ማስጠሪያ ግንብ እንገንባ ብለው መክረው ታላቅ ግንብ ገነቡ፡፡ አለቃቸውም ናምሩድ ይባላል፡፡ ሞትን የሚያመጡብን ሥላሴ ናቸው እነርሱን ወግተን ሞትን እናርቅ አላቸው፡፡ እነርሱም ከግንቡ ላይ ሆነው ጦር እየሰበቁ ይወረውሩ ጀመር፡፡ ሰይጣን በደመና በምትሀት ጦሩን ደም እየቀባ ይልክላቸዋል እነርሱም ደሙን እያዩ አሁን አብን ወጋነው አሁን ወልድን ወጋነው ይሉ ጀመር፡፡ ሥላሴ ምንም እንኳን ምህረታቸው የበዛ ቢሆንም ባቢሎናዊያን ዲያቢሎስ ስለሰለጠነባቸው ቋንቋቸውን ለያዩባቸው ከዚያም ውሃ ሲለው ጭቃ፣ ጭቃ ሲለው ደንጊያ የሚያቀብለው ሆነ፡፡ እንዲህ የማይግባቡ ቢሆኑ ተበታትነዋል፡፡ ባለማስተዋል የሰሩትም ሕንፃ ነፋስ ጠራርጎ አጥፍቶታል፡፡ ዘፍ.11 1-9 በዘመነ አብርሃምም የሰዶምና የገሞራ ሰዎች ወንድ ለወንድ እስከ መጋባት ድረስ ኃጢአት ሰሩ እግዚአብሔርንም በደሉ፡፡ የአብርሃም የወንድም ልጅ ሎጥ በዚያ ይኖር ነበር፡፡ ሊያድኑት ቢሹ ሁለቱን መላእክት ልከው እግዚአብሔር ሰዶምና ገሞራን አጠፋለሁ ብሏልና ሚስትህንና ልጆችህን ይዘህ ወደ ዞዓር ሂድ ስትሄድም ወደ ኋላ ዞረህ አትመልከት አሉት፡፡ ሎጥም ማልዶ ተነስቶ ሚስቱንና ልጆቹን ይዞ ከከተማ ወጣ፡፡ ሰዶምና ገሞራም ባህረ እሳት ሆኑ፡፡ የሎጥም ሚስት ወይኔ ሀገሬ ብላ መለስ ብትል የጨው ሀውልት ሆና ቀርታለች፡፡ ዘፍ.19 1-29 ይህ የተደረገው በወርኀ የካቲት እንደሆነ አባቶች ይናገራሉ፡፡ፍሬ ነገሩ ግን ይህን ያደረጉት ቅድስት ሥላሴ እንደመሆናቸው በዚህ ዕለት ይዘከራል ሁል ጊዜ በየዓመቱ በድምቀት ይከበራል ፡፡በመሆኑም የዘንድሮው ዓመትም እንደተለመደው በሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በታላቁ ካቴደራል በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በድምቀት ተከብሯል፡፡በበዓሉ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፤በፁዕ አቡነ አረጋዊ የመንበረ ጸባዖት ቅድሰት ሥላሴ ካቴድራል የበላይ ኃላፊ ፤በፁዕ አቡነ ማቲያስ የካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤በፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤በፁዕ አቡነ ዮናስ የአፋር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤በፁዕ አቡነ ስምኦን የምዕራብ ወለጋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤የካቴድራሉ ዋና አስተዳዳሪ ክቡር ቆሞስ አባ ገ/ሥላሴ በላይ፤የካትድራሉ ሰበካጉባኤ አባላትና መላው ማህበረ ካህናት እንዲሁም በብዙ ሺህ የሚቆጠር ሕዝበ ክርስቲያን በበዓሉ ላይ ተገኝተው በዓሉን በድምቀት አክብረዋል፡፡

03

የልደት በዓል በሁሉም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በድምቅት ተከበረ

                                                                                                     በመ/ር ዘሩ ብርሃኔ

 እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኀኒት ተወልዶላችኋል ሉቃ.2፥11

እንኳን ለጌታችን ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት በሰላም አደረሳችሁ፡፡

03

የጌታችን የአምላካችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከምታከብራቸው ታላላቅ በዓላቶች መካከል አንዱ ሲሆን ሁሌ በየዓመቱ ታኅሣሥ 29 እንደሚከበር ይታወቃል፡፡ እንደ ተለመደው የዘንድሮ በዓልም መከበር የጀምረው ከዋዜማው 12.00 ሰዓት ጀምሮ ሲሆን በሁሉም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማትና አድባራት ሥራዓተ ማኅሌት፤ሰዓታት እና ሥርዓተ ቅዳሴ ሲከናወን ያድራል ፡፡ በተለይም በአገሪቱ ዋና መዲና በሆነቸው በአዲስ አበባ ከተማ በሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በሚገኘው በመንበረ ጸባዖት ቅድሰት ሥላሴ ካቴድራል በዓሉ እጅግ በጣም በማቅ ሁኔታ ተከብሮ አድሯል፡፡በበዓሉ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፤ ዶ/ር ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ የበላይ ኃላፊ፤ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ፤በፁዕ አቡነ አረጋዊ የመንበረ ጸባዖት ቅድሰት ሥላሴ ካቴድራል የበላይ ኃላፊ ፤ካህናት እና በብዙ ሽህ የሚቆጠሩ ምዕመናን በበዓሉ ላይ ተኝተው በዓሉን በድምቀት አክብረዋል፡፡በዐቃቤ መንበር ፓትርያርክ በብፁዕ አቡነ ናትናኤል መልካም ፈቃድ ሥርዓተ ቅዳሴውን የመሩት ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ሲሆኑ በ3ቱም መንበር በሥላሴ፤በማርያምና በዮሐንስ ቤተ መቅደሶች ቅዳሴው የተቀደሰ ሲሆን ሥርዓተ ቅዳሴውም በተለመደው ሰዓት ተጠናቅቋል፡፡ በበዓሉ ላይ ለተገኙ መዕመናን በዐቃቤ መንበር ፓትርያርክ በብፁዕ አቡነ ናትናኤል አማካኝነት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ተሰጥቶ የበዓሉ ፍፃሜ ሁኗል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሁሌ በየዓመቱ የሚከበረው የቅዱስ በዓለ ወልድ በዐለ ንግሥ ታኅሣሥ 29/2005 ዓ.ም በድምቀት ተከብሮ ውሏል፡፡ቅዱስ በዓለ ወልድ በአዲስ አበባ ከሚገኙ ታላላቅ ገዳማትና አድባራት መካከል አንዱ ሲሆን የተመሠረተውም በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመን መንግስት በ1883ዓም እንደሆነ ይታወቃል፡፡

003

በዓመት ሁለት ጊዜ መጋቢት 29 እና ታኅሣሥ 29 ታቦተ ሕጉ ወጥቶ በዓሉ በድምቀት ይከበራል/ይነግሣል፤የዘንድሮ የ2005 ዓ.ም የጌታችን የአምላካችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደትም በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ተከብሮ የዋለ ሲሆን በበዓሉ ላይም በርካታ መእመናን ተገኝተዋል፡፡ በዓሉ መከበር የጀመረው ከዋዜማው ከታኅሣሥ 28 ጀምሮ ሲሆን የካቴድራሉ ካህናትና መዘምራን ከዋዜማው 12.00 ሰዓት ጀምሮ ለ18 ሰዓታት ያህል ሌሊትና ቀኑን ሙሉ ያለ ማቋረጥ ስብሐተ እግዚአብሔር ሲያቀርቡ ውለው አድረዋል፡፡የካቴድራሉ ሊቃውንት መዘምራን እንዲሁም ወጣት የሰንበት ት/ቤት መዘምራን ለበዓሉ የተዘጋጀውን ወረብ አቅርበዋል፡፡ ይህ መንፈሳዊ አገልግሎት ማለትም ሥርዓተ ማህሌተ፣ ሥርዓተ ቅዳሴ እንዲሁም ሰዓታትና ሰርክ ፀሎት በአጠቃለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሥርዓተ አምልኮ አፈፃፀም ልዩ በመሆኑ የእምነቱ ተከታዮች ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም እጀግ በጣም የሚስደንቅ በዓል ነው፡፡በበዓሉ ላይ የተገኙት ክቡር ሊቀ ሥልጣናት አባ ገ/ሥላሴ በላይ የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዋና አስተዳዳሪ በበዓሉ ላይ ለተገኙት መዕመናን ሰፋ ያለ ትምህርተ ወንጌል ተሰጥቶ የበዓሉ ፍፃሜ ሁኗል፡፡

abune_nathnael

ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የገና 2005ዓ.ም በዓለ ልደት ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ፡፡

                                                                                                      በመ/ር ዘሩ ብርሃኔ

abune_nathnael
ብፁዕ አቡነ ናትናኤል መግለጫ ሲሰጡ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልእክት “በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትኖሩ የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ በሕመም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችሁ እንዲሁም የሕግ ታሪሚዎች ሆናችሁ በማረሚያ ቤት የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት እንኳን ለ2005 ዓ.ም. የጌታችን የአምላካችንና የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዐለ ልደት በሰላም አደረሳችሁ፡፡” ካሉ በኋላ “በጌታችን ቤዛነት እንድን ዘንድ አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮአልና፤ እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር በዚህ አውቀናል፡፡ እግዚአብሔር ከፍጡራን ሁሉ የተለየና ከአእምሮ በላይ የሆነ መለኮታዊ ኀይል ያለው አምላክ በመሆኑ የባሕርዩን ጥልቅነት በምልአት ማወቅ ፈጽሞ የማይቻል ቢሆንም እርሱ ራሱ በገለጸልን መጠን የተወሰኑ ነገሮችን እናውቃለን፡፡

ቅዱስ መጽሐፍ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” ብሎ ምልአተ ፍቅሩን ካስረደ በኋላ በማስረጃ ሲያብራራ ቤዛ ሆኖ የሰውን ልጅ ያድን ዘንድ አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮአልና ፍቅሩን በዚህ አውቀናል” ይላል፡፡ እግዚአብሔር በልጁ መሥዋዕትነት ዓለምን ለማዳን ያደረገው ፍቅር ከሌላው ሁሉ የበለጠ በመሆኑ ልቆ ተነገረ እንጂ የእግዚአብሔር ፍቅር ከፍጡራን የተለየበት ጊዜ እንደሌለ ሁላችንም እናውቃለን፤ በስፋትም ልንገነዘብ ይገባልና፡፡” ብለዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል እግዚአብሔር ለፍጥረቱ በፍቅር ከሰጣቸው ስጦታዎች ሁሉ በቤተልሔም ለዓለም ስለሰጠው ስጦታ ሲናገሩ “የቤተልሔም ስጦታ ከስጦታዎች ሁሉ እጅግ በጣም የላቀ ነው፡፡ ምክንያቱም ሌሎች ስጦታዎች ከፍጥረቶቹ የሚገኙ የፍጥረት ውጤት ስጦታዎች ሲሆኑ የቤተልሔም ስጦታ ግን አንድ ልጁን ነውና” ብለዋል፡፡ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል በማጠቃለያ መልእክታቸው “እግዚአብሔር እኛን ይህን ያህል ከወደደን እኛም እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል፤ ከልደተ ክርስቶስ የምንማረው ትምህርት ወገንን ሁሉ ማለትም በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረውን የሰው ዘር ሁሉ መውደድና መርዳት ነው፡፡… ባለንበት ዘመን በተለያየ ምክንያት እናትና አባትን ያጡ፣ የወገንን ፍቅርና እንክብካቤ የሚሹ ብዙ የእግዚአብሔር ልጆች በየሠፈሩ አሉ፡፡ ለበዐል መዋያ ያዘጋጀነውን ኅብስተ በረከት ከተቸገሩት ሕፃናትና የሚላስ የሚቀመስ ካጡ ወገኖች ጋር በመሆን በኅብረት መመገብ ይገባናል፡፡ ይህን ስናደርግ በፍጹም ፍቅሩ የወደደንን እግዚአብሔርን በቤታችን ውስጥ እየጋበዝን እንደሆነ እርግጠኞች መሆን አለብን፡፡ “ተርቤ አብልታችሁኛልና ኑ ወደ እኔ” የሚል ቃል ኪዳን እንዳለበትም እናስታውስ፡፡” ብለዋል፡፡

02

በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ለሚጦሩ 15 አረጋወያን ለ3ኛ ጊዜ እረዳታ ተሰጠ

02

ከአሁን በፊት በዌብሳይታችን አማካኝነት ወጣት ብሩክ አስራት ከዛሬ 3 ወር በፊት ጀምሮ ለካቴድራሉ አረጋውያን የሚሆን በየወሩ ለአረጋውያኑ የሚያስፈልጋቸውን የምግብ እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን ስንዘግብ መቆየታችን የሚታወስ ሲሆን አሁንም እንደተለመደው ለ3ኛ ጊዜ ለገና በዓል መዋያ የሚሆን፡-

   25 ሌትር ጋዝ፤

    15 ሌትር ዘይት

   15 ኪሎ ስኳር፤

   15 ኪሎ በርበሬ፤

    15 ኪሎ ሽሮ፤5 ፓኬት ሻይ ቅጠል

    5 ኪሎ ጨው፤3 ኪሎ ቅቤ እና 20 ሰሙና

 

በእነ ወ/ሮ ማርታ ወርቄ፤በወንድሙ፤በወጣት ዳዊት መስፍን እና በጓደኞቹ አማካኝነት እርዳታውን የላከ ሲሆን ከ2 ሳምንት በፊት በወ/ሮ ማርታ ወረቄ፤በወ/ሮ ሮማን እሸቴ፤በወ/ሮ የምስራች አበበና በወጣት ዳግማዊ መስፍን አማካኝነት የአረጋውያኑ መኖሪያ ቤት የሆነውን የንግስት ዘውዲቱ መታሰቢያ ቤት አንድ ቀን ማጽዳታቸው ይታወቀል፡፡ በመሆኑም ወጣት ብሩክ አስራት ላደረገው ነገር ሁሉ ምስጋናችን እጅግ የላቀ መሆኑን እየገለፅን ሌሎችም የዚሁ የተቀደሰ ዓላማ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪያቸን እናስተላልፋለን መልካም የገና እና የጥምቀት በዓል እንዲሆንላችሁም ከልብ እንመኛለን፡፡

የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ልዩ እድሳት እንደሚያስፈልገው ተገለፀ፡፡

                   በመ/ር ዘሩ ብርሃኔ

የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሰበካ ጉባኤ አስተዳደር /ቤት እንደገለፀው የካቴድራሉ ህንፃ ወስጣዊም ሆነ ውጫዊው ክፍሉ ከጊዜ ብዛት የተነሳ የመሰነጣጠቅ ሁኔታ እየታየበት በመምጣቱ አስቸኳ የሆነ ሙሉ እድሳት እንደሚያስፈልገውና ጥናቱ በጥንቃቄ እንዲጠና ከበላይ አካልም ጭምር ስለታነበት በባለሞያዎች በምን ዓይነት ሁኔታ መታደስ እንዳለበት ከመጋቢት 2ዐዐ4 ዓ.ም ጀምሮ ጥንቃቄ በተሞላበት ሙሉ ጥናት ሲደረግበት ቆይቶ ሕዳር 15/03/2005 ዓ.ም ዶ/ር ብፁእ አቡነ ገሪማና ብፁእ አቡነ አረጋዊ በተገኙበት ለካቴድራሉ ሰበካ ጉባኤ አስተዳደር፤ለካቴድራሉ ልማት ኮሚቴና ለተለያዩ ምሁራን በነኢንጂነር ቀሲስ ደመቀ አማካኝነት ሙሉ ጥናቱ ቀርቧል፡፡ካቴድራሉ ለማደስ የባለሙያዎች አስተዋጽኦ ወሳኝ በመሆኑ በአስተዳደሩ አማካይነት የተለየዩ አዳዲስ ባለሙያዎች በልማት ኮማቴው እንዲሳተፉ ተደርጎ ካቴድራሉ በምን መልኩ መታደስ እንዳለበት ሰፊ ጥናት ሲያደርጉ ቆይቷል በማድረግ ላይም ናቸው፡፡ ውጤቱ ብፁአን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት ለካቴድራሉ ሰበካ ጉባዔና ልማት ኮሚቴ እንዲሁም ለተለያዩ ምሁራን የቀረበ ሲሆን ቀደም ሲል ጥናቱ ለቅዱስ አባታችን በሕይወት እያሉ ቀርቦ ጥሩ አድናቆት ተችሮት እንደነበር ከአንዳንድ የካቴድራሉ ሠራተኞች ለማወቅ ተችሏል፡፡ በገቢ ማሰባሰቢያ ረገድም በካቴድራሉ አውደ ምህረት ሲነገረ የቆየ ሲሆን በተለይም መጋቢት 1 ቀን 2ዐዐ4 . እና ሰኔ 24 ቀን 2ዐዐ4 . በካቴድራሉ ሁለገብ አዳራሽ የስብከተ ወንጌልና የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐግብር ተካሂዶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ከዚህም በተጨማሪ በካቴድራሉ ዌብ ሳይትና በካቴድራሉ ዐውደ ምህረት ላይ በሰፊው ሲገለጽ መቆየቱም አይዘነጋም፡፡

   

ልማትን በተመለከተ

 

በአሁኑ ወቀት የካቴድራሉን ሁለንተናዊ ችግር ሙሉ በሙሉ ይፈታል ተብሎ የተገመተው በ22 ማዞሪያ አካባቢ በ47,ዐዐዐ,ዐዐዐ.ዐዐ (አርባ ሰባት ሚሊዮን ብር) አዲስ ባለ አራት ፎቅ ዘመናዊ ሁለገብ ሕንፃ እያስገነባ ሲሆን ነገር ግን ሥራው ቀደም ሲል ከ3 ዓመታት በፊት መሬቱ እንዳይወሰድ ሲባል ብቻ የተጀመረ ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት ግን ያን ያህል ገንዘብ አግኝቶ ሥራውን ለመሥራት ካቴድራሉ እጅግ በመቸገሩና ከአቅሙ በላይ በመሆኑ ከባለቤቶቹ ምእመናን ጋር በመወየየትና የተለያዩ አማራጮችን በማመቻቸት ላይ ይገኛል፡፡በመሆኑም ጉዳዩ የሁሉም ምእመን ጉዳይ በመሆኑ ምእመንበገንዘባቸውና በእውቀታቸው የቻሉትን የህል የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ቤተክርስቲያኒቱ ጥሪዋን በማስተላለፍ ላይ ትገኛለች፡፡

           

 

የካቴድራሉ መቃብር ሥፍራ ከዓመታት በፊት በማለቁ ምክንያት ምእመናን በመቸገር ላይ መሆናቸው ለሁላችን ግልጽ ነው፡፡ በመሆኑም ጊዜያዊ መፍትሔ ይሰጥ ይሆናል ተብሎ በካቴድራሉ ቅፅረ ግቢ በብር 7ዐዐ,ዐዐዐ.ዐዐ (ሰባት መቶ ሺህ ብር) ወጭ ዘመናዊ የቀብር ፉካ እያሰራ እያሠራ ቢሆንም ዘላቂ መፍትሔ ለማግኘት ግን በመቃብር ዙሪያ የሚያጠና ኮሚቴ ተዋቅሮ ሥራውን በመሥራት ላይ ሲሆን ከአርበኞች ጋርም የቤተ ክርስቲያኒቱና የህዝበ ክርስቲያኑ ችግር ሊፈታ በሚችል መልኩ በሰፈው እየተመካከሩበት ይገኛል ፡፡በመሆኑም ምእመናን ሐሳባቸውና አስተያየታቸው እንዲሁም ምን መሠት እንዳለበት በአካልና በካቴድራሉ ዌብ ሳይት ባለው አድራሻ መጠቀም የበኩላቸውአስተዋፅኦ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

 

  በአጠቃላይ ካቴድራሉን በየትኛውም ዘርፍ መርዳት ለሚፈልጉ ምእመናን በአካልና በካቴድራሉ ውብሳይት ባለው    አድራሻና የባንክ አካውንት መጠቀም ካቴድራሉን ለማደስ መርዳት የምችሉ መሆኑንና እንዲሁም በካቴድራሉ ጽ/ቤት በአካል እየመጡ ችግሩን እያዩ የሚስፈልገውን ማቴሪያልም ይሁን ገንዘብ የሚችሉ መሆኑን ተገልጿል፡፡

 

   

 

በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ለሚጦሩ 15 አረጋወያን ለ2ኛ ጊዜ የምግብ እህል እረዳታ ተሰጠ

   

የዛሬ ሁለት ሣምንት አካባቢ ወጣት ብሩክ አስራት ከአሜሪካን አገር መጥቶ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በንግስት ዘውዲቱ መታሰቢያ ቤት ተጠልለው ለሚኖሩ 15 አረጋወያን በአካል ተገኝቶ የአረጋውያኑ የአኗኗር ሁኔታ እንደጎበኘና ለጊዜው የሚስፈልጋቸውን ልዩ ልዩ የአንድ ወር የምግብ አስቤዛ እርዳታ እንዳደረገላቸው መዘገባችን ይታወሳል፡፡

 

 

አሁንም ከአገር ቤት ተመልሶ ወደ አሜሪካ ከሄደ በኋላ ቀደም ሲል ቃል በገባው መሰረት ለሁለተኛ ጊዜ ለአንድ ወር የሚሆን የወር አስቤዛ በወንደሙና በጓደኞቹ አማካኝነት

                   100 ኪሎ ጤፍ፤

                   1 ኩንታል ከሰል፤

                   15 ሌትር ዘይት፤

                   15 ኪሎ ስኳር፤

                   15 ኪሎ በርበሬ፤

                   15 ኪሎ ሽሮ፤

                  5 ኪሎ ጨው፤

                  5 ፓኬት ሻይ ቅጠል፤

                  15 ሰሙና ለአረጋውያኑ እርዳታው እንዲደርሳቸው አድርጓል ፡፡

 

በዚሁ ዕለት በክቡር ሊቀ ሥልጣናት አባ ገ/ሥላሴ በላይ የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዋና አስተዳዳሪ አማካኝነት ለወጣት ብሩክ አስራት ቤተሰዎችና ለጓደኞቹ ጸሎትና ምስጋና እንዲሁም ቃለ ምእዳን ተሰጥተዋል ክቡር ሊቀ ሥልጣናት ኣባ ገ/ሥላሴ በላይ እንደገለፁት እንደ እነዚህ የመሰለ አቅመ ደካማ የሆኑ አረጋውያን መርዳትበእግዚአብሔር ዘንድ ወጋው እጅግ በጣም ትልቅ መሆኑን ገልፀው በተለይም በካቴድራሉ ቅፅረ ግቢ በንግስት ዘውዲቱ መታሰቢያ ቤት ተጠልለው የሚኖሩ አረጋውያን 24 ሰዓት እግዚአብሔር ሲለምኑ የመኖሩና እግዚአብሔር በሰዎች ላይ አድሮ የዕለት ጉርስ ከሚሰጥዋቸው ምዕመናን ውጭ ምንም ዓይነት ረዳት እንደሌላቸውና በአንዲት ጠባብ ቤት እስከ 8 የሚሆኑ አረጋውያን እናቶች ተጨናንቀው እንደሚኖሩና የምግብ ችግር ብቻ ሳይሆን የመፀዳጃ፤የማዕድ ቤት፤ የውሀና የንጽህና ችግርም እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡ አያይዘውም እነዚህ አረጋውያን እደሚያቸው ከ75 እስከ 98 ከዚያ በላይ በመሆኑ ራሳቸውን ችለው ምግብ ለማብሰልም ሆነ ለመንቀሳቀስ እንደሚያቅታቸውና ከሚኖሩበት ቤት ለመውጣትም ሆነ ለመግባት እንደሚቸገሩ ገልፀው አረጋውያኑን ልትመግብ፤ ልትንከባከብና ንጽህናቸውን ልትጠብቅ የምትቸል ሰራተኛ እንደሚያሰፈልጋቸው ክቡር ሊቀ ሥልጣናት ገልፀዋል ፡፡በመጨረሻም በወጣት ብሩክ አስራት ለተደረገው ነገር ሁሉ ምስጋናቸው እጅግ የላቀ መሆኑን ገልፀው ሌሎችም የዚሁ የተቀደሰ ዓላማ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

 

በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ለሚጦሩ 15 አረጋወያን እረዳታ ተሰጠ

          በመ/ር ዘሩ ብርሃኔ

ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ ምስጉን ነው፡፡መዝ. 40¸1

እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ2 ቆሮ. 9¸7

እርዳታውን የሰጠው በአሜሪካን አገር የሚኖረው ኢትዮጵያዊው ወጣት ብሩክ አስራት ነው፡፡ወጣት ብሩክ አስራት አረጋውያኑ የሚኖሩበት የንግስት ዘውዲቱ መታሰቢያ ቤት ተገኝቶ የአረጋውያኑ የአኗኗር ሁኔታ የጎበኘ/የተመለከተ ሲሆን በየሳምነቱ ሰኞ፤ረቡዕና ዓርብ በካቴድራሉ በኩል ለእያንዳንዳቸው 2 እንጀራ እንደሚሰጣቸውና ለዙሁም የተመደበላቸው በጀት 1000 ብር መሆኑን በዲ/ን ዘሩ ብርሃን የካቴድራሉ ም/ሠ/ክ/ኃላፊ አመካኝነት ገለፃ ተደርጓል፡፡

ወጣት ብሩክ አስራት በቀጣይ ቤተሰዎቹና ጓደኞቹን በማስተባበር አቅመ ደካማ የሆኑትን የካቴድራሉ አረጋውያን በተሻለ መልኩ መርዳት እንደሚችል ጠቁሞ ለጊዜው የሚሆን ግን በተሰዎቹ፤ጓደኞቹ፤ዲ/ን ዘሩ ብርሃን የካቴድራሉ ም/ሠ/ክ/ኃላፊ፤ቀሲስ ፀጋዬ ወርቁ የካቴድራሉ ሁለገብ አዳራሽ ክፍል ኃላፊና ቀሲስ መላኩ ጉልላት የካቴድራሉ ሰበካ ጉባዔ አባል በተገኙበት፡-

1. 100 ኪሎ ጤፍ፤

2. 1 ኩንታል ከሰል፤

3. 15 ሌትር ዘይት፤

4. 15 ኪሎ ስኳር፤

5. 15 ኪሎ በርበሬ፤

6. 15 ኪሎ ሽሮ፤

7. 5 ኪሎ ጨው፤

8. 5 ፓኬት ሻይ ቅጠል፤

9. 15 ሰሙና ለአረጋውያኑ እርዳት ሰጥቷል፡፡በመጨረሻም በቀሲስ ፀጋዬ ወርቁ አማካኝነት ለወጣት ብሩክ አስራት ጸሎትና ምስጋና እንዲሁም ቃለ ምእዳን ተሰጥተዋል፡፡

በተያያዘ ዜናም በዲ/ን ይትባረክ ማንያዘዋል አማካኝነት ነዋሪነታቸው በለንደን አገር የሆኑ ወ/ሮ መድኃኒት በለጠ 100 ኪሎ ጤፍ ለካቴድረሉ አረጋወያን አስገዝተው ልከዋል ለወዲፊቱም እንደሚልኩ ቃል ገብተዋል፡፡በስተመጨረሻም የካቴድራሉ አስተዳደር ለተደረገው ነገር ሁሉ ምስጋናው እጅግ የላቀ መሆኑን ገልጾ ሌሎችም የዚሁ የተቀደሰ ዓላማ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

 

 

 

በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የሠራተኞች የአስተዳደርና የቅርስ አያያዝ ስልጠና ተሰጠ

                          በመ/ር ዘሩ ብርሃኔ

መስከረም 18/01/05

  ይህ ስልጠና የተዘጋጀው በካቴድራሉ አስተዳደር ጽ/ቤት አማካኝነት ሲሆን ለዚሁ ስልጠና እንዲሰጡ የተጋበዙ ምሁራን አሰልጣኞች፡-

1ኛ. ዶ/ር አባ ኃለማርያም መለሰ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ዲን

2ኛ. መ/ር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/ የቅርሳቅርስና ቤተመዘክር ኃላፊ ሲሆኑ በተቀመጠላቸው መርሃ ግብር መሠረት በተሠጣቸው ርዕስ ስልጠናውን/ትምህርቱን በሚገባ ሰጥተዋል/አስተምረዋል

የአስተዳደርና የቤተ ክርስቲያን አገልገሎት በተመለከተ ስልጠናውን የሰጡት ዶ/ር አባ ኃለማርያም መለሰ ሲሆኑ ለ3 ሰዓታት ያህል ሰፋ ያለ ስልጠና ለካቴድራሉ ካህናትና ልዩ ልዩ ሠራተኞች ሰጥተዋል የካቴድራሉ ሠራተኞችም የተሰጣቸውን ስልጠና አስመልክተው በሰጡት አስተያየት ካቴድራሉ ዘመኑ የሚፈቅደውን የአስተዳደር ስልጠና መስጠቱ ወቅታዊና ተገቢ መሆኑን ጠቁመው ለተደረገላቸው ነገር ሁሉ የካቴድራሉ አስተዳደርና አሠልጣኙ ዶ/ር አባ ኃለማርያምን ከልብ አመስግነዋል በቀጣይም ስልጠናው በየደረጃው መቀጠልና መጠናከር እንዳለበት አስተያየተቸውን ሠጥተዋል ከዶ/ር አባ ኃለማርያም ቀጥሎ ስለ ቅርስ ምንነትና አያያዝ በተመለከተ ስልጠናውን የሰጡት መ/ር ዳንኤል ሰይፈሚካኤል ሲሆኑ ስለ ቅርስ ምንነትና አያያዝ በተመለከተ ሰፋያለ ጊዜ ወስደው ስልጠናውን ሠጥተዋል በተለይም ለኢትዮጵያ መኩሪያ የሆነው ይህ ካቴድራል በኢትዮጵያ ደረጃ በቅርስና በታሪክ ባለቤትነቱ ደረጃውን እንደጠበቀ ሲሆን አሁንም እነደቀድሞው ሁሉ ታሪክ በማስመዝገብ ላይ መሆኑን ገልፀዋል በመጨረሻም ይህ የኢትዮጵያ መኩሪያ የሆነውን ካቴድራል ሁላችንም በሚገባ መያዝና ምከባከብ ይኖርብናል በማለት ስልጠናውን አጠናቀዋል በቀጣይም ካቴድራሉ በሚጠይቀው /በሚፈልገው መልኩ ስለ ቅርስ አያያዝ በተመለከተ ስልጠና ለመስጠት ዝግጁ እንደሆኑም ለካቴድራሉ ሠራተኞች ገልፀዋል፡፡

 

የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሠራተኞች ስልጠናውን ሲካፈሉ በከፊል የሚያሳይ ፎቶ ግራፍ

 


የጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ሥርዓተ ቀብር በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈፀመ

 

ነሐሴ 27ቀን 2004 .

በመ/ር ዘሩ ብርሃኔ

የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የቀብር ስነስርዓት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ነሐሴ 27 ቀን 2004 . ከቀኑ 10 ሰዓት ተፈጽሟል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩን የቀብር ስነ ስርዓት በተመለከተ ከንጋቱ 11 ሰዓት በታለቁ ቤተ መንግስት ፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣የአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት ስራአስከያጅ፣6 የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችና የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ካህናት ጋር በህብረት ሙሉ ፀሎተ ፍትሐት አድርሰዋል በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ ከ15/2004 ዓ.ም መሐራ እግዚኦ ለነፍሰ መራሔ መንግሥት ገ/ማርያም፤ አቤቱ የመራሔ መንግሥታችን የገብረ ማርያምን ነፍስ ማር” በማለት ጸሎትዋን አድርሳለች በማድረስ ላይም ትገኛለች፡፡በተለይም በ26/2004 ለ27 አጥቢያ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ከ600 በላይ የሚሆኑ የአዲስ አበባ ካህናትና መዘምራን በህብረት ከምሽቱ 2 ሰዓት ጀምሮ ሙሉ ሌሊቱን ፀሎተ ፍትሐት ሲያደርሱ አድረዋል፡፡

በታላቁ ቤተ መንግስት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የህዝብ ተወካዮች /ቤት አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ፣ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች፣ ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ አምባሳደሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የመከላከያና የፖሊስ አባላት፣ ቤተሰቦቻቸውን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ተገኝተዋል፡፡

በመስቀል አደባባይም 25 በላይ የሀገራት መሪዎችና ርዕሳነ ብሔራት እንዲሁም በርካታ የአህጉራዊና አለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች፣ የመከላከያና ፌደራል ፖሊስ ሰራዊት፣ የመንግስት ሰራተኞችና እንግዶች አስከሬኑን ለመቀበል በስፍራው ተገኝተዋል፡፡  

ክብርት ባለቤታቸው ቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን እንዳሉት መለስን ከልጅነቱ ጀምሮ ነው የማወቀው፡፡ ዱሮም ጀምሮ ህልሙ የነበረው በኢትዮጵያ ፍትህ፣ ሰላምና እድገትን ማስመዝገብ ነበር፡፡ ሁሌም ያልም የነበረው ድህነትን ስለመታገል ነበር፡፡ ጊዜውን ሁሉ ይሰጥ የነበረው ህልሙን ለማሳካት ነበር፡፡ ልጆቼም የሚፈልገውን ጊዜ አልነፈጉትም፡፡ መለስ ለፍትህ፣ ለሰላምና ለፍቅር የቆመ ነበር፡፡ ይህንንም የኢትዮጵያ ህዝብ በማረጋገጡ በጣም አመሰግናለሁ ፡፡

እኔም ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን ሆኜ እሱ የጀመራቸውን የልማት ተግባራት ለማስቀጠል የበኩሌን አስተዋፅኦ አበረክታለሁ ብለዋል፡፡

8 ሰዓት 25 ደቂቃ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስከሬን ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የደረሰ ሲሆን፡፡ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራልም ለ30 ደቂቃ ያህል ደውል የተደወለ ሲሆን አስከሬኑም ከሰረገላው ወርዶ ወደተዘጋጀለት ልዩ የፀሎት ቦታ አርፏል፡፡ በካቴድራሉ ካህናትና መዘምራንም ስርዓተ ፀሎት ተካሂዷል፡፡

 

9 ሰዓት 10 ደቂቃ ላይ የፀሎት ስነ ስርዓት እንደተፈፀመ አስከሬኑ ቤተ ክርስቲያኑን በቀኝ በመዞር 9 ሰዓት 25 ደቂቃ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስከሬን ወደተዘጋጀለት የቀብር ቦታ ያረፈ ሲሆን፤የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀብር ስነ ስርዓት መጠናቀቁን በማስመልከት 21 ግዜ መድፍ ተተኩሷል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አጭር የህይወት ታሪክ

 

 

 

 

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ግንቦት 1 ቀን 1947 . ነው በትግራይ አድዋ ከተማ ከአባታቸው ከአቶ ዜናዊ አስረስ እና ከእናታቸው ወይዘሮ አለምነሽ ገብረልዑል የተወለዱት፡፡

ለቤተሰባቸው ሶስተኛ ልጅ የሆኑት አቶ መለስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በአድዋ ንግስተ ሳባ ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ ባሳዩት ከፍተኛ የትምህርት ብልጫ ከመላው ሀገሪቱ ከተመረጡ ተማሪዎች መካከል አንዱ በመሆን በአዲስ አበባ ጄነራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፡፡

1965 የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን በመቀላቀል ለሁለት አመታት በህክምና ፋካሊቲ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ቢቆዩም በወቅቱ የነበረውን ብሄራዊ ጭቆናን ለመታገል ህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይን በመቀላቀል በርሃ ገቡ፡፡

አቶ መለስ 1967 የተመሰረተው ህወሃትን ከተቀላቀሉ አንስቶ ከታጋይነት እስከ አመራርነት ለህዝቦች እኩልነትና ለኢትዮጵያ ጉስቁልናና ድህነት መወገድ ሲታገሉና ሲያታግሉ ቆይተዋል፡፡

በህዝቦች መሪር ትግልና መስዋዕትነት ደረግ መወገዱን ተከትሎ አቶ መለሰ ዜናዊ በፕሬዚዳንትነት የመሩት የኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት ሁሉንም የፖለቲካ ሃይሎች ያሳተፈ መንግስት ለመመስረት የላቀ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡

አቶ መለስ ዜናዊ የሚመሩት የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ኢህአዴግ ኢትዮጵያ ላለፉት 21 አመታት በሰላም፣ በልማትና በዴሞክራሲ እድገት እንድትጓዝ ጠንካራ አመራር ሰጥቷል፡፡

የኢትዮጵያን ህዝቦች ነባራዊ ሁኔታና የለም አቀፉን እንቅስቃሴ ያጤኑ ጠንካራ የልማት ፖሊሲዎችና ስትራተጂዎችን በመቅረፅና ስራ ላይ በማዋል ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የሚመሩት የኢፌዴሪ መንግስት ኢትዮጵያ በልማት እንድትጓዝ አድርጓል፡፡

የህዝቦች ኑሮ ለዘመናት ከነበረበት ጉስቁልና ተነስቶ በብሩህና በህዳሴ ጎዳና መራመድ የጀመረውም በዚሁ ወቅት ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አጀንዳዎች ላይ የመሪነት ሚና እንድትወጣ የኢትዮጵያና የአፍሪካ ድምፅ በአለም መድረኮች እንዲያስተጋባ ያደረጉት አስተዋፅኦ የላቀ ነበር፡፡

ባለፉት 21 አመታት የተመዘገቡ ተጨባጭ የሰላም የልማትና የዲሞክራሲ ውጤቶች እንዲጠናከሩና ኢትዮጵያ ወደ ከፍታ ማማ እንድትወጣ በመላ ኢትዮጵያውያን የታየውን ፅኑ ፍላጎት እውን ለማድረግ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሃሳብ አፍላቂነት ይፋ የሆነው የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ የኢትዮጵያን ህዳሴ በማረጋገጥ ላለፉት ሁለት አመታት ስኬት አስመዝግቧል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከትግል አጋራቸው ወይዘሮ አዜብ መስፍን ጋር በትዳር 25 አመታት በላይ ተጣምረዋል፡፡ በትዳራቸውም ሶስት ልጆች አፍርተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባደረባቸው ሕመም በውጭ አገር ሕክምና ሲከታተሉ ከቆዩ በኋላ ሰኞ ነሃሴ 14 ቀን 2004 .. 57 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ይታወቃል፡፡

የብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ

 

ነሐሴ 17 ቀን 2004 ..

በመ/ር ዘሩ ብርሃኔ

የብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ፣ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዝደንት፣ የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዝዳንት ሥርዓተ ቀብራቸው ነሐሴ 17 ቀን 2004 . እኩለ ቀን ላይ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ከአኀት አብያተ ክርስቲያናትና ከሌሎችም የተወከሉ የእምነት አባቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ምእመናን በተገኙበት በታላቅ ስነ ስርዓት ተፈጽሟል፡፡

    

የቅዱስነታቸው አስክሬን (ነሐሴ 16 ቀን 2004.) ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ በካህናት ፣በሰንበት ትምህርት ቤቶች ዘማሪያን ፣በፖሊስ ሠራዊት ኦርኬስትራ ማርሽ ባንድና በምእመናን ታጅቦ ከመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ወደ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ከተወሰደ በኋላ በዚሁ ቤተ ክርስቲያን ጸሎተ ፍትሐትና ማኅሌት ሲደርስ አድሯል፡፡ ንጋት ላይ ጸሎተ ቅዳሴው ከተከናወነ በኋላ ከግብፅ፣ከሶርያ፣ ከሕንድና ከአርመን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አኀት አብያተ ክርስቲያናት የተወከሉ አባቶች በየቋንቋቸው ጸሎት አድርሰዋል፡፡

             

የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ተወካይ በበኩላቸው ዓለማችን ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥማት ቀድመው የሚደርሱ እውነተኛ አባት ነበሩ። የእሳቸው ህልፈተ ህይወት ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለመላው የኦርቶዶክስ ክርስትያን አማኞች በሙሉ አስደንጋጭ ዜና ነው። አቡነ ጳውሎስ ለዓለም ሰላም በጣም አስፈላጊ ሰው ነበሩ በማለት ገልጸዋቸዋል፡፡

 

በሥርዓተ ቀብሩ ላይ የኢ... ፕሬዝደንት  የተከበሩ አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ የላኩትን የሐዘን መግለጫ በተወካያቸው አቶ አሰፋ ከሲቶ አማካኝነት የቀረበ ሲሆን፡-ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ለመላው ሰብዓዊ ፍጡር ትልቅ አክብሮት ያላቸውና በህዝቦች መካከል መልካም ጉርብትና እንዲኖር የሰሩ ብልህና መንፈሳዊ መሪ ናቸው። የአገሪቱ ህዝቦችና አፍሪካውያን ሰብዓዊ ቀውስ ሲያጋጥማቸው ፈጥነው የሚደርሱና ለህዝቦች ሰላም ሳይታክቱ የሰሩ አባት እንደነበሩ ተናግረዋል። እኚህ አባት በሰሩት ስራ ዓለም የማይረሳቸው እንደሆኑ የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ ለመላው የኦርቶዶክስ ክርስትያንና ቤተሰቦቻቸው መፅናናትን እንደሚመኙ መልዕክት አስተላልፈዋል ፡፡

በተመሳሳይ በስርዓተ ቀብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እንደተናገሩት ቅዱስነታቸው ባለፉት 20 ዓመታት መንግሥት የጀመረውን የልማት ጉዞ ለማሳካት ያለሰለሰ ጥረት ያደረጉ ታላቅ አባት ነበሩ።  በተለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን አገሪቱ በነደፈችው የልማት ስራ ላይ ተሳትፎ እንዲኖራት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ለልማቱ ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳዩ አባት ነበሩ ብለዋል። በሌላ በኩል በውጭ የሚገኙ የአገሪቱ ቅርሶች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ በማድረግ ረገድና በአገር ውስጥ ያሉ ቅርሶችም በአዓለም ቅርስነት እንዲመዘገቡ ሰዎችን በማስተባበር ከፍተኛ ስራ መስራታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ተተኪ የቤተክርስትያን አባቶችም የእሳቸውን ፈለግ በመከተል በመንግሥት የልማት ስራዎች ላይ በመሳተፍ አገሪቱን ከድህነት ለማውጣት በሚደረገው የልማት ጥረት የበኩላቸውን እንዲወጡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

እንዲሁም የአዲስ አበባ ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ በበኩላቸው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በአገሪቱ የኃይማኖት መቻቻል እንዲጎለብት ትልቅ ጥረት ያደሩጉ ታላቅ መንፈሳዊ መሪ እንደነበሩ አመልክተው በሞታቸው የተሰማቸውን ጥልቅ ኀዘን በከተማዋ ነዋሪዎች ስም ገልጸዋል። በተለይ የአክራሪነትን ጎጂ ባህል በማስተማርና የትምህርት ዕድል በአገሪቱ እንዲስፋፍ የበኩላቸውን የተወጡ ትልቅ አባት እንደነበሩ ጠቁመዋል፡፡ በአገሪቱ ጧሪና ቀባሪ ያጡትን በመደገፍና በጤናው መሰክ ኤች.አይ../ኤድስ በመከላከል ረገድ ያሳዩት ተግባር በተምሳሌት የሚጠቀስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ የዓለም አብያተ ክርስትያናት ተወካይ ባስተላለፉት መልዕክት እኚህ አባት በአገራት መካከል የሚከሰቱ አለመግባባቶችን በማብረድና ሰብዓዊ ቀውስ ያጋጠማቸውን ሀገራት በመደገፍና በማፅናናት ከፍተኛ ስራ የሰሩ ናቸው። በተለይ ሱዳን ውስጥ የነበረውን ችግር ለመፍታት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ይሰጡት የነበረው ጠቃሚ አስተያየት ዓለም የሚረሳው አለመሆኑን ገልፀዋል።

ብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ጥቅምት 25 ቀን 1928 .. በቀድሞው አጠራር በትግራይ ክፍለ ሀገር በአድዋ አውራጃ በእንዳ አባ ገሪማ ገዳም አካባቢ ከአባታቸው ከአፈ መምህር ገብረ ዮሐንስ ወልደ ሥላሴና ከእናታቸው ከወይዘሮ አራደች ተድላ ተወለዱ ሲሆን፡፡ ከስድስት ዓመታት ዕድሜ ጀምሮ እስከ ዕውቀት ድረስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ትምህርትን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንንና የአበው መነኮሳትን ሥርዓት የተከተለ ገዳማዊ ኑሮን በአባ ገሪማ ገዳም እያጠኑ አባቶችን እያገለገሉ እንዳደጉ የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል፡፡

ሥርዓተ ቀብሩን በመምራት ያስፈጸሙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አቃቤ መንበርና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል   ቃለ ምእዳንና ጸሎተ ቡራኬ ሰጥተዋል ብፁዕነታቸው በዚሁ መልእክታቸው የቅዱስ ፓትርያርኩን ቅድስና አውስተው ለመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንና ምእመናት መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡