009

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የትንሳኤ በዓልን አስመልክቶ መልዕክት አስተላለፉ

ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በእንተ ትንሣኤሁ ለእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ሎቱ ስብሐት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

009
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

1. በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ፤

2. ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትኖሩ፤

3. የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችኹ፤

4. በሕመም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችኹ፤

5. እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ኾናችኁ በማረሚያ ቤት የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤

በትንሣኤው ትንሣኤያችንን ያበሠረን ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳ ለ፳፻፭ ዓ.ም በዓለ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችኹ፡፡

‹‹እስመ ሐደሰ ለነ ፍኖተ ጽድቅ ወሕይወት ንቅረብ እንከ በልበ ጽድቅ›› ‹‹የሕይወትና የእውነት መንገድን አድሶልናልና ከእንግዲህ በቅን ልቡና ወደ እርሱ እንቅረብ›› (ዕብ. 10÷19) የሰው ልጅ ለማያረጅና ለማያልፍ ሕይወት የታደለ፣ በእግዚአብሔር አምሳልና አርአያ የተፈጠረ፣ እጅግ ክቡርና ታላቅ ፍጥረት እንደነበረ ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፤ በምድር በሚገኙ ፍጥረታት ሁሉ ላይ ያለው የበላይነት ሥልጣንም ይህን ያረጋግጣል፡፡

የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ዘንድ ይህን ያህል ጸጋ ቢኖረውም የተሰጠውን ክብርና ልዕልና በአግባቡ ጠብቆ መዝለቅ አልቻለም፤ በእግዚአብሔር ፊት በፈጸመው ከባድ በደል ምክንያት የተሰጠውን ጸጋና ክብር ከማጣቱም በላይ በሕይወት ፈንታ ሞትን፣ በእውነት ፈንታ ሐሰትን፣ በዘለዓለማዊነት ፈንታ ጊዜያዊነትን፣ በማያረጀው ፈንታ የሚያረጀውን ሕይወት ተላብሶ ወደ ምድረ ፍዳ ተባረረ፤ ከእግዚአብሔር ልጅነት ተራቁቶ ከማኅበረ መላእክት ተለየ፤ ረዳት የለሽና ጎስቋላ ሕይወት ተሸክሞ መኖር ጀመረ፡፡

{flike}{plusone}

ለእርሱ ያልተፈጠሩ የሞትና የመቃብር ጎዳናዎች እስከ ስቅለተ ክርስቶስ ድረስ በሰፊው ተጓዘባቸው፡፡ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ የነበሩ በሺሕ የሚቆጠሩ ዓመታት ለሰው ልጅ የፍዳ፣ የመርገም፣ የኵነኔ ዓመታት ነበሩ፡፡ ሲኦልና ገሃነም የሰው ዘርን በአጠቃላይ ለመዋጥ አፋቸውን የከፈቱበትና ሰውን ሁሉ በመራራ ሥቃይ የማገዱበት፣ ገነትና መንግሥተ ሰማያት አንድ ስንኳ ለእነርሱ የተገባ ፍጡር የሌለ እስኪመስሉ ድረስ ባዶአቸውን የቀሩበትና ተዘግተው የነበሩበት መራራ ጊዜ ነበር፡፡

እግዚአብሔር እውነተኛ ዳኛ እንደመኾኑ መጠን በሰው በደል ምክንያት ትክክለኛ ፍርዱን ቢያስተላልፍም ከፈራጅነቱ ጎን ለጎን መሐሪነቱን የማያርቅ ለፍጥረቱ እጅግ ሩኅሩኅ ነውና በሰው ላይ የተላለፈው የሞተ ነፍስ ፍርድ በጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሥዋዕትነት እንዲያከትም አደረገ፤ የተዘጋው የገነት በር እንዲከፈት፣ በሲኦል የተጋዙ ነፍሳት ወደ ገነት እንዲመለሱ፣ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የሰው ጉዞ ወደ ሲኦል መኾኑ ቀርቶ ወደ ገነት እንዲኾን በማድረግ ሰውን በክርስቶስ ደም ታረቀው፡፡ በዚህ ታላቅ መሥዋዕትነት ያረጀውን የሲኦል መንገድ ዘግቶ አዲስ የገነት መንገድን ስለከፈተልን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ÷ ‹‹አዲስ የእውነትና የሕይወት መንገድ ከፍቶልናልና ከእንግዲህ ወዲህ በቅን ልቡና ወደርሱ እንቅረብ›› እንዳለ በፍጹም ልባችን፣ በፍጹም ሐሳባችን፣ በፍጹም ኀይላችን ወደ እርሱ ልንቀርብ ይገባል፡፡

የተወደዳችኹ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ፤

ያረጀው ነገር ሁሉ በክርስቶስ ደም ተቀድሶና ነጽቶ ሐዲስ ኾኖአል፤ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሠርቶ የሚያሠራ የመልካም ነገር ሁሉ አርኣያና መሪ እንደመኾኑ መጠን አዲሱን መንገድ ከፍቶ እንድንጓዝ ሲያደርግ እኛም በሐዲስ መንፈስ በሐዲስ ሕይወት ልንመላለስበት እንጂ እንደገና ወደአረጀውና ወደአፈጀው ሕይወት ተመልሰን ልንዘፈቅ አይደለም፡፡ አዲስ ሕይወት ማለት እግዚአብሔር ለሰው ዘር ሁሉ መድኃኒት እንዲኾን በላከው በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የዘለዓለም ድኅነትን ማግኘት ነው፤ ምንም ዐይነት አማራጭ የማይገኝለትን ይህን የእግዚአብሔር የማዳን ጸጋ የሰው ዘር ሁሉ ተቀዳሚ ሥራው አድርጎ ሊቀበለው ይገባል፤ በዚህ በኩል ካልኾነ ሌላ የምንድንበት መንገድ የምናመልጥበት ዐውድ ፈጽሞ የለምና፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት በግልጽ እንደተቀመጠው የክርስትና ሃይማኖት በመልካም ሥነ ምግባር ገዝፎ የሚታይ ሃይማኖት እንጂ በእምነት ብቻ ተደብቆ የሚኖርበት ሃይማኖት አይደለም፤ በርቀት ያለችው ነፍሳችን በግዙፉ ሥጋ ኾና በምትሠራው ሥራ አማካይነት በአካላችን ውስጥ እንዳለች እንደምናውቅ ሁሉ አንድ ክርስቲያንም መልካም ሥራን አብዝቶ ሲሠራ በሥራ ገላጭነት ሃይማኖቱ ገዝፎ በጉልሕ ይታያል፤ በመኾኑም በክርስትና ሕይወት ሃይማኖትና ሥነ ምግባር እንደ ነፍስና ሥጋ ተዋሕደው በአንድነት ሲኖሩ ሕይወተ ነፍስን እንደሚያጎናጽፉ ልብ ብሎ ማስተዋል ይገባል፡፡

የተወደዳችኹ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ፤

ከክርስትና ሃይማኖት አስተምህሮ በሚመነጨው መርሕ መሠረት በሥራ በመትጋትና በፍጹም ፍቅር በመኖር ሕይወታችንን ይበልጥ ልናሳድገው ይገባል፤ ከሁሉ በፊት ሰው የተፈጠረው ለሥራና ለክብር እንደኾነ ከቶ ልንዘነጋው አይገባም፤ ይህም ከኾነ ሰው ለአንዲት ደቂቃ ያህል እንኳ እጅ እግርን አጣጥፎ ያለሥራ ሊቀመጥ እግዚአብሔር አልፈቀደም፤ አይፈቅድምም፡፡ በሐፈ ገጽከ ብላዕ ኅብስተከ፤ ወደወጣኽበት መሬት እስክትመለስ ድረስ ጥረኽ ግረኽ ላብኽን አንጠፍጥፈኽ ብላ ነውና የሚለው (ዘፍጥ.3÷19)፡፡ በዙሪያችንም ኾነ በሌላው አካባቢ የተሻለ ኑሮና ክብር ያላቸው ኾነው የሚታዩ ሁሉ የመክበራቸው ምስጢር ጠንክረው መሥራታቸው እንደኾነ በውል ልናጤነው ይገባል፤ እኛ ኢትዮጵያውያንም በታላቁ የሕዳሴ ግድባችን እንደሚታየው ኻያ አራት ሰዓት ሙሉ በትጋት ከሠራን በአጭር ጊዜ ሌሎች የበለጸጉ አገሮች ከደረሱበት የዕድገት ደረጃ የማንደርስበት ምክንያት አይኖርም፤ ዋናው ቁም ነገር ሁላችንም ኢትዮጵያውያን በኅብረት፣ በአንድነት፣ በስምምነት፣ በመተማመን፣ በመቻቻል ለሥራና ለሥራ ብቻ መነሣቱ ላይ ነው፡፡

ይህ ኹኔታ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ በአገራችን በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የምናየው ስለኾነ ለምንጣደፍለት የዕድገት ሽግግር ትልቅ መሣርያችን መኾኑን ዐውቀን እንደ ዐይን ብሌን ልንጠብቀው ይገባል፤ ይህ የኾነ እንደኾነ የሕዳሴውን ግድብ ጨምሮ በአገራችን የተጀመሩትን ታላላቅ ሥራዎች ኹሉ ያለጥርጥር ማሳካት እንችላለን፡፡ ‹‹የእውነትና የሕይወት መንገድ አድሶልናልና፤›› የሚለውን የፋሲካ ትምህርተ ሃይማኖት የሕዳሴውን ልማት በማፋጠንና በማሳካት ልንገልጸው ይገባል፡፡ በሌላ በኩል ታላቁን የፋሲካ በዓላችንን ስናከብር ለእኛ ብሎ፣ በእኛ ፈንታ መሥዋዕት ኾኖ የዘለዓለም ሕይወትን ካጎናጸፈን ጌታ ጋራ ማክበር አለብን፤ ፋሲካን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋራ ማክበር የምንችለው የተራቡትን በመመገብ፣ የተጠሙትን በማጠጣት፣ የታረዙትን በማልበስ፣ የታመሙትንና የታሰሩትን በመጠየቅ፣ እንግዶችን ተቀብሎ በማስተናገድ ነው፡፡ ስለኾነም ሕዝበ ክርስቲያኑ ከሃይማኖቱ፣ ከተቀደሰ ሥነ ምግባሩና ባህሉ በወረሰው ሥርዐት መሠረት እንደተለመደው በዓሉን በሰላም፣ በፍቅር፣ በስምምነትና በመረዳዳት፣ ድኾችን ይዞ በመመገብ በመንፈሳዊ ደስታ እንዲያከብር መንፈሳዊ መልእክታችንንና ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

የተቀደሰና የተባረከ የፋሲካ በዓል ያድርግልን፤ እግዚአብሔር አገራችንንና ሕዝባችንን ይባርክ፤ አሜን፡፡

አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያሪክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ሚያዝያ 27 ቀን 2005 ዓ.ም.

{flike}{plusone}

ዕለታተ ሰሙነ ሕማማት

                   ሰሙነ ሕማማት ምንድን ነው?

ከዕለተ ሆሣዕና ሰርክ እስከ ትንሣኤ ሌሊት ያለውን ጊዜ ወይም ቀናት የሚያመለክት ነው፡፡ ሐመ ማለት ታመመ ማለት ሲሆን ይህም የሰውን ዘር ሁሉ ከዲያብሎስ ባርነት ነፃ ለማውጣት ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፈቃዱ የተቀበላቸውን ጸዋትወ መከራዎች የሚያሳስብ ነው፡፡ ዕለታቱ የዓመተ ኩነኔ ወይም የዓመተ ፍዳ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ክርስቲያኖች የክርስቶስን ውለታ እያሰቡ እጅግ የሚያዝኑበት፣ የሚያለቅሱበት፣ የሚሰግዱበት ቤት ንብረታቸውን ትተው ከሌላው ቀናትና ጊዜያት በተለየ መልኩ ቤተ ክርስቲያናቸውን የሚማጸኑበት፤ ጧት ማታ ደጅ የሚጠኑበት፤ ኃጢአታቸውን በቤተ ክርስቲያን አደባባይ ለካህኑ የሚናዘዙበት በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚገኝ ሳምንት ነው፡፡ በዚህ ሳምንት በመራብ በመጠማት በመውጣት በመውረድ በመስገድ በመጸለይ በመጾም በየሰዓቱ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ጸዋትወ መከራዎች በማሰብ አብዝቶ ይሰገዳል፡፡ መከራውን፣ ሕማሙን፣ ድካሙን የሚያስታውሱ ከቅዱሳት መጻሕፍት ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ መዝሙረ ዳዊት ግብረ ሕማማት ወዘተ በየሰዓቱ ይነበባል፡፡ መስቀል መሳለም የለም፡፡ ካህናትም እግዚአብሔር ይፍታህ አይሉም የሳምንቱ ሥርዓተ ፍትሐት አይደረግም፡፡ ይኸውም ይህ ሳምንት ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገርንበት ከጨለማ ወደ ብርሃን የተጓዝንበት የመሸጋገሪያ ወቅት ምሳሌ በመሆኑ ነው፡፡ በዕለተ ምጽአት መላእክት የመለከት ድምጽ በማሰማት የዳግም ምጽአትን ዕለት ለማሳሰብ ምእመናን ጥሪውን ሰምተው ለዚህም አስቀድመው ተዘጋጅተው የበዓሉ ታዳሚዎች መሆናቸውን በማጠየቅ በዚህ ሳምንት ዲያቆኑ ቃጭል እየመታ በየሰዓቱ ምእመናኑን ያሳስባል፡፡

በሰሙነ ሕማማት የሚገኙ ዕለታትና ስያሜያት

ለተ ሰኑይ /ሰኞ/ ይህ ዕለት አንጾሖተ ቤተ መቅደስ /የቤተ መቅደስ መንጻት/ እና መርገመ በለስ የተፈጸመበት ዕለት ነው፡፡ /ማር.11-11፣ ማቴ.21-18-22 ሉቃ.13-6-9/፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ «ወመሰለ ሎሙ ወይቤሎሙ አሐዱ ብእሲ በለሰ ቦቱ ውስተ አጸደ ወይኑ ወየሐውር ይንሣእ ፍሬሃ ወኢይረክብ …»፤ ይህንም ምሳሌ አለ ለአንድ ሰው በወይኑ አትክልት የተተከለች በለስ ነበረችው ፍሬም ሊፈልግባት ወጥቶ ምንም አላገኘም፡፡ በማለት በበለስ ስለተመሰለ የሰው ልጅ ሕይወት በማሰብ እንዲመለስ ንስሐ እንዲገባ በሕይወትም እንዲኖር እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ማሳሰቡን ያጠይቃል፡፡ ንስሐ አልገባም አልመለስም ያለም በለሷ እንደጠወለገችና እንደተቆረጠች ሁሉ ፍሬ ባለማፍራታቸው እንደሚቆረጡ እንዲሁም ወደ እሳት እንደሚጣሉ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስረዳል፡፡ በለስ የተባለች ቤተ እስራኤል ፍሬ የተባለ ደግሞ ሃይማኖትና ምግባርን ነው፡፡ ሁላችን ቤተ እስራኤላውያን ፍሬ ሃይማኖት ወምግባር አስተባብረን ይዘን መገኘት ይገባናል፡፡ ፍሬ አልባ እንዳንሆን ጌታ ሲመጣም እንዳናፍር የመጽሐፉን ቃል ልንጠብቅና ልንፈጽም ይገባናል፡፡ በዚህ የሕማማት የመጀመሪያ ቀን ዕለተ ሰኑይ የምናስበው የምንዘክረው የሰው ልጅ ሕይወት በከንቱ በቸልተኝነት እንዳይደክም እንዳይጠወለግ እንዳይደርቅ ወደ እሳትም እንዳይጣል ማድረግ ይገባናል፡፡

{flike}{plusone}

ዕለተ ሠሉስ /ማክሰኞ/ ይህ ቀን ጌታችን ሰኞ በተናገረውና ባደረገው ላይ አይሁድ ጥያቄ ያቀረቡበት እርሱም መልስ በመስጠት ያስተማረበት ዕለት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የጥያቄ እና የትምህርት ቀን በመባል ይታወቃል፡፡ ጥያቄውም ጌታ ባደረገው አንጽሖተ ቤተ መቅደስ ምክንያት ለጸሐፍትና ፈሪሳውያን ይኸውም ትምህርት ማስተማር፣ ተአምራት ማድረግ፣ ገበያ መፍታትን በማን ሥልጣን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ?» የሚል ነበር፡፡ /ማቴ.21-23-27/፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ «ወይቤሎሙ ኢየሱስ አማን እብለክሙ ከመ መጸብሓውያን ወዘማውያት ይቀድሙክሙ ውስተ መንግሥተ እግዚአብሔር»፤ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው እውነት እላችኋለሁ ቀራጮችና ጋለሞቶች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአችኋል ሲል አስተምሯል፡፡ /ማቴ.21-28/

ዕለተ ረቡዕ ይህ ዕለት ደግሞ የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንደሚችሉ ምክር የጀመሩበት ቀን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ዕለቱ የምክር ቀን በመባል ይጠራል፡፡

ዕለተ ሐሙስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዕለት ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ መሆኑን ለመግለጥ እና ለአርአያነት ጸሐፍት ፈሪሳውያን የአይሁድ ካህናት መጥተው እስኪይዙት ድረስ ሲጸልይ በማደሩ ምክንያት ጸሎተ ሐሙስ በመባል ይታወቃል፡፡ ትሕትና ፍቅር መታዘዝ እንዲሁም የአገልግሎትን ትርጉም ለማስረዳትና ለማስገንዘብ የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠቡ ሕጽበተ ሐሙስ በመባልም እንደሚጠራ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይናገራሉ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስም «ወሶበ ኀፀቦሙ እገሪሆሙ ነሥአ አልባሲሁ ወረፈቀ ካዕበ ወይቤሎሙ አእመርክሙኑ ዘገበርኩ ለክሙ … ወሶበ አነ እንከ ሊቅክሙ ወእግዚእክሙ ኀፀብኩክሙ እገሪክሙ ከማሁኬ አንትሙኒ ይደልወክሙ ትኅፅቡ እግረ ቢጽክሙ፡፡»፤ «እግራቸውንም አጥቦ ልብሱንም አንሥቶ ዳግመኛ ተቀመጠ እንዲህም አላቸው ያደረግሁላችሁን ታስተውሉታላችሁን?… እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ እናንተ ደግሞ እርስ በእርሳችሁ ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል ሲል ተናግሯል፡፡ /ዮሐ.13-12-20/፡፡ ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚቆረሰው ሥጋዬ ነው እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ስለ እናንተ የሚፈስ ደሜ ነው ከእርሱ ጠጡ በማለት ምሥጢረ ቁርባንን የመሠረተበት ወይም ራሱ ምስጢረ ቁርባንን የጀመረበት ቀን በመሆኑ የምስጢር ቀን ተብሎ ይጠራል፡፡ ይኸውም የሰው ልጆች ሥጋውንና ደሙን ተቀብለን ከእርሱ ጋር አንድነትና ኅብረት እንዲኖረን ጥንተ ጠላት ዲለብሎስንም ፍጹም ድል ነሥተን ሰማያዊት ርስት መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ ለማስቻል ነው፡፡ /ማቴ.26-26-29/፡፡ አይሁድ ጌታችንን ለመያዝ በእነርሱ ጥበብና ፍላጐት ቀስ ብለው መጥተው የያዙበት ቀን ስለሆነ በዚህ ዕለት በለሆሳስ /ብዙ የድምጽ ጩኸት ሳይሰማ/ የቅዳሴ ሥርዓት ይፈጸማል፡፡ ስለሆነም መላው ሕዝበ ክርስቲያን በዚህ የሕጽበት፣ የምስጢር፣ የጸሎት ቀን በተባለው በዚህ ዕለት በንስሓ ታጥበው ሥጋ ወደሙ እንዲቀበሉ ቤተ ክርስቲያን በአጽንኦት ታስተምራለች፡፡

ዕለተ ዐርብ ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ «አውቀውስ ቢሆን የክብርን ጌታ ባልሰቀሉት» /1ቆሮ.1-18/፡፡ እንዳለ ይህ ዕለት የአይሁድ ካህናት ያለበደል ያለጥፋት ንጹሕና ጻድቅ የሆነውን ጌታ የሰቀሉበት ዕለት ነው፡፡ ዕለቱም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም ሁሉ መድኃኒት ለአዳምና ለልጆቹ ሲል በመልእልተ መስቀል በቀራንዮ አደባባይ ተሰቅሎ መዋሉን የምናስብበት ታላቅ ቀን ነው፡፡ /ማቴ.27-35-75/፡፡ በዚያን ጊዜ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ እንደተፈረደበት አይቶ ተጸጸተ ሠላሳውንም ብር ለካህናት አለቆችና ለሽማግሎች መልሶ ንጹሕ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ አለ፡፡ እነርሱ ግን እኛስ ምን አግዶን? አንተው ተጠንቀቅ አሉ፡፡ ብሩንም በቤተ መቅደስ ጥሎ ሔደና ታንቆ ሞተ፡፡ የካህናት አለቆችም ብሩን አንሥተው የደም ዋጋ ነውና ወደ መባ ልንጨምረው አልተፈቀደም አሉ፡፡ ተማክረውም የሸክላ ሠሪ መሬት ለእንግዶች መቃብር ገዙበት፡፡ ስለዚህ ያ መሬት እስከ ዛሬ ድረስ የደም መሬት ተባለ፡፡ /ማቴ.27-3-9/ የሰው ልጆች በዘር ኃጢአት /ቁራኝነት/ ይኖሩበት የነበረው የጨለማ ሕይወት ያከተመበት ፍጹም ድኅነት ያገኙባት ታላቅ ዕለት ናት፡፡ ክርስቲያኖች ሁልጊዜም ዕለተ ዓርብ ሲመጣ ሕማሙን ስቅለቱን ሞቱን የሚያስቡበት ጊዜ ነው፡፡ በሮማውያን ሕግና ሥርዓት መስቀል የወንጀለኞች መቅጫ ምልክት የሕይወት መቅጫ አርማ ሆኖ ሳለ ለእኛ የዲያብሎስ ድል መንሻ ስላደረገው በስቅለቱና በሞቱም ሕይወትን ስለአገኘን በዚህም ምክንያት መልካሙ ዓርብ በመባል እንደሚታወቅ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ያትታሉ፡፡

ቀዳሜ ስዑር ዕለተ ቅዳሜ እግዚአብሔር የሚታዩትንና የማይታዩትን፣ በእግር የሚሄዱትን እና በክንፍ የሚበሩትን በባሕር የሚዋኙትን እንስሳትን በመጨረሻም ሰውን በአርአያውና በአምሳሉ ፈጥሮ ያረፈበት ዕለት ነች፡፡ ይህች የመጀመሪያው ቅዳሜ ለእግዚአብሔር የዕረፍት ዕለት ናት እግዚአብሔርን ሥነ ፍጥረት ፈጥሮ ስላረፈበት ሰንበት ዐባይ /ታላቋ ሰንበት/ ትባላለች ታላቋን ሰንበት እስራኤላውያን እንዲያከብሯት ታዟል፡፡ ዘፍ.1፡3፡፡ ዕለተ ቀዳሚት /ሰንበት ዐባይ/ በዘመነ ሐዲስም የተለየ የደኅነት ሥራ ተከናውኖባታል፡፡ ጥንት ሥነ ፈጥረትን በመፍጠር ዕረፍት እንደ ተደረገባት ሁሉ የፍጥረት ሁሉ ቁንጮ የሆነውን አዳምን ለማዳን ሕማምና ሞት የተቀበለው ቸሩ አምላክ በመቃብር አርፎባታል፡፡ ማቴ.27፡61፡፡ በዚህች ዕለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከርሰ መቃብር ዐርፎ የዋለባት ዕለት በመሆኗ «ቀዳሜ ስዑር » ትሰኛለች፡፡

ስዑር ቀዳሜ የተባለችው በዓመት አንድ ቀን ስለ ምትጾም ነው፡፡ ምክንያቱም እናቱ ድንግል ማርያም ወዳጆቹ ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታ ተላልፎ ከተሰጠበት ዕለት አንስተው ብርሃነ ትንሣኤውን እስኪያዩ ድረስ እህል ውኃ በአፋቸው አልዞረም፡፡ ይመኩበትና ተስፋ ያደረጉት የነበረ አምላካቸው በመቃብር ስላረፈ ዕለቷን ሞቱን በማሰብ ትንሣኤውን በመናፈቅ በጾም አክብረዋታል፡፡ ከቅዱሳን ሐዋርያት ሲወርድ ሲወራረድ በመጣው ትውፊት መሠረት ቅዱሳን ሐዋርያት በማዘን በመጾምና በመጸለይ ዕለቷ እንዳከበሯት የተዋሕዶ ልጆች የተቻላቸው ከዓርብ ጀምረው የሚያከፍሉ /የሚጾሙ/ ለሁለት ቀን እህል ውኃ ሳይቀምሱ ያድራሉ ያልተቻላቸው ደግሞ ዓርብ ማታ በልተው ቅዳሜን በመጾም ትንሣኤን ያከብራሉ፡፡ በዚህ ዕለት ከሰኞ ከሆሣዕና ማግሥት ጀምረው እስከ ስቅለተ ዓርብ ድረስ በስግደት እና በጾም ያሳለፉ ምእመናን በዕለተ ቅዳሜ በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ይሰበሰባሉ፡፡ የጠዋቱ ጸሎት ሲፈጸም ካህናቱ «ገብረ ሰላመ በመስቀሉ፡-በመስቀሉ ሰላምን መሠረተ» የምሥራች እያሉ በቤተ ክርስቲያን ለተሰበሰቡት ምእመናን ቄጠማ ይታደላል ቄጠማው የምሥራች ምልክት ነው፡፡ ቄጠማው የምሥራች ምልክት ተደርጐ የተወሰደው በኖህ ዘመን ከተፈጸመው ታሪክ ጋር በማቆራኘት ነው፡፡

ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን በጻድቁ ኖኅ ዘመን የነበሩ ሕዝቦች ከሕገ እግዚአብሔር ውጪ ሆነው እጅግ የሚያሳዝን ኃጢአት በሠሩ ጊዜ በንፍር ውኃ ተጥለቅልቀዋል፡፡ በወቅቱ ጻድቁ ኖኅ ወደ መርከብ ይዞአቸው ከገባው እንስሳት መካከል የውኃውን መጉደል ለመረዳት ርግብን በመርከብ መስኮት አሾልኮ ይለቃታል፤ እርሷም ቄጠማ በአፍዋ ይዛ ትመልሳለች፡፡ ዘፍ.9-1-29፡፡ ኖኅም በዚህ ቄጠማ የውኃውን መድረቅ ተረድቶ ተደስቷል፡፡

«ቄጠማ»፣ ለጥፋት ውኃ መድረቅ የምሥራች መንገሪያ እንደሆነ አሁንም በክርስቶስ ሞት ሞተ ነፍስ ከሰው ልጆች ተወገደ ስትል ቤተ ክርስቲያን ለልጆቿ ቄጠማ ታድላለች፡፡ ምእመናንም የምሥራች ተምሳሌት የሆነውን ቄጠማ በግንባራቸው ያስሩታል፡፡ የክርስቶስ ተከታዮች ሁሉ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሚያቃጥለው ዋዕየ ሲኦል /የሲኦል ቃጠሎ/ ወደ ልምላሜ ገነት ጥንተ ማኅደራቸው መመለሳቸውን በዚህ አኳሃን እየገለጡ በዓለ ትንሣኤን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያከብራሉ፡፡

{flike}{plusone}

002

በዓለ ሆሳዕና እና ሰሙነ ሕማማት

           እንኳን ለበዓለ ሆሳዕና በሰላም አደረሳችሁ!!

002

የሆሳዕና በዓል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ ኢየሩስአሌም ሲገባ የሚቀድሙት እና የሚከተሉት ህዝብ በተለይም አእሩግ እና ህጻናት “ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም ሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሳዕና በአርያም “ በማለት ጌታችንን መቀበላቸው የሚታወስበት በዓል ነው።

ሆሣዕና ከስምንቱ የዐቢይ ጾም እሑዶች አንዱና የመጨረሻው ሳምንት ተብሎ የሚጠራው ከትንሣኤ ቀድሞ የሚገኝ የሕማማት መግቢያ ዋዜማ ነው።

ሆሣዕና ከረቡዕ ጀምሮ የሚታሰብ ታላቅ የቤተክርስቲያን የበዓል ቀን እንደሆነ ይታወቃል። ይህ በዚሁ በዓለ ሰንበትና በዋዜማዎቹ ዕለታት የሚዘመረው ጾመ ድጓ ‘ሆሣዕና በአርያም’’ ‘ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት’’ ‘ዕለተ ሆሣዕናሁ አርአየ… ‘ ወዘተ. በማለት ሆሣዕና የሚለውን ቃል ቅዱስ ያሬድና ሌሎችም አባቶች በየቦታው እየጠቀሱና እየተዘመረለት በአህያ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ኢየሩሳሌም የገባበትን ሁኔታ እየተረከ ስለሚዘምር ይህ ሰንበት በጌትነትና በክብር በውዳሴና ቅዳሴ ሆሣዕና በአርአያም እየተባለ በሽማግሌዎችና በሕፃናት አንደበት በድንጋዮችም ልሳን ሳይቀር እየተመሰገነ ወደ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም በከብር ሲገባ ለሰጣቸው ለተቀደሰ ሰላሙና ፍቅሩ መታሰቢያ ሆኖ የተሰጠ ነው። አስቀድሞም በነቢየ እግዚአብሔር ዘካሪያስ እንደተነገረው ‘አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበለሽ ፣አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል በይ እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው ትሑትም ሆኖ በአህያም በአህያያቱም ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል… ሰላምን ይናገራል’’ ዘካ.9፣9። በማለት እንደሚመጣና የሠላምንም ብሥራት እንደሚያበሥር ተናገሮ ነበር። ሲመጣም ‘ሁሉም ፈጥነው ልብሳቸውን ወሰዱ በሰገነቱም መሰላል እርከን ላይ ከእግሩ በታች አነጠፉት።’’ በማለት ሊደረግለት የሚገባውን ገልጿል። 2ኛ ነገ. 9፣13 ።

የሆሣዕና በዓል በቤተክርስቲያን ጌታ ወደ ቤተመቅደስ ሲገባ ሕዝቡ ፀበርት ወይም ዘንባባ በመያዝ ‘ቡርክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር – በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረክ ነው።’’ መዝ.117፣26 በማለት ስለተቀበሉት ይህን በማሰብና በማድረግ ቤተክርስቲያናችን ዘንባባ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ታድላለች። በቤተክርስቲያን በአራቱም ማዕዘናት ይህን በዓል የሚመለከቱ የቅዱስ ማቴዎስ (ማቴ. 21፣1-17)፤ የቅዱስ ማርቆስ፣(ማር.11፣1-10)፤ የቅዱስ ሉቃስና (ሉቃ.19፣29-38)፤ የቅዱስ ዮሐንስ (ዮሐ.12፣12-15) ወንጌላት ይነበባሉ ።

ታዲያ አኛ ይህን ዐቢይ በዓል የምናከብረው እንዴት ነው? በነቢያቱ ከላይ እንደተገለጠው በወንጌላቱም አንደተፈጸመው እርሱ ወደ እኛ የሚመጣበት ጊዜ መቼ ነው? ሲመጣስ ምን እናድርግ? የእግዚአብሔርን መምጫ ጊዜ ማሰብና መዘጋጀት ያለብን እንዴት ነው? ምክንያቱም

{flike}{plusone}

በዓሉ ከምንም በላይ የሚጠቅመን ለእኛ ነውና ።

 

ስለዚህ ይህን በዓል ስናከብር ሰላምንና ፍቅርን የእርሱን የክብር አመጣጥ እያሰብን ልንተገብረው ይገባል። ለጌታ የማያስፈልግ ፍጥረት የለም ይልቁንም የክብር ዘውድ አድርጎ በመልኩ የፈጠረው ሰው ያስፈልገዋል።ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ የተፈጠረ ማንም የለም።እያንዳንዳችን በእግዚአብሔር ዓላማና ዕቅድ የተፈጠርን እንደመሆናችን መጠን እግዚአብሔር የሚከብርበትን ሥራ ልንሠራ ይገባል።አህያ በሰው ሰውኛ ሲታይ የንቀትና የውርደት ሲመስል ይችላል ።የአህያን ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ስንመለከት ግን

 1.  በለዓም በሥጋዊ ገንዘብ መንፈሳዊ ዓይኑ ታውሮ እግዚአብሔር ያልረገማቸውን እስራኤላውያንን ሊራገም ሲሄድ እስራኤላውያንን እንዳይራገም ለመንገር ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከው መልአክ በሚሄድበት መንገድ ላይ ቆሞ ሳለ ከበለዓም ይልቅ ያየችው የበለዓም አህያ ነበረች ። አህያይቱም መልአኩን አክብራ መንገዱን እንደለቀቀችለት ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል። ዘኅ.22፣23።
 2.  በትንቢተ ኢሳያስ 1፣3 ‘ሰማይ ስሚ ምድርም አድምጪ በሬ የገዢውን አህያም የጌታውን ጋጣ አወቀ እሥራኤል ግን አላወቀም’’ እንደተባለው ጌታ በተወለደ ጊዜ ትንቢቱን ምሳሌውን የሚያውቁ እሥራኤላውያን ባላወቁ ባለተቀበሉ ሰዓት በዚያ በብርድ ወራት እናቱ የምታለብሰው ልብስ አጥታ ቅጠል አልብሳው በነበረ ጊዜ ለጌታ ሙቀት የገበሩለት እረኞቻቸውን ተከትለው የመጡ ከበቶች ላሞችና አህዮች ናቸው። ‘ወአስተማወቅዎ አድግ ወላህም’’ እንዲል አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም።
 3.   በሆሣዕና ዕለት ከሌሎች እንስሳት ይለቅ ጌታን በከብር የተሸከመችው አህያ ናት። ጌታን የተሸከመችው አህያ ከዚያ በፊት ያላየችውና ያልተደረገላት ክብር ተደርጉላታል። አህያ ከዚህ በፊት ለኛ እህል ተሸክማ ስትሄድ ሂጂ እያልን በዱላ እንደበድባት ነበር፡ ነውም። ነገር ግን በሆሣዕና ዕለት እንኳን በዱላ ልትደበደብ ቀርቶ ሰዎች በእርሷ ላይ ለተቀመጠው ጌታ ሲሉ ልብሳቸውን ሁሉ እያነጠፉላት በንጣፍ ላይ ተራምዳለች ።

ስለዚህ ክርስቶስ በአህያይቱ ላይ እንዲቀመጥባት ልብስም እንደ ተጎዘጎዘላት እኛም ጌታ በፀጋውና በረድኤቱ እንዲያድርብን ልባችንን ከኃጢአትና ከተንኮል አንጽተን ፍቅርንና ትሕትና ልንጎዘጎዝ ይገባል። ጌታ በኛ ላይ በፀጋው ሲያድር በእርሱና በቅዱሳኑ ዘንድ ያለን ክብርና ፀጋ ታላቅ ነው። በነገር ሁሉ መከናወን ይሆንልናል።ክርስቶስን በመሸከሟ የአህያይቱ ታሪክ እንደተለወጠ ሁሉ በክርስቶስ ማደሪያነታችን ያለፈው መጥፎ ታሪካችን ይለወጣል።እንግዲህ በእለተ ሆሣዕና ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ ሕዝቡ ሁሉ በደስታ በዝማሬ እንደ ንጉሰ እንደተቀበሉት እኛም ሀሴትን አድርገን ‘ሆሣዕና እምርት እንተ አቡነ ዳዊት…’’ በማለት እናመሰግናለን።

የሰሙነ ሕማማት ሃይማኖታዊና ቱፊታዊ ክንዋኔዎች

በዐቢይ ጾም ከሰርክ ሆሳዕና ጀምሮ እስከ ትንሳኤ ሌሊት ያሉት ዕለታት የሚገኙበት ሳምንታት ሰሙነ ሕማማት ይባላል፡፡ ዕለታቱም የዓመተ ፍዳ፣ የዓመተ ኩነኔ መታሰቢያ ናቸው፡፡ በእነዚህ ዕለታት ውስጥ የተለያዩ ትውፊታዊ እና ሃይማኖታዊ ክንዋኔዎች አሉ፡፡ ከነዚህ ክንዋኖዎች ውስጥ አለመሳሳም፣ አክፍሎት፣ ቄጤማ ማሰር፣ ጥብጠባ፣ ጉልባን እና ሕፅበተ እግር ይገኙበታል፡፡ ስለእነዚህ ክንዋኔዎች በቅድስት ቤተ ክስቲያን ስላለው ትውፊታዊ አፈፃፀም መዛግብት አገላብጠን እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡

አለመሳሳም፡- በሰሙነ ሕማማት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች መስቀል እንደማይሳለሙት ሁሉ መጨባበጥ፣ መሳሳምን የትክሻ ሰላምታ መለዋወጥን አይፈጽሙም፡፡ ሰላምታ የማንለዋወጥበት ምክንያት አይሁድ ጌታን ለመስቀል ሰኞ እና ማግሰኞ መከሩ አልሰመረላቸውም፡፡ ምክረቸው የተፈጸመው ረቡዕ ነው፡፡ ስለዚህ አይሁድ እያንሾካሾኩ እንሰቀለው ፤እንግለው ብለው ይማከሩ ነበር፡፡ በዘመነ ፍዳ ወቅት ሠላምና ፍቅር አለመኖሩን የሚገልፅልን በመሆኑ ያንን ለማስታወስ ስላምታ አንለዋወጥም፡፡ መስቀልም አንሳለምም፡፡ ሳምንቱ የክፋት ምክር የተመከረበት እንጂ የፍቅርና የደስታ ሳምንት የታየበት ባለመሆኑ ይህንን በማሰብ ሰላምታ አንለዋወጥም፡፡ አይሁዳ ጌታን በጠላቶቹ ለማስያዝ እኔ የምስመው እርሱ ነው ያዙት ብሎ በሰላምታው ምልክት ሰጣቸው ይህ ሰላምታ አምሐ ቅድሳት አይደለም ተንኮል የተሞለበት እንጂ፡፡ የዲያቢሎስም ሰላምታ ተመሳሳይ ነው፡፡ ሔዋንን ስላም ለኪ ብሎ ነው ያታለላት የይሁዳም ሰላምታ ሰይጣናዊ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ወቅትና ሁኔታ ለማሰብ በሰሙነ ሕማማት ሰለምታ ልውውጥ የለም፡፡ ዛሬ እየተስተዋለ ያለው ይኽው ሰላምታ ያለመለዋወጥ ሁኔታ ስርወ መሰረቱ ይህ ነው፡፡ ከጥንት ጀምሮ እዚህ ትውልድ ላይ ደርሷል፡፡ ይቀጥላልም፡፡

ሕፅበተ እግር፡- ጌታ በፍጹም ትህትና የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጠበበት፣ ከሐዋርያት ጋር ግብር የገባበትና የክርስትና ህይወት ማሕተም የሆነውን ምስጢረ ቁርባን ያከናወነበት ዕለት ነው ጸሎተ ሐሙስ ሕፅበተ እግር ጌታችን በዚህ እለተ እናንተ ለወንድማችሁ እንዲሁ አድርጎ ለማለት የደቀ መዛሙርቱን አግር በማጠቡ ምክንያት የተሰጠ ምሳሌ ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው እኔ ለእናንተ እንዳደረኩ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና እውነት እውነት እላችኋለሁ ባሪያ ከጌታው አይበልጥም መልእክተኛም ከላከው አይበልጥም ይህን ብታውቁ ብታደርጉትም ብጹዓን ናችሁ፡፡ ዮሐ 13፡16-17 በማለት ትህትናውን አሳይቷል ጌታ በዚህ እለተ የደቀ መዛሙርቱን እግር ሲያጥብ እኔ መምህራችሁ ስሆን እግራችሁን ካጠብኳችሁ አርአዬን ሰጥቻችኋለሁ እናንተም የወንድማችሁን እግር ታጥቡ ዘንድ ይገባል፡፡ ነገር ግን ከእናንተ አንዱ ለሞት አሳልፎ ይሰጠኛል አለ ደቀ መዛሙርቱም ማንይሆን አሉ፡፡ ጌታም ህብስት ቆርሼ፣ ከወጡ አጥቅሼ የምሰጠው እርሱ ነው አላቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ደንግጠዋል ይሁዳን ማመልከቱ ነበር ለጊዜው አልገባቸውም፡፡ ጌታችን መዳኃኒታችን የሐዋርያቶቹን እግር በማጠብ ትሕትናን ካስተማረቸው በኋላ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን የሰጣቸው የኦሪትን መስዋዕት የሻረው እና መስዋዕተ ሐዲስን የሠራው በዚሁ እለት ነው፡፡

አክፍሎት፡- በሰሙነ ሕማማት እለተ ዓርብ ከስግደት በኋላ ምእመናን በየቤታቸው ጥቂት ነገር ለቁመተ ሥጋ ቀምሰው እስከ እሁድ /የትንሳኤ በዓል/ ይሰነብታሉ፡፡ ይህ አክፍሎት ይባላል፡፡ ከዓርብ እስከ ቅዳሜ ሌሊት ለእሁድ አጥቢያ ማክፈል የብዙዎች ነው፡፡ አንዳንዶች ግን ከሐሙስ ጀምረው ያከፍላሉ፡፡ ይህም እመቤታቸን ያዕቆብ እና ዩሐንስ የጌታን ትንሳኤ ሳናይ እህል ውኃ አንቀምስም ብለው እስከ ትንሳኤ መቆየታቸውን ተከትሎ የመጣ ትውፊት ነው፡፡ ይህንን ትውፊት አስመልክቶ ሄሬ ኔዋስ አውሳብዩስ የተባሉ ጸሀፍተ ሐዋርያት በስሙነ ህማማት ከደረቅ ዳቦ እና ከትንሽ ውሃ በቀር እንደ ማይመገቡ እና ከሐሙስ ጀምረው እንደሚያከፍሉ ጽፈዋል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ሐዋሪያት ሌሎቹንም እንዲያከፍሉ እንዳሳሰቡና ከሐሙስ ጀምሮ ያልተቻለው ቢያንስ ከዓርብ ጀምሮ እንዲያከፍል ማዘዛቸውን ጽፈዋል፡፡ የእኛ ቤተ ክርስቲያን ትምህርትም ይኽው ነው፡፡ ቅዳሜ ይበላል ማለት ግን ቅዳሴው ሌሊት ስለሆነ በልቶ እንደ ማስቀደስ እና በልቶ እንደመቁረብ ይቆጠራል፡፡ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታዮችም ይህንኑ ትውፊት ሲከውኑ አያሌ ዘመናት ተቆጥሯል፡፡

ጉልባን እና ቄጠማ፡- ጉልባን ከባቄላ ክክ፣ ከስንዴ ወይንም ከተፈተገ ገብስ ጋር አንድ ላይ ተቀቅሎ የሚዘጋጀና የጸሎት ሐመስ እለት የሚበላ ንፍሮ ነው፡፡ የጉልባን ትውፊት እስራኤላውያን ከግብጽ ተሰደው በሚነጡበት ጊዜ በችኮላ ስለነበር አቡክተው ጋግረው መብላት ያለመቻላቸውን ሁኔታ ያመለክታል፡፡ ያን ጊዜ ያልቦካው ሊጥ እያጋገሩ ቂጣ መብላት ንፎሮም ቀቅለው ስንቅ መያዝ ተግባራቸው ነበር፡፡ ይህን ለማሰብ በሰሙነ ሕማማት ቂጣና ጉልባን በማዘጋጀት በዓል ይታሰባል፡፡ በጸሎተ ሐሙስ ይህንን መሰረት በማድረግ የሚዘጋጀው ጉልባን እንዲሁም ቂጣ ጨው በዛ ተደርጎ ይጨመርበታል፡፡ ጨው ውሃ የሚያስጠማ በመሆኑ የጌታን መጠማት ያስታውሳል፡፡ ይህ ትውፊታዊ ስርዓት በእስራኤላውያን የመጣ ሲሆን በኢትዮጵያ አብዛኛዎቹን የትውፊት ክንዋኔዎች የብሉይ ኪዳን መነሻ ስላላቸው ስርዓቱ ዛሬም ይከበራል፡፡

ጥብጠባ፡- በሰሙነ ሕማማት እለተ ዓርብ ስቅለቱ መታሰቢያ ነው፡፡ ምእመናኑ በሰሙነ ሕማማት የሰሩትን ይናዘዛሉ፡፡ ካህናቱን በወይራ ቅጠል ትከሻቸውን እየጠበጠቡ ቀን ከሰገዱት ስግደት በተጨማሪ ሌላ ስግደት ያዟቸዋል፡፡ ጥብጠባው የተግሳፅ ምሳሌ ነው፡፡ ጥብጠባው የሚደረግለት ሰው በህማማቱ ወቅት የፈጸማ በደል ወይም ኃጢአት ካለ ይህንኑ በመናገር የስግደቱ ቁጥር ከፍ እያለ እንዲል ያደርጋል፡፡ ይህ በስቅለተ ቀን የሚፈጸም ስነ ስርዓት ሲሆን ጥብጣቤ ማለት ቸብ ማድረግ ማለት ነው፡፡ ህዝብ ክርስቲያኑ በእለተ ስቅለት ሲሰግድ ሲጸልይ ሲያነብ ከዋለ በኃላ ሰርሆተ ህዝብ (የህዝብ መሰነባበቻ) ከመሆኑ በፊት በወይራ ቅጠል እያንዳንዱን ምዕመን ጀርባ ቸብ ቸብ መደረጉ የጌታን ግርፋት ያስተውሳል፡፡ ማቴ 26፡26 ማቴ 19፡1-3

ቄጠማ(ቀጤማ)፡- በቀዳም ስዑር ቀሳውቱን ዲያቆናቱ ቃጭል /ቃለ አዋዲ/ እየመቱ ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ትንሳኤሁ አግሃደ የሚለውን ያሬዳዊ ዜማ በመዘመር ጌታ በመስቀሉ ሰላምን እንደሰጠ እና ትንሳኤውንም እንደገለጠልን በማብሰር ቄጤማውን ለምእመናን ይሰጣሉ፡፡ ምእመኑም ለቤተ ክርስቲን አገልግሎት የሚውል ገጸ በረከት ያቀርባሉ ቀጤማውንም በራሳቸው ያስራሉ፡፡ ይህም አይሁድ ጌታችንን እያሰቃዩ ሊሰቅሉት ባሉ ጊዜ የእሾህ አክሊል ጭንቅላቱ ላይ ያሰሩበትን ድርጊት የሚያስተውስ ነው፡፡ በዚህ እለት ልብስ ተክህኖ የለበሱ ካህናትና ዲቆናትን ቄጠማ ተሸክመው ቃጭል ሲቃጭሉ መታየታቸው እለተ ትንሳኤውን ለሚናፍቅ ምእመን ትልቅ ብስራት ነው፡፡

ቄጠማው የምሥራች ምልክት ተደርጐ የተወሰደው በኖህ ዘመን ከተፈጸመው ታሪክ ጋር በማቆራኘት ነው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን በጻድቁ ኖኅ ዘመን የነበሩ ሕዝቦች ከሕገ እግዚአብሔር ውጪ ሆነው እጅግ የሚያሳዝን ኃጢአት በሠሩ ጊዜ በንፍር ውኃ ተጥለቅልቀዋል፡፡ በወቅቱ ጻድቁ ኖኅ ወደ መርከብ ይዞአቸው ከገባው እንስሳት መካከል የውኃውን መጉደል ለመረዳት ርግብን በመርከብ መስኮት አሾልኮ ይለቃታል፤ እርሷም ቄጠማ በአፍዋ ይዛ ትመልሳለች፡፡ ዘፍ.9-1-29፡፡ ኖኅም በዚህ ቄጠማ የውኃውን መድረቅ ተረድቶ ተደስቷል፡፡ «ቄጠማ»፣ ለጥፋት ውኃ መድረቅ የምሥራች መንገሪያ እንደሆነ አሁንም በክርስቶስ ሞት ሞተ ነፍስ ከሰው ልጆች ተወገደ ስትል ቤተ ክርስቲያን ለልጆቿ ቄጠማ ታድላለች፡፡ ምእመናንም የምሥራች ተምሳሌት የሆነውን ቄጠማ በግንባራቸው ያስሩታል፡፡ የክርስቶስ ተከታዮች ሁሉ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሚያቃጥለው ዋዕየ ሲኦል /የሲኦል ቃጠሎ/ ወደ ልምላሜ ገነት ጥንተ ማኅደራቸው መመለሳቸውን በዚህ አኳሃን እየገለጡ በዓለ ትንሣኤን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያከብራሉ፡፡

መጽሐፈ ግብረ ሕማማት ታሪኩ ይዘቱና አገልግሎቱ

ግብረ ሕማማት የሚለው የቃሉ ፍቺ የሕማም የመከራ የስቃይ ሥራ ማለት ነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳምና ለዘሩ ደኅነት የተቀበለውን ጸዋትወ መከራ በእለትና በሰዓት ከፍሎ የሚናገር የሚያሳስብ መጽሐፍ በመሆኑ በቤተ ክርስቲያን በሰሙነ ሕማማት የሚደርሱ የምንባብትና የጸሎታትን ዝርዝር በምን ዓይነት ሁኔታና በማን ሊከናውኑ እንዲገባ የሚበይን /የሚናገር/ በመሆኑ ‹‹ግብረ ሕማማት›› ተብሏል፡፡

ታሪኩ፡- የመጽሐፊ ግብረ ሕማማት መቅድም እንደሚገልጸው ‹‹ሐዋርያት ለስብከተ ወንጌል በሚፋጠኑበት ጊዜ ስለ እርሱ ስለጌታችን ታሪኩንና ተአምራቱን ይከታተሉ ከነበሩት መካካል የተከበሩትና የታወቁ ሊቃውንት በኢንፎስና በገማልያል እጅ ተጽፎ በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም በክብር ቦታ ተቀመጦ የተገኝ ነው›› ይላል ይኸው መጽሐፈ ግብረ ሕማማት የመጽሐፉን የትመጣ ታሪክ ሲተነትን በየትኛው ገብርኤል እነደነበር አይታወቅ እንጂ ገብርኤል በሚባል የእስክንድርያ ፓትርያርክ የፕትርክና ዘመን የአባ መቃርዮስ ገዳም ሊቃውንት በነበረው ይዘቱና አገልግሎቱ ላይ የማሻሻያ /የማሟያ/ ሥራ እንደተሠራለት ያትታል፡፡/የግብረ ሕማማት መግቢያ/ መፅሐፍ ግብረ ሕማማት በወርቃማው የኢትዮጵያ የስነ ጸሑፍ ዘመን በካልዕ ሰላማ ወደ ልሳነ ግእዝ ተተርጎመ ከ 1340-1380 ግብረ ሕማማት ዘእሁድ ገጽ 466 ለዘመናት ከብራና ወደ ብራና በብዙ ድካም ሲገለበጥ የኖረው ‹‹መጽሐፈ ግብረ ሕማማት›› በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ዘመን ፕትርክና ታትሞ ተሰራጭቷል፡፡

ይዘቱ፡- የመጽሐፍ ግብረ ሕማማት ይዘት እጅግ አስደናቂ ነው፡፡ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጪ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ሥራዎች መድበልም ነው የነገረ ሃይማኖት፣ የታሪክ፣ የተአምራት፣ የሥርዓትና የህገ መጽሐፍ ነው፡፡ ወይም እኒህን ሁሉ በይዘቱ አካቷል፡፡ የመጽሐፉን ይዘት የሚመረምር ሰው ብሉይንና ሐዲስን ነቢያትና ሐዋርያትን ሊቃውንትን አዋልድ መጻሕፍትን በብዛት ያገኛል፡፡ ይኸውም በዕለት እና በሰዓት ተከፍሎ በሥርዓት የተዘጋጀ የትምህርትና የጸሎት መዝገበ መጻሕፍት ነው፡፡ ለምሳሌ ወቅቱን የሚመለከቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን፣ኦሪትን፣ ነቢያትን፣ ሐዲሳትን፣ ሃይማኖተ አበውን፣ ተግሳጽን፣ ተአምረ ኢየሱስን ተአምረ ማርያምን፣ ወዘተ የያዘ መጽሐፍ ነው፡ ለመፅሐፈ ግበረ ሕማማት ይዘት የኢትዮጵያ ሊቃውንት ፈርጥ የሆኑት ቅዱስ ያሬድና አባ ጊዮርጊስም የድሻቸውን በዜማ የሚጸልዩትን አካትተውልናል፡፡

አገልግሎቱ፡- መፅሐፍ ግብረ ሕማም የስርዓት የምንባብና የጸሎት መጽሐፍ ነው፡፡ ከሆሳዕና ዋዜማ እስከ ትንሳኤ መንፈቀ ሌሊት በእለትና በሰዓት ከፍሎ፣ የቅድመ ተከተሉን መሰረት በማን ምን መባል እልዳለበት እንደ መጽሐፈ ቅዳሴ ሁሉ ይበል ካህን፣ ይበል ዲያቆን እያለ እንዴት ሊፈጸም እንደሚገባ ጽና ይያዙ፣ ጥቁር ይልበሱ፣ በዚህ በኩል ይግቡ፣ በዚህኛው ይውጡ የሚለውን ሥርዓታዊ መመሪያ ለመስጠት ለካህናትና ለምእመናን የሚገባውን ለይቶ የሚተነትን የምስጢርና የትምህርት መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፈ ግብረ ሕማማት ሕማማተ እግዚእነ ከመንገር ባሻገር ለእንባና ለተመስጦ፣ ለትምህርትና ለተግሳፅ ያገለግላል የልሳነ ግእዝ አንባብያንም በስሙነ ሕማማት ሳይገድፉ በማንበብ ተግባራቸውን በጥንቃቄ የሚፈጽሙበትን የንብብ ችሎታቸውን የሚያሳዩበትም ነው፡፡ በብዙ ጥንታዉያን ገዳማትና አድባራት የብራና ቅጂ ያለው መጽሐፈ ግበረ ህማማተ በስሙነ ሕማማት ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ ለጥናትና ምርመር ምእመናንን በብዙ መልኩ ሊጠቅም የሚችል ይዘት ያለው ነው፡፡

{flike}{plusone}

0002

በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ለሚጦሩ አረጋወያን ለ7ኛ ጊዜ እረዳታ ተሰጠ

“ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ ምስጉን ነው እግዚአብሔር ከክፉ ያድነዋል፡፡” መዝ. 40÷1

“እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ”2ኛ ቆሮ. 9÷7

0002

ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ በድህረ ገፃችን አማካኝነት ወጣት ብሩክ አስራት የክርስትና ስሙ ግርማ ጽዮን ከዛሬ 7 ወር በፊት ጀምሮ ለካቴድራሉ አረጋውያን የሚሆን በየወሩ ለአረጋውያኑ የሚያስፈልጋቸውን የምግብ እርዳታ እያደረገላቸው መሆኑን ስንዘግብ መቆየታችን የሚታወስ ሲሆን አሁንም እንደተለመደው ለ7ኛ ጊዜ ለ1 ወር የሚሆን በእነ ወ/ሮ ማርታ ወርቄ፤በወንድሙ እና በጓደኞቹ አማካኝነት እርዳታውን ልኳል፡፡

በዚሁ ዕለት ቄሰ ገበዝ አባ ገ/ዮሐንስ የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቄሰ ገበዝ አማካኝነት ለወጣት ብሩክ አስራት፤ለቤተሰዎቹና ለጓደኞቹ ጸሎትና ምስጋና እንዲሁም ቃለ ምእዳን ተሰጥተዋል ፡፡ በወጣት ብሩክ አስራት እየተደረገ ላለው ነገር ሁሉ ምስጋናቸው እጅግ የላቀ መሆኑን ገልፀው ሌሎችም የዚሁ የተቀደሰ ዓላማ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በመጨረሻም ቄሰ ገበዝ አባ ገ/ዮሐንስ ለወጣት ብሩክ አስራትና ለቤተ ሰዎቹ እያደረገው ላለው ነገር ሁሉ በዓጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ ስም ካቴድራሉን በመወከል ምስጋናቸውን አቅርበዋል ፡፡

እነዚህ አረጋውያን ከዛሬ 45 ዓመታት በፊት ከዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት ጀምሮ በንጉሱ አማካኝነት በካቴድራሉ በጎ አድራጎት /ምግባረ ሠናይ ክፍል ሥር በቃለ ዓዋዲ መሠረት የተቋቋመ ሲሆን ቀደም ሲል በብዙ መልኩ የተደራጀ እንደነበር የሚነገር ሲሆን አሁንም በካቴድራሉ አስተዳደር አማካኝነት እንደቀድሞ ለማጠናከር ከፍተኛ የሆነ ጥረት እየተደረገ ነው በመሆኑም በዘላቂነተ የአረጋውያኑ ችግር በመጠኑ ለመቅረፍ እንደ ወጣት ብሩክ አስራት የክርስትና ስሙ ግርማ ጽዮን አቅማችሁ የፈቀደውን/የቻላችሁትን ያህል እርዳታ እንድታድርጉ እናሳስባለን፡፡ አረጋውያኑ ከሚያስፈልጓቸው መሠረታዊ ነገሮች መካከል፡-

 1. ምግብ፣
 2. መጠለያ፣
 3. ንጽህና፣
 4. ልብስና
 5. ሞግዚት ሲሆኑ የቦታው ጉዳይ በተመለከተ አሁን አረጋውያኑ ያሉበት ቤትና አጠገቡ ያለውን ቦታ ከካቴድራሉ ጽ/ቤት ጋር በመነጋገርና በማስፈቀድ በዘመናዊ መልኩ ቤቱ መሥራት ከመቻሉም በላይ አቅም በፈቀደ መጠን ተጨማሪ ረዳት አልባ አረጋውያንና ሕፃናት መርዳት ይቻላል፡፡

{flike}{plusone}

በሃይማኖት ሽፋን ቅ/ኤልያስ መጥቷል ብለው በኤልያስ ስም ሲነግዱ የነበሩ ግለሰቦች ንፁሀን ዜጎችን ሲያስደበድቡና ሁከት ሲፈጥሩ እጅ ከፍንጅ ተይዘው ታሰሩ

ቀደም ሲል በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ በተለያዩ የቤተክርስቲያኒቷ አገልጋዮች የተፃፉትን ጽሑፎች በአህጉረ ስብከታችን ዌብ ሳይት ስናስነብብ መቆየታችን አይዘነጋም፡፡

ምንም እንኳን ጉዳዩ ዘግይቶ በተለያዩ ሚዲያዎች መሰራጨት የጀመረ ቢሆንም ቀደም ሲል ከሁለት ዓመታት በፊት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጀርባ በተለምዶ ቆሎ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው መንደር ቤተክርስቲያኑንና ህብረተሰቡን ሲረብሹ የቆዩ ሲሆን የካቴድራሉ ጽ/ቤት ጉዳዩን እየባሰ ሲሄድ በመስከረም ወር 2ዐዐ5 ዓ.ም ጉዳዩ በፍርድ ቤት እንዲታይ ክስ መስርቶ በፍ/ቤት ትእዛዝ ግለሰቦቹ ከተከራዩት ቤት እንዲወጡና አከራዮችም ተከራዮቹ በአስቸኳይ እንዲያስወጡ ውሳኔ ተወስኖ ነበር፡፡

ይሁንና ግን በአፈፃፀም ሂደት የሚመለከታቸው አካላት እስከ አሁን ድረስ እልባት ባለማግኘቱ ካቴድራሉንና በካቴድራሉ ጀርባ ያሉ ነዋሪዎች ከመጠን በላይ ሲቸገሩ ቆይተዋል፡፡ ግለሰቦቹ መኖሪያ ቤታቸው የት እንደሆነ በእርግጠኛነት ማወቅ ባይቻልም ሁሉም የሚገናኙት ከሥላሴ ጀርባ በተከራዩት ቤት ነው የመገናኛ ሰዓታቸውም ከቀኑ በ11 ሰዓት እስከ ሌሊቱ 6፡3ዐ ነው፡፡

የተከራዩት ቤት መጠኗ አነስተኛ ብትሆንም እስከ 4ዐዐ የሚደርሱ ሰዎች ኃይማኖትን ይሁን ፖለቲካ፣ እብደት ይሁን ስካር ባልታወቀ ሁኔታ ከበሮ እየመቱ እጣን እያጨሱና መጠጥ እየጠጡ እንደሚያመሹ የሰፈሩ ሰዎች በግልጽ ከመናገራቸውም በላይ ከቅዳሜ በስተቀር ሁልጊዜ እዛው ቦታ ላይ የሚሰበሰብ ሲሆን ከቤቱ ጎን ያሉ ነዋሪዎች ማለፍ አትችሉም፣ ጫማችሁን አውልቁ ወዘተ እያሉ በሕገ መንግስቱ የተሰጣቸውን በሰላም የመኖር መብት ሲያሳጧቸው የቆዩ ከመሆናቸውም በላይ ይባስ ብሎ በ15/ዐ8/2ዐዐ5 ዓ.ም ከምሽቱ 2፡3ዐ ላይ እንደ ሰፈሩ ሰዎች አባባል ቁጥራቸው ከ5ዐ – 1ዐዐ የሚሆኑ በሰፈሩ ሰዎች ላይ ለማድረስ ጀምረውት የነበረውን የድብደባ ጥቃት በአካባቢ ባሉት የፖሊስና የመከላከያ ኃይል አማካይነት ጉዳቱ ሊቀንስ ቢችልም በዚሁ ዕለት ጉዳዩን በዋናነት ሲመሩ የተገኙት (የነበሩት)እጅ ከፍንጅ ተይዘው 4 ኪሎ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው ይገኛሉ፡፡ ቦታው ድረስ በአካል ሄደን ለማረጋገጥ እንደቻልነው 3 ሰዎች ተመትተው እቤታቸው ተኝተው አይተናል፡፡

የሚመለከታቸው የመንግስት አካላትም ቦታው ድረስ በመሄድ በጉዳዩ ላይ ከፍተኛ የሆነ ክትትል እያደረጉ ሲሆን የካቴድራሉ ጽ/ቤትም ከአሁን ቀደም ከቤቱ እንዲወጡ ፍ/ቤቱ የወሰነበትን ውሳኔ አያይዞ ለፖሊስ ጣቢያው ልኳል፡፡ የአካባቢው ማኀበረሰብም ፖሊስ ጣቢያው ድረስ በመሄድ ለዓመታት በዚሁ ችግር ሲኖሩ መቆየታቸውንና አሁን የደረሰባቸውን ችግር ገልፀው ክስ መስርተውባቸዋል፡፡

በመሆኑም የሚመለከታቸው የቤተክርስቲያኒቱ ባለድርሻ አካላት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር የቤተክርስቲኒቷን ስም በማጥፋታቸው በህግ መጠየቅ ይገባቸዋል እንላለን፡፡

“ተረፈ አይሁዳዊነት በኤልያሳዊነት ስም ሲበቅል” አዲስ ሃይማኖት

ሰሞኑን በከተማችን አዲስ አበባ ““የኢትዮጵያ ትንሳኤ ሊያረጋግጥ ኃያል ባለስልጣን ቅዱስ ኤልያስ ከብሔረ ሕያዋን መጥቷል፤ የአለም ፍጻሜ ቀርቧል” የሚሉ አካላት ተነስተዋል፡፡ እነሱ እንደሚሉት ነብዩ ኤልያስ መጥቶ አዲስ አበባ ይገኛል፡፡ ቤተመንግሥቱንና ቤተክህነቱን ለማጥራት ተዘጋጅቷል ፡፡ ከሚያጠራቸው የቤተክህነት ጉዳዮችም ሦስቱ ትኩረት አግኝተዋል ይላሉ፡፡ “የመጀመሪያው ኦርቶዶክስ የሚለው ስም ስህተት ነው ፤ ስማችን ተዋህዶ ነው ፤ መለበስ ያለበት ልብስ ነጭ ብቻ ነው ፤ እሱም ቢሆን ጥለቱ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ መሆን መቻል አለበት ፤ አሁን ያሰርነውን ክር በመበጠስ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ክር ማሰር አለብን” የሚል ነው፡፡

በየአጋጣሚው ቤተክህነቱንና ቤተ መንግሥትን በመንቀፍ አሁን የሚታዩትን ችግሮች መሰረት አድርጎ ህዝቡ መጥቷል የተባለው ኤልያስን መከተል እንጂ ወደ ቤተክርስቲያን መሄዱ ጥቅም እንደሌለው እየተነገረ ነው፡፡ የሚከናወኑ ማናቸውም የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችም የኤልያስን መምጣት የሚያመላቱ እንጂ ምዕመና ሊሳተፍባቸው የሚገቡ አለመሆናቸው ይነገራል ፡፡ እስኪ እነዚህ ነገሮችን በዝርዝር እንመልከታቸው፡፡

ኤልያስ ማነው?

ኤልያስ ማለት ከክርስቶስ ልደት በፊት በስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ ከእስራኤል የተነሳ ነብይ ነው፡፡ኤልያስ የሚታወቀው በሶስት ሃይማኖታዊ ተግባሮች ነው፡፡

የመጀመሪያው በእስራኤል ተንሰራፍቶ የነበረውን የባአድ አምልኮ ያጠፋና አምልኮተ እግዚአብሔርን ያጸና መሆኑ ሲሆን ፤ ሁለተኛው ደግሞ ንጉስ አክአብ አሕዛባዊት ኤልዛቤልን አግብቶ ይፈጽም የነበረውን ግፍና ጥፋት ሳይፈራና ሳያፍር ፊት ለፊት የገሰጸና ለእውነት ብቻ የቆመ ነብይ መሆኑ ነው፡፡ በዚህ አቋሙ ምክንያት በሰሜን እስራኤል በሚገኙ ሰንሰለታዊ ተራሮች ፈፋ ለፈፋ ሲንከራተት ኖሯል፡፡ መጀመሪያ ቁራዎች ሲመግቡት ቆይተው ከዚያ በሰራፕታ የምትገኝ አንዲት መበልት አገልግለዋለች፡፡ ይህ ቆራጥነቱና ለአምልኮተ እግዚአብሔር ቋሚ መሆኑ በእግዚአብሔር ዘንድ ባስገኝለት ሞገስ የተነሳ ኤልያስ ከኄኖክ ቀጥሎ ሳይሞት ወደ ብሔረ ሕያዋን በመወሰዱ ይታወቃል፡፡ ዮርዳኖስን ወንዝ ከደቀ መዝሙሩ ከኤልሳዕ ጋር ከተሻገረ በኋላ የእሳት ሰረገላ መጥቶ ኤልያስን ወስዶታል፡፡ ይህ ኤልያስ የሚታወቅበት ሦስኛው ነገር ነው፡፡

ኤልያስ ይመጣል ?

ከ470 እስከ 440 በኢየሩሳሌም ትንቢት የተናገረው ነብዩ ሚልኪያስ “የእግዚአብሔር ቀን ነብዩ ኤልያስን እልክላችኋለሁ” ብሎ ትንቢት ተናግሮ ነበር፡፡ (ሚል 4፤5) ይህንንም በመያዝ አይሁድ በፋሶች ፤ በግሪኮች ፤ በሶሪያውያንና በሮማውያን መከራ በተፈራረቁባቸው 400 ዓመታት ውስጥ ነብዩ ኤልያስን ሲጠባበቁት ነበር፡፡ በየምኩራባቸውም የኤልያስ መንበር የተባለ ከፍ ብሎ የተሰራ ባለ መከዳ ወንበር ያስቀምጡ ነበር፡፡ ከክርስቶስ ልደት 6 ወራት ቀድሞ ተወለደውና ከበረሀ የመጣው መጥምቁ ዮሐንስ በብዙ መልኩ ኤልያስን ይመስለው ስለነበረ የተወሰኑት የአይሁድ ክፍሎችና በኋላም ክርስቲያች ይመጣል የተባለው ነብዩ ኤልያስ እርሱ ነው ብለው ተቀብለውታል፡፡ ዮሐንስ መጥምቅ እንደ ኤልያስ ሁሉ በርኽኛ ባህታዊ ነው፡፡ እንደ ኤልያስ ሁሉ ጸጉር የለበሰ ነው ፤ እንደ ኤልያስ ሁሉ እስራኤል ተስፋ የቆረጠችበት ዘመን የመጣ ነው ፤ እንደ ኤልያስ ሁሉ ሄሮድስን ሳያፍርና ሳይፈራ የገሰጸ ነው ፡፡ በእነዚህ እና በሌሎች ምክንያቶች መጥምቁ ዮሐንስ ኤልያስን ይመስለው ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ይመጣል የተባለው ኤልያስ መጥምቁ ዮሐንስ መሆኑን መስክሮለታል፡፡(ማቴ 11፤14 17፤10-13 ፤ ሉቃ 1፤17) ስለ ኤልያስ መምጣት የሚነግረን ሌላው መጽሀፍ የዮሐንስ ራዕይ ነው፡፡

ዮሐንስ ራዕይ በምዕራፍ 11 ላይ ዓለምን የሚያጠፋው ሀሳዊ መሲህ ከመጣ በኋላ ዙፋኑን አደላድሎ የዓለምን ክርስቲያኖች ሲጨርስና ምስክር ሲጠፋ ሁለት ምስክሮች መጥተው 1260 ቀናት ምስክርነት እንደሚሰጡና በመጨረሻም በሐሳዌ መሲህ እንደሚገደሉ ይገልጣል፡፡ ከሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ የተነሱ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እነዚህን ሁለት ምስክሮች ኄኖክና ኤልያስ መሆናቸውን ተርጉመዋል፡፡ ሐሳዊ መሲሕ ሲነሳና ሁሉንም እንደ ሰም አቅልጦ እንደ ገል ቀጥቅጦ ሲያጠፋ ፤ ለእውነት የሚመሰክርም ሲጠፋ ፤ ምዕመናንም በሚደርሰው መከራ ምክንያት የሚከተሉት የእምነት መንገድ “ስህተት ይሆን…” ብለው ሲጠራጠሩ እነዚህ ሁለቱ ሳይሞቱ ወደ ብሔረ ሕያዋን ያረጉ ነብያት መጥተው እውነትን በመመስከርና የሐሳዌ መሲሕን ነገር በማጋለጥ ምስክርነታቸውን በደም እንደሚያጸኑ የሊቃውንቱ ትርጓሜ ያብራራል፡፡ ዮሐንስ አፈወርቅ ፤ አቡሊዲስ ዘሮምና ቪክቶሪያንስ እንደሚገልጡት ኤልያስና ኄኖክ በኢየሩሳሌም ያስተምራሉ ፤ በኢየሩሳሌም ተዓምራት ያደርጋሉ ፤ በኢየሩሳሌም ይገደላሉ ፤ በኢየሩሳሌም ይነሳሉ ፤ በኢየሩሳሌም ያርጋሉ ፡፡ ይህም ለጌታችን መምጣት የመጨረሻው ምልክት ነው፡፡ ከኤልያስና ኄኖክ መምጣት በኋላ የሚጠበቀው የክርስቶስ ለፍርድ መምጣት ነው፡፡

በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ነብዩ ኤልያስ መጥቷል ይባላል፡፡ የሚኖረው አራት ኪሎ ነው፡፡ አንዳንድ ታዋቂ የሆኑ ሰዎች በተለይም አርቲስቶች ተከታዮች ሆነናል ይላሉ፡፡ ይህንን ሁኔታ ከቅዱሳት መጻህፍትና ከሊቃውንት ትምህርት ጋር ስናነጻጽረው ትክክል ሆኖ አናገኝውም፡፡ መጀመሪያ ነገር ኤልያስ ብቻውን አይመጣም፡፡

በነብዩ ሚልኪያስ ለብቻው እንደሚመጣ የተነገረለት ኤልያስ መጥምቁ ዮሐንስ መሆኑን ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ስለ መሰከረ ሌላ ምስክር ማምጣት አያስፈልግም፡፡ በሌላ በኩልም አሁን መጥቷል ተባለው በመጨረሻው ዘመን የሚመጣው ኤልያስ ከሆነ ደግሞ እንደ ሊቃውንቱ ትምህርት ብቻውን አይመጣም ፤ አብሮት ኄኖክም ይመጣል፡፡ አሁን ግን ኤልያስ ከኄኖክ ተነጥሎ ነው መጣ የተባለው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ነብዩ ኤልያስ የሚመጣበት ጊዜ በራዕይ ዮሐንስ ላይ ምዕራፍ 11 ተገልጧል፡፡

አስቀድሞ ሐሳዊ መሲህ ይመጣል፡፡ ዙፋኑንም በተቀደሰችው ከተማ በኢየሩሳሌም ይዘረጋል፡፡ ምዕመናንም(በተለይም የስድስት ስድሳ ስድስትን አምልኮ ያልተቀበሉትን) በግፍ ይገድላቸዋል፡፡ በዚህም ጊዜ እውነት ትቀጥንና ምስክር ታጣለች ፤ ኤልያስና ኄኖክ የሚመጡትም እውነትን በአደባባይ ለመመስከር ነው፡ ይህ ከሆነና በአዲስ አበባ እየተባለ እንዳለው ኤልያስ ከመጣ ሐሳዊ መሲህ መጥቷል ማለት ነው፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ምዕመናን በግፍ ተገድለዋል ፤ በዓለምም ላይ አማኞች በአብዛኛው አልቀዋል ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሲፈጸም አላየነውም፡፡ በኢየሩሳሌምም ሐሳዊ መሲህ ገና አልነገሰም፡፡ ሌላም ሦስተኛ ነገር መነሳት አለበት፡፡ ሐሳዊ መሲሕ የሚነግሠው ፤ ኄኖክና ኤልያስም የሚገለጡት ‹በተቀደሰችው ከተማ” በኢየሩሳሌም ነው፡፡ የሚሠውትም እዚያ መሆኑን “እርስዋም በመንፈሳዊ ምሳሌ ሶዶምና ግብጽ የተባለችው ደግሞ ጌታችን የተሰቀለባት ናት› ብሎ ኢየሩሳሌም መሆኗን ነግሮናል(ራዕይ 11፤8) ፡፡ አሁን ግን ኤልያስ ተገለጠ የተባለው ያለው አዲስ አበባ አራት ኪሎ ላይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ተልዕኮውም ከመጽሀፍት ጋር የሚጣረስ ነው፡፡

ጌታ የተሰቀለው አራት ኪሎ ነው ካላልን በቀር፡፡ ራዕይ ዮሐንስ እንደሚነግረን ኄኖክና ኤልያስ ምስክርነት የሚሰጡት ለ1260 ቀናት ወይም ለ42 ወራት ወይም ለሦስት ዓመት ከስድስት ወራት ነው፡፡ አሁን ግን አዲስ አበባ መጣ የተባለው ኤልያስ መጣ ከተባለ አራት ዓመት ሊያልፈው ነው፡፡

ምጽአትና መሲሕን መናፈቅ

በዓለም ሆነ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የምጽአትን ቀን የመናፈቅና የምጽአትን ምልክቶች ደርሰዋል ብሎ የመጨነቅ አዝማሚያ የሚከሰትባቸው ምክንያቶች አሉ፡፡ እነዚህም ኢኮኖሚያዊ ፤ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውሶች ሲከሰቱና ሕዝብ ተስፋ ሲቆርጥ ነው፡፡ እስራኤራዊያን ከፋርሶችና ከግሪኮች ወረራ በኋላ ሀገራቸው ስትመሰቃቀል ፤ መንፈሳዊነት ሲጎድልና መንግሥታቸው ፈርሶ ተስፋ ወደ መቁረጥ ሲመጡ “መሲሕ እየመጣ ነው ፤ ኤልያስ እየደረሰ ነው” የሚል አስተምህሮ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በ2ኛው መቶ ክፍተ ዘመን ጀምረው ነበር፡፡

በዚህ የተነሳ አንዳንድ ሰዎች ይመጣል የተባለው መሲሕና ኤልያስ እኛ ነን እያሉ አጋጣሚውን ሊጠቀሙበት ሞክረው ነበር፡፡ ከእነዚህ መካከል ከክርስቶስ ልደት በፊት በ2ኛውና አንደኛው መ.ክ.ዘ ላይ የተነሱ ቴዎዳስና ይሁዳ ይጠቀሳሉ፡፡ ቴዎዳስ አራት መቶ ሰዎችን አስከትሎ ነበር ፡፡ በኋላ ግን ሐሰተኛ መሆኑ ሲታወቅ ሕዝቡ ተወው ፡፡ ይሁዳም ሕዝቡን አስነስቶ እስከ ማሸፈት ደርሶ ነበር፡፡ መጨረሻው ግን አላማረም(የሐዋ 5፤37-39) በቅርብ ጊዜ በኡጋንዳ ኢኮኖሚ ሰደቅና የእርስ በርስ ጦርነት ሲባባስ ይህም የሕዝቡ ማኅበራዊ ሕይወት ሲያቃውሰው “እኔ ክርስቶስ ነኝ” የሚል ሰው ተነስቶ በአንድ አዳራሽ ውስጥ የነበሩ ተከታዮች መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ሲሉ በእሳት ተቃጥለው እንዲያልቁ አድርጓቸው ነበር፡፡ በአሜሪካ የደረሰው ኢኮኖሚ ድቀት ካስከተላቸው መዘዞች አንዱ በየአካባቢ “እኔ መሲሕ ነኝ” የሚሉ እና ሕዝቡ ችግሩን ከማሸነፍ ይልቅ ችግሩን እንዲረሳው የሚያደርጉ ሰዎች መከሰታቸው ነው፡፡ በ2012 የተደረሰ አንድ ጥናት ባለፉት 3 ዓመታት በአሜሪካ ውስጥ 132 ሰዎች መሲሕ ነን ብለው ተነስተው ወደ 4.5 ሚሊየን የሚደርስ ሕዝብ አስከትለዋል፡፡ በሀገራችን ታሪክ በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በተከሰተው የግራኝ ጦርነት በኋላ ሕዝቡ መንፈሳዊ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተስፋ መቁረጥ ደረጃ ደርሶ ነበር፡፡

አብያተ ክርስያናቱ ተቃጠሉ ፤ ኢኮኖሚው ወደመ ፤ መንግስት ተዳከመ ፤ ትዳና መስተጋብር የመሰሉ ማኅበራዊ ተቋማት ፈረሱ፡፡ ብዙ ሰዎች ሞቱ ፡፡ ይህ ሕዝቡ ላይ ባስከተለው ተስፋ መቁረጥ የተነሳ ከዚህ መከራ እና ስቃይ የሚያወጣውን አንዳች ሰማያዊ ኃይል ይጠብቅ ነበር፡፡ ከግራኝ ጦርነት በኋላ በአጼ ሰርጸ ድንግል ወራሾች መካከል በተፈጠረው የርስ በርስ ውጊያ ሀገሪቱ ስትታመስና ሕዝቡ በተደጋጋሚ ጦርነትና የሕዝብ ፍልሰት ሲታወክ እኔ ክርስቶስ ነኝ ፤ ሕዝቡንም ከችግር ላወጣውና መንግሥተ ሰማያት ላወርሰው መጥቻለሁ የሚል ሐሳዊ መሲሕ በአማራ ሳይንት አካባቢ ተነስቶ ነበር ፡፡ አስራ ሁለት ሐዋርያት ፤ 72 አርእድትንና 36 ቅዱሳት አንስትንም መርጦ ነበር፡፡ ብዙውም ሕዝብ በተስፋ መቁረጥ ላይ ስለነበረ ተከትሎት ነበር፡፡ በኋላ ግን በሞት መቀጣቱን አቡነ ጎርጎርዮስ በኢትዮጰያ ቤተክርስቲያን ታሪክ መጽሐፋቸው ጠቅሰውታል፡፡

በቅርቡ በሀገራችን ታሪክ ዐጼ ምኒሊክ አርፈው ሞታቸው በተደበቀበት ጊዜ ፤ በታህሳስ ግርግር ጊዜ ፤ በአብዮቱ ዋዜማና ማግስት ፤ እንዲሁም ኢሕአዴግ አዲስ አበባ በገባበት ጊዜ አያሌ “ባሕታውያን” ተነስተው ነበር፡፡ ይህ ነገር መጣ ፤ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ስለ ንግሥት ዘውዲቱ ዘመን በጻፉት የትዝታ መጽሀፋቸውም ይህንን ገልጠውታል፡ ይህም ያም ነገር ታየ ፤ ተገለጠ የሚለው ብሂልም ነባርና የሀገር አለመረጋጋትና በኑሮ ተስፋ መቁረጥ ተገን አድርገው የሚመጡ ናቸው፡፡

የኤልያሳውያን ሁለት አስተምህሮዎች

አሁን በዘመናችን የተከሰቱ ኤልያሳውያን ሁለት ነገሮች ላይ አተኩረው እየሰሩ ነው፡፡ የመጀመሪያው “ኦርቶዶክስ” ትክክለኛ ስም አይደለም የሚለው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሰንደቅ አላማን ከጽድቅና ከኩነኔ ጋር ማያያዛቸው ነው፡፡ ኦርቶዶክስ የሚለው ቃል የግሪክ ሲሆን “ኦርቶ” ርቱዕ “ዶክስ” ደግሞ እምነት ፤ መንገድ ፤ ጠባይ ፤ ባህል ማለት ነው፡፡ ይህንን ስም የክርስቲያን አብያ ክርስያናት መጠቀም የጀመሩት በ325 ዓ.ም በተደረገው ጉባኤ በኋላ ነው፡፡ ከጉባኤ ኬልቄዶን የ451 ዓ.ም ጉባኤ በኋላ ደግሞ የምዕራብ አብያተክርስቲያናት ካቶሊክ ሲባሉ ምስራቆቹ “ኦርቶዶክስ” የሚለውን ስም ይዘው ቀሩ ፡፡ በምስራቆቹ መካከል የጉባኤ ኬልቄዶንን ውሳኔ በመቀበልና ባለመቀበል መካከል ልዩነት ስላለ የግሪክ መሰል አብያተክርስቲያናት የምስራቅ ኦርቶዶክስ ሲባሉ ፤ አርመን ፤ ግብጽ ፤ ሕንድ ፤ ሶሪያና ኢትዮጵያ ደግሞ “ኦሪየንታል ኦርቶዶክስ” ተባሉ፡፡ ኦርቶዶክስ ፤ ኦርዶክሳዊ የሚለው ስም በሀገራችን ቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ በሁለት መንገድ ተገልጠዋል፡፡ በአንድ በኩል ጥሬ ቃሉ እንዳለ የተቀመጠ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ወደ ግዕዙ ተተርጉሞ “ርቱዕ ሃይማኖት” እየተባለ ተቀምጧል፡፡ ፍትሐ ነገስት ‹ይኩን ምእመነ ኦርቶዶክሳዌ ይላል› (42፤2) ያዕቆብ ዘእልበረዲም ‹ሃይማኖት ኦርዶክሳዊት› ሲል እምነቱን ይገልጣል፡፡ መጽሐፈ ቄርሎስም ‹ሃይማኖተ ርቱዕ› እያለ ተርጉሞ ይገልጠዋል፡፡ ‹ተዋሕዶ› የሚለው ቃል ነጥሮ የወጣው በጉባኤ ኤፌሶን በ431 ዓ.ም ነው፡፡ በጉባኤው ንስጥሮስን ባሕል ለማየት የተሰበሰቡ አበው በእስክንድርያ ቄርሎስ የተሰጠውን ትምህርት በመቀበል ሁለት ባሕርይ የሚለውን አውግዘው መለኮት ከስጋ ተዋህዶ ሥግው ቃል ሆነ የሚለው ርቱዕ እምነት መሆኑን መሰከሩ፡፡

ይህ ቃል የእምነት ዶክትሪን መገለጫ ሆኖ ነው የኖረው ፡፡ በኬልቄዶን ጉባኤ በኋላም ይህ ስያሜ የኦርቶዶክሶቹ ዋና መጠሪያ እየሆነ መጣ፡፡ በኢትዮጵያ ጥንታዊ መጻሕፍት ላይ ተዋህዶ እምነት ሆኖ እንጂ የቤተክርስቲያ መጠሪያ ሆኖ አናገኝውም ‹ኦርቶዶክሳዊ› የሚለው ቃል የምናገኝውን ያህል ‹ተዋህዶ› የሚል መገለጫ አናገኝም ተዋሕዶ የሚለው ቃል በነገረ ሥጋዌ ትምህርት ላይ በሀገር ውስጥ የተነሳ የተለየ አስተያየት ስላልነበረ መጠሪያነቱ አልጎላም፡፡ በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከአውሮፓ በመጡ ካቶሊካውያን ምክንያት የተፈጠረውን የእምነት ክፍፍል ተከትሎ ይህ የእምት መጠሪያ የአማያንና የወገን መጠሪያ እየሆነ መጣ፡፡ በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቅባትና ጸጋ የሚባሉ ባሕሎች መጥተው ነበር፡፡ እነዚህን ባሕሎች የሚቃወሙትና ኢየሱስ ክርስስ መለኮት ከስጋ በተዋሕዶ ሥግው ቃል እንጂ እንደ ነገስታትና ነቢያት በመቀባት አይደለም ያሉት ደግሞ መጠሪያቸው ከእምነታቸው ተወስዶ “ተዋሕዶዎች” ተባሉ፡፡ ከቦሩ ሜዳ ጉባኤ በኋላም የቤተክርስቲያኒቱ ሕጋዊ ስም ‹‹ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ›› የሚለው ጎላ፡፡ ኦርቶዶክስ የሚለው ስም ቤተክርስቲያኒቱ በዓለም የምትታወቅበት የወገን ስሟ ነው፡፡ ሌሎችም ‹የግብጽ ኦርቶዶክስ› ፤ ‹ የሕንድ ኦርቶዶክስ› ብለው ይጠሩ እና ከአካባቢያቸው ራሳቸውን ለመለየት ደግሞ ‹የግብጽ ኮፕት ኦርቶዶክስ› ፤ ‹የሶርያ ያዕቆባዊት ኦርቶዶክስ› እያሉ ይጠራሉ፡፡ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንም ‹ኦርዶክስ ተዋሕዶ› ትባላለች ፡፡ አንዳንድ ሰዎች በዘመናውያን መዛግብት ቃላት ስለ ‹ኦርቶዶክስ› የተሰጡ ፍቺዎችን ይዘው ይሞግታሉ፡፡ ኦርቶዶክስን ‹ከአክራሪነትና ከለውጥ አለመቀበል› ጋር እያዛመዱ ይፈቱታል፡፡ በዚህ ምክንያት ኦርቶዶክስ የሚለው ቃል ለኮንሰርቫቲቭ ፓርቲዎችና ለአይሁድ ሲሰጡት ይታያሉ፡፡ ይህ ግን ኦርቶዶክስ የሚለው ስም ከመነጨበት ጠባይ በእጅጉ የራቀ ነው፡፡

አሁን ወደ ሁለተኛ ነጥብ እንመለስና ሰንደቅ አላማን እንመልከት፡፡ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ የኢትዮጵያውያን መለያ ናት፡፡ ለዚች ሰንደቅ አላማ ብዙዎች ውድ ሕይወታቸውን ከፍለዋል፡፡ ከእነዚህ ውድ ሕይወታቸውን ከከፈሉ መካከልም የቤተክርስቲያኒቱ አባቶችና ልጆች ይገኙበታል፡፡ ቤተክርስቲያኒቱ ታሪክን ከማቆየት ፤ ባሕልን ከማሻገርና ኢትዮጵያዊነትን ከማስረጽ ሚናዋ አንጻር ሰንደቅ አላማንም በማስከበርና ለትውልድ በማስተላለፍ የበኩሏን ድርሻ ተወጥታለች፡፡ የኢትዮጵያ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ አላማ ከሀገራዊ እሴትነቱ ፤ መስዕዋትነትና ነጻነት ከማንጸባረቁም ፤ ለኢትዮጵያውያን ከደማቸው ጋር የተዋህዶ ልዩ ምልክት ከመሆን አልፎ ግን ጽድቅና ኩነኔ ውስጥ የሚገባ ፤ እርሱን ያልተቀበለ እና ያላደረገ ሰማያዊ ዋጋ የሚቀርበት ፤ ከእርሱ ውጪ ቀለም ያለው ነገር የለበሰና ማህተብ ያሰረ ሃጥያት እንደሰራ ተቆጥሮ ንስሃ የሚገባበት ግን አይደለም፡፡

ከኢትዮጵያ ውጪ ያለ ዜጋ የቤተክርስቲያኒቱ አባል ለመሆን የቤተክርስቲያቱን ዶግማ እና ቀኖና መቀበልን እንጂ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራን መቀበል ግዴታው አይደለም፡፡ በኡጋንዳ ባንዲራ ፤ በአሜሪካ ባንዲራ ፤ በሶማሊያ ባንዲራ አሸብርቆም ቢሆን የኦርዶክስ ተዋሕዶ ልጅ መሆን ይችላል፡፡ አስከ አሁን በቀኖና በሚደነገጉ መጻህፍቶች ውስጥ ሰንደቅ አላማን የተመለከተ ቀኖና የለንም፡፡ በመሆኑም ሰንደቅ አላማችን ከኢትዮጵያዊነታችን ጋር እንጂ ከኦርቶዶክስ እምነታችን ጋር የታሪክ እንጂ የድኅነት ተዛምዶ የለውም፡፡ እንደዚህ አይነት አመለካከቶች የሚያይሉት እንዲሁ አይደለም፡፡ በሕዝቡ ዘንድ ኢትዮጵያዊ ስሜት ደብዝዟል ፤ ለሰንደቅ አላማና ለሀገራ እሴቶች የሚሰጠው ዋጋ ቀንሷል ተብሎ ሲታሰብ ሰንደቅ አላማን የመሰሉ ሀገራዊ እሴቶች ጉልበት ያገኙ ዘንድ ተጨማሪ ሃይማኖታዊ ኃይል ይሰጣቸዋል፡፡ ቤተክርስቲያቱ የሰንደቅ አላማን ክብርና ትርጉም ማስተማርዋ እና በትውልድ ውስጥ ማስረጿ ባልከፋ ፡፡ አስተምህሮ ግን ከሀገራዊ ግዴታ የሚመጣ እንጂ ከሃይማኖታዊ ግዴታ የሚመጣ መሆን የለበትም፡፡ ከሕዝብ እሴቶች እንደ አንዱ ሆኖ እንጂ ከጽድቅና ኩነኔ ጋር መሆን ለበትም፡፡

ምን ይደረግ ?

የሃይማኖት ትምህርት በሚገባ መሰጠት ሲያቆምና ሰዎችም በተደላደለው እምነት መንገድ ላይ በእውቀትና በእምነት እየተመሩ መጓዝ ሳይችሉ ሲቀሩ ‹ባለ ተስፋዎች ይሆናሉ› ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች በላከው መልዕክቱ መጀመሪያ ላይ ‹በኤፌሶን ላሉት ቅዱሳን ፤ በክርስቶስ ኢየሱስ ባሉት ምዕመናን› በማለት የገለጠው አባባል ታላቅ ነገር አለው፡፡ ምእመናኑ በሁለት ዓለም መኖራቸውን እንዳይረሱ ለማድረግ ነው፡፡ ‹በክርስቶስና በኤፌሶን› ክርስቲያችም ምድራዊነታቸውንም ሰማያዊነታቸውንም መርሳት የለባቸውም፡፡

አንዳንድ ጊዜ ግን ምድራዊ ጎዳና ሲያቅተንና ፈተና ሲበዛበት ፤ የኢኮኖሚ የፖለቲካ ሁኔታ አልቃና ሲል ፤ የምናየው የምንሰማው ተስፋ ሲያሳጣን ፤ ምድር ላይ መሆናችንን ፈጽመን ረስተን ኅሊናችን ወደሚፈጥረው ልዩ አለም እንገባለን፡፡ ያንንም እጅግ ከመመኝታችን የተነሳ የደረስንበት ይመስለናል፡፡ በዚህ ጊዜ የሚሰጡ ትምህርቶች ለሰዎች ቀላል የሆኑ ፤ ንባብና ትምህርትን የማይጠይቁ ፤ በቀላሉ የሚተገበሩ ፤ የሚነኩና የሚዳሰሱ ይሆናሉ፡፡ ቡና መጠጣት አለመጠጣት ፤ አረንጓዴ ቢጫ ክር ማሰር አለማሰር ፤ በባዶ እግር መሄድ አለመሄድ ፤ ጸጉርን ማስረዘም አለማስረዘም ፤ መቁጠሪያ አለስርዓቱ ማሰር አለማሰር ፤ ከመምህራን ቃል ይልቅ የሰይጣንን ቃል መቀበልና ማመን እየሰለጡ ይመጣሉ፡፡

ለዚህ ትልቁ መፍትሔው የእምነት ተቋማት የራሳቸውን ሥራ (ወንጌል ማስተማር) ትተው በሰዎች ስራ ውስጥ መግባታቸው ነው፡፡ ስለዚህ ተቋማቱ መጀመሪያ ራሳቸውን ወደ ተልዕኳው መልሰው ፤ የማይጨበጥ ተስፋ የሚዋልለውን ሕዝብንም ወደ ትክክለኛ ኑሮ እና ተስፋ መመለስ አለባቸው፡፡ እዚህ ኤልያስ ነኝ ፤ እዚያ ድንግል ማርያም ነኝ ፤ እዚያ አቡዬ ነኝ የሚሉ በተነሱ ቁጥር ሕዝቡ ስራና ትዳር ፈትቶ ተንከራቶ አይዘልቀውም፡፡ ይህ አዲስ እንቅስቃሴ ለምእመናኑ የተለየ ፋይዳ ይዞ አልመጣም፡፡

በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴደራል ሁለተኛና መሰናዶ ት/ቤት ዓመታዊ የእግር ኳስ ስፖርት ውድድር ተካሄደ

ጨዋታው በሁለት ምድብ ተከፍሎ በሁለተኛና መሰናዶ ተማሪዎች መካከል በወንዶችና በሴቶች በ21 ሴክሽን መካከል የተካሄደ ሲሆን ይኸውም ዘጠኝ ሴክሽን የሁተለኛ መሰናዶ ተማሪዎች ሲሆኑ 12 ሴክሸን ደግሞ የመሰናዶ ተማሪዎች ናቸው፡፡

በዚሁም መሠረት የሁለተኛ ደረጃ የዘጠኝ ሴክሸን አሸናፊ የ1ዐA ክፍሎች ተማሪዎች ሲሆኑ የ12 ሴክሽን አሸናፊ 12B ክፍል ተማሪዎች ናቸው፡፡ በዚህ ውጤት መሠረት የ1ዐA አንድ ዋንጫና የ3ዐዐዐ ብር ተሸላሚ ሲሆኑ የ11ኛ እና 12ኛ ክፍል አሸነፊዋች የ12B ክፍል የ12ዐዐ.ዐዐ ብር እና በመሰናዶ ት/ቤቱ ስም የአንድ ዋንጫ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

በዚህ ውጤት መሠረት የሁለተኛ ደረጃ ተመሪዎችን ወክለው የተጫወቱት የ1ዐA ክፍል ተማሪዎች የ12B ክፍልን 5 ለ 1 በሆነ ውጤት የአሻናፊዎች አሸናፊ በመሆን የ2ዐዐ5 ዓ/ም የሁለት ዋንጫ ተሸላሚ በመሆን በት/ቤቱ ውስጥ መምህራንና ተማሪዎች በአንድ ላይ በመሆን ደስታቸውን ኬክ በመቁርስ ለትምህርት ቤቱ ማኅበረ ሰብና ለተማሪዎች ደስታቸውን ገልጸዋል ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የወንዶች ኮካብ ተሸላሚ የሚካኤል አረጋይ 12c ክፍል የ100 ብር ተሸላሚ ሲሆን ኮከብ ተጨዋች ቢኒያም ኑር የ100 ብር ሲሆን ኮካብ ተጨዋች ሴቶች ከ12B ክፍል ኪብሩን ተሻገር የ100 ብር ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

የፀባይ ዋንጫ ተጨዋች የ11ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው፡፡ በሴቶች በሁለኛና በመሰናዶ ተማሪዎች የእግር ኳስ ጨዋታ የመሰናዶ ተማሪዎች ሁለት ለባዶ በሆነ ውጤት ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን አሸንፈዋል፡፡ በዚሁ ውጤት የመሰናዶ ሴት ተማሪዎች አንድ ዋንጫ አንስተዋል እንዲሁም የቅርጫት ኳስ ውድድር በ12D ክፍል የሁለተኛ ደረጃና የመሰናዶ ተማሪዎች በመሸነፍ የዓመቱ የአሸናፊ አሸናፊ አንድ ዋንጫ አግኝተዋል፡፡

በዚሁ ዕለቱ የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አስተዳደር፤ የክፍለ ከተማ የስፖርት ክፍል ኃላፊ ፤የተለያዩ የካቴድራሉ ሠራተኞች፤ የት/ቤቱ የአስተዳደር ሠራተኞችና መምህራን እንዲሁም ተማሪዎች በተገኙበት የአምስት ዋንጫና የ8ዐዐ.ዐዐ ብር የገንዘብ መበረታቻ ሽልማት ለተማሪዎች በክቡር ሊቀ ሥልጣናት አባ ገ/ሥላሴ በላይ የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዋና አስተዳዳሪ አማካኝነት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል ፡፡

በሌላ ዜና በክፍለ ከተማ ደረጃ በተዘጋጀው የተማሪዎች የፈጠራ ውድድር የካቴድራሉ የ1ኛ ደረጃ ተማሪዎች በፈጠራ ሥራ 2ኛ ደረጃ በመውጣት የዋንጫ ተሸላሚ ሲሆኑ እንደዚሁም በክፍለ ከተማ ደረጃ በተዘጋጀው የተማሪዎች ጥያቄና መልስ ውድድር በ8ኛ 3ኛ እና በ4ኛ ክፍል 2 ደረጃ ወጥተዋል፡፡ ይህም ት/ቤቱ ምን ያህል ውጤታማ ተማሪዎች እያፈራ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡

0020

በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል መሠረታዊ የኮምፒውተር አጠቃቀም ሥልጠና ተጀመረ

0020
የካቴድራሉ ሠራተኞች ሥልጠናውን ሲከታተሉ

በሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በካቴድራሉ አስተዳደር አማካኝነት መሠረታዊ የኮምፒውተር ትምህርት /ሥልጠና በካቴድራሉ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ለካቴድራሉ ጽ/ቤት ሠራተኞች እና ለተወሰኑ ማህበረ ካህናት ከመጋቢት 20/07/2005 ዓ.ም ጀምሮ ሥልጠናው በመካሄድ ላይ ነው፡፡

የሥልጠናው ዋና አስተባባሪ መ/ር ዘሩ ብርሃኔ እንደተናገሩት፤ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ትምህርት ማስተማር ዘመኑን የዋጀ መንፈሳዊና መኅበራዊ አገልግሎት መስጠት ያስችላል በመሆኑም ትምህርቱን እየተከታተሉ ያሉ የከቴድራሉ ሠራተኞች በኮምፒውተር ትምህርት መሠልጠናቸው የመረጃ ሥርዓትና ተዛማጅ ሥራዎች በዘመናዊ መልክ ለማከናወን እንደሚያግዛቸውም ተናግረዋል፡፡ የካቴድራሉ ጽ/ቤት ሥልጠናውን አዘጋጅቶ የካቴድራሉ አባቶች ካህናትና የጽ/ቤት ሠራተኞች በአንድነት እንዲሠለጥኑ ማድረጉ ቤተ ክርስቲያንን በልማት ለማሳደግ ያለውን ርእይ እንደሚያሳይ ጠቁመው፤ ወደፊትም የተለያዩ ሲስተሞችን ለምሳሌ

 • የሰበካ ጉባኤ አባላት መመዝገቢያ ሶፍት ዌር፣
 • የመዝገብ ቤት ፋይል መያዣ ዳታ ቤዝ ሶፍት ዌር፣
 • ኤች አር ሲስተም/HRS/፣
 • እስታስቲካዊ የሆኑ የጋብቻ፣
 • የልደት እና የመሳሰሉ ሲስተሞችን አዘጋጅቶ ሠራተኞች በቀላሉ መደበኛ ሥራቸውን በፍጥነትና በጥራት ማከናወን እንዲቺሉ በባለሞያዎች ሥልጠና ሊሰጥ እንደሚቺል ተናግረዋል ፡፡

የመጀመሪያውን ዙር መሠረታዊ የኮምፒዩተር ሥልጠና እየተከታተሉት ያለው ሥልጠና/ የትምህርት ዓይነት

 • አጠቃላይ ስለ ኮምፒዩተር መግቢያ /Introduction to computer/IT
 • ኤም ኤስ ዊንዶውስ (Ms-wodows /Window XP /7)
 • ማክሮሶፍት ወርድ 2007/10/ Micro soft office word 2007/10
 • ማይክሮሶፍት ኤክሲኤል 2007/10/ Micro soft office excel 2007/10
 • ማይክሮሶፍት አክሰስ 2007/10/ Micro soft office access 2007/10
 • ማይክሮሶፍት ፓወር ፖይንት 2007/10/ Micro soft office PowerPoint 2007/10
 • ማይክሮሶፍት ፐብሊሸር 2007/10/ Micro soft office publisher 2007/10
 • የኢንተርኔት አጠቃቀምና
 • አጠቃላይ ቴክኖሎጀው ለቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊና መኅበራዊ አገልግሎት ያለው ጠቀሜታ የተመለከተ መሆኑን አስተባባሪ ጠቁሞው፣ ሥልጠናው ሠራተኞች አገልግሎታቸውን በተቀላጠፈ ሁኔታ ለመሥራት እንደሚረዳ እና በአጣቃላይ ዘመኑ/ትክኖሎጂው የደረሰበትን ደረጃ እና የአሰራር ሄደት ለሠራተኞች በወቅቱና በሰዓቱ ማስተዋወቁ ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ሥልጠናውን ለ2 ወራት ያህል እየሰጡ ያሉት አሠልጣኞች በአሁኑ ጊዜ በኮምፒዩተር ሳይንስ/በአይቲ ሙያ በተለያዩ ተቋማት የሚያስተምሩ/የሚሠሩ አባላት እንደሆኑ አስተባባሪው አስረድቷል፡፡ ለወደፊትም ሥልጠናውን ከካቴድራሉ በተጨማሪ ወደ ሌሎች መሰል አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት እና መሥራቤቶች በመሔድ ለሚመለከታቸው ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሠረተኞች ይህን የመሰል ሥልጠና መስጠቱ ተገቢ መሆኑን ጨምረው ገልፀዋል፡፡

የኮምፒዩተር ሥልጠናው ካለቀ በኋላም በሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ሲፈቀድ ሌሎች ሥልጠናዎች ማለትም የአስተዳደር እና የሒሳብ አያያዝ ሥልጠናዎች በካቴድራሉ ሊሰጡ እንደሚቺሉ ጠቁመዋል፡፡

የካቴድራሉ አስተዳደር ቀደም ሲል ከ2 ዓመት በፊት ዘመናዊ ድረ ገጽ/ዌብ ሳይት ያሰራ ሲሆን ከ3 ዓመት በፊት በ2ኛ ደረጃ ት/ቤት አገልግሎት በመስጠት ላይ ያለው የብሮድ ባንድ ኢንተርኔት ከካቴድራሉ ጋር ከ500 ሜትር በላይ የሆነውን ርቀት በኔትዎረክ በማገኛት በአሁኑ ሰዓት የካቴድራሉ ጽ/ቤት ሙሉ በሙሉ የብሮድ ብንድ ኢንተርኔት አገልግሎት ለሠራተኞች መስጠት መጀመሩ አስተዳደሩን እጅግ የሚያስመሰገን የሥራ ውጤት ነው፡፡

ይህም ካቴድራሉን ጨምሮ የካቴድራሉን ሙዝዬም፤የካቴድራሉ ዘመናዊ ት/ቤት በማስተዋወቅ እና ካቴድራሉ በልማቱ በኩል ለሚያደርው እንቀስቃሴ በመላው ዓለም ላይ ከሚገኙ የዕምነቱ ተከታዮች ምዕመናን ጋር እንደ አንድ ሚዲያ ሆኖ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት በመስጠት ላይ ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ቴክኖሎጂ የካቴድራሉ አስተዳደር በቀላሉ ት/ቤቱን ለመቆጣጠር፤መረጃን በቀላሉ ለመለዋጥ እና ፕሪንተርና የመሳሰሉትን ሼር ለመድረግ እንዲሁም የሠረተኛውን አቅም በመገንበታ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡

በሌላ ዜና የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን መጋቢት 18 እና 19 ቀን 2005 ዓ.ም በጊዮን ሆቴል ለ318 በአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሥር ለሚሠሩ ሰባኪያነ ወንግል በሙስና ዙሪያ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና ሰባኪያነ ወንጌሉ ሙስናን በመከላከል ረገድ በሕብረተ ሰቡ ውስጥ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ የ2 ቀን ሙሉ ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡

0030

በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል መሰናዶ እና 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ከወላጆች ጋር በመማር መስተማር ሄደት ላይ ውይይት ተካሄደ

                                          በመ/ር ዘሩ ብርሃኔ

0030

የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል 1ኛና 2ኛ ደረጃ ዘመናዊ ት/ቤት ከመዋዕለ ህጻናት እስከ የ2ኛ ደረጃ እና መሰናዶ ት/ቤት ደረጃ ያለውን ት/ቤት አቋቁሞ ተማሪዎች መንፈሳዊና ሥጋዊ ጥበብ እንዲማሩ በማደረግ ላይ ነው፡፡ ሥጋዊ ጥበብ የሚባለውም በቀደሙት አባቶቻችን አባባል ቀለም በጥብጦ፣ ብራና ፍቆ፣ ብዕርን ቀርፆ፣ መፃህፍትን መፃፍ፣ መጠረዝና መደጎስ እንዲሁም እርሻ ማረስ፣ ንግድ መነገድና የመሳሰለ ሲሆን እንደ ዘመኑ አባባል ደግሞ የቀለም ት/ቤቶችን አቋቁሞ /ከፍቶ በዘመኑ ቴክኖሎጂ በመታገዝ እስከ ዮኒቨርሲቲ ያለውን ትምህርት መስጠት ማለት ነው፡፡ በመሆኑም የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል 1ኛና 2ኛ ደረጃ ዘመናዊ ት/ቤት መስከረም 14 ቀን 1955 ዓ.ም. ተቋቋሞ የማስተማር ሥራውን የጀመረው የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ት/ቤት በወቅቱ የህብረተ ሰቡ የመማር ፍላጎትና የተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ በመሄዱ መጠነኛ የሆነ ክፍያ እንዲከፍሉና የተሻለ የትምህርት አገለግሎት እንዲያገኙ ከህብረተሰቡ ጥያቄው በመቅረቡ በ1962 ዓ.ም. መጠነኛ ክፍያእንዲከፈል ተወስኖ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ትምህርት ቤቱ በክፍያ ማስተማር የጀመረ ሲሆን የት/ቤቱ ፈላጊ ሕብረተሰብ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥሩ እየጨመረ በመሄዱና ማስተናገድ ከሚችለው በላይ በመሆኑ የተማሪ ቅበላ የሚከናወነው በየዓመቱ ኮሚቴ እየተቋቋመ ኮሚቴው በሚያወጣው የመቀበያ መስፈርት አማካይኝነት እንደ ነበረ የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ በወቅቱ የተማሪ ቁጥር እያደገ ሲሄድ አሁን 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ያለበትን ቦታ ይዞ ከ1962 ዓ.ም. ጀምሮ 12ኛ ክፍል በዚሁ ት/ቤት የብሔራዊ ፈተና ማስፈተን የጀመረ ሲሆን አሁንም ከመቸውም በተጠናከረ መልኩ በቴክኖሎጂ እና ብቁ በሆነ የሰው ኃይል በመታገዘ የመማር ማስተማሩ ሂደት ቀጥሎ በየዓመቱ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስፈተን በከፍተኛ ውጤት ወደ ዩኒቨርሲቲ እንዲገቡ በመድረግ ላይ ላይ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ዛሬ የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ት/ቤት በሦስት የትምህርት ዕርከኖች ወይም ደረጃዎች ተደራጅቶ በርካታ ወጣቶችን እያስተማረ ይገኛል፡፡ እነዚህም ት/ቤቶች፡- 1. አፀደ ህፃናት 2. የ1ኛ ደጃ ት/ቤት 3. የ2ኛ ደረጃ እና መሰናዶ ት/ቤቶች ናቸው፡፡ በአሁኑ ሰዓት በ1996 ዓ.ም. አዲስ ባሠራው ህንፃ የ2ኛ ደረጃና ኮሌጅ መሰናዶ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተናገደ ይገኛል፡፡ት/ቤቱ ትምህርት ሚኒስተር ያወጣውን ሥርዓተ ትምህርት በመከተልና ባለ 3 ፎቅ የራሱ ህንፃ ገንብቶ ት/ቤቱን ከ2ኛ ደረጃ ት/ቤት ወደ ተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል ፡፡በመሆኑም ት/ቤቱ በአሁኑ ሰዓት ከመዋዕለ ሕጻናት እስከ ኮሌጅ መሰናዶ ድረስ ከ2,500 ያላነሱ ተማሪዎችን እየተቀበለ ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት በመስጠት ላይገኛል፡፡

0031

ከትምህርቱ ጥራትም የተነሳ ተማሪዎች በሁሉም ብሔራዊ ፈተናዎች ከፍተኛ ውጤት እያመጡ ከደረጃ ወደ ደረጃ እያለፉ ስለመጡ የመንበረ ጸበዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ት/ቤት በተገልጋዩ ህብረተሰብ ዘንድ በአዲሰ አበባ ከሚገኙ እውቅ ት/ቤቶች አንዱ ለመሆን በቅቷል፡፡በዚህም ምክንያት ት/ቤቱ በአሁኑ ጊዜ ለህብረተሰቡ እየሰጠ ያለው ት/ት ካቴድራሉን ብቻ ሳይሆን የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክርስቲያንም የሚያኮራና የሚያስመሰግን ት/ቤት እየሆነ መጥቷል፡፡ በመሆኑም የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል መሰናዶ እና 2ኛ ደረጃ ት/ቤት እንደ ቀድሞው ሁሉ ደረጃውን ጠብቆ የተሻለ ሥራ ለመስራት ታስቦ በ15/07/05 ዓ.ም ከተማሪ ወላጆች ጋር ለ3ኛ ጊዜ ውይይት የተደረገ/ያካሄደ ሲሆን ስብሰባውን የመሩት ክቡር ሊቀ ሥልጣናት አባ ገ/ሥላሴ በላይ የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዋና አስተዳዳሪ ሲሆኑ የካቴድራሉ ትምህርት ቤት ዋና ርዕሰ መምህርና ምክትል ርዕስ መምህር በስብሰባው ላይ ተገኝተዋል፡፡በአጠቃላይ ከ1000 በላይ የሚሆኑ የተማሪ ወላጅ በስብሰባው ላይ የተገኙ ሲሆን በመማር መስተማሩ ሂደት ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ክቡር ሊቀ ሥልጣናት አባ ገ/ሥላሴ በላይ እንደ ገለፁት ተማሪዎች የተወሰነ የማርፈድና ከክላስ የመቅረት ችግር አልፎ አልፎ እንደ ሚታይ ጠቁመው ይህ ሊስተካከል የሚችለው ደግሞ ት/ቤቱ እና ወላጆች ባላቸው ኃላፊነት የበኩላቸውን ግዴታ ሲወጡ ብቻ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ት/ቤቱ ከመቸውም በላይ ከወላጆች ጋር እየተመካከረ እየሰራ መሆኑን ገልፀው ወላጆች ልጆቻቸውን በአግባቡ ሊከታተሉና ሊቆጣተሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ቅዳሜ በሚሰጠው የማጠናከሪያ ት/ት ላይ ተማሪዎች ዩኒፎርም ሳይለብሱ እየመጡ በተወሰኑ ተማሪዎች ላይ የተወሰነ ችግር እንደነበር ገልፀው ቀደም ሲል ከወላጆች ጋር በተደረገው ስምምነት ሁሉም ተማሪዎች ቅዳሜ ለማጠናከሪያ ትምህርት ሲመጡ ዩኒፎርማቸውን እንዲለብሱ በመደረጉ ሙሉ በሙሉ ችግሩ መቀረፉን ጨምረው ገልፀዋል፡፡ ከዚህ ስብሰባ በኃላም የማርፈዱ ችግር ሙሉ ለሙሉ እንደሚቀረፍ እምነታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡በቀጣይም በተመሳሳይ ሁኔታ እንደተለመደው ከወላጆች ጋር ስብሰባ ሊኖር እንደሚችል ጠቁመው የካቴድራሉ ት/ቤት ለሚያደርገው ጥሪ ተባባሪ እንዲሆኑ አሳስበዋል

0014

በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ለሚጦሩ አረጋወያን ለ6ኛ ጊዜ እረዳታ ተሰጠ

                          በመ/ር ዘሩ ብርሃኔ

“ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ ምስጉን ነው፡፡” መዝ. 40÷1

“እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ”2ኛ ቆሮ. 9÷7

0014

ከዚህ በፊት በዌብሳይታችን አማካኝነት ወጣት ብሩክ አስራት የክርስትና ስሙ ግርማ ጽዮን ከዛሬ 6 ወር በፊት ጀምሮ ለካቴድራሉ አረጋውያን የሚሆን በየወሩ ለአረጋውያኑ የሚያስፈልጋቸውን የምግብ እርዳታ እያደረገላቸው መሆኑን ስንዘግብ መቆየታችን የሚታወስ ሲሆን አሁንም እንደተለመደው ለ6ኛ ጊዜ ለ1 ወር የሚሆን በእነ ወ/ሮ ማርታ ወርቄ፤በወንድሙ እና በጓደኞቹ አማካኝነት እርዳታውን የላከ ሲሆን ከ4 ወር በፊት በወ/ሮ ማርታ ወረቄ፤በወ/ሮ ሮማን እሸቴ፤በወ/ሮ የምስራች አበበና በወጣት ዳግማዊ መስፍን አማካኝነት የአረጋውያኑ መኖሪያ ቤት የሆነውን የንግስት ዘውዲቱ መታሰቢያ ቤት አንድ ቀን ሙሉ ማጽዳታቸው ይታወቀል፡፡

አሁንም ከአገር ቤት ተመልሶ ወደ አሜሪካ ከሄደ በኋላ ቀደም ሲል ቃል በገባው መሰረት ለ6ኛ ጊዜ ለአንድ ወር የሚሆን የወር አስቤዛ በወንደሙና በጓደኞቹ አማካኝነት እርዳታውን ልኳል፡፡ በዚሁ ዕለት ሊቀ ጠበብት ዘለዓለም መንግስቱ የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ም/ስብከተ ወንጌል እና የትምህርት ክፍል ኃላፈ አማካኝነት ለወጣት ብሩክ አስራት፤ለቤተሰዎቹና ለጓደኞቹ ጸሎትና ምስጋና እንዲሁም ቃለ ምእዳን ተሰጥተዋል ፡፡

ሊቀ ጠበብት ዘለዓለም መንግስቱ እንደገለፁት እንደ እነዚህ የመሰለ አቅመ ደካማ የሆኑ አረጋውያን መርዳትበእግዚአብሔር ዘንድ ወጋው እጅግ በጣም ትልቅ መሆኑን ገልፀው በተለይም በካቴድራሉ ቅፅረ ግቢ በንግስት ዘውዲቱ መታሰቢያ ቤት ተጠልለው የሚኖሩ አረጋውያን ለ24 ሰዓታት እግዚአብሔር ሲለምኑ የመኖሩና እግዚአብሔር በሰዎች ላይ አድሮ የዕለት ጉርስ ከሚሰጥዋቸው ምዕመናን ውጭ ምንም ዓይነት ረዳት እንደሌላቸውና በአንዲት ጠባብ ቤት እስከ 8 የሚሆኑ አረጋውያን እናቶች ተጨናንቀው እንደሚኖሩና የምግብ ችግር ብቻ ሳይሆን የመፀዳጃ፤የማዕድ ቤት፤ የውሀና የንጽህና ችግርም እንዳለባቸው ገልፀዋል ፡፡

0018

በወጣት ብሩክ አስራት እየተደረገ ላለው ነገር ሁሉ ምስጋናቸው እጅግ የላቀ መሆኑን ገልፀው ሌሎችም የዚሁ የተቀደሰ ዓላማ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በመጨረሻም በሊቀ ጠበብት ዘለዓለም መንግስቱ አማካኝነት ለወጣት ብሩክ አስራትና ለቤተ ሰዎቹ እያደረገው ላለው ነገር ሁሉ በዓጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ ስም ካቴድራሉን በመወከል ምስጋናቸውን አቅርበዋል ፡፡

እነዚህ አረጋውያን ከዛሬ 45 ዓመታት በፊት ከዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት ጀምሮ በንጉሱ አማካኝነት በካቴድራሉ በጎ አድራጎት /ምግባረ ሠናይ ክፍል ሥር በቃለ ዓዋዲ መሠረት የተቋቋመ ሲሆን ቀደም ሲል በብዙ መልኩ የተደራጀ እንደነበር የሚነገር ሲሆን አሁንም በካቴድራሉ አስተዳደር አማካኝነት እንደቀድሞ ለማጠናከር ከፍተኛ የሆነ ጥረት እየተደረገ ነው በመሆኑም በዘላቂነተ የአረጋውያኑ ችግር በመጠኑ ለመቅረፍ እንደ ወጣት ብሩክ አስራት የክርስትና ስሙ ግርማ ጽዮን አቅማችሁ የፈቀደውን/የቻላችሁትን ያህል እርዳታ እንድታድርጉ እናሳስባለን፡፡

The Holy Trinity Cathedral charity was established during the time of Emperor Haileselassie. It is still in existence helping the needy. During the time of the former king, he was providing Fund worth enough to feed and cloth the poor. But after the dethronment of the Emperor, things have become different and the charity run out of funds as a result of which the needy are in dire shortage to provide the necessary provisions. It would be worthwhile to make clear that those of you who have the interest of extending help for the subsistence of the service of the charity. The church we in advance express our indebtedness of any contribution. At present the charity assistances 15 aged and helpless women.