01610

ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ዘተናገረ በእንተ በዓለ ልደት ዓቢይ ዘእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ሎቱ ስብሐት

01610

ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ  ዘተናገረ በእንተ በዓለ ልደት  ዓቢይ ዘእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ሎቱ ስብሐት
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
•በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣
•ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤
•የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
•በሕመም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤
•እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤
የርስተ መንግሥቱ ወራሾች እንሆን ዘንድ በጌታችን በአምላካችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ዳግመኛ የወለደን እግዚአብሔር አምላክ እንኳን ለሁለት ሺሕ ስምንተኛው የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት በሰላም አደረሳችሁ !!
‹‹ወበዝንቱ ተዐውቀ ፍቅሩ ለእግዚአብሔር ላዕሌነ እስመ ለወልዱ ዋሕድ ፈነዎ ውስተ ዓለም ከመ ንሕየው በእንቲአሁ፤ የእግዚአብሔር ፍቅሩ በዚህ በእኛ ላይ ታወቀ፤ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደዓለም ልኮታልና፤ (1ዮሐ.4፡9)፡፡
የእግዚአብሔር ባሕርይ ፍቅር እንጂ ጥላቻ አይስማማውም፤ ጽድቅ እንጂ ሐሰት አይዋሐደውም፤ ብርሃን እንጂ ጨለማ አይቀርበውም፤ ሕይወት እንጂ ሞት በእርሱ ዘንድ የለምና በፍጹም ፍቅሩ እኛን ለመፈለግ ሥጋችንን ለብሶ በመካከላችን ስለተገኘ ለእርሱ የሚገባ የአምልኮ ምስጋና እናቀርባለን ፡፡
እግዚአብሔር ፍጹም በሆነ ፍቅሩ ሰማያትንና ምድርን እንደዚሁም በውስጣቸው የሚገኙትን፣ የሚታዩና የማይታዩትን ፍጥረታት ሁሉ ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶአል፤ ወይም አስገኝቶአል፣
ፈጣሬ ፍጥረታት የሆነ እግዚአብሔር አምላካችን በየዓይነቱ የፈጠራቸው ፍጥረታት በእርሱ ዘንድ ከሚታወቁ በስተቀር በፍጡራን ዓቅም ተቆጥረው የሚዘለቁ ባይሆኑም በጥቅሉ የሚታዩና የማይታዩ፣ ሕይወት ያላቸውና የሌላቸው ተብለው ሊመደቡ ይችላሉ ፡፡
ከፍጡራን መካከል ሕይወት ያለውና በግዙፋኑ በኩል ሊታይ የማይችለው የቀደመ ስሙ ሳጥናኤል የኋላ ስሙ ሰይጣን፣ ወይም ዲያብሎስ የተባለ ረቂቅ መልአክ፣ ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ነጻ ፈቃድ ለክፉ ነገር በመጠቀም በፈጸመው ትልቅ በደል ለፍርድና ለቅጣት ተዳርጎአል (ኢሳ. 14፡12-15፤ ይሁ1፡6) ፡፡
ይህ ስሑት ፍጥረት በራሱ ስሕተት ሳያበቃ ሕያው ሆኖ በግዘፍ የሚታየውን ሰው በማሳሳት እንደእርሱ ለፍርድና ለቅጣት እንዲጋለጥ አደረገ (ዘፍ 3፡1-24፤ ራእ፣ 12፡7-9)
በዚህም ምክንያት ሰው ሕይወቱን አጣ፤ ሕይወት ማጣት ማለት እግዚአብሔርን ማጣት ወይም ከእግዚአብሔርና ከመልካም ስጦታው መለየት፣ መራቅ፣ መወገድ ማለት ነው፡፡
ዲያብሎስ በዘረጋው ወጥመድ ተሰነካክሎ የወደቀውና ሕይወቱን ያጣው ሰው ለድርብ የሞት ፍርድ ተዳረገ፤
በዚህ ፍርድ መነሻነትም አዳም ከነልጆቹ በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስ፣ በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ገሃነም ወይም ሥጋው በመቃብር ነፍሱ በገሃነም እንዲቀጣ ተፈረደበት (ዘፍ.2፡17፤3፡ 16-20)
ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው አዳም ከእግዚአብሔር በመለየቱ ነው፤ ከእግዚአብሔር የተለየች ሕይወት ለጊዜው ያለች እንኳ ብትመስል ለዘለቄታው የለችምና በቁም ሳለች የሞተች ናት ፡፡
ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ከግንዱ የተለየ ዛፍ ፍሬን ማፍራት እንደማይችል ሁሉ በእኔ የማይኖርም እንደቅርንጫፍ ወደውጭ ይጣላል፣ ይደርቅማል፣ በእሳትም ያቃጥሉታል›› ሲል ያስተማረን ከእግዚአብሔር ውጭ የሆነ ሁሉ ሕይወትን ጨምሮ ምንም ምን ሊያገኝ የማይችል መሆኑን ለማስረዳት ነው (ዮሐ15፡4-6)፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት
ከሰው ልጅ ቀዳማዊ ታሪክ በመነሣት የተፈጸመውን እውነታ ስናስተውል ሰው የሕይወት ራስ የሆነውን እግዚአብሔርን በማጣቱ ከባድ የሆነ የሞት ቅጣት እንዳጋጠመው እናያለን፡፡
ከዚህ በኋላ የተነሣው ጥያቄ ሰው ከዚህ የሞት ቅጣት እንዴት ሊድን ይችላል? የሚለው ነው፡
እግዚአብሔር በልጁ በኩል መልሱን እንደነገረን ሰው ሊድን የሚችለው በፍቅረ እግዚአብሔር ነው፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል ‹‹እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እስከዚህ ድረስ ወዶታል›› ብሎ የድኅነት መነሻውና መድረሻው ፍቅረ እግዚአብሔር እንደሆነ ነግሮናልና ነው (ዮሐ.3፡16-18)
የጌታችን ደቀመዝሙር የሆነው ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስም ‹‹እግዚአብሔር ፍቅር ነው፣ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ አንድ ልጁን ወደዓለም ልኮአልና የእግዚአብሔርን ፍቅር በዚህ ዓውቀናል፤ በፍቅር የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል፤ እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል››ሲል የሕይወታችን ማግኛ ቁልፍ ነገር ፍቅረ እግዚአብሔር እንደሆነ ያረጋግጣል፤ (1ዮሐ4፡16)
ሁሉን የፈጠረና ሁሉን የሚችል ቃለ እግዚአብሔር ወልድን ስቦና ጎትቶ ወደኛ ያመጣው ሌላ ባዕድ ኃይል ሳይሆን በባሕርዩ ውስጥ ያለው ፍጹም ፍቅር ነው ፡፡
ቃለ እግዚአብሔር ወልድ በዚህ ፍቅር ምክንያት ወደእኛ መጣ፣ መጥቶም ሥጋችንን ከማይሞተው አካለ መለኮቱ ጋር በማዋሐድ መለያየትን አስወግዶ ወደእርሱ አቀረበን፡፡
የመለኮትና የሥጋ ተዋሕዶ መጋቢት 29 ቀን በማኅፀነ ማርያም ሲፈጸም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ባሕርየ መለኮት፣ ባህርየ ሥጋን ገንዘብ አደረገ፤ ባህርየ ሥጋም፣ ባህርየ መለኮትን ገንዘብ አደረገ፤ በዚህም መሠረት የአምላክና የሰው ተዋሕዶ ተፈጸመ፡፡
ሰው የሆነው ቃለ እግዚአብሔር ወልድ በተፀነሰ በዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን፣ በታሕሣሥ ወር፣ በዛሬው ዕለት ከቅድስት ድንግል ማርያም በቤተልሔም ተወለደ፤
በዳዊት ከተማ በቤተልሔም የተወለደው ቃለ እግዚአብሔር ወልድ ሥጋችንን ተዋሕዶ በፈጸመው የኃጢአት ካሣ፣ እኛ ከሞት ፍርድ ነጻ ወጥተን ወደ ሕይወት ለመሸጋገር በቅተናል፤ ይህም የሆነው በፍቅረ እግዚአብሔር ነው ፡፡
በመሆኑም ዛሬ በማክበር ላይ የምንገኘው ዓቢይ በዓል በእግዚአብሔር ፍቅር ተመሥርቶ ሰውን ለማዳን የተፈጸመው የጌታችን የአምላካችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት ነው፤ (ሉቃ.2፡6-20)
የልደተ ክርስቶስ በዓል የሰላምና የደስታ፣ የአንድነትና የፍቅር፣ የነጻነትና የእኩልነት በዓል ነው፤ በዚህ ዕለት ሰማያውያን መላእክትና ምድራውያን እረኞች በአንድነትና በፍቅር ‹‹በምድርም ሰላም ይሁን›› እያሉ ስለ ሰላምና ደስታ ዘምረዋል፤
ይህ ዕለት ምድራውያን ነገሥታትና በዝቅተኛ ኑሮ የሚኖሩ እረኞች ፈጣሪያቸውን በእኩልነት ያዩበትና የሰገዱበት፣ በሰማያውያንና በምድራውያን ማለትም በእግዚአብሔርና በሰዎች፣ በሰዎችና በመላእክት መካከል ልዩ ግንኙነት እንደተፈጠረ የተገለፀበት፣ የተበሠረበትና የተዘመረበት ቀን በመሆኑ በዓሉ የሰላምና የደስታ፣ የአንድነትና የፍቅር፣ የነጻነትና የእኩልነት በዓል ተብሎ ይታወቃል፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፤
የዚህ በዓል ዓቢይ መልእክት ‹‹ሰላም በምድር ይሁን›› የሚል መሆኑን በውል መገንዘብ አለብን (ሉቃ. 2፡14)
እግዚአብሔር ጥላቻን፣ መነቃቀፍን፣ መለያየትን፣ ራስ ወዳድነትን አይወድም ባህርዩ ፍቅር የሆነ እግዚአብሔር እነዚህን የማይወድ መሆኑን በማወቃቸው ነው ሰማያውያኑና ምድራውያኑ በአንድነት ሆነው ሰላም በምድር ይሁን ብለው የዘመሩ፤
ማንም ይሁን ማን፣ በየትኛውም ደረጃ ወይም አካባቢ ይኑር፣ ከሰላም ውጭ ጥቅሙን ማረጋገጥ የሚችል የለም፣ ሊኖርም አይችልም፤ በሰላም ውስጥ ሆኖ ግን ሁሉንም ማግኘት እንደሚቻል ባለፉት ሁለት ዐሥርት ዓመታት ውስጥ የታየው ውጤት ምስክር ነው፡፡
ዛሬም ዓለማችንም ሆነ ሀገራችን ከሰው ሠራሽና ከተፈጥሮ አደጋዎች በቀላሉ ማምለጥ የሚችሉት ከሁሉ በፊት ሰላምን በአስተማማኝ ሁኔታ ይዘው ሲጓዙ ነው፤
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም ተመላልሶ ሰውን ከሞት ያዳነው ማንንም ሳይጎዳ በሰላም ጎዳና ብቻ ተጉዞ ነው ፡፡
ጥላቻና ራስ ወዳድነት ሲያፈርሱና ሲያጠፉ እንጂ ሲያለሙና ሲገነቡ በየትኛውም የዓለማችን ክፍል ታይተውም፣ ተሰምተውም፣ በታሪክ ሲደገፉም አይተን አናውቅም፤
ሀገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በልማትና በዕድገት እየገሠገሠች ያለች፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነገ ብሩህ ተስፋ ትሆናለች ተብላ ተስፋ የተጣለባት ሀገር ነች፤
ይህ ተስፋ እግዚአብሔር ባርኮልን በሃይማኖት፣ በዘር፣ በቋንቋ፣ በቀለም ወዘተ ሳንለያይ መላ ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነን ያስገኘነው የልማት ፍሬ እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው፡፡
የተገኘው ፍሬ ልማት እየበረከተና እየደለበ ወደፊት እንዲቀጥልና እንዲያድግ እንጂ በማናቸውም ምክንያት ወደኋላ እንዲመለስ ሕዝባችን መፍቀድ የለበትም፡፡
መላው ሕዝባችን በሚገባ ማጤን ያለበት ነገር ቢኖር ምንጊዜም የችግር መፍትሔ ሰላምና ልማት እንጂ ሌላ አማራጭ መፍትሔ የሌለ መሆኑን ነው፡፡
ስለሆነም ሁሉም የሀገራችን ሕዝቦች የገናን የሰላም መዝሙር እየዘመሩ ለጋራ ዕድገትና ለእኩልነት፣ ለሕዝቦች አንድነትና ለዘላቂ ልማት በጽናት መቆም ይኖርባቸዋል ፡፡
ሰላም ትልቁ የገና ስጦታ ነው፤ ልማትም የህልውና ማረጋገጫ ጸጋ ነው፤ ሁሉንም በእኩል እንጠብቃቸው፡፡
በመጨረሻም
በዚህ ዓመት በሀገራችን በተከሠተው የዝናም እጥረት ምክንያት ለምግብ እጦት የተጋለጡ በርካታ ወገኖቻችን የወገንን እጅ በተስፋ እየተጠባበቁ ይገኛሉ፤
እነዚህ ወገኖች ግማሽ አካላችን መሆናቸውን ተገንዝበንና ጌታችን እኛን ለመፈለግ ወዳለንበት የመጣበትን ፍቅር አብነት አድርገን፣ እኛም እነርሱ ወዳሉበት በፍቅር በመሄድ በሁሉም ነገር ልንረዳቸውና አለን ከጎናችሁ ልንላቸው ይገባል፤
አነሰ ሳንል በወቅቱ ፈጥነን እጃችንን ልንዘረጋላቸውና በአጠገባቸው ሆነን ልናበረታታቸው ይገባል፤ እግዚአብሔር ሁላችንን እንደወደደን እኛም ወንድሞቻችንን በመመገብ፣ በማልበስና ችግራቸውን ሁሉ በመጋራት ለእግዚአብሔርና ለወንድሞቻችን ያለንን ፍቅር ዛሬውኑ በተግባር እንድናሳይ መልእክታችንን በእግዚአብር ስም እናስተላልፋለን ፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክ
መልካም የልደት በዓል ያድርግልን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
አሜን

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ታሕሣሥ 28 ቀን 2008 ዓመተ ምሕረት
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

{flike}{plusone}

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና ታቦተ ጽዮን

እግዚአብሔር አምላክ ሕዝበ እስራኤልን ከግብጽ ባርነት ካወጣቸው በኋላ የአምልኮ ሥርዐታትን ይፈጽሙበት ዘንድ የምስክሩን ድንኳን፣ የቃል ኪዳኗ ታቦትንና ለአምልኮ ሥርዐቱ ማከናወኛ የሚያገለግሉ ልዩ ልዩ ንዋያተ ቅድሳትን እንዲሠሩ በሙሴ በኩል ታዘው ነበር፡፡ ከቃል ኪዳኗ ታቦት ውስጥም በእግዚአብሔር ጣት ዐሥርቱ ትእዛዛት የተጻፉበት የሕጉ ጽላት፣ አርባ ዓመት ሙሉ እስራኤላውያን በሲና ምድረበዳ የተመገቡትን መና የያዘች መሶበ ወርቅ፣ አሮን ለክህነት አገልግሎት ስለመመረጡ ምስክር የሆነችው ለምልማና ፍሬ አፍርታ የተገኘችው የአሮን በትር ይገኙባታል፡፡(ዕብ.9፡4)
ታቦተ ጽዮን በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትመሰላለች፡፡ ይህን ለመረዳት ግን ስለ ታቦተ ጽዮን አሠራርና መንፈሳዊ ትርጉም አስቀድመን ልንረዳ ይገባናል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ታቦተ ጽዮንን እንዲሠራ ብልሃትን፣ ጥበብን፣ ማስተዋልን፣ ዕውቀትን ይለይ ዘንድ መንፈሱን ያሳደረበትን ከይሁዳ ወገን የሆነውን ባስልኤልን መረጠ ፡፡(ዘፀ.25፡9) እርሱም እግዚአብሔር በሰጠው ማስተዋል ከማይነቅዝ እንጨት ርዝመቷ ሁለት ክንድ ተኩል፤ ወርዱዋም አንድ ክንድ ተኩል፣ ቁመቷም አንድ ክንድ ተኩል እንዲኖራት አድርጎ ታቦቷን ሠራት፡፡ በመቀጠል በውስጥም በውጪም በጥሩ ወርቅ ለበጣት፣ ከታቦቷም ዙሪያ የወርቅ አክሊልን አደረገላት፡፡
ካህናት ታቦተ ጽዮንን ለመሸከም እንዲረዳቸውም በዐራቱም መዓዘናት በወርቅ የተሠሩ ቀለበቶችንና በእነርሱም ውስጥ የሚገቡ ሁለት መሎጊያዎችን ሠራ፡፡ ከጥሩ ወርቅም የስርየት መክደኛውን በቃል ኪዳን ታቦቷ ላይ በርዝመቷና በወርደዋ ልክ ሠራ፡፡ የስርየት መክደኛውን እንዲጋርዱት አድርጎም ጥሩ ከሆነ ከተቀጠቀጠ ወርቅ ኪሩቤልን ሠራ፤ በስርየት መክደኛው ግራና ቀኝም አደረጋቸው፡፡ እነዚህ በጥሩ ወርቅ የተሠሩት ሁለቱ ኪሩቤል ፊታቸው ወደ ስርየት መክደኛው ሆኖ እርስ በእርሳቸው የሚተያዩ ተደርገው የተሠሩ ናቸው ፡፡ በዚህ በስርየት መክደኛው በሁለቱ ኪሩቤል መካከል እግዚአብሔር ለሙሴ በመገለጥ ሰው ከባልንጀራው እንደሚነጋገር ያነጋግረው ነበር፤ ለሕዝቡ በደመና ዐምድ ይታያቸው ነበር፡፡(ዘፀ.25፡22፤33፡8-11)
ወደ ትርጓሜው ስንመጣ ታቦተ ጽዮን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ስትሆን፣ በውስጡዋ የያዘችው የሕጉ ጽላት የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ ታቦቷ ከማይነቅዝ እንጨት መሠራቷ የጌታን እናት ንጽሕናን የሚያመለክት ሲሆን በውጪም በውስጧም በጥሩ ወርቅ መለበጡዋ የቅድስናዋና ድንግል በሕሊና ወድንግል በሥጋ መሆኗን የሚያስረዳን ነው፡፡ ታቦቷን ዐራት ሌዋውያን ካህናት ይሸከሟት ዘንድ በግራና በቀን በተዘጋጁ ዐራት ከወርቅ የተሠሩ ቀለበቶች ሲኖሩአት፤ በነዚያ የወርቅ ቀለበቶች ውስጥ ሁለት መሎጊያዎች ይገቡባቸዋል፡፡ ታቦተ ጽዮንን ለማንቀሳቀስ ሲፈለግ ዐራት ካህናት

በመሎጊያዎቹ ይሸከሟታል፡፡
ይህ ሥርዓት በሰማያትም የሚታይ እውነታ ነው፡፡ የጌታን መንበር ገጸ ንሥር፣ ገጸ ሰብእ፣ ገጸ ላህም፣ ገጸ አንበሳ ያላቸው አርባዕቱ እንስሳት ይሸከሙታል፡፡(ኢሳ.6፡1-5፤ ሕዝ.1፡1-16) እንዲሁም ለአማናዊቷ ታቦት ቅድስት ድንግል ማርያም የምሥራች የሚናገሩ፣ ሰላምንም የሚያወሩ፣ የመልካምንም ወሬ፣ መድኃኒትንም የሚያወሩ፣ ጽዮንንም አምላክሽ ነግሦአል የሚሉ እግሮቻቸው በተራሮች ላይ እጅግ ያማሩ ናቸው የተባለላቸው የእርሱዋንና የጌታችን ስም ተሸክመው የሚሰብኩ ወንጌላውያን አሏት፡፡(ኢሳ.52፡7)የስርየት መክደኛው ታቹ መቀመጫው ንጹሐን አንስት ላዩ መክደኛው የንጹሐን አበው ግራና ቀኙ የወላጆቹዋ የሐናና የኢያቄም ምሳሌ ነው፡፡ እርሱን በክንፎቻቸው የጋረዱት ኪሩቤል የጠባቂ መልአክ ቅዱስ ሚካኤልና የአብሣሪው መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ምሳሌዎች ናቸው፡፡
የስርየት መክደኛው ስርየቱ የሚፈጸምበት ስፍራ ነው፡፡ ነገር ግን እውነታውን ስንመለከት በዚህ ቦታ ምንም ዓይነት መሥዋዕት ሲቀርብ እንዳልነበር እንረዳለን፡፡ ይህም በጊዜው አማናዊው መሥዋዕት ገና እንዳልተሠዋ ያስገነዝበናል፡፡ ይህ ስፍራ እግዚአብሔር ለሙሴ የሚገለጥበት ቦታ ነው፤ ከእርሱ ውጪ ሌላ ነገር በእዚያ ላይ ማረፍ የለበትም፡፡ ይህ በራሱ የሚሰጠን አንድ ማስተዋል አለ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለአዳም የገባውን ቃል ኪዳን ሊፈጽም ሰው በሆነ ጊዜ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርብበት ልዩ ስፍራ እንዳለ ያመላክተናል፡፡ ስለዚህም ይህ ስፍራ ለዚህ እንደተጠበቀ ወይም በዚህ ምሳሌ አማናዊ መሥዋዕት የሚቀርብበት ሥፍራ እንደሚያስፈልግ የሚያሳስብ ነው፡፡ ይህ እንደሆነ ለማመልከት ሲባል ለኃጢአት የቀረበው መሥዋዕት ከታረደ በኋላ ካህኑ ደሙን በጣቱ በመንከር ሰባት ጊዜ በስርየት መክደኛው አንጻር በመገናኛ ድንኳን ውስጥ ይረጨው ነበር፡፡(ዘሌዋ.4፡6) ነገር ግን ይህ ደም ከዚያ ስርየት መክደኛው ላይ አያርፍም ነበር ምክንያቱም በዚህ ስፍራ መቅረብ ያለበት መሥዋዕት መለኮት የተዋሐደው ነፍስ ግን የተለየው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ክቡር ሥጋውና ቅዱስ ደሙ ነውና፡፡
ይህ የስርየት መክደኛ ሌላም ለእኛ የሚያስተላለፈው መልእክት አለው፡፡ መልእክቱም አማናዊው መሥዋዕት መቅረቡ እንደማይቀርና፣ መሥዋዕቱ የሚቀርብበት ስፍራ በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ሆኖ እግዚአብሔር በምሕረት በሚገለጥበት በጸጋ ዙፋኑ በጽላቱ ላይ መሆን እንዳለበት ነው፡፡(ዕብ.4፡16) በዚህም እግዚአብሔር አምላክ በነቢዩ ሚልክያስ ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይሆናልና በየስፍራውም ስለስሜ ዕጣንን ያጥናሉ ንጹሕም ቁርባን ያቀርባሉ(ሚል.1፡11) እንዳለው የስርየት መክደኛው በዓለም ዙሪያ ላለችው አንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን ምሥጢረ ቁርባንን ለምትፈጽምበት ጽላት ወይም ታቦት ምሳሌ መሆኑን ያሳየናል፡፡ በሐዲስ ኪዳን ጽላቱ(ታቦቱ) የሚያርፍበት ስፍራ መንበር ተብሎ ሲጠራ የእግዚአብሔር ስም የተጻፈበትና ቅዱስ ሥጋው ክቡር ደሙ የሚፈተትበት ደግሞ ጽላት ወይም ታቦት ወይም መሠዊያ ተብሎ ይጠራል፡፡

የስርየት መክደኛው በታቦቱ አናት ላይ መሆኑም ቅዱስ ኤፍሬም የእኛን ሥጋ ለነሣኸውና ፣ መልሰህ ለእኛ ለሰጠኸን ፣ ለአንተ ክብር ምስጋና ይሁን ፡፡ ከእኛ በሆነው ሥጋህ በኩል እጅግ የበዛውን የአንተን ስጦታ ተቀበልን፡፡ብሎ እንዳመሰገነ፤ እግዚአብሔር ቃል ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረቡን ያሳየናል፡፡ የስርየት መክደኛውን የሚጋርዱት በጥሩ ወርቅ የተሠሩት የኪሩቤል ምስሎችም አማናዊው መሥዋዕት በሚሠዋበት ጊዜ በዙሪያው ረበው የሚገኙ የመላእክት ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ይህን ለማስገንዘብ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በመንበረ ታቦቱ ላይ ምስለ ፍቁር ወልዳ እንዲቀመጥ ታዝዛለች፡፡ ምስለ ፍቁር ወልዳን ላስተዋለ ሰው በትክክል የታቦተ ጽዮንን መንፈሳዊ ትርጉምን ይረዳል፡፡
ይህን ድንቅ የሆነ መንፈሳዊ ትርጉምን ይበልጥ ለመረዳት አንድ ምሳሌ የሚሆነንን እውነታ እንመልከት፡፡ ንጉሥ ዳዊት የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑ ታቦት ከአቢዳር ቤት ወደ ጽዮን ከተማ ባስመጣበት ጊዜ በታቦተ ጽዮን ፊት ለእግዚአብሔር በሙሉ ኃይሉ በደስታ እየዘለለ መንፈሳዊ መዝሙርን አቅርቦ ነበር ፡፡(2ሳሙ.6፡12-17) ይህን ዓይነት ተመሳሳይ ድርጊት በሐዲስ ኪዳንም ተፈጽሞል ፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድስት ኤልሳቤጥን በተሳለመቻት ጊዜ የስድስት ወር ፅንስ የነበረው ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ የጌታችንን እናት የሰላምታ ድምፅ በሰማ ጊዜ እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ከእናቱ ማኅፀን ውስጥ ሳለ በደስታ ዘሎአል(ሰግዶአል)፡፡ (ሉቃ.1፡44) ቅዱስ ዳዊት በታቦተ ጽዮን ፊት እንዲያ ደስ መሰኘቱና ለአምላኩ የምስጋና ቅኔን መቀኘቱ ለሰው ልጆች ሁሉ የመዳናቸው ምክንያት የሆነችውን ቅድስት ድንግል ማርያምንና ልጁዋን ኢየሱስ ክርስቶስን በታቦተ ጽዮን በኩል በማየቱ ነበር፡፡
ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያን አባቶችም ይህንን እውነታ ይጋሩታል ፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ኤፍሬም፡- ከአዳም ጎን በተገኘችው አንዲት አጥንት ምክንያት ሰይጣን ከአዳም ማስተዋልን አራቀ፡፡ ነገር ግን ከእርሱ አብራክ በተገኘችው በቅድስት ድንግል ማርያም ምክንያት በእርሱ ላይ ሠልጥኖ የነበረው ሰይጣን እንደ ዳጎን ተሰባብሮ ወደቀ፡፡ ታቦተ ጽዮን በተባለችው በቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን ውስጥ ባደረው በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የድል አዋጅ ታወጀ ፡፡ በቃል ኪዳኑዋ ታቦት ሥር ዳጎን ተሰባብሮ እንደተገኘ እንዲሁ ክፉው ሰይጣን በታመኑበት ፊት ድል ተነሳ፡፡
እግዚአብሔር በቃል ኪዳኗ ታቦት ኃይሉን በመግለጥ ዳጎንን ሰባብሮ እንደጣለው እንዲሁ እግዚአብሔር ቃል ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ በመወለድ በኃጢአት ምክንያት በእኛ ላይ ሠልጥኖ የነበረውን ሰይጣንን ድል ነሳው፡፡ (1ሳሙ.5፤6) ሲል ቅዱስ ጀሮም ደግሞ  ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድስትና ንጽሕት ነበረች፡፡ በቃል ኪዳኗ ታቦት ውስጥ የሕጉ ጽላት ብቻ እንደነበር እንዲሁ እርሷም በሕሊናዋ ከእግዚአብሔር ሕግጋት ውጪ ሌላ ምንም ሃሳብ አልነበራትም፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም በውስጥም በውጪም ነውር የሌለባት ንጽሕት ናት፡፡ እንደ ቃል ኪዳኗ ታቦት በውጪም በውስጥም በቅድስና የተጌጠችና ሕጉንም ጠብቃ የተገኘች የክርስቶስ ሙሽራ ናት ፡፡ በቃል ኪዳን ታቦቱ ውስጥ ከሕጉ ፅላት ውጪ ሌላ ምንም ነገር እንደሌለ እንዲሁ አንቺም ቅድስት ሆይ በሕሊናሽ ምንም ነውር የሌለብሽ ቅድስት ነሽ፡፡ብሎ ሲያመሰግናት፤ የእስክንድርያው ዲዮናስዮስ ደግሞ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካህን ይሆን ዘንድ በሰው እንዳልተመረጠ እንዲሁ ቅድስት ድንግል ማርያም የጌታ ማደሪያ ትሆን ዘንድ በእግዚአብሔር የተመረጠችና በመንፈስ ቅዱስ ለእርሱ ማደሪያነት የተዘጋጀች ናት፡፡ የመለኮት ማደሪያ ቅድስት ድንግል ማርያም እግዚአብሔር የከተመባት ከተማ ሆና ትኖር ዘንድ ለዘለዓለም በእግዚአብሔር ታትማለች  በማለት ስለእርሱዋ ይመሰክራል፡፡
አዳም ድኅነቱ ከሴት ወገን በሆነች በቅድስት ድንግል ማርያም በኩል እንደሆነ ተረድቶ ለሚስቱ  ሔዋን ብሎ ስም እንደሰጣት እንዲሁ ንጉሥ ዳዊት በቅድስት ድንግል ማርያም በኩል እንደሚድን በመረዳቱ አምባዬና መጠጊያዬ ነሽ ሲላት ጽዮን ብሎ ለድንግል ስያሜን እንደሰጣት በመዝሙራቱ ማስተዋል እንችላለን፡፡ጽዮን የንጉሥ ዳዊት ተራራማዋ ከተማ ስትሆን፣ የስሟ ትርጓሜ አምባ፣ መጠጊያ ማለት ነው፡፡ ይህን ይዘው ብዙዎች ነቢያት ስለድንግል ሲናገሩ ጽዮን የሚለውን ስም ተጠቅመዋል፡፡
ነቢያት ስለቅድስት ድንግል ማርያም ሲናገሩ ጽዮን የሚለውን ስም እንደሚጠቀሙ ወደ ብሉይ ኪዳን ሳንገባ በሐዲስ ኪዳን ብቻ ስለ ጽዮን የተጻፉትን በማንሣት ማረጋገጥ እንችላለን፡፡ ለምሳሌ ነቢዩ ኢሳይያስ ከአይሁድ ወገን የሆኑ የራሳቸውን ሥርዐትና ሕግ ለማቆም ሲሉ በክርስቶስ ከማመን ስለተመለሱት ሲጽፍ፡- እነሆ በጽዮን የእንቅፋት ድንጋይና የማሰናከያ ዐለት አኖራለሁ(ኢሳ28፡16፣8፡14) አለ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ስለክርስቶስ የተነገረ ነው በማለት በሮሜ 9፡33 ላይ ጠቅሶት እናገኛለን፡፡ስለዚህም ነቢዩ ኢሳይያስና ቅዱስ ጳውሎስ ጽዮን ያሏት ቅድስት ድንግል ማርያምን እንደሆነ በዚህ ኃይለ ቃል መረዳት እንችላለን፡፡ የማሰናከያ ዐለት የተባለው ክርስቶስ እንደሆነም እነሆ የብዙዎች ልብ ሐሳብ ይገለጥ ዘንድ ይህ ለእስራኤል ላሉት ለብዙዎች ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ተሾሞአል፡፡(ሉቃ.2፡34-35) ተብሎ ተጽፎአል፡፡ ስለዚህ የማሰናከያ አለት የተባለውን ክርስቶስን ፀንሳ የወለደችው ቅድስት ድንግል ማርያም ጽዮን መባሉዋን በእነዚህ ጥቅሶች ማረጋገጥ እንችላለን፡፡
ነቢዩ ዳዊትና ኢሳይያስ ጽዮን ከተሰኘች የሙሴ ፅላት ካህኑ በሚያቀርበው መሥዋዕት አማካኝነት አፋዊ ድኅነት እንደተደረገ፣ ከእመቤታችን ከተወለደው አማኑኤል አማናዊ ድኅነት እንዲፈጸምልን መድኃኒት ከጽዮን ይወጣል ከያዕቆብም ኃጢአተኝነትን ያስወግዳል(መዝ.13፡10፤ኢሳ.59፡20) በማለት ስለክርስቶስ ትንቢትን ተናግረዋል፡፡ ይህንንም ቅዱስ ጳውሎስ ለጌታችን ለመድኃኒታችን ሰጥቶ በሮሜ.11፡26 ላይ ተጠቅሞበታል፡፡ በዚህም ቦታ ጽዮን ያሏት ቅድስት ድንግል ማርያምን መሆኑን ማስተዋል እንችላለን፡፡ ምክንያቱም እርሱ ከእርሱዋ እንጂ ከሌላ አልተወለደምና፡፡ ነገር ግን መድኃኒትየተባለው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለመሆኑ መልአኩም እንዲህ አላቸው፡- እነሆ ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁ በዳዊት ከተማ መድኅኒት እርሱ ክርስቶስ ተወለደ(ሉቃ.2፡10) በማለት ገልጾልናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ኢየሱስ ማለት መድኃኒት ማለት ነው (ማቴ.1፡21) የኢየሱስም እናት ደግሞ ቅድስት ድንግል ማርያም መሆኑዋን ማንም የማይክደው ሐቅ ነው፡፡ ስለዚህም ነቢያቱ መድኃኒት ከጽዮን ይወጣልሲሉ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጽዮን ከተባለችው ከቅድስት ድንግል ማርያም ይወለዳል ማለታቸው እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡
ምንም እንኳ ቅዱስ ዳዊትና ሌሎች ነቢያት ስለቅድስት ድንግል ማርያም ለመናገር ሲሉ ጽዮን የሚለውን ስም አብዝተው ይጠቀሙ እንጂ አልፎ አልፎ ግን ጽዮን በማለት ስለ ከተማዋ ተናግረው እናገኛለን፡፡ ለምሳሌ ሚክያስ ስለዚህ በእናንተ ምክንያት ጽዮን ትታረሳለች(ሚክ.3፡12)ይላል፡፡ ይህ በቀጥታ ስለጽዮን ከተማ የተነገረ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ስለጌታችን መናገር ሲፈልግ ስለእርሱ የሚናገሩትን ብቻ መርጦ እንደተጠቀመ እንመለከታለን፡፡ እኛም እንዲሁ ለቅድስት ድንግል ማርያም የተነገሩትን አስተውለን ልንለያቸው ይጠበቅብናል፡፡ ምክንያቱም አንዳንድ ስለቅድስት ድንግል ማርያም ያልተጻፉ ነገር ግን ጽዮን የሚለውን ስም ይዘው የሚገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት አሉና፡፡ ቢሆንም ስለታቦተ ጽዮን የተጻፉ ገቢረ ተአምራት ሁሉ እግዚአብሔር ቃል ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለዶ ለፈጸማቸው ታላላቅ የድኅነት ሥራዎች ምሳሌዎች ናቸው፡፡
በዚህም መሠረት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በብሉይ ኪዳን በታቦተ ጽዮን የተፈጸሙትን ገቢረ ተአምራት ለድንግል ማርያምና ለጌታችን ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በመስጠት ተርጉማ ለልጆቹዋ ታስተምራለች፡፡ በኅዳር 21 ቀንም በታቦተ ጽዮን የተፈጸሙት ታላላቅ ተአምራት የሚታሰቡበት ቀን ነው፡፡ በዚህ ቀን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በታቦተ ጽዮን የተፈጸሙትን ታላላቅ ተአምራት እግዚአብሔር ቃል ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ በመወለድ ከፈጸማቸው ታላላቅ የድኅነት ሥራዎች ጋር በማነጻጸር በድኅነታችን ውስጥ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ድርሻ ምን እንደሆነ ትገልጻለች፡፡ ለምሳሌ ታቦተ ጽዮንን የተሸከሙ ካህናት እግራቸው የዮርዳኖስን ባሕር በመንካቱ ባሕሩ ለሁለት እንደተከፈለ እንዲሁ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ ተወልዶ ጥምቀትን በራሱ ጥምቀት በመመሥረት ከሰይጣን ባርነት ወደ እግዚአብሔር ልጅነት እንዳሸጋገረን እናወሳበታለን(ኢያ.3፤ ማቴ.3፡13-17) ፡፡
ፍልስጥዬማውያን ከእስራኤላውያን ጋር ውጊያ በገጠሙ ወቅት ታቦተ ጽዮንን ማርከዋት ዳጎን በሚባለው ቤተ ጣዖታቸው ውስጥ አኑረዋት ነበር፡፡ ነገር ግን ታቦቷ ዳጎኑን በፊቷ ሰባብራ እንደጣለችው እንዲሁ ከቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደው በጌታችን በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ላይ ሠልጥኖ የነበረው ሰይጣን ድል መነሳቱን እናወሳበታለን፡፡ ((1ሳሙ.5፤6)
 እግዚአብሔር አምላክ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ረድኤትና በረከት ያሳትፈን፡፡ የእግዚአብሔር አብ ጸጋ የእግዚአብሔር ወልድ ቸርነት የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አንድነት በእኛ ላይ ለዘለዓለም ጸንቶ ይኑር አሜን!!

{flike}{plusone}

01369

የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት በተለምዶ 22 ማዞሪያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሕንፃ ግናባታው ተጀምሮ ቆሞ የነበረውን ሕንፃ ግንባታ ለማስጀመር የውል ሰነድ ተፈራረመ

                                                                                                                                              በመ/ር አምሃ ኃብቴ(BA)

01369

የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሰበካ ጉባኤና ልማት ኮሚቴ ቀደም ሲል ከበጎ አድራጊው ክቡር በኵረ ምዕመናን ከበደ ተካልኝ 1634 ካሬ ሜትር ቦታ በስጦታ አግኝቶ በ1070 ካሬ ሜትሩ ላይ የሕንፃ ግንባታው ከተጀመረ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች ለተወሰኑ ዓመታት ቆሞ የቆየ ቢሆንም የዲዛይን ክለሳ ተደርጎለት በአሁኑ ሰዓት  ሕንፃውን ለማስጀመር ተገቢውን ሕጋዊ የጨረታ ሂደት ካከናወነ እና ከፈጸመ በኋላ ጥቅምት 20 ቀን 2008 ዓ.ም ጨረታውን ካሸነፈው ከባማኮን ኢንጂነሪንግ ኃ.የተ.የግ.ማኅበር ጋር የውል ስምምነት ፈጸመ፡፡ የካቴድራሉ ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት ከላይ ከተጠቀሰው ድርጅት ጋር የውል ስምምነቱን ሲፈጽም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ተወካይ ልዑካን፣ የኤም ጂ ኤም ኮንሰልት ኃ.የተ.የግ.ማኅበር ተወካይ፣ የካቴድራሉ ሰበካ ጉባኤ፣ ልማት ኮሚቴ አባላትና የአስተዳደር ሠራተኞች በተገኙበት የፊርማ ስነ ሥርዓቱ ተከናውኗል፡፡
የሕንፃው አጠቃላይ ወጪ ብር ቫትን ጨምሮ 72‚280‚478.00 (ሰባ ሁለት ሚሊዮን አራት መቶ ሰባ ስምንት ብር ብቻ) ሲሆን ነገር ግን የግንባታ ሥራው በሁለት ምዕራፍ እንዲሠራ ከተቋራጭ ድርጅቱ ጋር ስምምነት ላይ በመደረሱ ለመጀመሪያው ምዕራፍ ሥራ ውል ተፈጽሟል፡፡የመጀመሪያው ምዕራፍ ሥራው የሚያካትተው፡-
1.የኮንክሪት ሥራ ሙሉ ለሙሉ
2.የጣሪያ ሥራው ሙሉ በሙሉ
3.የግድግዳ ሥራ ማለትም ብሎኬትና ጡብ ሥራ በአጠቃላይ
4.የብረት ውቅር ሥራና ተያያዥ ሥራዎች በሙሉ
5.የልስንና ተያያዥ ሥራዎች በሙሉ
6.የመብራት መስመር ዝርጋታ 1-10.3 ድረስ
7.የንፁህ ውሃ አቅርቦትና የፍሳሽ ማስወገጃ መስመር ዝርጋታ ሥራዎች ከተራ ቁጥር 4-5 ድረስ ያካትታል፡፡ ይህንን ሥራ ለመሥራት አጠቃላይ ወጪው ከቫት በፊት ብር 27‚681‚604.80 (ሃያ ሰባት ሚሊዮን ስድስት መቶ ሰማንያ አንድ ሺህ ስድስት መቶ አራት ብር ከሰማንያ ሳንቲም) ሲሆን ሥራውን ለማጠናቀቅ 365 ቀናት የሚያስፈልጉት መሆኑንም ስምምነት በተደረገበት ቀን ተገልጿል፡፡ በዚህ አጋጣሚ የተቋራጭ ድርጅቱ ባለቤት ክቡር ኢንጂነር ግርማ ገላው  ከዚሁ ገንዘብ ላይ የ4% (የአራት በመቶ) ቅናሽ ያደረጉልን በመሆኑ ስለአደረጉልን ቅናሽ የካቴድራሉ አስተዳዳሪ ክቡር ሊቀ ሥልጣናት አባ ገብረ ሥላሴ በላይ በካቴድራሉ ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት ስም አመስግነው አጠር ያለ ትምህርት ከሰጡ በኋላ የፕሮግራሙ ፍጻሜ ሆኗል፡፡
የሕንፃው አጠቃላይ ይዘት ሕንፃው በ1070 ካሬ ሥፋት ቦታ ላይ ያረፈ ሲሆን ቤዝመንት፣ ምድር ቤት፣ መዳረሻ፣ አምስት ወለል (ፎቅ) እና  መዳረሻ (B+G+M+5+M)  ያለው ዘመናዊ ሕንፃ ነው፡፡
ሕንፃው የሚሰጠው አገልግሎት ሕንፃው ሁለገብ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን ቤዝመንቱ ለመኪና ማቆሚያ (parking lot) ፣ ምድር ቤቱ ለባንከ፣ ለኢንሹራንስና ሌሎች ተያያዥ አገልግሎት ለሚሰጡ ሥራዎች የሚሆን ሲሆን አምስቱ ወለሎች ደግሞ ለቢሮ፣ለሱቅ፣ አዳራሾችና ተያያዥ አገልግሎት የሚሰጡ ክፍሎች ያሉት ነው፡፡

{flike}{plusone}

000921

የእስክንድርያ ፖፕ እና የመንበረ ማርቆስ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዎድሮስ ዳግማዊ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው

                                                   በመ/ር ዘሩ ብርሃኔ(MA)

000921

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዎድሮስ ዳግማዊ የአሌክሳንድሪያ ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ማርቆስ መንበረ ፓትርያርክ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በመስቀል ደመራ በዓል ላይ እንዲገኙ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በተደረገላቸው ግብዣ መሠረት ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል።
በዚሁም መሠረት ቅዱስነታቸው መስከረም 14 ቀን 2008 ዓ.ም. ከሌሊቱ 9:00 ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በሚደርሱበት ጊዜ  በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት  ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆነ በነጋታው ቅዳሜ መስከረም 15 ቀን 2008ዓ.ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፤ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጰሳት ፣  የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማት እና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ መዘምራንና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች፣ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት፣ ‹‹የእንኳን ደኅና መጡ›› ፕሮግራም ተከናውኗል፡፡ ቅዱስነታቸውም በበአሉ ላይ  ለተገኙ ህዝበ ምእመናን ቡራኬ ሰጥተዋል፡፡
ቅዱስነታቸው  ስለ ሁለቱም አብያተ ክርስቲያናት ታሪካዊ ግንኙነት በሰፊው ከገለፁ በኋላ ኢትዮጵያ ለዕድገቷ የምታከናውናቸውን ተግባራት የግብፅ ቤተክርስቲያን እንደምትደግፍ ተነግረዋል። “አንድ ከሚያደርጉንና ከሚያስተሳስሩን ጉዳዮች ዋናው ነገር የዓባይ ወንዝ ነው” ያሉት አቡነ ታዎድሮስ “የአገራቱ መሪዎችም ምንም ዓይነት ልዩነትና ፀብ እንደማይፈጥሩ እርግጠኞች ነን” ብለዋል። “የዓባይ ወንዝ እግዚአብሔር በነፃ የሰጠን ስጦታ ነው፣ ሁሉም የሰው ልጆች ከፀሐይና ከነፋስ በነፃ እንደሚጠቀሙ ሁሉ ከዚህም ወንዝ በነፃ ይጠቀማሉ ይህንንም ስጦታ በነፃ እየተጠቀምን በፀጋ እንኖራለን” ሲሉ ነው የተናገሩት።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ አቡነ ማትያስ በበኩላቸው አገራቱ ባህልን፣ ቋንቋን፣ሥነ ጽሑፍን፣ ንግድን፣ መንፈሳዊና ማሕበራዊ ጉዳዩችን ያካተተ የቆየ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰዋል።”ከዚህም ባለፈ የአባይ ወንዝን በጋራ የምንጠጣ ታሪካዊያን ሕዝቦች ነን” ሲሉ ተናግረዋል።
ወንዙን በአግባቡና በፍትኃዊነት ከተጠቀምንበት ለሌሎች አገራት ጭምር የሚበቃ ማለቂያ የሌለው የአምላክ በረከት መሆኑን ገልፀዋል።ይህን ወንዝ በሠላማዊ መንገድ በመጠቀም የሁለቱ አገራት መንፈሳዊና ማኅበራዊ ግንኙነቶች ለዓለም ምሣሌ በሚሆን መልኩ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው አባታዊ ምክራቸውን አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስና የግብፅ ኮፒቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያናት መንፈሳዊ ግንኙት ከ1 ሺህ 600 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ መሆኑን የታሪክ ድርሳት ያስረዳሉ።

{flike}{plusone}

0908

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የ2008 ዓ.ም የዘመን መለወጫ መልእክት አስተላለፉ

0908

ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በእንተ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወሰምንቱ ዓመተ ምሕረት
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
-በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣
-ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤
-የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
-በሕመም ምክንያት በየፀበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤
-እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤
የዘመናት ፈጣሪ የሆነው አምላካችን እግዚአብሔር ያለፈውን ዓመት በሰላም አስፈጽሞ እንኳን ለአዲሱ የሁለት ሺሕ ስምንት ዓመተ ምሕረት ዘመነ ዮሐንስ በሰላም አደረሰችሁ!!
‹‹ወኀሊ ዓመተ ለትውልደ ትውልድ፤ የብዙ ትውልድን ዓመታት አስብ›› (ዘዳ. 32፡7)፡፡
የሁሉም አስገኝና ፈጣሪ የሆነው እግዚአብሔር አምላካችን ከፈጠራቸው ፍጥረታት መካከል አንድ ስንኳ ጥቅም የለሽ የሆነ ፍጥረት አይገኝም፡፡
ፍጥረታት ሁሉ በእርሱ ዘንድ ውብና የየራሳቸው ዓላማና ተግባር ያላቸው ናቸው (ዘፍ.1፡25)
እግዚአብሔር የፈጠራቸው ፍጥረታት በፍጡር ዓቅም ሙሉ በሙሉ ተቆጥረው የሚዘለቁ አይደሉም፤ ከጥቂቶቹ በስተቀር ሁሉንም በዓይነ ፍጡራን ማየት ስለማይቻል ቅዱስ መጽሐፍ ፍጡራንን ጠቅለል አድርጎ በአጭር ቃል ሲገልጽ ‹‹በሰማይና በምድር ያሉት፣ የሚታዩትና የማይታዩት›› ይላቸዋል፤ (ቈላ. 1፡15)
በምድር ላይ እያሉ ከማይታዩት መካከል አንዱ ዘመን ወይም ጊዜ ነው፤ ጊዜ በድርጊት ከሚታወቅ በቀር በዓይን የሚታይ ግዙፍ አካል ወይም ልዩ ቀለም ያለው ፍጡር አይደለም፡፡ይሁን እንጂ ባለመታየቱ ብቻ የለም ብሎ መደምደም ወይም መናገር አይቻልም፤ ምክንያቱም ከድቁቅ ስፍረ ጊዜ አንሥቶ ሰዓታትን በቀናት፣ ቀናትን በሳምንታት፣ ሳምንታትን በወራት፣ ወራትን በዓመታት ከዚያም በልዩ ልዩ አዕዋዳት እየጠቀለለ ሲያሽከረክር በተግባር እናያለንና ነው፡፡ዘመን የድርጊት መሣሪያ ስለሆነ በአንድ ወቅት በተፈጸመ መልካም ወይም መጥፎ ነገር ይገለጻል፤ ከዚህም የተነሣ ዘመኑ መልካም ነው ወይም መጥፎ ነው ሲባል እንሰማለን ፡፡
ይሁንና የእኛ መሠረታዊ ጉዳይ ሊሆን የሚገባው የዘመን መታየትና አለመታየት ሳይሆን ለፍጡራን ከሚሰጠው ጥቅም አኳያ ግንዛቤ ወስደን ተጠቃሚ ለመሆን መንቀሳቀሱ ላይ ነው ፡፡
ዘመን ከዓለም መፈጠር በፊት ያልነበረ ከዓለም ጋር አብሮ የተፈጠረ፣ በሰማይ የሌለና ለምድራውያን ፍጡራን ብቻ አገልግሎት ሊሰጥ የተፈጠረ ነው፤ (ዘፍ.1፡14) ፡፡
የዘመን ሀብት ባይኖር ሰው ምድራዊ ሕይወቱን በትክክል መምራት አይችልም ነበር፡፡በመሆኑም ምድራውያን ፍጥረታት በአጠቃላይ፣ በተለይም ደግሞ የሰው ልጅ ሥርዓት ባለውና ቅደም ተከተሉን ጠብቆ በዕቅድ ሥራውን በማከናወን ሕይወቱን በትክክል መምራት ይችል ዘንድ ሀብተ ዘመን ያስፈልገዋል ፡፡ዘመን ለተግባር ከሚያበረክተው አገልግሎት በተጨማሪ በትምህርት ሰጪነቱ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ያለፈውን ዘመን እንድናስታውስ እንጂ እንዳንረሳ የልጅ ልጅ ዘመናትን አስብ ብሎ እግዚአብሔር ይነግረናል፡፡ምክንያቱም ለወደፊቱ የተሻለ ሥራ መሥራት የምንችለው ካለፈው ዘመን ትምህርት ቀስመን፣ ልምድና ተሞክሮ ወስደን ስለሆነ ነው፤ ሥራን ከዘመን ለይቶ ወይም ነጥሎ ማስቀመጥ በፍጹም አይቻልምና ፡፡
ስለሆነም ዘመን ለአጠቃላዩ ሥራችን ተቀዳሚ መሣሪያ ሆኖ እንዲያገለግለን እግዚአብሔር የሰጠን ሀብት ነውና ጊዜን በከንቱ ሳናባክን በምልአት ልንጠቀምበት ይገባል ፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!!
ሀገራችን ኢትዮጵያ ሁሉንም የተፈጥሮ ሀብት ተሟልቶ የተሰጣት፣ ድንቅና ውብ ሀገር ናት፤
ምድራዊት ገነት በሆነች በዚች ሀገር ተቀምጠን ስለድህነት ማውራት ከእንግዲህ ወዲህ እንዲያከትም ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነት መረባረብ አለበት፤
ልማታችንን በአስተማማኝ ደረጃ ዘላቂ ለማድረግ የድህነታችን ምሥጢር የት እንዳለ በውል ማወቁ ይጠቅማል ፡፡እንደ እውነቱ ከሆነ የድህነታችን ምሥጢር ተደብቆ ያለው የሥራ ባህልን አዳብሮ፣ የጊዜን ጥቅም አውቆና አንዲት ደቂቃ ስንኳ ሳያባክን በሀገሩ ውስጥ ሠርቶ ለመለወጥ ያለን ተነሣሽነት አናሳ መሆኑ ላይ ነው፡፡ በተለይም ወጣቱ ትውልድ ይህንን ተገንዝቦ መሠረታዊ የአስተሳሰብና በጊዜ ሠርቶ የመለወጥ ባህል ሊያጎለብት ይገባል፤ ይህንን ክፍተት በውል ስናውቅና በሥራ ስንታገለው ድህነትን ከሥር መሠረቱ ነቅለን መጣል እንችላል ፡፡
ዛሬ አደጉ በለፀጉ ተብሎ የሚነገርላቸው ሀብታም ሀገሮች አብዛኛዎቹ እንደ ኢትዮጵያ ያለ ለእርሻና ለልዩ ልዩ አዝርእት የተመቸ ለም መሬት፤ ለእንስሳ ርባታና ለሰው ኑሮ የተመቸ አየርና  ንጹሕ ውሀ፣ በልዩ ልዩ ማዕድን የተሞላ ነገር ግን ገና ያልተፈተሸ ድንግል መሬት ኖሮአቸው ሳይሆን፣ ያላቸውን ውሱን ሀብት በበለፀገ የሥራ ባህል ማለትም ሥራን ሳያማርጡ፣ ጊዜን በከንቱ ሳያባክኑ ያለ ዕረፍት ሌት ተቀን በመሥራታቸው ያገኙት ጸጋ እንደሆነ ማስተዋል አለብን ፡፡
በመሆኑም ኅብረተ ሰባችን በአጠቃላይ በተለይም ወጣቱ ትውልድ አዲሱን ዘመን ሲቀበል አዲሱን ዓመት ከሀገራችን የሕዳሴ መርሐ ግብር ጋር በማቀናጀትና ጠንክሮ በመሥራት ግዙፍ የሆነ የልማትና የዕድገት ስኬት ለማረጋገጥ ከዳር እስከ ዳር ተባብሮ እንዲንቀሳቀስ አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን መልካም አዲስ ዓመት ያድርግልን፡፡
እግዚአብሔር ይባርካችሁ ይቀድሳችሁ አሜን
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
መስከረም 1 ቀን 2008 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣
ኢትዮጵያ {flike}{plusone}

2648

የሐምሌ ሥላሴ በዓለ ንግሥ በመንበረ ጸባዖት ቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከብሮ ዋለ!!

2648

በየዓመቱ ሐምሌ 7 ቀን የሚከበረው የአጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ መለኮታዊ በዓለ ንግሥ በዘንድሮው ዓመት 2007 ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና በርካታ ምዕመናን በተገኙበት በታላቅ ድምቀት የተከበረ ሲሆን ሥርዓተ ቅዳሴው በብፁዕ አቡነ ሄኖክ የምሥራቅ ወለጋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተመርቶአል፡፡
በሥርዓተ ቅዳሴው አጋማሽ ላይ “የእግዚአብሔር ቸርነት ምድርን ሞላች ፣ በእግዚአብሔር ቃል ሰማዮች ፅኑ ፣ ሠራዊታቸው ሁሉ በአፉ እስትንፋስ” መዝ 33፤6 የሚለው የዳዊት መዝሙር በዜማ ተሰምቶአል፡፡ በመቀጠልም “ዮሐ 8፤51 ላይ እውነት እውነት እላችኋለሁ ቃሌን የሚጠበቅ ቢኖር ለዘለዓለም ሞትን አያይም የሚለው የወንጌል ቃል ተነቧል፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ የበዓሉ መሠረታዊ የት መጣ በኦሪት ዘፍጥረት ምዕ 20 እና 22 ላይ የተመሠረተው የአባታችን የአብርሃም ታሪክ የተፈጸመበት ጥንተ ታሪክ ነው፡፡ አብርሃም የጣኦት አምልኮ ከተስፋፋበት ከካራን በመውጣት ወደ ተቀደሰችው ምድረ ርስት ወደ ከነአን የገባበት ታሪክ ሲሆን ከካራን ከወጣ በኋላ እግዚአብሔር አብርሃምን ለመፈተን እና የእምነቱን ፅናት ለማረጋገጥ አብርሃምን ልጅህ ይስሐቅን ሰዋልኝ ባለው ጊዜ አብርሃም ሳያመነታ ፣ ልጁን ይስሐቅን አስከትሎ ፣ እንጨት፣ ቢላዋና እሳት ይዞ ወደ መሰዊያ ቦታ ወደ ተራራ ወጣ፡፡
አብርሃም ልጁ ይስሐቅን ለእግዚአብሔር መስዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ዝግጁ ቢሆንም እግዚአብሔር ግን ለይስሐቅ ተለዋጭ የሆነ ቀንዶቹ ብዕፀ ሳቤቅ የታሠሩ ነጭ በግ በማቅረቡ ከሰማይ የተላከው ነጭ በግ የይስሐቅ ተለዋጭ በመሆን የተሰዋ መሆኑን ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በድርሰቱ ሲአብራራ “አብርሃም ወሰዶ ለይስሐቅ ወልዱ ከመይሱኦ አውረደ ሎቱ ቤዛሁ በግአ” በማለት አብራርቶአል፡፡ ከሰማይ የወረደው የይስሐቅ ተለዋጭ የሆነው ያ በግ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ መሆኑን የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ይገልፃሉ፡፡ 
በዚሁ እለት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ታለቁንና መለኮታዊ የሆነውን የአጋዕዝተ ዓለም ሥላሴን በዓል አስመልክተው ያስተላለፉትን ትምህርትና ቃለ በርከት እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
ዘአቀበ ቃልየ ኢይጥእሞ ለሞት ዮሐ 8፤5
በዚህ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ የተሰበሰብን የሥላሴ ፍጡሮች ነን፡፡ ሥላሴ ሰማዩን፣ ምድሩን፣ ሰውን እና እንስሳውን የፈጠሩ ናቸው፡፡ ጸሎታችንን ተቀብለው የለመናቸውን ይሰጡናል፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃሌን የጠበቀ ሞትን አያይም ብሏል፡፡ አይሁድ ግን አባታችን አብርሃም ሞቷል አንተ ከማን ትበልጣለህ አሉት፡፡ አይሁድ ሳይገባቸው ጌታን ነቀፉት ፤ ሰው የጽድቅን ሥራ ከሠራ ዘለዓለማዊ ሕይወት ያገኛል፡፡ ስለዚህ ክርስቲያን የእግዚአብሔር ስጦታ ይጠብቀዋል፡፡ ሁሉም መንገደኛ ነው ፤ በዚህ ዓለም ላይ ሆነን ድሆችን በመርዳት የታመሙትን በመጠየቅ የተጨነቁትን በማጽናናት መልካም ሥራ መሥራት አለብን፡፡
ሥላሴ በመካከላችን አሉ ፤ ቃሉን ጠብቀን ከኖርን የመንግሥተ ሰማያት ዜጎች እንሆናለን፡፡ ቃሉን የጠበቀ ሞተ ነፍስን አይቀምስም ሥለሴ በአብርሃም ቤት ተስተናገዱ በሚለው መሠረትነት ነው በዓላችንን ያከበርነው ፤ ሥላሴ በረከታቸውን ያሳድሩብን በማለት ቅዱስነታቸው ሰፋ ያለ መልእክት ካስተላለፉ በኋላ የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል፡፡

{flike}{plusone}

0908

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የ2007 ዓ.ም. የትንሣኤ በዓልን አስመልክተው መልእክት አስተላለፉ

0908

ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በእንተ ትንሣኤሁ ለእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ሎቱ ስብሐት፡፡
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡
– በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣
– ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤
– የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
– በሕመም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤
– እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤
በሞትና በመቃብር ላይ ሥልጣን ያለው ኃያሉና አሸናፊው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ ፡፡
‹‹ወበከመ በእንተ አዳም ኵልነ ንመውት ከማሁ በክርስቶስ ኵልነ ነሐዩ፤ ሁላችን በአዳም እንደምንሞት እንደዚሁም ሁላችን በክርስቶስ ሕያዋን እንሆናለን›› (1ቆሮ. 15÷22)፡፡
እዚህ ላይ በተገለፀው ቃለ እግዚአብሔር መሠረት የሰዎች መጻኢና የመጨረሻ ዕድል ከሁለት አዳማዊ ውርስ ጋር የተያያዘ ሆኖ ይገኛል ፡፡
በቅዱስ መጽሐፍ በግልጽ እንደተጻፈው ሰው ሁሉ ከቀዳማዊ አዳም በሥጋ ተወልዶአል፤ የእርሱ የሆነውንም ሁሉ ወርሶአል፤
ይህም ማለት በሥጋው በኩል የግብረ ኃጢአት ዝንባሌን፣ ሞተ ሥጋን፣ ወሪደ መቃብርን፣ በመቃብር ውስጥ መበስበስንና መፍረስን ሲወርስ በነፍሱ በኩል ደግሞ ከእግዚአብሔር መለየትን፣ በኃጢአት ተሸንፎ የዲያብሎስ ሎሌ መሆንን፣ በኃጢአቱ ምክንያት ለኵነኔ ሲኦል ተጋላጭ መሆንን እና የመሳሰሉትን ሁሉ ወርሶአል ማለት ነው፡፡
ጠቅለል አድርገን ስናየው ቀዳማዊ አዳም በሥጋና በነፍስ ከባድ ውድቀትን ለልጆቹ አውርሶአል ማለት ነው ፡፡
ከቀዳማዊ አዳም የውድቀት ዘመን ጀምሮ እስከ ስቅለተ ክርስቶስ በነበረው ረጅም ዘመን የሰው ዘር በአጠቃላይ ከቀዳማዊ አዳም ባገኘው ውርስ ምክንያት በሥጋው ርደተ መቃብርን፣ በነፍሱ ርደተ ሲኦልን ተፈርዶበት በድርብ መከራ ሲማቅቅ ኖሮአል ፡፡
ያ ዘመን ከመከራው ብዛት የተነሣ ዓመተ ፍዳ፣ ዓመተ ኵነኔ ፣ ዓመተ መርገም ተብሎ ተሰይሞአል ፡፡
ይሁን እንጂ ለምሕረቱና ለይቅርታው ወሰን የሌለው እግዚአብሔር አምላክ የሰውን ውድቀት በትንሣኤ ለመቀልበስ ሲል የባህርይ ልጁ የሆነ እግዚአብሔር ወልድን ወደዚህ ዓለም ላከ፡፡
እርሱም የኛን ሥጋ ተዋሕዶ ሰው ሆነ፤ በመካከላችን ተገኝቶም ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከመቃብር ወደ ትንሣኤ የሚወስደውን መንገድ በቅዱስ ወንጌሉ አስተማረን ፤ (ዮሐ.5÷24)
የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ በመለኮቱ የአብ ልጅ ቢሆንም በሥጋው የሰው ልጅ ነውና ዳግማዊ አዳም ተብሎ ይጠራል (1ቆሮ15÷45 – 48)፡፡
በመሆኑም ዳግማዊ አዳም የተባለው ጌታችን፣ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በበኩሉ ቀዳማዊ አዳም ለልጆቹ ላወረሰው ውርስ ተቃራኒ የሆነውን ለሰው ዘር ሁሉ አውርሶአል፤ ይኸውም፡-
– በኃጢአት ዝንባሌ ፈንታ ጽድቀ መንፈስን፣
– በሞት ፈንታ ዘላለማዊ ሕይወትን፣
– በርደተ መቃብር ፈንታ ትንሣኤን፤
– በርደተ ሲኦል ፈንታ ዕርገትን፣
– በመለያየት ፈንታ ከእግዚአብሔር ጋር በአንድነት መኖርንና የመሳሰሉትን ለልጆቹ አውርሶአል፡፡
ይህ ሁሉ በክርስቶስ ቤዛነት ምክንያት ለሰው ልጅ በመሰጠቱ ከክርስቶስ ልደት ወዲህ ያለው ዘመን ዓመተ ሥጋዌ፣ መዋዕለ ንሥሐ፣ ዓመተ ምሕረት ተብሎ ይጠራል፡፡
ይሁንና ሰው ሁሉ ከቀዳማዊ አዳም በሥጋ ዘር በመወለዱ የእርሱ የሆነውን ሁሉ እንደወረሰ፣ አሁንም በተመሳሳይ ሁኔታ የዳግማዊ አዳም የሆነውን ሁሉ ለመውረስ ከዳግማዊ አዳም በመንፈስ መወለድ የግድ ያስፈልገዋል፡፡
ሰው በእምነት ተፀንሶ በጥምቀት ከመንፈስ ቅዱስ ሲወለድ የዳግማዊ አዳም ልጅ ይሆንና የእርሱ የሆነውን ሁሉ ይወርሳል፤ ከዚህ ዳግም ልደት በመንፈስ የተወለዱ ሰዎች ሁሉ የቀዳማዊ አዳም ውርስ አይነካቸውም (ሮሜ.8÷1 )፡፡
የዳግማዊ አዳም ውርስ በዳግም ምጽአተ ክርስቶስ እውን ለማድረግ ቀጠሮ ተይዞለታል፤ ያን ጊዜ በመቃብር ያሉ ሙታን ሁሉ በቅፅበት ሲነሡና በሕይወት ያሉትም በአንድ ጊዜ በቅፅበት ሲለወጡ የዳግማዊ አዳም ውርስ በግልጽ ይታያል ፡፡
በዚህ ጊዜ የሚሞተውና የሚበሰብሰው አካላችን የማይሞተውንና የማይበሰብሰውን ሲጎናፀፍ ሞትና መቃብር ይሸነፋሉ፤ ህልውናቸውም ያከትማል፡፡ /1ቆሮ. 15÷52-57)
በዚያን ጊዜ ከቀዳማዊ አዳም በመጣ የኃጢአት ውርስ ምክንያት የሞቱ ሁሉ ከዳግማዊ አዳም በተገኘ የጽድቅ ውርስ ምክንያት ሕያዋን ሆነው ይነሣሉ /1ቆሮ.15÷49)
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፤
ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሙስና መቃብርን አጥፍቶና ሞትን ድል አድርጎ የተነሣበትን በዓለ ፋሲካ ዛሬ በታላቅ ድምቀትና በደስታ ማክበራችን ‹‹ሞቴንና ትንሣኤዬን አስቡ›› (1ቆሮ.11÷26) ያለውን ቃሉን ከመፈጸም ባሻገር የኛንም ትንሣኤ በእርሱ ትንሣኤ እያየን በሃይማኖትና በማይናወጽ ተስፋ ፀንተን እንድንኖር ለማድረግ ነው፡፡
በእርግጥም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤዛነቱ ካቀዳጀን ጸጋ አንዱና ዋነኛው እኛን ለትንሣኤና ለዘላለማዊ ሕይወት ማብቃቱ ነው፡፡
ከጌታችን ትንሣኤ የምንገነዘበው ዓቢይ ነገር እርሱ በመቃብር ውስጥ ሙስና መቃብር ማለትም መበስበስና መፍረስ ሳይነካው ሞትን ድል አድርጎ በመነሣት ወደሰማያዊ ክብሩ እንዳረገ፣ እኛም ከእርሱ በወረስነው የጽድቅ ውርስ መሠረት እንደእርሱ ከመቃብር ተነሥተንና የዘላለምን ሕይወት ተቀዳጅተን ወደሰማያዊ መንግሥቱ የምናርግ መሆናችንን ነው፡፡
የክርስቶስ ትንሣኤ የትንሣኤያችን ማሳያ መስተዋትና የዘላለማዊው ሕይወታችን ማረጋገጫ ነውና (1ተሰ.4÷13 – 18)፡፡
ይሁን እንጂ የትንሣኤያችን ጉዞ የሚጀምረው ዛሬ በሕይወተ ሥጋ እያለን መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡
ገበሬ በመኸር ወራት ጥሩ ምርትን ለማፈስ ልፋቱን በግንቦትና በሰኔ እንደሚጀምር፣ ያን ካላደረገ ደግሞ የሚያገኘው ምርት እንደማይኖር ሁሉ፣ እኛም የትንሣኤያችን ሃይማኖታዊና ሥነ ምግባራዊ ጉዞ ዛሬ በዚህ ዓለም ሳለን ካልጀመርነው በዳግም ምጽአት የምናገኘው ነገር አይኖርም (ማቴ 25÷ 1 – 13)፡፡
ሁላችንም እንደምንገነዘበው አምላካችን እግዚአብሔር ሠርቶ የሚያሠራ አምላክ እንጂ መክሊቱን ቀብሮ በስንፍና የሚኖረውን የሚወድ አምላክ አይደለም፤(ማቴ.25÷24 – 30)
አምላካችን ከባህርይ አምላክነት በስተቀር ሁሉን በሁሉ የሚያሳትፍ አምላክ እንደሆነ ምን ጊዜም አንርሳ፤ ቅዱስ ተብሎ ቅዱሳን እንድንባል፣ ጻድቅ ተብሎ ጻድቃን እንድንባል፣ ክቡር ሆኖ ክቡራን እንድንሆን፣ ሕያው ሆኖ ሕያዋን እንድንሆን ፈቅዶልናል (1ጴጥ. 1÷16)፡፡
በመሆኑም እርሱ የመልካም ሥራ ሁሉ ባለቤት እንደሆነ እኛም የመልካም ሥራ ባለቤቶች በመሆን ትንሣኤያችንን ከዚህ እንድንጀምር ተሳትፎውን ማለትም እርሱን መምሰልን ከእኛ ይፈልጋል፡፡ /ማቴ. 5÷48)
ዛሬ ዓለማችን በፀጥታ እጦት እየታመሰች የምትገኘው ከሥነ ምግባር ጉድለት የተነሣ እንደሆነ ሁሉም ሊያውቀውና ሊገነዘበው ይገባል ፡፡
በልዩ ልዩ የዓለማችን ሀገራት ውስጥ የሚገኙ የትምህርት ተቅዋማት የሥነ ምግባር ትምህርትን እያስተማሩ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ዓለማችን በመልካም ሥነ ምግባር ከመበልፀግ ይልቅ በዘቀጠና ለአእምሮ በሚዘገንን ነውረ ኃጢአት ክፉኛ እየተናጠች ትገኛለች ፡፡
ይህ ሁሉ የሥነ ምግባር ውድቀት ሊመጣ የቻለው በየትምህርት ቤቱ የሚሰጠው የሥነ ምግባር ትምህርት በፈሪሀ እግዚአብሔር ያልተቃኘ ከመሆኑ የተነሣ እንደሆነ ሊሠመርበት ይገባል (መዝ. 110÷10፤ 1ቆሮ 1÷20 – 21)፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!
ኢትዮጵያ ሀገራችን በእግዚአብሔር ፊት ልዩ ተቀባይነት ያላት ሀገር እንደሆነች ቅዱስ መጽሐፍ ሊመሰክርላት የቻለው በተቀደሰው ባህሏና በመልካም ሥነ ምግባሯ፣ በጸናው ሃይማኖቷና በእውነተኛው ትውፊቷ እንጂ በሌላ በምንም እንዳልሆነ በአጽንኦት መገንዘብ ያሻል፡፡ (መዝ. 71፡9፤ 67፡31)
በሀገራችን ከምናስታውሰው ነባሩና ሃይማኖታዊ ባህላችን አንዱ ለብቻ መመገብ እንደነውር የሚወሰድ መሆኑን ነው፡፡ ይህ መልካም ሥነ ምግባራችንና ቅዱስ ባህላችን ዛሬም ተጠብቆ እንዲቀጥል ማድረግ የሁላችንም ኃላፊነት ነው ፡፡
የትንሣኤያችንን ጉዞ ዛሬ እንጀምር ስንል የተራበውን ማጉረስ፣ የተጠማውን ማጠጣት፣ የታረዘውን ማልበስ፣ ያዘነውን ማጽናናት፣ የታመመውን መጠየቅና መርዳት፣ ስደተኛውን ማስተናገድ፣ የታሠረውን መጠየቅ፣ የሥራ ጊዜን በአልባሌ ቦታ አለማጥፋት፣ ለሰላም፣ ለሀገር ልማትና ለዕድገት በአንድነት መሰለፍ፣ ሁሉንም ነገር በፍቅርና በስምምነት ብቻ መፍታት የመሳሰሉትን ሁሉ የሕይወታችን መርሆዎች አድርገን በተግባር እናውላቸው ማለታችን ነው፤ ይህንን የምናደርግ ከሆነ እውነትም የትንሣኤን ጉዞ በትክክል ጀምረናል ማለት ነው ፡፡
በመጨረሻም
ሁላችሁም ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን በተቀደሰው እምነት ጸንታችሁ፣ ፈሪሀ እግዚአብሔርን መሠረት ያደረገ ሥነ ምግባር አንግባችሁ፣ የሀገራችንን ሰላም በጽኑ እንድትጠብቁ፣ ልማቷንና ዕድገቷን እንድታፋጥኑ፣ አንድነታችሁንና እኩልነታችሁን አጥብቃችሁ እንድትይዙ፣ በዓለ ፋሲካውንም የተራቡትን በመመገብ፣ የታረዙትን በማልበስና የተጠሙትን በማጠጣት፣ በሰላምና በፍቅር እንድታከብሩ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር! አሜን!
 እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክ አሜን
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ሚያዝያ 4 ቀን 2007 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

{flike}{plusone}

0019

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖ 2ኛ ዓመት በዓለ ሲመት ተከበረ

0019

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት 2ኛ ዓመት የፕትርክና በዓለ ሲመት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የካቲት 24 ቀን 2007 ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ የሃይማኖት መሪዎች፤ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት፤ አምባሳደሮች፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያ ኃላፊዎች፤ የድርጅት ኃላፊዎች፤ የኮሌጅ ኃላፊዎች፤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፤ ሠራተኞች፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ካህናት፤ ምዕመናንና ምዕመናት በተገኙበት በታላቅ መንፈሳዊ ድምቀት ተከብሯል፡፡
ቅዱስነታቸው በበዓሉ ላይ በሰጡት ቃለ ምእዳን “የእግዚአብሔር መንግሥት ማእከል የሆነችው ቤተ ክርስቲያን ጌታችን በሐዋርያት እንድትጠበቅ አድርጓል፡፡ ሐዋርያትም በበኩላቸው በተኳቸው ጳጳሳት እና ቀሳውስት ጠባቂነት ቤተ ክርስቲያን እንድትመራና እንድትጠበቅ አድርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ሐዋርያዊት፤ አንዲትና ቅድስት እንደመሆኗ መጠን ከመጀመሪያው አንስቶ መንፈሳዊውን ጥበቃ በጳጳሳትና በቀሳውስት ስታከናውን ኖራለች፡፡ አሁንም እያከናወነች ነው፤ ወደፊትም በዚሁ ትቀጥላለች” ብለዋል፡፡
ቅዱስነታቸው አያይዘውም ጳጳሳትና ቀሳውስት የተሰጣቸውን የጠባቂነት ሚና አስመልክቶም “ይሁንና በዘመናችን እየተነሳ ያለው መሠረታዊ ጥያቄ የእግዚአብሔር መንግሥት ተጠሪ የሆኑት ጠባቂዎች ሓላፊነታቸውን በሚፈለገው ሁኔታ እየተወጡ ነው ወይ? የሚለው ጥያቄ በአሁኑ ጊዜ ዓለም አቀፋዊና የወቅቱ ጥያቄ ሆኖ ይገኛል፡፡ የእግዚአብሔር መንጋ የሆኑት ክርስቲያኖችን በባሕር ማእበል ሞገድ እንደሚናጥ መርከብ በጥርጣሬ እየተናጡ አጉል መንገድ ላይ እንዲቀሩ እያደረገ ነው፡፡ ከመንጋው ተነጥሎ እንደሚቅበዘበዝ በግ ባለማመን ማእበል እያንጓለሉት ነው፡፡ በጠባቂነት የተሾምን ሁሉ ከተጠያቂነት ለመዳን በዛሬው እለት የበዓለ ሲመተ ክህነትን ለማክበርና ማሰብ በተሰባሰብንበት ቀን የመንጋ ጥበቃ ሥራችን የት ላይ እንዳለ ማሰላሰል አለብን፡፡ መንጋው እየበዛ ነው ወይስ እየቀነሰ፤ ጤናማ ነው ወይስ በሽተኛ? የሚለውን ጥያቄ አንስተን ተጨባጭ መልስ ልንሰጥ ይገባል” በማለት ተናግረዋል፡፡
ከተወቃሽነት ለመዳን መደረግ ስለሚገባው አገልግሎት ሲገልጹም “የተመረጥንበት የጥበቃ ሓላፊነት በትክክል ካልሰራንበት በመንጋውም፤ በታሪክም፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ በእግዚአብሔር ፊት ወቀሳ እንደማይቀርልን ተገንዝበን ከተጠያቂነትና ከተወቃሽነት ለመዳን የጥበቃ ሥራችንን በርትተን መሥራት ይገባናል፡፡ የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ ተብለናልና” ብለዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ የወላይታ ኮንታ ደውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በበኩላቸው 56ኛውን በዓለ ሲመተ ፕትርክና እና 2ኛውን የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በዓለ ሲመተ ፕትርክናን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልእክት “እግዚአብሔር ለቅዱሳን ያለው ፍቅር በርቀት የሚመዘንና የሚለካ አይደለም፡፡ እነሱ በአጠገቡ ሆነው የእሱን ሥራዎች እንዲሠሩ ፈቅዶላቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በምድር ላይ መጋቢዎች፤ እንዲሁም አስታራቂዎች አድርጓቸዋል፡፡ “ለአባቶቻችን ያዘዘውን ለሚመጣው ትውልድ ለልጆቻቸው ያስታውቋቸውም ዘንድ አልሰወሩም” እንዲል ቅዱስ ዳዊት ዛሬ በዚህ ዐውደ ምሕረት ላይ እንደምንመለከተው ቅዱስነትዎ ከአባቶችዎ የተረከቡትን ሓላፊነት በታማኝነት ለመጠበቅ ቃል የገቡበትን እለት ለማስታወስ ነው” ብለዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የስብከት ወንጌል መምሪያ የበላይ ጠባቂና የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ  በቅዱስ ፓትርያሪኩ ትምህርት እንዲሰጡ የተጋበዙ ሲሆን ቅኔውንና ትምህርቱን አዋህደውና አዋዝተው ሰማዕያኑን እጅግ በአስደነቀ መልኩ አቅርበዋል፡፡

በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያሪክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፤ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም፤ ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጥተው የበዓሉ ፍፃሜ ሁኗል።
{flike}{plusone}

0005

በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የአንድነት ጉባኤ መርሃ ግብር ተካሄደ

0005

የካቲት 14 እና 15 2007 ዓ.ም ብፁአን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና ሊቃውንት ቤተ ክርስቲያን በተገኙበት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ  ልዕኮ ዋና ክፍል አስተባባሪነት የአንድነት ጉባኤው ተጀምሯል፡፡ በዚሁ የአንድነት ጉባኤ መርሃ ግብር ላይ የተለያዩ መምህራን ወቅቱን አስመልክተው ለምዕመናን ትምህርተ ወንጌል የሰጡ ሲሆን እንደዚሁም ወቅቱን የተመለከቱ የተለያዩ  መዝሙሮች በተለያዩ ዘማሪያን ቀርበዋል፡፡
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልዕኮ ዋና ክፍል አስተባባሪነት የተጀመረው ይህ የገዳማት እና   አድባራት የአንድነት ጉባዔ የተጀመረው የካቲት 14 ቀን 2007 ዓ.ም በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል  ሲሆን የዚሁ ዓይነት ጉባዔም በሁሉም የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት ሊካሄድ እንደሚችል ታውቋል፡፡ የአንድነት ጉባዔው ምደባ  ከሶስት አድባራት እስከ አስር አድባራት የሚያጠቃልል  እንደሆነም ነው የተገለፀው፡፡
የዚህ ዓይነት የአንድነት ጉባኤ ቀደም ሲል ሲካሄድ የነበረ ቢሆንም ለተወሰነ ጊዜ የአንድነት ጉባዔው ተቋርጦ የነበረ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ ይሁን እንጂ የአንድነት ጉባዔው ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት፤ ምዕመናንን ወደ ንስሐ ለማቅረብና በሃይማኖታቸው ጸንተው እንዲኖሩ ለማድረግ የአንድነቱ ጉባኤ መቀጠል ጠቀሜታው እጅግ የጎላ በመሆኑ የክፍላተ ከተማ  የስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊዎች እና የሀገረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌል ዋና ክፍል ባደረጉት የጋራ ምክክርና ውይይት ቀደም ሲል ተጀምሮ የነበረው የአንድነት ጉባዔ በማህበረ ካህናትም ሆነ በማህበረ ምዕመናን ዘንድ እጅግ ተወዳጅ የነበረ መሆኑን በማውሳት ለወደፊቱም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል በማለት ስምምነት ላይ የተደረሰ በመሆኑ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትም በጉዳዩ ላይ ትኩረት በመስጠት ለሁሉም አድባራት ባስተላለፈው መመሪያ መሠረት  የአንድነት ጉባዔው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን  ጾም ምክንያት በማድረግ ጉባዔው በሰባቱም ክፍላተ ከተሞች ተጠናክሮ እንዲቀጥል በመደረግ ላይ ነው፡፡ የአንድነቱ ጉባዔ የሚካሄድባቸው ቀናት በየሳምንቱ ቅዳሜ እና እሁድ እየተከተለ ሲሆን በተለይም በርካታ ምዕመናን የሚገኙባቸውን ወርሃ በዓላት እና ዓመት በዓላትን ምክንያት በማድረግ ነው፡፡
 የስብከተ ወንጌል አገልግሎት እንዲሰጡ የሚጋበዙ መምህራነ ወንጌል በገዳማት  እና  አድባራት ጽ/ቤት ጠያቂነት ከጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ በየገዳማቱ  እና  አድባራቱ  ተመድበው የሚያገለግሉ ሰባክያነ ወንጌል እና በትሩፋት የሚያገለግሉ የወንጌል አገልጋዮች ናቸው፡፡ መነሻውን ከመንበረ ፀበኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ያደረገው ይህ ዐቢይ የአንድነት ጉባኤ በተለያዩ ገዳማት  እና  አድባራት  የሚከናወን ሲሆን መጋቢት 26 እና 27/2007 ዓ.ም በቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም ካቴድራል እንደሚካሄድ ለማወቅ ተችሏል፡፡

{flike}{plusone}

trinity

እንኳን ለአጋዕዝተ ዓለም ቅድስት ሥላሴ አመታዊ ክብረ በአል በሰላም አደረሳችሁ

               ቅድስት ሥላሴ

trinity

“ሥላሴ” የሚለው ቃል “ሠለሰ፤ ሦስት አደረገ” ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙ ሦስት ማለት ነው፡፡ ይህን ሦስትነት ለጌታ ስንቀጽለው “ልዩ የሆነ ሦስትነት” የሚለውን ፍቺ ያመላክታል፡፡
 
የእነርሱን /የቅድስት ሥላሴን/ ሦስትነት ልዩ የሚያደርገው በሦስትነት ውስጥ አንድነት፣ በአንድነት ውስጥ ሦስትነት ያላቸው በመሆኑ ነው፡፡ ይህን በሚመለከት የሚሰጠው ትምህርተ ሃይማኖት “ምሥጢረ ሥላሴ” ይባላል፡፡ ይህ ትምህርት ምሥጢር መባሉ በዐይነ ሥጋ የማናየው፣ በዕደ ሥጋ የማንዳስሰው፣ በሥጋዊ ምርምር ፈጽሞ የማይደረስበት በመሆኑ ነው፡፡ ሆኖም ምሥጢረ ሥላሴ የሰላም ወንጌልና የእምነታችን መሠረት ነው፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ “ትምህርተ ሰላምነ ነአምን አበ ፈናዌ ወነአምን ወልደ ተፈናዌ ወነአምን መንፈሰ ቅዱስ ማኅየዌ አሐደ ህላዌ፤ በሰላማችን ትምህርት ላኪ አብን እናምናለን፤ ተላኪ ወልድንም እናምናለን፤ አዳኝ መንፈስ ቅዱስንም በአንድ ባሕርይ እናምናለን” እንዲል፡፡

ቅድስት ሥላሴ የእግዚአብሔር ልዩ መጠሪያው ነው፡፡ እግዚአብሔር ስንልም ስለ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ መናገራችን ነው፡፡ ሊቁ “አንሰ ሶበ እቤ እግዚአብሔር በእንተ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ” እንዲል፡፡ ቢሆንም ግን የእርሱን ነገር ልንመረምረው አንችልም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች እግዚአብሔር “ቅዱስ” ተብሎ በወንድ አንቀጽ፣ “ቅድስት” ተብሎ ደግሞ በሴት አንቀጽ /ቅድስት ሥላሴ/ ተብሎ ሲጠራ እውነትም ከምርምር በላይ ነው ይላሉ፡፡ ይሁን እንጂ የሚመራመር አእምሮን ስለሰጠን በተወሰነ መልኩ “ቅዱስ እና ቅድስት”፣ “ልዩ ሦስትነት” የሚባልበትን ሃይማኖታዊ ምሥጢር በጥቂቱ እንመለከታለን፡፡
1.    ቅዱስና ቅድስት መባል

ቅዱሳት መጻሕፍት ጾታ የሌላቸውን አካላት በወንድና በሴት አንቀጽ መጥራት ልማዳቸው ነው፡፡ ለምሳሌ ቅዱሳን መላእክትን በወንድ አንቀጽ ሲጠራቸው “ወይሴብሕዎ ኩሎሙ መላእክቲሁ፤ መላእክቱ ሁሉ ያመሰግኑታል” ሲል በሴት አንቀጽ ሲጠራቸው ደግሞ “ሰማያት ይነግራ ስብሐተ እግዚአብሔር፤ ሰማያት (መላእክት) የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ” ይላል (መዝ. 148÷1-2)፡፡ ነፍስንም በወንድ አንቀጽ ሲጠራ “መንፈስ እምከመ ወጽአ ኢይገብእ፤ ነፍስ ከተለየ በኋላ አይመለስም” ሲል በሴት አንቀጽ ደግሞ “ትባርኮ ነፍስየ ለእግዚአብሔር፤ ነፍሴ እግዚአብሔርን ታመሰግነዋለች” ይላል /መዝ. 77÷39፣ መዝ. 102÷1/፡፡ እንዲሁም ፀሐይን በወንድ አንቀጽ ሲጠራ “ፀሐይኒ አእመረ ምዕራቢሁ፤ ፀሐይ መግቢያውን ዐወቀ” ሲል በሴት አንቀጽ ደግሞ ”ወድቀት እሳት ወኢርኢክዋ ለፀሐይ፤ እሳት ወደቀች ፀሐይን አላየኋትም” ይላል /መዝ. 103÷19፣ መዝ. 57÷8/፡፡ ስለዚህ ልማደ መጻሕፍት መሆኑን በዚህ ይረዷል፡፡

ሌላው ምክንያት ደግሞ የቅድስና ሕይወት ለወንዱም ሆነ ለሴቷ የተሰጠ መሆኑን ያመላክታል፡፡ እዚህ ላይ የሚጠቀሰው የሰው ልጅ የእኩልነት ሚዛን ደግሞ “ቅድስና” ነው፡፡ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን ወንዶች እንዳሉ ሁሉ ቅዱሳት ሴቶች መኖራቸው ለዚህ ማሳያ ነው፡፡ ይልቁንም የእመቤታችን የቅድስተ ቅዱሳን የድንግል ማርያምን ቅድስና ስናስብ እንዲያውም በወንድ ምን ቅድስና አለና! ያሰኛል፡፡ በእግዚአብሔር መንግሥት /በቤተ ክርስቲያን/ ፍትሕ፣ ርትዕ እንጂ ዓመፅና አድልዎ የለም፡፡ “ዘአኮ ይዔምፅ እግዚአብሔር ከመ ይርሳዕ ምግባሪክሙ ወተፈቅሮተክሙ ዘአርአይክሙ በስሙ ወተልእክምዎሙ ለቅዱሳን ወትትለአኩሂ፤ እግዚአበሔር ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ እስከ አሁንም ስለምታገለግሉአቸው ያደረጋችሁትንም ሥራ ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለምና፡፡ “እንዲል /ዕብ. 6÷10፡፡ እኛም ሃይማኖታችን የእኩልነት፣ የነጻነት፣ የሰላምና የአንድነት ሥርዓት እንጂ የሴቶች መጨቆኛ መሣሪያ አይደለም የምንለውም ለዚህ ነው፡፡ አሁንም ቤተ ክርስቲያንን የሚቃወሙ ወገኖች ይህን የጠራ አስተምህሮዋን በእምነት መነፅር መረዳት አለባቸው፡፡

እግዚአብሔር አምላክ “ቅዱስ” እና “ቅድስት” የመባሉን ነገር ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በምሳሌዊ አገላለጽ “ኀበ ርኅራኄክሙ በዝኀ ወኀበ አልቦቱ መሥፈርት እለ ትሠመዩ በስመ ብእሲት ሥላሴ ዕደወ ምሕረት ግናይ ለክሙ፤ ቸርነታችሁ ከበዛና መሥፈሪያም ከሌለው ዘንድ “ቅድስት” ተብላችሁ በሴት ስም የምትጠሩ የይቅርታ ወንዶች ሥላሴ ሆይ ለእናንተ መገዛት ይገባል” በማለት ምሥጢሩን እንደ ወርቅ አንከብልሎ እንደ ሸማ ጠቅልሎ አስተምሯል፡፡

የሥላሴ በወንድና በሴት አንቀጽ መጠራት ምሳሌነት አለው ማለት ነው፡፡ ወንድ ኃያል ነውና ቢመታ ያደቅቃል፤ ቢወረውር ያርቃል፤ ቢያሥር ያጠብቃል፡፡ ሥላሴም ከቸርነታቸው በቀር ፍጥረቱን ሁሉ እናጥፋው ቢሉ ይቻላቸዋል፡፡ አንድም ወንድ ወጥቶ ወርዶ ነግዶ ሚስቱን ይመግባል፤ ልጆቹን ያሳድጋል፡፡ ሥላሴም በፈጢር ወላድያነ ዓለም ናቸውና የፈጠሩትን ፍጥረት በዝናብ አብቅለው፣ በፀሐይ አብስለው ይመግቡታልና በወንድ አንቀጽ “ቅዱስ” ይባላሉ፡፡

“ቅድስት” ተብለው በሴት አንቀጽ መጠራታቸው ደግሞ ሴት /እናት/ በልጁዋ ወለደችው /አልወለደችው/ ተብላ እንደማትጠረጠረው ሁሉ ሥላሴም ይህን ዓለም ፈጠሩት አልፈጠሩት ተብለው አይጠረጠሩም፡፡ ሁሉም ከእነርሱ፣ ለእነርሱ፣ በእነርሱ ሆኗልና፡፡ ሴት /እናት/ ልጅዋ ቢታመምባት ወይም ቢሞትባት አትወድም፤ ሥላሴም ከፍጥረታቸው አንዱ እንኳ በዲያብሎስ እጅ ቢገዛባቸው አይወዱም፡፡ አንድም ሴት /እናት/ ፈጭታ ጋግራ ቤተሰቦቿን ትመግባለች፤ ሥላሴም በዝናም አብቅለው በፀሐይ አብስለው ፍጥረቱን ሁሉ ይመግባሉና በሴት አንቀጽ “ቅድስት ሥላሴ” እያልን እንጠራቸዋለን፡፡
2.    ልዩ ሦስትነት

ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ልዩ ሦስትነት የሚለው የምሥጢረ ሥላሴ ሃይማኖታዊ ትምህርት በቅድምና፣ በፈጣሪነት፣ በሥልጣን፣ በማሰገድ፣ በመመስገን፣ በክብር፣ በፈቃድ አንድ /እግዚአብሔር/ ሲሆኑ በስም፣ በአካል፣ በግብር ሦስት (ሥላሴ) የሚለውን ይገልጻል፡፡
2.1.    በስም

የስም ሦስነታቸው አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ መባል ነው፡፡ ይኸንንም ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል /ወልድ/ “እንግዲህ ሒዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርቴ አድርጓቸው” ሲል አስተምሯል /ማቴ. 28÷19/ ታዲያ አብ በራሱ ስም አብ ቢባል እንጂ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አይባልም፡፡ ወልድም ወልድ ቢባል እንጂ አብ መንፈስ ቅዱስ አይባልም፡፡ መንፈስ ቅዱስም መንፈስ ቅዱስ ቢባል እንጂ አብ ወልድ አይባልም፡፡ ስማቸው ፈጽሞ የማይፋለስ (የማይተባበር) ነውና፡፡

አንዳንድ የእምነት ድርጅቶች ይህን ትምህርት በአግባቡ ካለመረዳታቸው የተነሣ “ኢየሱስ ብቻ /Only Jesus/” በማለት የአብንና የመንፈስ ቅዱስን ስም ለኢየሱስ (ለወልድ) ብቻ በመስጠት ስመ ተፋልሶ እያመጡ ኑፋቄን ይዘራሉ፡፡ እኛ ግን በቅድስት ሥላሴ ዘንድ ስመ ተፋልሶ እንደሌለ እናምናለን፡፡ በአንጾኪያ ከቅዱስ ጴጥሮስ ቀጥሎ በሦስተኛነት ተሹሞ የነበረው ቅዱስ አግናጥዮስ “አብሂ አብ ውእቱ ወኢኮነ ወልደ ወመንፈሰ ቅዱሰ፣ ወልድሂ ወልድ ውእቱ ወኢኮነ አበ ወኢመንፈሰ ቅዱሰ፣ መንፈስ ቅዱስሂ መንፈስ ቅዱስ ውእቱ ወኢኮነ አበ ወኢወልደ፣ ኢይፈልስ ስመ አብ ለከዊነ ስመ ወልድ ወመንፈስ ቅዱስ፣ ወኢይፈልስ ለከዊነ ስመ አብ ወወልድ፤ አብ አብ ነው ወልድን መንፈስ ቅዱስን አይደለም፣ ወልድም ወልድ ነው አብን መንፈስ ቅዱስንም አይደለም፡፡ መንፈስ ቅዱስ መንፈስ ቅዱስ ነው፤ አብን ወልድን አይደለም፤ አብ ወልድንና መንፈስ ቅዱስን ለመሆን አይለወጥም፣ ወልድም አብንና መንፈስ ቅዱስን ለመሆን አይለወጥም፣ መንፈስ ቅዱስም አብንና ወልድን ለመሆን አይለወጥም” ሲል፣ ዮሐንስ ዘአንጾኪያም “አስማትሰ ኢየኀብሩ፤ ስሞች ግን አይተባበሩም” ብሏል/ ሃይ አበው ዘቅዱስ አግናጥዮስ ምዕ. 11 ገጽ. 18፣ ሃይ አበው ዘዮሐንስ/፡፡

ይህ የቅድስት ሥላሴ ስም እንደ ሰው ስም አካል ቀድሞት ኋላ የተገኘ አይደለም፡፡ የሰው ስሙ አካሉ ቀድሞት ኋላ ይገኛል፡፡ ወንዱን በ40 ቀኑ “እገሌ” ሲሉት ሴቲቱን በ80 ቀኗ “እገሊት” ይሏታል፡፡ የተወለደ ዕለትም እናት አባቱ ዓለማዊ የመጠሪያ ስም ያወጡለታል፡፡ “ሰው” ሲባል ስሙ ከአካሉ አካሉ ከስሙ ሳይቀድም እንደተገኘ ሁሉ የሥላሴም ስማቸው ከአካላቸው፣ አካላቸው ከስማቸው ሳይቀድም ቅድመ ዓለም የነበረ ስም ነው እንጂ ድኅረ ዘመን የተገኘ አይደለም፡፡ ቅድምናቸው ዘመኑን ቢወስነው እንጂ ዘመኑ ቅድምናቸውን አይወስነውምና፡፡ (መንገደ ሰማይ-በብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ገጽ. 32/፡፡

ሊቁ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ገባሬ መንክራት “ወናሁ ንቤ ካዕበ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ወአኮ እሉ አስማት ዘቦኡ ላዕሌሆሙ ድኅረ አላ እሙንቱ እስመ አካላት ወብሂለ ሰብእሂ አኮ ውእቱ ስም ዳዕሙ ፍጥረት ውእቱ… ወአካሎሙኒ ለሥሉስ ቅዱስ ወአስማቲሆሙ አልቦ ውስቴቶሙ ዘይዴኀር አላ እሉ እሙንቱ ብሉያነ መዋዕል እምቀዲሙ ዘእንበለ ጥንት ወዘመን፤ አሁን ደግሞ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ እንላለን ግን አካላት ተቀድመው ተገኝተው እሊህ ስሞች ኋላ የተጠሩባቸው አይደለም፤ ሰው ማለት ኋላ የወጣ ስም ሳይሆን ባሕርዩ ነው … የሥላሴ አካላቸውም ቀድሞ ስማቸው ከአካላቸው በኋላ የተገኘ አይደለም፡፡ ጥንት ሳይኖራቸው ዘመን ሳይቀድማቸው የነበሩ ናቸው እንጂ” እንዲል /ሃይ-አበው ዘቅዱስ ጎርጎርዮስ ገባሬ መንክራት 13-4-8/፡፡
2.2.    በአካል

የቅድስት ሥላሴን የአካል ሦስትነት ስናይ ደግሞ አብ በተለየ አካሉ ፍጹም አካል፣ ፍጹም ገጽ፣ ፍጹም መልክእ አለው፡፡ ወልድም በተለየ አካሉ ፍጹም አካል፣ ፍጹም ገጽ፣ ፍጹም መልክእ አለው፡፡ መንፈስ ቅዱስም በተለየ አካሉ ፍጹም አካል፣ ፍጹም ገጽ፣ ፍጹም መልክእ አለው፡፡ ይህን እውነት ሊቁ አቡሊደስ “ነአምን በአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ከመ ሠለስቱ ገጻት ፍጹማነ መልክእ ወአካል እሙንቱ እንዘ አሐዱ መለኮቶሙ፤ ባሕርያቸው በእውነት አንድ ሲሆን በመልክ፣ በአካል ፍጹማን የሚሆኑ ሦስት ገጻት እንደሆኑ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን” ብሏል /ሃይ አበው ዘአቡሊደስ ምዕ. 39-3/፡፡

ይህ አካላቸው ምሉዕ በኩለሄ፣ ስፉሕ፣ ረቂቅ ሲሆን ዳር ድንበር፣ ወሰን የለውምና ከጽርሐ አርያም በላይ ቁመቱ፣ ከበርባሮስ በታች መሠረቱ፣ ከአድማስ እስከ ናጌብ ስፋቱ ተብሎ አይመረመርም፤ ቢመረመርም አይደረስበትም፡፡ ሁሉን ሥላሴ ይወስኑታል እንጂ የሚወስናቸው የለምና፡፡ «ንሕነ ናገምሮ ለኩሉ ወአልቦ ዘያገምረነ አልቦ ወኢምንትኒ እምታሕቴነ እስመ ለኩሉ የዐውድ ዕበየ ኃይልነ አልብነ ውሳጤ ወአፍአ አልቦ ሰማይ ዘያገምረነ ወኢምድር ዘይጸውረነ፤ ሁሉን እኛ እንሸከመዋለን እንጂ እኛን የሚሸከመን የለም፤ ከእኛ በላይ ከእኛም በታች ቦታ የለም፣ ባሕርያችን ሁሉን ይወስናል እንጂ የሚወስነው የለም» እንዲል /መጽ. ቀሌምንጦስ/፡፡
2.3.    በግብር

በግብር ሦስትነታቸው ደግሞ የአብ ግብሩ መውለድ ማሥረጽ ነው፤ ወልድን ወልዷል፣ መንፈስ ቅዱስንም አሥርጿልና፡፡ የወልድ ግብሩ መወለድ ነው፤ ከአብ ተወልዷልና፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ግብሩ መሥረጽ ነው፤ ከአብ ሠርዷልና፡፡ “እግዚአብሔር አለኝ አንተ ልጄ ነህ”፣ “ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል” እንዲል /መዝ. 2÷7፣ ዮሐ. 3÷16/፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተረዳነው /ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንደተማርነው) አብ ወልድን ቢወልድ፣ መንፈስ ቅዱስንም ቢያሠርፅ እንጂ አይወለድም፣ አይሠርጽም፡፡ ወልድ ቢወለድ እንጂ አይወልድም፤ አይሠርጽም፤ አያሠርጽም፡፡ በመሆኑም ቅድስት ሥላሴ በዚህ ግብራቸው አብ ወላዲ፣ ወልድ ተወላዲ፣ መንፈስ ቅዱስ ሠራጺ ተብለው ይጠራሉ፡፡

የወልድ ከአብ መወለዱና የመንፈስ ቅዱስ ከአብ መሥረጹ እንደምንድን ነው? ቢሉ ቃልና እስትንፋስ ልብ ሳይቀድማቸው አካላቸው ከልብ ሳይለይ ቃል እንደሚወለድና እስትንፋስ እንደሚወጣ ሁሉ ወልድና መንፈስ ቅዱስም ቅድመ ዓለም አብ ሳይቀድማቸው እንበለ ተድኅሮ አካል ዘእም አካል ባሕርይ ዘእምባሕርይ ወልድ ከአብ ተወለደ፤ መንፈስ ቅዱስም ከአብ ሠረጸ፡፡ “ከመ ልደተ ቃል ወጸአተ እስትንፋስ እምልብ ከማሁ ልደቱ ለወልድ ወጸአቱ ለመንፈስ ቅዱስ እም አብ፤ ወልድ ከአብ የሚወለድበት ልደትና መንፈስ ቅዱስ ከአብ የሚወጣበት አወጣጥ ከልብ እንደሚሆን እንደ ቃል መወለድና ከልብ እንደሚሆን እንደ እስትንፋስ አወጣጥ ነው” እንዲል /ርቱዐ ሃይማኖት/፡፡ ይሁን እንጂ ይህን ድንቅ ምሥጢር አሁንም ቢሆን በዕፁብ ይወሰናል እንጂ በምርምር አይደረስበትም፡፡

ሆኖም ኦርቶዶክሳውያን አበው የመጽሐፍ ቅዱስን የቀና አስተምህሮ መሠረት በማድረግ መንፈስ ቅዱስ ከአብ ብቻ እንደ ሠረጸ አስተምረዋል፡፡ ዳግመኛም በቁስጥንጥንያ በተካሔደው ዓለም አቀፍ ጉባኤም ላይ መቅዶንዮስን ተከራክረው የረቱ መቶ ሃምሳው ቅዱሳን ሊቃውንት “ወነአምን በመንፈስ ቅዱስ እግዚእ ማኅየዊ ዘሠረጸ እም አብ ንስግድ ሎቱ ወንሰብሖ ምስለ አብ ወወልድ፤ ሕይወትን በሚሰጥ ጌታ ከአብ በሠረጸ ከአብና ከወልድ ጋር በሚሰገድለት በነቢያት አድሮ በተናገረ መንፈስ ቅዱስ እናምናለን” በማለት ከቅዱስ ወንጌል እውነታ በመነሣት ትክክለኛውን እምነት ገልጸዋል /ጸሎተ ሃይማኖት/፡፡

በአንጻሩ ግን ይህን ትምህርተ ሃይማኖት ወደ ኋላ በመተው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከጊዜ በኋላ መንፈስ ቅዱስ “ዘሠረጸ እም አብ ወወልድ፤ ከአብ ከወልድም የሠረጸ” የሚል ሥርዋጽ አስገብተዋል፡፡ ይህ የስሕተት አስተምህሮ በላቲን “ፊሊዮኬ (Filio tve)” ሲባል ትርጉሙ “እንዲሁም ከወልድ” ማለት ነው፡፡ ይህ አመለካከት ኑፋቄ በመሆኑ በእኛ ቤተ ክርስቲያን መቼም ቢሆን ተቀባይነት የሌለው ትምህርት ሲሆን በላቲኖች ዘንድ ግን ተቀባይነትን ያገኘ አስተምህሮ ነበር፡፡

ለእነርሱ የስሕተት ትምህርት መሠረት የሆናቸው አውግስጢኖስ የተባለው ሰው (dusia is the Sours of trinity)፣ አብ ፍቅር ነውና ልጁን ወዳጅ ነው (The father is the one who loves or/over)፣ ወልድ ደግሞ በአብ ዘንድ ተወዳጅ ነው /The son is the one who is Loved or Beloved፣ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በሁለቱ ፍቅር መካከል ያለ አያያዥ ነው /The Sprit is Love bond)” በማለት አስቀድሞ ያስተማረውን ችግር ያለበት ትምህርት በመቀበላቸውና መመሪያ በማድረጋቸው ሲሆን ይህን ተከትለው በ589 ዓ.ም በስፔን ቶሌዶ ካካሔዱት ጉባኤ ጀምሮ በ1014 ዓ.ም ተቀብለውት በቅዳሴያቸው አስገብተውታል፡፡ /The Doctrine of God P. 172/.

በእርግጥ ምሥጢረ ሥላሴን በሚገባ መረዳት ለማንም ቢሆን አይቻለውም፡፡ እርሱ ባወቀ ግን ምሥጢረ ሥላሴ በምሥጢረ ጥምቀት ተገልጧል፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በመጽሐፈ ሰላምታው ላይ “ለምህሮ ትሥልስት ሥላሴ በሌሊተ ጥምቀት ሐዲስ ዘአስተርአይክሙ በዮርዳኖስ በአምሳል ዘይሤለስ ግናይ ለክሙ፣ በዐዲሲቱ ጥምቀት ሌሊት ሦስትነታችሁን ለማስተማር በሦስት አካላት በዮርዳኖስ የተገለጣችሁ ሥላሴ መገዛት ለእናንተ ይገባል” እንዲል፡፡
  
 እንግዲህ እምነታችንን በቅድስት ሥላሴ ላይ በማድረግ በርትዕት ሃይማኖት ልንጸና ይገባል፡፡ “ወአኮ ዘንብል አሐዱ ከመ አዳም ቀዳሜ ኩሉ ፍጥረት አላ ሠለስቱ እንዘ አሐዱ ህላዌ ናሁ ንሰምዖሙ ለአይሁድ እኩያን ወለእስማኤላውያን ጊጉያን እለ ይብሉ አሐዱ ገጽ እግዚአብሔር ወአሐዱ አካል በኢለብዎቶሙ ዕውራነ ልብ እሙንቱ፤ የሰው ሁሉ መጀመሪያ እንደሆነ እንደ አዳም አንድ ነው አንልም፤ ነገር ግን በባሕርይ አንድ ሲሆን በአካሉ ሦስት ነው እንላለን እንጂ፡፡ ክፉዎች አይሁድን በደለኞች እስማኤላውያንን እነሆ እናያቸዋለንና እግዚአብሔርን አንድ አካል አንድ ገጽ ሲሉ ባለማወቃቸው በልቡናቸው የታወሩ ናቸውና” በሚል ተግሣጽ አዘል ምክር ተችሮናልና /ቅ.ማርያም ቁ. 70/፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

{flike}{plusone}