የአስተዳዳሪው መልእክት

ከሁሉ አስቀድሜ የሥራና የጊዜ ባለቤት የሆነው አምላካችን እግዚአብሔር ለሀገርና ለወገን የሚጠቅም መልካም ሥራ የምንሠራበትን ጊዜ በቸርነቱ ስለሰጠን ክብርና ምስጋና ሁሉ ለእርሱ ይሁን፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በሁለንተናዊ መልኩ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያበረከተቺው አስተዋፅዖ ታሪክ የማይረሳው ፤ይልቁንም ታሪኩ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሳይቋረጥ ሲሻጋገር የሚኖር የታሪክ ባለቤት ናት፡፡ ቀደምት የቤተ ክርስቲያን አባቶቻችን በነበራቸው ከፍተኛ የቤተ ክርስቲያን፣የሀገርና የህዝብ ፍቅር ዘመኑ በፈቀደላቸው መጠን ለሀገርና ለወገን የሚጠቅምና የሚያኮራ ሥራ በመሥራት ቤተ ክርስቲያናችን በመላው በዓለም ላይ ሐዋርያዊት፣ታሪካዊት እና ብሔራዊት እንድትሆን አስችለዋታል፡፡

የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል 2ኛና መሰናዶ ት/ቤት ድርጅታዊ አቋም

የቦታው ሁኔታ

 • በአራዳ ክ/ከተማ አራት ኪሎ ከፓርላማ አጠገብ ወይም ከወ.ወ.ክ.ማ. ጀርባ ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን፣
 • ወጣ ገባ የሌለው ግቢው በአስፋልት የተነጠፈ ለትምህርት ሥራ ምቹነት ያለው ከማንኛውም የፀጥታ ችግር የተከለለ፣
 • ፀጥታንና ጤናን ከሚያውኩ ችግሮች፣
 • የውሃ፣ የመብራት፣ የትራንስፖርትና የስልክ አገልግሎት ያሟለ፣
 • ከተመሳሳይ ደረጃ ት/ቤቶች ተገቢ ርቀት ያለው፡፡

የምድረ ግቢው ገጽታና አደረጃጀት

 • ዙሪያው ግንብ አጥር የተከለለ፣
 • ብሎኮችና ክፍሎች ለትምህርት ሥራ አመቺ ሆነው የተሠሩ፣
 • ለመኪና ማቆሚያ፣ ለመዝናኛ ሜዳ ያለውና ለክፍል ውጪ ትምህርት ተስማሚ ቦታ ያለው

የምድረ ግቢው ስፋት

 • ከ3000 ካሬ ሜትር በላይ ስፋት ያለው ግቢ ላይ የሰፈረ

የሕንፃው አሠራርና አደረጃጀት

 • ሕንፃዎቹና ክፍሎቹ ከብሎኬት፣ የተሠሩና ደረጃቸውን የጠበቁ ናቸው፣
 • እያንዳንዱ ክፍል 7.75 x 6.75 የሆነ የመማሪያ ክፍል ያለው፣
 • ልዩ ልዩ የአስተዳደር ክፍሎች ያሉት፣
 • የቤተመጻሕፍት፣ የትምህርት ማበልፀጊያ ማዕከል፣ የቤተሙከራ ክፍል፣ የቴክኒካል ድሮዊንግ ክፍልና የካምፒውተር ክፍሎች ያሉት፣
 • የሠራተኞችና የተማሪዎች መፀዳጃ በየጾታው ያለው፣
 • የመሰብሰቢያ አዳራሽና የሻይ ክበብ ያሟላ ነው፡፡

የቤተመጻሕፍት ውስጥ አደረጃጀት

 • በየትምህርት ዓይነት ለየክፍል ደረጃው የሚመጥኑ በቂ ቁጥር ያላቸው የማጣቀሻና የተማሪው መጻሕፍት፣
 • በቂ ቁጥር ያላቸው የመጻሕፍት መደርደሪያዎች፣
 • ኮምፒውተሮች፣ ካርታዎች፣ የአማርኛና የእንግሊዝኛ ቋንቋ መዝገበ ቃላት፣ ኢንሳይክሎፒዲያዎችና ልዩ ልዩ ቻርቶች፣
 • ለክፍሉ ሠራተኞች አገልግሎት የሚውል ጠረጴዛና ወንበር፣
 • በሙያው የሰለጠነ ሠራተኛ ያለው፡፡

የትምህርት ማበልፀጊያ ማዕከል አደረጃጀት

 • ለወርክሾኘና ለዕቃ ማስቀመጫ የሚያገለግል ክፍል፣
 • ለወርክሾኘ አገልግሎት የሚውሉ ልዩ ልዩ መሣሪያዎች፣
 • በቂ የሆኑ ወንበሮችና ጠረጴዛዎች፣
 • በሙያው ችሎታ ያለው መምህር ያሟላ ነው፡፡

የቴክኒካል ድሮዊንግ ክፍል አደረጃጀት

 • ለሥራው የሚያገለግል በቂ ክፍል ያለው፣
 • ለሥራው የሚያገለግሉ ወንበሮችና ጠረጴዛዎች ያሉት፣
 • ለሥራው የሚያገለግሉ ልዩ ልዩ መሣሪያዎች ያሉት፡፡

የኮምፒውተር ክፍል አደረጃጀት

 • ለኮምፒውተር አገልግሎት የሚውል ክፍል፣
 • በቂ ኮምፒውተሮች ከነሙሉ አክሰሰሪአቸው፣
 • በቂ ወንበሮችና የኮምፒውተሮች ማስቀመጫ ጠረጴዛዎች፣
 • የማስታወቂያ ሰሌዳ፣
 • በሙያው የሠለጠነ መምህር ያለው፣
 • ሙሉ ኢኒተርኔት አገልግሎት /ብሮድ ባንድ/ ለተማሪዎች ለአስተማሪዎችና ከቢሮዎች ጋር የተያያዘ የ24 ሰዓት አገልግሎት

የቤተሙከራ ክፍል አደረጃጀት

 • ለ3ቱም ሣይንስ ዘርፎች የሚያገለግሉ ደረጃቸውን የጠበቁ የቤተሙከራ ክፍሎች፣
 • ለቤተሙከራው አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶች፣ መሣሪያዎችና ኬሚካሎች፣
 • የውሃና የኤሌክትሪክ አገልግሎት፣
 • የመምህሩና በቂ የተማሪዎች ዲሞኒስትሬሽን ቴክሎች ስቱሎች፣
 • ለቁሳቁሶች፣ ለመሣሪያዎችና ለኬሚካሎች ማስቀመጫ የሚያገለግሉ በቂ ካፖርዶች፣
 • የሰለጠኑ የላቦራቶሪ ቴክኒሽያኖችን የሟላ መሆኑ፡፡

የመምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች ሁኔታ

 • ለሁሉም ትምህርት ዘርፎች በሙያው የሰለጠኑ የመጀመሪያ ዲግሪና በላይ ያላቸው 34 ቋሚ ቅጥር መምህራን፣
 • የ2ኛ ዲግሪና ሥልጠና ያለው ቋሚ ር/መምህር ዋና እና ም/ር/መምህር፣
 • ከር/መምህራን ጀምሮ በልዩ ልዩ ክፍሎች የማያገለግሉ የሰለጠኑ ቋሚ ሠራተኞች ተመድበው የሚሠሩ፡፡

በብሔራዊ ፈተናዎች ያለው ውጤታማነት

 • ለተከታታይ 6 ዓመታት 1ዐኛ ክፍል ሲያስፈትን የዘንድሮን ሳይጨምር ለፈተና ከቀረቡት ጠቅላላ ተማሪዎች በአማካይ 98.8% ለመሰናዶ ትምህርት የማብቃት ሪከርድ ያለው፣
 • ለ4 ዓመታት የመሰናዶ ተማሪዎችን ያስፈተነ ሲሆን የዘንድሮን ሳይጨምር ጠቅላላ ከተፈተኑት ተማሪዎች 100% ለከፍተኛ ትምህርት እንዲበቁ አድርጓል፡

የስፖርት ሜዳዎች

 • ደረጃውን የጠበቀ የእጅ ኳስ ሜዳን፣ የመረብ ኳስ ሜዳን የያዘ
 • ሙሉ መሣሪያዎች ኳሶች፣ ለዚሁ አገልግሎት የሚውል መሳሪያ የተሟላለት

የተለያዩ ክበባት

 • የቤተክርስቲያንህን እወቅ
 • የስርዓተ ፆታ ክበብ
 • የተለያዩ ዲፓርትመንቶች ክበብ
 • የፀረ ኤድስ ክበብ
 • ስነ-ዜጋና ስነምግባር ክበብ
 • የሳይንስና ቴክኖሎጂ ክበብ
 • የሚኒ ሚዲያ ክበብ ከነ ቢሮውና ከነመሳሪያዎቹ

እነዚህ ክበባት የቢሮ በአባላት የተደራጀና ሙሉ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ተግባራዊ ለውጥ እየመጡ ያሉ ናቸው

የትምህርት አሰጣጥና የክፍል ክፍል ዝውውር ሁኔታ

 • በሁሉም ክፍል ደረጃና የትምህርት ዓይነት ትምህርት ሚኒስቴር ባወጣው የትምህርት ፖሊሲ መሠረት በሙሉ ቀን ኘሮግራም በቀን 7 x 45 ክፍለ ጊዜ የሚስተምርና ሴኩላር የሆነ ትምህርት ቢሮ በሚወስነው የክፍል ክፍል ዝውውር ፖሊሲ መሠረት የሚሠራ፣
 • በየትምህርት ዘመኑ በትምህርት ቢሮ በሚወስነው የክፍል ክፍል ዝውውር ፖሊሲ መሠረት የሚሠራ፣
 • ለየክፍል ደረጃው የሚሰጡ ቴስቶችና ዋና ፈተናዎች በትምህርት ቢሮ ዓመታዊ የትምህርት ካሌንደር መሠረት እየሰጠ የሚገኝ መሆኑ፡፡
 • የመንግስትን ሥርዓተ ትምህርት ጠብቆ ሳያጓድል የሚሠራ፣
 • የተማሪ ክፍል ጥምርታ የትምህርት ጥራትን አስቦ የተደራጀ፣

የመ/ጸ/ቅ/ሥላሴ ካቴድራል አገልግሎቶች ፎቶዎች

የቤተክርስቲያን ነዋየ ቅድሳት መሸጫ

{gallery}pic-service-churchitemsshop{/gallery}

የሙካሽ ስራ

{gallery}pic-service-embroidery{/gallery}

የቤት ኪራይ

{gallery}pic-service-houserent{/gallery}

የመቃብር ቦታ

{gallery}pic-service-tombs{/gallery}

ታሪክ

የስብከተወንጌል አጀማመር

 • ወንጌልን (የምስራቹን ቃል) መስበክ የጀመረው ራሱ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ማቴ. 4፣17

በደዌ ሥጋ የታሠሩትን በመፈወስ በደዌ ኃጢአት የተያዙትን ከኃጢአት በማንፃት የመንግሥቱን ወንጌል ሰበከ፡፡ ሐዋርያትን ሰብስቦ ካስተማራቸው በኋላ ወደ ዓለም ሁሉ እንዲሄዱና ወንጌልን እንዲሰብኩ ያዘዛቸው እሱ ነው፡፡ ማቴ. 28፣19 ማር. 16፣15

ስብከተወንጌል በሐዋርያት ዘመን

ቅዱሳን ሐዋርያት የተሰጣቸውን አምላካዊ ትዕዛዝ በደስታ ተቀብለው የሰው ዘር ባለበት ሁሉ እየሄዱ ቃለ ወንጌልን ሰበኩ፣ በስሙ አጋንንትን አወጡ፣ ድውያንን ፈወሱ፣ ሙታንን አስነሡ፣ የወንጌል ብርሃን በዓለም ሁሉ እንዲበራ አደረጉ፡፡

ስብከተወንጌል በሐዋርያውያን አበው ዘመን

በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተመሠረተው በሐዋርያት የተስፋፋው ስብከተ ወንጌል ከሐዋርያት ቀጥለው በተነሡ አበውም በነአግናጥዮስ፣ በነአትናቴዎስ፣ በነዮሐንስ አፈወርቅ፣ በነቅዱስ ቄርሎስ፣ ወ ዘ ተ  በሕይወት መስዋዕትነት ጭምር ተሰብኳል፡፡ ይህን ለወደፊቱ በቤተክርስቲያን ታሪክ የትምህርት ዓምድ ይጠብቁን፡፡

ስብከተወንጌል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን

 • ይህን የምሥራች ቃለ ወንጌል ኢትዮጵያ አምና የተቀበለችው ገና በዚየው በኢየሩሳሌም አከባቢ እየተሰበከ በነበረበት ዘመን በ34ኛው ዓመተ ምሕረት መሆኑ በቅዱስ መጽሐፍ ላይ ስለተጻፈ  ሁሉም የተረዳው ጉዳይ ነው (ግ/ሐ/8፣26-4ዐ)

በዚህ መሠረት የኢ/አ/ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዛሬም እንደትናንቱ ወንጌለ መንግሥተ ወልደ እግዚአብሔርን በሐዋርያዊ ትጋት እየሰበከች ትገኛለች

ስብከተወንጌል አሁን ባለንበት ዘመን

አሁን እየኖርንበት ባለው በሀያ አንደኛው ምዕት ዓመት የስብከተወንጌል አገልግሎት በዓለም ዙሪያ ለመቃኘት (ለጠቅላላ ግንዛቤ) በቀጣዩ እንሄድበታለን፡፡ በኛ በኢትዮጵያችን ግን ምን ጊዜም ለኢትዮጵያውያን የዕውቀት መሠረት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሕንፃ ቤተክርስቲያኑ ባለበት ቦታ ሁሉ (ከሰውና ከፋይናንስ ዕጥረት የተነሣ ከተወሰኑ አካባቢዎች በስተቀር) የስብከተወንጌል አገልግሎት ይካሄዳል፡፡

አውደ ወራዙት (ወጣትነት በቤተክርስቲያን)

“ልጆቻችሁ በጐልማሳነታቸው እንደአትክልት አደጉ ፡፡ ሴቶች ልጆቻችሁም በግንብ ሥር እንዳለ አንደተወቀረ የማዕዘን ዐምድ ይሆኑ ዘንድ” መዝ.4 ፡ 02

 • 1. ወጣትነት ምንድን ነው;

ወጣትነት የሚለው ቃል ታላቅና ለጆሮ የሚያስደስት ቃል ነው፡፡ ወጣትነት በሰው ልጅ እድሜ ቀመር የእሳትነት ወቅት የሚባልው ሲሆን በቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ ከ15 እስከ 50 ወይም ከ20 እስከ 40 ዓመት ያለውን እድሜ ክልል ያጠቃልላል፡፡ በኢትጵያ ህግ መሠረት ደግሞ ከ 18 ዓመት በላይ ከ 40 ዓመት በታች ያለው የወጣትነት ዘመን ይባላል፡፡  ወጣቶች በአትክልት ውስጥ እንደሚገኙ አበቦችና እንደ ጥዋት ፀሐይ ጮራ ናቸው፡፡ የወጣትነት ዘመን በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ የተሻለው ተፈላጊ ምርጥ ጊዜ ነው፡፡

በሰው ልጆች ህይወት ውስጥ የጥፋት ጨለማ ተወግዶ ብርሃን፤ እንዲሁም ቁንጅናም ሊታይ – የሚችለው በወጣትነት ነው፡፡፡ የወጣትነት ዘመን ሰው እውነተኛ ጠባዩን ፤ባሕርዩንና ተግባሩን የሚገነባበት፤ በሰዓቱ የሚጠናቀቅበትና ሳይመለስ የሚያልፈው ደቂቃው እንዳያመልጠው የሚገነዘብበት ጊዜ ነው፡፡ ወጣቶች በጊዜያቸው ቢሠሩ ያከናውናሉ፤ ቢናገሩ ያሳምራሉ፤ ቢነሡ የጀመሩትን ዳር ያደርሳሉ፤ ቢጣሩ ይሰማሉ፡፡ ወጣቶች ቤተክርስቲያንና በጠቅላላ የሰዎች ልጆች ማኀበራዊ አቋሞች የሚደገፉባቸው አዕማድ ናቸው፡፡ ወጣቶች በአባቶቻቸው ሥፍራ የሚተኩ ቤተሰብን፤ ቤተክርስቲያንንና አገርን የሚዋጉትን ክፋቶች የሚቋቋሙ ጠንካራ ኃይላት ናቸው፡፡ ወጣቶች በህይወታቸው አስተዋዮች፣ ደፋሮችና  አሸናፊዎች፣ በውስጣቸው ዕውቀትን ብልሃትን ፍልስፍናን የያዙና፤ ስለ ደኀና ኑሮ በውስጣቸው የሚቃጠሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡

በቅዱስ መጽሐፍ ሀዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወጣቱንና ደቀመዝሙሩን ጢሞቴዎስን እንዲህ ይለዋል “ማንም ሕፃንነትህን ወይም ወጣትነትህን አይናቀው ነገር ግን ለምእመናን ምሳሌ ሁን፡፡» ጢሞ 4 ፡02. ከዚህ እንደምንረዳው ወጣትነት ከሕጸንነት ወደ ጉልምስና ወይም እርግና መሸጋገሪያ ድልድይ ነው፡፡
ማንኛውም ሕዝብ በማንኛውም ዘመን የሚያሳየውን አካሄድና እርምጃ የሚታወቀው በወጣቶች አስተሳሰብ ነው:: ወጣቶች በሃይማኖት ክፍልም ሆነ በማህበራዊ አቋም የነገው አባቶችና የወደፊቱን ብርሃን ሰጪዎች ናቸው፡፡ በህብረተሰብ ክፍል ውስጥ ከማንኛውም በላይ በንቃት በብርታት በመሥዋዕትነት በመቆጨት ገስግሦ በመራመድ የሚሠሩ ወጣቶች ናቸው፡፡ ወጣቶች ንጹህ ወገን የሥልጣኔ የዕውቀት ምልክት ለመልካም ነገር ቀናተኞችና የኑሮ መሠረት የሕይወት ምንጮች ኃይሎች ናቸው፡፡ “የጐበዛዝቱ ጌጽ ጉልበታቸው ናት” ምሳ. 1፡19.
ወጣትነት ከሕይወታችን የተወሰነ ዘመን አይደለም:: ነገር ግን የአሰተሳሰብና የመንፈስ ርቀት ጐዳይ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ካመንን በነፍስና በስጦታህ ከተማመንን ወጣት ነን:: ለወደፊቱም ከፍ ያለ ተስፋ አለን:: ለመጪው ጊዜ በራስ ተማምነን ካልዳንን በምንም መልክ ወጣት አይደለንም፡፡ ወጣቶች በዕድሜያቸው ሊመዘኑ አይገባም ጉዳዩ የዕድሜ ብዛት ሳይሆን የጤንነት የኃይል የንቃት ምኞት ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወጣትነት፣ በወጣትነት ዘመን መደረግ ስለሚገባችው ነገሮች፣ ብዙ ተብሏል፡፡ ለአብነት ያህል “በወጣትነትህ ወራት ፈጣሪህን አስብ፡፡” መክ 2 ፡1
አንዳንድ ወጣቶች ከእምነት መጻሕፍት በወጣ መልኩ የእግዚአብሔር መኖር የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን ይጠይቃሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ እንስሳ የለመለመ ሳርን አይቶ እንደሚበላ& እንዲሁ ማስረጃ መታየትና መዳበስ አለበት ይላሉ፡፡ ነገር ግን ሰዎች የእንስሳት ባሕርያት ብቻ ያሏቸው አይደሉም፡፡ የማሰብ ችሎታ ስላላቸው አእምሮአቸው የሚያቀርብላቸውን ማሰረጃ ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ሰው የመዝሙርን አስደሳችነትና የቅዱሳት ሥዕላትን ቁንጅና የሚረዳውና የሚገነዘበው በአእምሮ ነው፡፡ እንስሳ ግን የሙዚቃን ድምጽ ሰምቶ ወይም ሥዕልን ተመልክቶ መመሰጥ አይችልም፡፡

ስለዚህ ወጣትነት በሚታዩ ቅዱሳት ሥዕላት፣ በሚደመጡ መዝሙራት፣ በሚነበቡ ቅዱሳት መጻሕፍት ቶሎ የሚሳብና ወደ መንፈሳዊም ሆነ ስጋዊ ለውጥ በፍጥነት የሚታይበትና ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚቻልበት የእድሜ ክልል ነው፡፡  ባጠቃላይ “ልጆቻችሁ በጐልማሳነታቸው እንደአትክልት አደጉ ፡፡ ሴቶች ልጆቻችሁም በግንብ ሥር እንዳለ አንደተወቀረ የማዕዘን ዐምድ ይሆኑ ዘንድ” መዝ.4 ፡ 02  እንደተባለ ወጣትነት እንደአትክልት በልዩ ኩትኮታ የሚታደግበት በግንብ እንዳለና እንደተወቀረ የማዕዘን ዐምድ የሚኮንበት  ወሳኝ የእድሜ ክልል ነው፡፡

 • 2. በወጣትነት ዘመን ላይ የተጋረጡ እንቅፋቶች ( ይቀጥላል………..)

የመ/ጸ/ቅ/ሥላሴ ካቴድራል ስብከተ ወንጌል

መግቢያ፡- ስብከተ ወንጌል ማለት ምን ማለት ነው

ስብከተ ወንጌል ማለት የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሰው መሆን፣ የሰውን ልጅ ወደ ቀደመ ክብሩ (ልጅነቱ) መመለስ የሚያበሥረውን ቃል ማብሠር፣ ማስተማር፣ ማሳመን….ማለት ነው፡፡ ይኸውም በደመ ወልደ እግዚአብሔር የተዋጀችው ቤተክርስቲየን ዕለት ዕለት የምትታነጽበት ቃል ወንጌል ነው፡፡

የስብከተ ወንጌል ዓላማ

ዋናው የስብከተ ወንጌል ዓላማ ሰው ሁሉ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወራሽ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ይኸም ሲባል እግዚአብሔር ለሰው ያለውን የማይለወጥ አምላካዊ ፍቅሩን በመስቀል ላይ ቤዛ ሆኖ መግለጹን ማሳየት፡፡ ዮሐ. 3፣16
ለዘለዓለማዊ ክብርና ሕይወት ወራሽነት ማብቃት፣ የሰዎችን ልብ ከክፋት ወደ በጐነት በስብከት መለወጥ ነው፡፡ 2ኛ ቆሮ. 1ዐ፣3-6

የስብከተወንጌል ጥቅም

በፈጣሪው አርዓያ በእግዚአብሔር የተፈጠረው ሰው ፈጣሪውን አውቆ በማመንና በትእዛዙ በመሄድ ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ የሚኖረው በወንጌል ቃል ሕይወቱ ሲገነባ ነው፡፡ ለዚህም ነው “ይህን የማይለወጥ የዘለዓለም ድኅነት ቅዱስ ወንጌል ከፀሐይ መውጫ እስከ መጥለቂያው ድረስ በሐዋርያት እጅ የላከው” ማር. 16፣8

 • ስለዚህ ስብከተ ወንጌል የቤተክርስቲያን ሕይወት ነው፡፡
 • ስብከተ ወንጌል የቤተክርስቲያን ልማት ነው፡፡
 • ስብከተ ወንጌል የቤተክርስቲያን ሁለንተናዊ እድገት ነው፡፡

የስብከተ ወንጌል ታሪክ

ስብከተወንጌል እንዲጠናከር ምን መደረግ አለበት

ስብከተወንጌል የቤተክርስቲያኗ ሕይወት ነው፣ ሁሉ ነገር ደግሞ ቅድሚያ ለሕይወት ደኅንነት ነው፡፡ ስለዚህ፡-

 • ለአገልግሎቱ በቂ ዕውቀት ያላቸው መምህራንን ዘመኑ በሚጠይቀው የአገልግሎት ደረጃ አሰልጥኖ በሁሉም ቦታ መመደብ፣
 • ማዕከሉን ያልጠበቀ (የተዘበራረቀ) የስብከተወንጌልን እንቅስቃሴ ወደ ሥርዓት ማስገባት፣
 • በመላዋ ኢትዮጵያ የሚገኙ ካህናትን ደረጃ በደረጃ የግንዛቤና የስብከተወንጌል ተልዕኮ ሥልጠና በመስጠት ሁሉም ለአገልግሎቱ መንፈሳዊ ቅናት እንዲኖራቸው ማድረግ፣ የሙያ ክህሎታቸውን ማሳደግ፣
 • ቤተክርስቲያን ካላት ገቢ ላይ ከፍተኛውን የገንዘብ ኃይል ለዚህ አገልግሎት መመደብ (በጀት መያዝ)፣
 • የምሁራኑን ሞራል መጠበቅ፣
 • በቂ ዕውቀት ሳይኖራቸው፣ ቤተክርስቲያኗ የሙያ ማረጋገጫ ሳትሰጣቸው ራሳቸውን በራሳቸው መምህራን (ሰባክያን) አድርገው ወደ መድረክ የሚወጡትን በመጀመሪያ ወደ ትምህርት ገበታ እንዲገቡ ማድረግ፣
 • እነዚህና ሌሎችም ያልተጠቀሱ ጉዳዮች በጥናትና እቅድ እየተደገፉ ቢሠሩ ስብከተወንጌሉ ከመስፋፋቱና ከመጠናከሩ ቤተክርስቲያኗም በመንፈሳዊ ሕይወቷ ከመለምለሟም ጐን በአገልግሎቱ ላይ እንደእንቅፋትና ፈተና እየሆኑ ያሉ ያለ በቂ ዕውቀት በተለይ በምሥጢረ ሥላሴና በምሥጢረ ሥጋዌ ላይ ያለእውቀት በድፍረት ሕፀፀ አእምሮ እየወለዳቸው ያሉትን ክስተቶች እንዳይከሰቱ በማድረግ የተሻለ ውጤት ይገኛል፡፡

መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል

ለኢ/ኦ/ተ/ቤክ/ስብከተ ወንጌል መጠናከር ያደረገው አስተዋፅኦ

በካቴድራሉ ቀደም ባሉት ዓመታት እንዴት ይሰጥ እንደነበር

ከካቴድራሉ ሕንጻዊ ሥነጥበብ ጀምሮ የኢ/አ/ተ/ቤ/ከ ልዕልና መገለጫ በሆነው መ/ጸ/ቅ/ሥላሴ ካቴድራል ማዕከልነት ለመላዋ ኢትዮጵያ ይሰጥ የነበረው ስብከተ ወንጌል በወቅቱ “ብሥራተ ወንጌል” በሚል የሬድዮ ፕሮግራም በየቀኑ የሚተላለፉ ትምህርቶችን የሚያዘጋጁ ምሁራንን ያቀፈ የኢ/አ/ተ/ቤ/ክ ሐዋርያዊ ድርጅት በሚል ሥያሜ የተቋቋመው በዚሁ ካቴድራል ውስጥ ሆኖ በመሥራት አቅሙ በፈቀደው መጠን ሐዋርያዊ ተልዕኮውን ሲፈጽም ቆይቷል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ያ እንቅስቃሴ በሚገባ ተጠናክሮ በጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት ስብከተወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ ዋና መምሪያ ሆኗል፡፡

አሁን በካቴድራሉ ያለው የስብከተ ወንጌል ልዩ ልዩ መርሐግብር

ከላይ እንደተገለጸው ከጥንት ጀምሮ የስብከተ ወንጌል ማዕከል የሆነው ካቴድራል የቤተክርስቲያኗን ሥርዓተ አስተምህሮ ሳይለቅ የዘመኑን ስልትና የትምህርት አቀራረብ ዘዴ በመጠቀም የስብከተ ወንጌል አገለግሎቱ ከዚህ በሚከተለው መልኩ ተጠናክሮ እና ተስፋፍቶ በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡

 • 1. የየዕለት መርሐግብር

ከወር እስከ ወር ከዓመት እስከ ዓመት ድረስ ለሚሰጠው ትምህርተ ወንጌል በየቀኑ መደበኛ መምህራን ተመድበው ከሌላም ቦታ የሚያስተምሩ ብቃት እና ጥራት ያላቸው መምህራን ተጋብዘው በየቀኑ ትምህርቱ ከቀኑ 11፡ዐዐ-1፡ዐዐ ሰዓት ድረስ ይሰጣል፡፡

 • 2. የዕለተ ሰንበት

በየሳምንቱ በዕለተ እሑድ ለቦታውም ጭምር ከፍተኛ ፍቅር ያላቸው እጅግ ታላላቅና እምነተ ጠንካራ ምእመናን በብዛት በጸሎተ ቅዳሴውና በትምህርቱ ላይ የሚገኙበት በመሆኑ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ በሊቀ ሥልጣናቱና በካቴድራሉ ምሁራን መደበኛ ሰባክያነ ወንጌል የምእመኑን መንፈስ በሚያረካ ሁኔታ እየተሰጠ ይገኛል፡፡ 3. በመዋዕለ ጾም በታላቁ (ዐቢይ) ጾም እና በጾመ ፍልሰታ ለማርያም ከቀኑ 5.3ዐ-6፡3ዐ ያለው ሰዓት የስብከተ ወንጌል ነው፡፡ በዚህ ጾሙ ተጀምሮ እስከ ሚፈጸም ድረስ በየቀኑ የትምህርት አርእስቶች ወጥተው ብቃቱ ያላቸው የቦታው መምህራነ ወንጌል እንዲሁም ከጠቅ ላይ ቤተክህነትና ከመንፈሳዊያን ኮሌጆች ተመድበው በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጭምር ትምህርቱ ይሰጣል፡፡

3. በመዋዕለ ጾም

በታላቁ (ዐቢይ) ጾም እና በጾመ ፍልሰታ ለማርያም ከቀኑ 5.3ዐ-6፡3ዐ ያለው ሰዓት የስብከተ ወንጌል ነው፡፡ በዚህ ጾሙ ተጀምሮ እስከ ሚፈጸም ድረስ በየቀኑ የትምህርት አርእስቶች ወጥተው ብቃቱ ያላቸው የቦታው መምህራነ ወንጌል እንዲሁም ከጠቅ ላይ ቤተክህነትና ከመንፈሳዊያን ኮሌጆች ተመድበው በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጭምር ትምህርቱ ይሰጣል፡፡

 • 4. በወርኃዊያን በዓላት

በወርኃዊያን በዓላት ሕዝበ ክርስቲያኑ በብዛት ወደ ቤተክርስቲያን የሚጐርፍበት መሆኑ ይታወቃል፡፡ የሕዝቡን ብዛትና ሃይማኖታዊ አመጣጥ በማሰብ የስብከተ ወንጌል ክፍሉ ሃይማኖቱ ለሰበሰበው ሕዝብ ምን ትምህርት መሰጠት እና እግዚአብሔርን በመዝሙር እንዴት ማመስገን እንዳለበት በሰፊው በመዘጋጀት ከቀኑ 1ዐ እስከ ምሽቱ 1፡3ዐ ሰዓት ድረስ ይሰጣል፡፡

 • 5. ዓመታዊያን እና ልዩ ልዩ ጉባዔያት

ዓመታዊ በዓለ ንግሥን አስመልክቶ እና ለትምህርተ ወንጌል ተብሎ በእቅድ ተይዘው የሚሠሩ የትምህርት ጉባዔያት ከሌላው ቀን ለየት ባለ መልኩ የሚካሄደው አስደሳች የካቴድራሉ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ነው፡፡ ይህ በይዘቱም ብዙ መርሐ ግብሮችን የሚያቅፍ ስለሆነ ከቀኑ 9፡3ዐ-1፡3ዐ ሰዓት የሚፈጅ መርሐ ግብር ነው የሚካሄደው፡፡
በተጨማሪም በክርስቲያኖች ሥርዓተ ጋብቻ ላይ የሚሰጠው ስብከተ ወንጌል በጸሎተ ሙታን ጊዜም ሁሉ እየተሰጠ ባለው ትምህርት ተጋቢዎች ተደስተው ኀዘንተኞች በእግዚአብሔር ተጽናንተው እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ይገኛሉ፡፡
እንዲሁም በዚህ ድህረ ገጽ ለምትጠቀሙ የስብከተወንጌል ክፍሉ ከላይ ከተዘረዘሩት በተጨማሪ፡-

 • 1. መሠረታዊ የቤተክርስቲያኗን ትምህርት፣
 • 2. የቤተክርስቲያንን ታሪክ፣
 • 3. ወቅቱን የተመለከተ ትምህርት የምናስተላልፍ መሆኑን እንገልፃለን፡፡

ልዑል እግዚአብሔር አገልግሎታችን ይባርክልን አሜን

አገልግሎቶች

 • ሁለገብ አዳራሽ

ይህ አዳራሽ በሊቀ ሥልጣናት አባ ገብረ ማርያም አጽብሐ የተሠራ ሲሆን እጅግ ዘመናዊ እቅድን ተከትሎ የተሠራ ሆኖ ለሠርግ፣ ለስብሰባ፣ ለሙት ዓመት፣ መታሰቢያና ለመሳሰሉት አገልግሎቶች፣ ለአገልጋዮች በነፃ አገልግሎት ሲሰጥ ለውጭ ሰዎች ደግሞ በገንዘብ ይከራያል፡፡ ከአዳራሹ ጋር ተያይዞ የተሠራው የፉካ መቃብርም ለ7 ዓመታት ውል እየተከራየ የካቴድራሉን ገቢ በማሳደግ ላይ ከመሆኑም ሌላ አብሮ የተገነባው ፎቅም ለልዩ ልዩ ድርጅቶች ተከራይቶ ቋሚ ገቢ በማስገኘት ላይ ነው፡፡

 • ከፍተኛ ክሊኒክ

ይህ ሕንፃ በአንዲት የተከበሩ የቤተክርስቲያን ልጅ ከሆኑት ከወ/ሮ እስከዳር ገ/ሕይወት አስተዋጽኦ ጭምር የተገነባ ዘመናዊ ክሊኒክ ሲሆን ሥራው ተጠናቆና ተመርቆ ካቴድራሉ ለባለሙያዎች አከራይቶት ሥራውን እያካሄደ ይገኛል፡፡

 • ዘመናዊ ት/ቤት

የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ት/ቤት በሦስት የትምህርት ዕርከኖች ወይም ደረጃዎች ተደራጅቶ በርካታ ወጣቶችን እያስተማረ ይገኛል፡፡ እነዚህም

 • 1.    አፀደ ህፃናት
 • 2.    የ1ኛ ደጃ ት/ቤት
 • 3.    የ2ኛ ደረጃ እና መሰናዶ ት/ቤቶች ናቸው፡፡

በ2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎችን እንደገና ማስተናገድ የጀመረው በ1ኛ ደረጃው ት/ቤት በ1996 ዓ.ም 9ኛ ክፍል በመክፈት ነበር፡፡
በ1997 ዓ.ም. አዲስ ያሰራውን ህንፃ ለ2ኛ ደረጃና ኮሌጅ መሰናዶ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተናገደ ይገኛል፡፡

 

 • የተለያዩ ካፌዎችና መኖሪያ ቤቶቾ
 • በአሁኑ ወቅትም  በ22 ማዞሪያ ባለ 4 ፎቅ ህንፃ በመሠራት ላይ ይገኛል

ሰንበት ትምህርት ቤት

ሰ/ት/ቤት በዘመነ ብሉይ

የሰንበት ት/ቤት ከዘመነ ብሉይ ጀምሮ የነበረው ነው፡፡ ለምሳሌ በዘዳግም “እነዚህ ቃሎች በልባችሁና በነፍሳችሁ አኑሩ እነርሱንም ለምልክት በእጃችሁ ላይ እሰሩአቸው በአይኖቻችሁም መካከል እንደክታብ ይሁን ልጆቻችሁንም አስተምሩአቸው በቤትህም ስትቀመጥ በመንገድህም ስትሄድ ስትነሳም አጫውታቸው” የሚል እናነባለን (ዘዳ 1÷6-9)
ከዚህ በላይ እንደተጠቀሰው እስራኤላውያን ልጆቻቸውን ሕገ እግዚአብሔር እንዲያስተምሩአቸው ታዘዋል በትእዛዙም መሰረት ሕፃናቶቻቸውን በቤተ እግዚአብሔርና በቤታቸው ሕገ ኦሪትን እያስተማሩ ያሳድገôቸው እንደነበር ለማወቅ እንችላለን፡፡

ሰ/ት/ቤት በዘመነ ሐዲስ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባስተማረበት ዘመንም ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው በመንግስተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጥ ማን ነው; ባሉት ጊዜ አንድ ሕፃን ጠርቶ በመካከላቸው አቆመ /እውነት እውነት እላችኋለሁ ካልተመለሳችሁ እንደ ሕፃናትም ካልሆናችሁ ወደ መንግስተ ሰማያት ከቶ አትገቡም/ ብሎ ሕፃናትን ለቤቱ ስራ ምሳሌ አድርጎ እንዳቀረባቸው እንረዳለን፡፡ ስለ ትሕትናም ለማስተማር በፈለገ ጊዜ አንድ ሕፃን ጠርቶ /ሰው ለክብር ቢወድ ከሁሉ በኋላ የሁሉም አገልጋይ ይሁን/ ካለ በኋላ እንደዚህ ካሉ ሕፃናት አንዱ/ በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል/ በማለት ሕፃናት ለሁሉም ምሳሌ እንደሆኑ ተናግሯል፡፡ / ማቴ 17÷ 2-4 ፣ ማር 9÷35-36፣ ሉቃስ 9÷46-47/

በሌላውም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ሕፃናትን ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲመጡ አይተው ይገስጻôቸው ጀመር እርሱ ግን ሕጻናትን ተዋቸው ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ አትከልክላôቸው መንግሥተ ሰማያት እንደ እነርሱ ላሉት ናትና / በማለት ወደ እግዚአብሔር መቅረብ የሚገባቸው መሆኑን አስገንዝባôቸዋል /ማቴ 19 ፥14/
በመሆኑም ሰ/ት/ቤት በዘመነ ሐዲስ በ 200 ዓ.ም. በፈረንሳይ ሀገር በፓሪስ ከተማ ተጀምሯል ከዚያም በኋላ አውሮፓ እንደተስፋፋ እና በሌሎች አህጉራትም እንደተቀôቀôመ ተረጋግጧል፡፡
ይህንን መሰረት በማድረግ ቤተክርስቲያናችን ሕገ ወንጌልን ለማስፋፋት ከሚያስፈልገôት ዋና ዋና ነገሮች አንዱ የሰ/ት/ቤትን ማቀôቀôምና ማደራጀት መሆኑን ተገንዝባ ሰ/ት/ቤትን በየአጥቢያ ቤተክርስቲያን በስፋትና በጥልቀት እንዲቀôቀôም አድርጋለች፡፡

በአገራችን በኢትዮጵያም በዘመናዊ መልክ እንደ አሁኑ ባይቀôቀôምም እንካô ከሁሉ በፊት እንደ ነበር የታመነ ነው፡፡ ይኽውም በኢትዮጵያ ሊቃውንት ወይም መምህራን በየቤተክርስቲያኑ በየደጀ ሰላሙና በየዛፉ ስር በየመንደሩም ጭምር ሕጻናትን በመሰብሰብ ያስተምሩት የነበረው የሰንበት ትምህርት ቤት መሰረትና መነሻ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

ሰ/ት/ቤት በአገራችን በዘመናዊ መልክ በመንበረ ጸባዖት ቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል መቋቋም

ለሰ/ት/ቤት መጀመርና መስፋፋት የመጀመሪያ የሚሆነው ይህው ታላቅ ካቴድራል ሲሆን ካቴድራሉ ከመቆርቆሩ ቀደም ብሎ በዳግማዊ ምኒሊክ በ 1883 ዓ.ም መካነ ሥላሴ የዛሬው በ®ለ ወልድ እየተባለ የሚጠራው ቤተክርስቲያን ተተክሎ ለ41 ዓመታት እየተገለገለበት ከቆየ በኋላ ለአዲሱ ካቴድራል ምስረታ በ1924 ዓ.ም. የመሰረት ድንጋይ ተጥሎ በታኅሳስ 30 ቀን 1936 ዓ.ም. ተፈጽሞ በይፋ መካነ ሥላሴ የነበረው በ®ለ ወልድ ተብሎ አዲሱ ቤተክርስቲያን ደግሞ መ/ጸ/ቅ/ሥላሴ ካቴድራል በሚል ስያሜ ተመርቆ ዓለም አቀፋዊ አገልግሎቱን የጀመረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለዚህ ታላቅ የምርቃት ሥነ-ስርዓት ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ከተለያዩ አገራት የጠሯቸውን የውጭ አገር እንግዶች፣ የአገር ውስጥ ባለስልጣናት እና ሰፊውን ሕዝብ በአግባቡ ለማገልገል ይቻል ዘንድ የወንድ ወጣቶች እገዛ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል፡፡ በመሆኑም የተለያዩ ወጣቶች ተሰብስበው ስለ ዕለቱ የመስተንግዶ ሥራና ሊኖር የሚገባውን የሥነ-ምግባር ሥርዓተ-ትምህርት ከተሰጣቸው በኋላ በምርቃቱ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ የተጣለባቸውን አደራ ተወጥተዋል፡፡ እንግዶቹና ምዕመናኑ በታላቅ አክብሮት ለንጉሠ ነገሥቱ ምስጋና በማቅረባቸውና የወጣቶቹ የመስተንግዶ አገልግሎት ቀጣይነት እንዲኖረው ፈቃድ በመስጠቱ የካቴድራሉ አስተዳደርም ለወጣቶቹ መምህር በመመደብ ትምህርቱን ቀጠለ፡፡
በመሆኑም በዚሁ ዓመት ማለትም በ1936 ዓ.ም. በወቅቱ የካቴድራሉ የመጀመሪያው መምህር /አስተዳዳሪ/ ሆነው በተሾሙት በሊቀ ሥልጣናት በአባ መልዕክቱ / በኋላም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ የኢትዮጵያ ፓትርያሪክ ተብለው በተሾሙት/ አገልግሎቱ ቀጣይነት እንዲኖረው እንደተቋቋመ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን በኋላም ከሦስት አመት በኋላ በ1939 ዓ.ም. በምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም አሁን ተምሮ ማስተማር እየተባለ በሚጠራው ማህበር ተጠናክሮ ተቀôቀôመ፡፡

ወጣቶቹ በሚያገኙት ትምህርት በየሳምንቱ ዕውቀት እያገኙ በመምጣታቸውና ለቅዳሴ የሚመጡትን ምዕመናንንና እንግዶችን በተገቢው መንገድ ከማስተናገድም በተጨማሪ የነገሥታቱንና የመኳንንቱን ልጆች በቅዳሴ ሥነ-ስርዓት እንዳያውኩ በአዳራሽ እያስተማሩ የቀጠሉ ሲሆን የወጣቶቹም እንቅስቃሴ እየተጠናከረ በመምጣቱ ለካቴድራሉ አገልግሎት ትልቅ ደረጃ መድረስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡
ጉዞው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠነከረና እየተስፋፋ ለመምጣቱ ዋናውና ጉልህ ያደረገው ንጉሠ ነገሥቱና ሹማምንቱ በወጣቶቹ አገልግሎት በመደሰታቸውና ትኩረትም በመስጠታቸው ሲሆን ከዚሁም ጎን ለጎን በወቅቱ በቦታው ሲመሩና ሲያገለግሉ የነበሩ ሊቃውንትና ካህናት ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት መሆኑን ታሪክ ያስረዳናል፡፡
ቀስ በቀስም የሰ/ት/ቤት አገልግሎት በመላ አገሪቱ አድማሱን እያሰፋ በመምጣቱ በቤተክርስቲያን አገልግሎትም አዲስ ምዕራፍ መክፈቱ ከዕለት ወደ ዕለት ይፋ እየሆነ መጣ፡፡ በመቀጠልም የሰ/ት/ቤት አገልግሎት በወንዶች ብቻ ተወስኖ እንዳይቀር ማህበረ ክርስቶስ የሴት ልጅ እድገት በሃይማኖት የደናግል ሴቶች ማህበር በሚል ስም የሴቶች እንቅስቃሴ እንደተጀመረ የመ/ጸ/ቅ/ሥላሴ ካቴድራል የ 10 ዓመት የስራ ውጤት በሚል በተዘጋጀው መጽሐፍ ላይ የሚገልጸውን በአጭሩ እንመልከት፡፡

ሴቶች ልጆች በዘመናዊ ትምህርት ከወንዶች ጎን ተሰልፈው እኩል መማር የጀመሩበት ጊዜ ረጅም ባይሆንም በተለይ በቤተ ክርስቲያን በኩል ሁሉ ነገር በወንዶች ብቻ ተወስኖ መቆየቱ ግልጽ ነው፡፡ የሴቶች ከቤተክርስቲያን አገልግሎት መራቅ ምክንያት በማድረግ ማኅበረ ክርስቶስ ሰኔ 1/1956 ዓ.ም. ከ 20 በማይበልጡ በዳግማዊ ሚኒሊክ ትምህርት ቤት ወጣት ሴት ተማሪዎች በተለይም በእህት አፀደክርስቶስ ተፈራ አሰባሳቢነት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ስር ለመሰባሰብ ቻሉ፡፡ በዚያን ጊዜ እንደዚህ አይነቱ ማኀበር በአገራችን ውስጥ የመጀመሪያ ስለነበር በሕዝቡ ዘንድ ብዙ ትችትና መገረምን አስከትሎ ነበር፡፡ ቢሆንም ሰው ካሰበው እግዚአብሔር የፈቀደው ይበልጣልና በአምላክ ቸርነት በአንዳንድ ሰዎች አበረታችነትና ደጋፊነት እንዲሁም በልጆቹ መንፈሰ ጠንካራነት ማኀበሩ ሥራውን ቀጠለ፡፡

ማኀበሩ ስሙ እንደሚያመለክተው በክርስቶስ የተመሰረተ ስለሆነ ዓላማው ክርስቲያናዊ ትምህርትን ተምሮ ማስተማር’ ሰብዓዊ ርኀራኄና በክርስቲያናዊ ትምህርት መሰረት መፈጸም’ ክርስቲያናዊና ብሔራዊ ባህልን ለመጠበቅና ለማስከበር እንዲሁም ሴት ልጅ በማህበራዊ ኑሮ በቤተክርስቲያንና በቤተሰብ በሚገባ አገልግሎትን መስጠት እንድትችል ለማድረግ ነው፡፡ በሚል ይህ ለህትመት የበቃው መጽሐፍ አስነብቧል፡፡
በዚህ መልክ የተጀመረው የሴቶች የአገልግሎት አድማሱን በማስፋት በቤተክርስቲያን ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የቅዳሴ ተሰጥዎን ለመቀበል የበቁት የዚሁ ማኀበር አባላት መሆናቸውን ማንም የማይዘነጋው ሲሆን ከዚህም በላይ የተለያዩ መዝሙሮችን በማጥናት ከቅዳሴ ሥነ-ስርዓት በኋላና በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ጊዜ የደንብ ልብስ ለብሶ በመዘመር ለቤተክርስቲያን ድምቀት ሰጥተዋታል፡፡ በተለይም ቅድስት ቤተክርስቲያን ሴትና ወንድ ብላ ሳታበላልጥ ለሴት ልጆች እውቀት መሻሻልና የጾታ ልዩነት እንዳይፈጠር ከፍተኛ ጥረት አድርጋለች ከነዚህም መካከል ድምጸ ተዋህዶ እየተባለ በሚወጣው ወርሐዊ ጋዜጣ ላይ የሴቶች አምድ በሚል ርዕስ የሴት ልጅን እኩልነት ለማስተማር ቀዳሚ መሆኗንም ታሪክ ያስረዳል፡፡

ከዚህ ቀደም ብሎ በካቴድራሉ ከ1936 ዓ.ም. ከሰንበት ት/ቤቱ አመሰራረት ጀምሮ የነበረና በሐዋርያዊ ድርጅት ስር በካቴድራሉ የበላይ ጠባቂነት ይመራ የነበረ ማህበረ እስጢፋኖስ ግብረ ልዑካን የመነኮሳትና የዲያቆናት እንዲሁም የወጣቶች ማህበር በሚል ስያሜ የተቋቋመ ማህበር ነበር፡፡ ይህ ማህበር የአዲስ አበባ አድባራት ካህናትን አጠቃሎ በመያዝ የሚሰራ ሲሆን ካቴድራሉ ሁሉንም እንደየ ችሎታውና ፍላጎቱ በማደራጀት መንፈሳዊ አገልግሎቱ ዘመናዊና የተሟላ እንዲሆን አስችሎታል፡፡ ማኅበሩ ወጣቶችን ያቀፈ እንደ መሆኑ መጠን በቅንጅት መልካም ስራዎችን በመስራት ላይ እያለ በገጠመው የውስጥ ችግር ምክንያት ብዙ ፈተና አሳልፎ በመጨረሻም በወቅቱ በነበሩት የካቴድራሉ አስተዳዳሪና በሚመለከታቸው ሰዎች ብርቱ ጥረት በድጋሚ የወንድ ወጣቶቹን እንቅስቃሴ በማጠናከርና እንዲንሰራራ በማድረግ እንዲሁም የደንብ ልብስ /ዩኒፎርም/ በማሰፋት ማህበረ ሥላሴ በሚል መጠሪያ በድጋሚ እንዲደራጅ ተደርጓል፡፡ ይህ በአዲስ መልክ የተደራጀው ማኅበር ውስጣዊ አቅሙን እያጠናከረና እየሰፋ ከመምጣቱም ባሻገር በሌሎች አድባራት እየሄዱ ልምድ በማካፈል ለሌሎች ወጣቶች መንፈሳዊ ቅናትን በማሳደር ቀስ በቀስ በሁሉ ቦታ እንዲስፋፋ በማድረግ ከፍተኛ ለውጥ አመጡ፡፡ ማህበሩም እስከ 1968 ዓ.ም. ድረስ በዚሁ መጠሪያ ስም ይጠራ ነበር፡፡
ከላይ በአጭሩ የተገለጸው የሰ/ት/ቤት እንቅስቃሴ እጅግ በጥልቅና ሰፋ ባለ መልኩ በተለይ ንጉሠ ነገሥቱ በሥልጣን እስከነበሩበት ጊዜ ድረስ በየዓመቱ የ4 እና የ6 ወር እንዲሁም የዓመት ትምህርት ያገኙ ተማሪዎች ከንጉሠ ነገሥቱ የሠርተፊኬትና የተለያዩ ሽልማትን በማግኘት በውጭ ሃገር ጭምር በመሄድ ተሳትፎአቸውን ሲያደርጉ መቆየታቸውን ታሪክ ይነግረናል፡፡

በመቀጠልም እንቅስቃሴውን እስከ 1966 ዓ.ም እያስፋፋ ከቆየ በኋላ በወታደራዊው ደርግ ዘመነ መንግስት ቀደም ሲል ከ1966 ዓ.ም በፊት የነበረው እውቅና ቀርቶ በቤተክርስቲያን ብቻ ተወስኗል፡፡ በመሆኑም በወንዶች ማህበረ ሥላሴ በሴቶች ማህበረ ክርስቶስ በሚል መጠሪያ ይታወቁ የነበሩት ሁለቱ ማህበራት በወቅቱ የካቴድራሉ አስተዳዳሪ የነበሩት ሊቀ ሥልጣናት ዶ/ር አባ ሀ/ሥላሴ ተስፋ / በኋላም አቡነ ጢሞቴዎስ/ ለአመራርና ለቁጥጥር እንዲያመች ሁለቱ ማኅበራት በአንድነት ተዋህደው መመራት አለባቸው ስላሉ አባላቱም ጉዳዩ ስላስደሰታቸው በ1969 ዓ.ም. በአንድነት ተዋህደው የማኅበሩ መጠሪያ ስም ማኅበረ ክርስቶስ ዘመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፡፡ ተብሎ ተሰየመ፡፡

መኅበሩም ማኅበረ ክርስቶስ በሚል መጠሪያ አገልግሎቱን በመቀጠል ላይ ሳለ በስንዴ መካከል እንክርዳድ አይጠፋምና መናፍቃን በታላቁና ለሰ/ት/ቤቶች መሰረት በሆነው የወጣት ማኀበር በመግባታቸው ውስጥ ውስጡን ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ነገሮችን ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥረው አላማቸውን ከግብ ከማድረሳቸው በፊት በፈቃደ እግዚአብሔርና በወቅቱ የካቴድራሉ አስተዳዳሪ በነበሩ በሊቀ ሥልጣናት አባ ተክለሚካኤል አባይ /በኋላም አቡነ ሚካኤል/ እንዲሁም በካቴድራሉ ሰራተኞችና አስተዳደር ስለተደረሰባቸው ቤቱን ጥለው እንዲወጡ ተደርጓል፡፡ በመሆኑም ማኅበረ ክርስቶስ ዘመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፡፡ ተብሎ ይጠራ የነበረውን የወጣቶች ማኅበር በድጋሚ በአዲስ መንፈስ እንቅስቃሴውን ይቀጥል ዘንድ በወቅቱ በነበሩት በእኚህ አባት ትኩረት ስለተሰጠው ስሙ ተቀይሮ የመ/ጸ/ቅ/ሥላሴ ካቴድራል ሰንበት ት/ቤት መባል አለበት በሚል ማሳሰቢያ የሰጡ ሲሆን ይህም ተቀባይነት አግኝቶ በዚሁ መጠሪያ እንዲጠራ ሆኗል፡፡

ከዚህ በኋላ የሰ/ት/ቤቱ የተለያዩ ንብረቶች በተለያየ መንገድ የተበታተኑ ሲሆን በመጨረሻም ጥቂት በሆኑ ወጣቶች እንደገና ለማጠናከር ተሞክሮ ለውጥ ማሳየት ባለመቻሉ እንደገና በካቴድራሉ አስተዳደር ቀና ድጋፍና በወቅቱ የሰ/ት/ቤቱ ያሬዳዊ ዜማና የመጽሐፍ ቅዱስ መምህር በነበሩት በመምህር ኤልያስ አብርሃ / በኋላም ንቡረዕድ ሆነው በተሾሙና የጠቅላይ ቤተክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ በሆኑት/ ብርቱ ጥረት በድጋሚ እንዲቋቋም ተደርጎ በአሁኑ ሰዓት ያለምንም ችግር በ12 ዓመት 4 አመራር ሂደት አጠናቆ አሁን በ 5ኛ አመራር በጥሩ ሁኔታ እንቅስቃሴ እየሰጠ ይገኛል፡፡

የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ት/ቤት

በ1955 ዓ.ም. መስከረም 14 ቀን በማታ ፕሮግራም ሥራውን የጀመረው የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ት/ቤት በወቅቱ የተቀበላቸው ተማሪዎች 8 ብቻ ሲሆኑ እነዚህን መነኮሳትና ዲያቆናት ነበሩ፡፡ በ1956 ዓ.ም. ከ1ኛ እስከ 4ኛ ባሉ ቁጥራቸው 39 የሚደርሱ ተማሪዎችን ይዞ የመደበኛ ትምህርት ጀመረ፡፡ በዚያን ጊዜ የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ት/ቤት “የኢትዮትያ ኦርቶዶክስ ሐዋርያዊ ድርጅት” በመባል ይታወቅም ነበር፡፡

ት/ቤቱን ለመክፈት ያስፈለገበት ዓላማም የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ዘመናዊ ትምህርት እንዲያገኙ ታስቦበት ሲሆን ለዚህም ተግባራዊነት የጥንቱ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ት/ቤት የ1ኛና 2ኛ ደረጃ ት/ቤት መዘጋቱ ለት/ቤቱ በዚያን ወቅት መጀመር ተጽዕኖ እንደነበረው ይነገራል፡፡ የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዘመናዊ ት/ቤት ሊቋቋም የተጠና ዓላማ ይዞ ነበር፡፡

ይኽም ዓላማ ካህናትን ዘመናዊ ትምህርት ለማስተማር ነው፡፡ በወቅቱ ለነበሩ መነኮሳትና ዲያቆናት የዘመናዊ ትምህርት እንዲማሩ ማድረግ በቀላሉ የተከናወነ ሳይሆን በወቅቱ የነበሩ የካቴድራሉ የበላይ አስተዳዳሪዎች ጥብቅ ቁጥጥርና እርምጃ እያደረጉ የቤተክርስቲያኑ አገልጋዮች ት/ቤት ገብተው እንዲማሩ በማድረጋቸው ነበር፡፡

ምንም እንኳ ት/ቤቱ በተጀመረበት ወቅትና ከዚያ ቀጥሎ ባሉት ዓመታት በት/ቤቱ በየዓመቱ ይማሩና ያስተምሩ የነበሩ መምህራን የመማሪያ ክፍሎች ብዛትና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ሠራተኞችና ክፍሎች በስርዓቱ መረጃ ባለመያዙ ምክንያት በዚሁ ጽሑፍ ውስጥ ለማቅረብ የተሞከረው የተገኘው መረጃ ብቻ ነው፡፡

ተ.ቁ ዓ.ም. የተማሪ ቁጥር የመምህራን ቁጥር
1 1955 8 የማታ ተማሪ ብቻ አልታወቀም
2 1956 39 መደበኛ ተማሪ አልታወቀም
3 1958 3ዐዐ ተማሪዎች አልታወቀም
4 1964 425 ተማሪዎች 15
5 1965 78ዐ ተማሪዎች 20
48 2003 2354 ተማሪዎች 34

ቀደም ሲል ለቀሳውስት መነኮሳትና ዲያቆናት ዘመናዊ ትምህርት እንዲያገኙ ታስቦ የተቋቋመው የካቴድራሉ ት/ቤት አገልግሎቱን ወደ ሌላው የህብረተሰብ ክፍል እንዲዳረስ አድርጓል፡፡ የቤተክርስቲያኗ አንዱ ዓላማ ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት ሲሆን ልጆቻቸው እንዲማሩላቸው ይጠይቁ የነበሩ ችግረኛ የህብረተሰብ ክፍሎች ያለክፍያ እንዲማሩ ሲደረግ በአካባቢ የነበሩ ጫማ ጠራጊዎች፣ መጽሔትና ጋዜጣ ሻጮች የትምህርት ዕድሉን እንዲያገኙ ተደርጓል።

ቀደም ሲል በት/ቤቱ ይሰጥ የነበረው ሥርዓተ ትምህርት

 • የቤተ ከርስቲያን ታሪክ
 • የመጽሐፍ ቅዱስ
 • የኃይማኖት ትርጓሜ
 • ቅኔና ዜማ

ከዘመናዊ ሥርዓተ ትምህርቶች ጋር ይሰጥ ስለነበረ ት/ቤቱ ታዋቂነትና ዝና ያገኘው በጣም በፈጠነ ሁኔታ ነበር፡፡ ለዚህም በዋነኝነት ሲጠቀስ የሚችለው ተማሪዎች በትምህርት ችሎታቸው በትህትናቸውና በሥርዓት አክባሪነታቸው ተለይተው ስለሚታወቁና ይኸም የህብረተሰቡን ትኩረት መቆጣጠር በመቻሉ ነበር፡፡

የተማሪዎች ቁጥር ሲጨምርና ት/ቤቱም ሲያድግ ተማሪዎች መጠነኛ ክፍያ እንዲከፍሉና የተሻለ የትምህርት አገለግሎት እንዲያገኙ ከህብረተሰቡ ጥያቄው በመቅረቡ በ1962 ዓ.ም. መጠነኛ ክፍያ-አምስት ብር-እንዲከፈል ተወስኖ ከዚያ ጀምሮ ትምህርት በክፍያ ሆነ፡፡
ት/ቤቱን ፈላጊው ሕብረተሰብ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥሩ እየጨመረ በመሄዱና ማስተናገድ ከሚችለው በላይ በመሆኑ የተማሪ ቅበላ የሚከናወነው በየዓመቱ ኮሚቴ እየተቋቋመ ኮሚቴው በሚያወጣው የመቀበያ መስፈርት አማካይነት ነበረ፡፡

ት/ቤቱ መጀመሪያ ሲቆረቆር ይዞት የነበረው ቦታ አሁን የካቴድራሉ ጽ/ቤት ጀርባ በነበሩ ክፍሎተ ነበር፡፡ የተማሪ ቁጥር እያደገ ሲሄድ ደግሞ አሁን 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ያለበትን ቦታ ይዞ እስከ 1968 ዓ.ም. ድረስ 12ኛ ክፍል ደረጃ አድርሶና 12ኛ ክፍል በዚሁ ት/ቤት አንድ ጊዜ የብሔራዊ ፈተና አስፈትኖ በወቅቱ በተደረገበት ተጽዕኖ ደረጃው ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ባለው ደረጃ በቻ እንዲሆን ተደረገ፡፡

የ1966 ዓ.ም. አብዮትን ተከትሎ የመጣው ሥርዓት በት/ቤቱ ዕድገት ላይ ተጽዕኖ ቢኖረውም በእርሾነት እንዲቆይና ለዛሬው ደረጃ እንዲደርስ የካቴድራሉ አስተዳዳሪዎችና ሠራተኞች ከፍተኛ ጥረትና መስዋዕትነት መክፈላቸው የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ይኸም በመሆኑ ዛሬ የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ት/ቤት በሦስት የትምህርት ዕርከኖች ወይም ደረጃዎች ተደራጅቶ በርካታ ወጣቶችን እያስተማረ ይገኛል፡፡ እነዚህም ት/ቤቶች፡-

 • 1.    አፀደ ህፃናት
 • 2.    የ1ኛ ደጃ ት/ቤት
 • 3.    የ2ኛ ደረጃ እና መሰናዶ ት/ቤቶች ናቸው፡፡

በ2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎችን እንደገና ማስተናገድ የጀመረው በ1ኛ ደረጃው ት/ቤት በ1996 ዓ.ም 9ኛ ክፍል በመክፈት ነበር፡፡
በ1997 ዓ.ም. አዲስ ያሰራውን ህንፃ ለ2ኛ ደረጃና ኮሌጅ መሰናዶ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተናገደ ይገኛል፡፡

በመሆኑም ት/ቤቱ በአሁኑ ጊዜ ከመዋዕለ ሕጻናት እስከ ኮሌጅ መሰናዶ ድረስ ከ2,000 ያላነሱ ተማሪዎችን እየተቀበለ ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት በመስጠት ላይገኛል፡፡ከትምህርቱ ጥራትም የተነሳ ተማሪዎች በሁሉም ብሔራዊ ፈተናዎች ከፍተኛ ውጤት እያመጡ ከደረጃ ወደ ደረጃ እያለፉ ስለመጡ የመንበረ ጸበዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ት/ቤት በተገልጋዩ ህብረተሰብ ዘንድ በአዲሰ አበባ ከሚገኙ እውቅ ት/ቤቶች አንዱ ለመሆን በቅቷል፡፡በዚህም ምክንያት ት/ቤቱ በአሁኑ ጊዜ ለህብረተሰቡ እየሰጠ ያለው ት/ት ካቴድራሉን ብቻ ሳይሆን የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክርስቲያንም የሚያኮራና የሚያስመሰግን ት/ቤት ሆኗል፡፡

 

 

የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተ መዘክር (ሙዚየም)

አደረጃጀትና ይዘት በአጭሩ

ቀደም ባሉት ጊዜያት ካቴድራሉ በሙዚየምነት ሲጠቀምበት የነበረው ከካቴድራሉ ቤተ መቅደስ አንደር ግራውንድ (ምድር ቤት) የሚገኘውን የዕቃ ግምጃቤት እንደ ነበረ ቀደምት ታሪኩን እናስታውሳለን፡፡ ይህ ደግሞ ከምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን መጠበቅና ሥርዓት አንፃር ቦታው ለጉብኝቱ ሂደት አመች አልነበረም፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ባላቸው ፅኑዕ እምነት፣ ለቱሪዝም ዕድገትና መስፋፋት በነበራቸው ከፍ ያለ ራዕይና ከውጭው ዓለም ተሞክሮ በመነሣት ባደረባቸው መንፈሳዊ ቅንዓት በመነሳሳት በተከበሩ በከCረ ምዕመናን ከበደ ተካልኝ በግል ገንዘባቸው ተሠርቶ በበጎ አድራጎት ለሥላሴ ከተሰጠው ዘመናዊ የሙዚየም ሕንፃ ቅርሶቹ ተዛውረው ከተደራጁ በኋላ ጥር 6 ቀን 1998 ዓ.ም. በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም፣ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚዳንትና የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዚዳንት ቡራኬ ተመርቆ ከተከፈተበት ጊዜ ጀምሮ ከቱሪዝም መዳረሻዎችና መስህቦች አንዱ ክፍል ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡

በዚህም ደረጃውን በጠበቀ ዘመናዊ ሙዚየም ውስጥ በጥሩ አደረጃጀትና ጥበቃ ተይዘው በመጎብኘት ላይ ያሉ በርካታ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ቅርሶች ይገኛሉ፡፡ እነዚህም ውድና ማራኪ የሆኑ ቅርሶች በዋጋ ሊተመኑና በምንም ሁኔታ ሊተኩ የማይችሉ ናቸው የተሰጡትም ከቀድሞ ነገሥታት፣ ከእቴጌዎቹ፣ ከብፁዓን አባቶች፣ ከቤተ መንግሥት ልዑላንና ልዕልቶች፣ ከቀድሞ ከመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ከበጎ አድራጊ ክርስቲያኖችና ከ5ቱ አኅት ዐቢያተ ክርስቲያናትም ጭምር ሲሆን ደኅንነታቸውም ለረጅም ዘመናት በሚባ ተጠብቆላቸው ከዚህ ትውልድ ደርሰዋል፡፡

የተሠሩትም ከወርቅ፣ ከብር፣ ከነሐስና ከመሳሰሉት ማዕድናት ሲሆን የወርቅና የብር ቅቦችንም ያጠቃልላል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ከጥልፍ (ሙካሽ) ሥራ የተዘጋጁ የቤተ መቅደስ አልባሳት፣ ድባብ ጥላዎችና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ይልቁንም በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ በተለያዩ ጸሐፍትና አርእስት በግእዝ ቋንቋ የተጻፉ በርካታ ሃይማኖታዊ የብራና ቅዱሳት መጻሕፍትም የዚሁ ሙዚየም ታዳሚዎች ናቸው፡፡

ከእነዚህም ቅዱሳት መጻሕፍት መካከል በ6ኛው መ/ክፍለ ዘመን በቅ/ያሬድ በ8 የዜማ ምልክቶችና በ3 የዜማ ቅኝቶች ከተደረሱት አምስቱ የዜማ መጻሕፍት ውስጥ አንዱና ከ5ዐዐ ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆረጠው ድጓ ተብሎ የሚታወቀው መጽሐፍ በይዘቱም ሆነ በጣዕመ ዜማው በእጅጉ ከሚመስጡትና ከሚያስደንቁት ዋነኛው ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንም ከእነዚህ ከ3ቱ ቅኝቶች ውጭ የሆኑ የዜማ ስልቶች የሏትም አትጠቀምም፡፡ ቅኝቶቹም ዘመን የማይሽራቸው ጊዜ የማይገድባቸውና የማይሰለቹ ሰማያዊ ስጦታዎች ናቸው፡፡

በተጨማሪም ሀገራችን ኢትዮጵያ ከመንፈሳዊው ምንጭ የተቀዳ የራሷ የሆነ ፊደል፣ አኃዝ (ቁጥር)፣ ቀናትና አዝማናት መቁጠሪያ (ካላንደር) ያላት በመሆኗ ከሌላው የዓለም ክፍል ይልቅ በዚህ መንፈሳዊና ሥጋዊ ጥበቧ የተለየች ያደርጋታል፡፡

የሙዚየሙ ዋና ዓላማ

 • 1.    ሃይማኖታዊና ታሪካዊ የሆኑትን የቤተክርስቲያን ቅርሶች በሙዚየም ውስጥ በማደራጀት በልዩ ጥበቃና እንክብካቤ ይዞ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር ጐብኝዎች በማስጐብኘት የቤተክርስቲያኒቱን ታሪካዊ ገጽታ በዓለም ደረጃ እንዲታወቅ ማድረግ፣

እነዚህኑ አስደናቂ ታሪኮችንና ሃይማኖታዊ ቅርሶችን በጥንቃቄ ጠብቆ በመያዝ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ነው፡፡

ከእነዚህም መካከል ለአብነት ያህል በየክፍላቸው መድበን እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡

1ኛ. ከታሪካዊ ቅርሶች

 • የነገሠታቱ የቤተ ክርስቲያን ውስጥ የክብር ዙፋኖች፣
 • የነገሥታቱ የአርበኝነት አልባሳት፣
 • በሞዛይክ ቅርፅ የተዘጋጀ የአፄ ኃይለ ሥላሴ ምስል (ፖርትሬት) እና ሌሎችም፣

2ኛ. ከሃይማኖታዊ ቅርሶች

 • በተለያየ ዲዛይን የተሠሩ መስቀሎች፣
 • ልዩ ልዩ ጽዋዎችና ጻሕሎች ከነእርፈ መስቀሎታቸው፣
 • የተለያዩ ወርቀ ዘቦና የብር ጥልፍ (ሙካሽ) ሥራ ካባዎችና ድባብ ጥላዎች፣
 • የተለያዩ የብራና ቅዱሳት መጻሕፍት ገበታቸው በወርቅና በብር የተለበጡ ጭምር፣
 • ከዕንቀ፣ ከብርና ከሞዛይክ የተሠሩ ቅዱሳት ሥዕላት፣ ሥነ-ስቅለትና የመሳሰሉት ይገኛሉ፣

የሰጭዎቹም ዘርዝር

 • ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና ከሌሎችም አባቶች፣
 • ከዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ፣
 • ከቀ አፄ ኃይለ ሥላሴ፣
 • ከንግሥት ዘውዲቱ፣
 • ከእቴጌ ጣይቱ፣
 • ከእቴጌ መነን፣
 • ከልዑላትና ከልዕልቶቹ፣
 • ከቀድሞ ቤተ መነግሥት ባለሥልጣናት፣
 • ከበጎ አድራጊ ክርስቲያኖች፣
 • ከአኀት አብያተ ክርስቲያናትና ከሌላም

እነዚህም ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ቅርሶች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ይልቁንም ባለሀብቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚገባ ጠብቆና ተንከባክቦ ለቱሪዝም ሴክተሩ እንቅስቃሴ ቢጠቀምባቸው በብዙ መልኩ ከፍ ያለ ሀገራዊ ፋይዳ ይኖራቸዋል እንላለን፡፡ሙሉውን መረጃ ለማግኘት መጥታችሁ ትጐበኙ ዘንድ ቤተ ክርስቲያናችን በአክብሮት ትጋብዛችኋለች፡፡