የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ት/ቤት

በ1955 ዓ.ም. መስከረም 14 ቀን በማታ ፕሮግራም ሥራውን የጀመረው የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ት/ቤት በወቅቱ የተቀበላቸው ተማሪዎች 8 ብቻ ሲሆኑ እነዚህን መነኮሳትና ዲያቆናት ነበሩ፡፡ በ1956 ዓ.ም. ከ1ኛ እስከ 4ኛ ባሉ ቁጥራቸው 39 የሚደርሱ ተማሪዎችን ይዞ የመደበኛ ትምህርት ጀመረ፡፡ በዚያን ጊዜ የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ት/ቤት “የኢትዮትያ ኦርቶዶክስ ሐዋርያዊ ድርጅት” በመባል ይታወቅም ነበር፡፡

ት/ቤቱን ለመክፈት ያስፈለገበት ዓላማም የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ዘመናዊ ትምህርት እንዲያገኙ ታስቦበት ሲሆን ለዚህም ተግባራዊነት የጥንቱ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ት/ቤት የ1ኛና 2ኛ ደረጃ ት/ቤት መዘጋቱ ለት/ቤቱ በዚያን ወቅት መጀመር ተጽዕኖ እንደነበረው ይነገራል፡፡ የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዘመናዊ ት/ቤት ሊቋቋም የተጠና ዓላማ ይዞ ነበር፡፡

ይኽም ዓላማ ካህናትን ዘመናዊ ትምህርት ለማስተማር ነው፡፡ በወቅቱ ለነበሩ መነኮሳትና ዲያቆናት የዘመናዊ ትምህርት እንዲማሩ ማድረግ በቀላሉ የተከናወነ ሳይሆን በወቅቱ የነበሩ የካቴድራሉ የበላይ አስተዳዳሪዎች ጥብቅ ቁጥጥርና እርምጃ እያደረጉ የቤተክርስቲያኑ አገልጋዮች ት/ቤት ገብተው እንዲማሩ በማድረጋቸው ነበር፡፡

ምንም እንኳ ት/ቤቱ በተጀመረበት ወቅትና ከዚያ ቀጥሎ ባሉት ዓመታት በት/ቤቱ በየዓመቱ ይማሩና ያስተምሩ የነበሩ መምህራን የመማሪያ ክፍሎች ብዛትና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ሠራተኞችና ክፍሎች በስርዓቱ መረጃ ባለመያዙ ምክንያት በዚሁ ጽሑፍ ውስጥ ለማቅረብ የተሞከረው የተገኘው መረጃ ብቻ ነው፡፡

ተ.ቁ ዓ.ም. የተማሪ ቁጥር የመምህራን ቁጥር
1 1955 8 የማታ ተማሪ ብቻ አልታወቀም
2 1956 39 መደበኛ ተማሪ አልታወቀም
3 1958 3ዐዐ ተማሪዎች አልታወቀም
4 1964 425 ተማሪዎች 15
5 1965 78ዐ ተማሪዎች 20
48 2003 2354 ተማሪዎች 34

ቀደም ሲል ለቀሳውስት መነኮሳትና ዲያቆናት ዘመናዊ ትምህርት እንዲያገኙ ታስቦ የተቋቋመው የካቴድራሉ ት/ቤት አገልግሎቱን ወደ ሌላው የህብረተሰብ ክፍል እንዲዳረስ አድርጓል፡፡ የቤተክርስቲያኗ አንዱ ዓላማ ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት ሲሆን ልጆቻቸው እንዲማሩላቸው ይጠይቁ የነበሩ ችግረኛ የህብረተሰብ ክፍሎች ያለክፍያ እንዲማሩ ሲደረግ በአካባቢ የነበሩ ጫማ ጠራጊዎች፣ መጽሔትና ጋዜጣ ሻጮች የትምህርት ዕድሉን እንዲያገኙ ተደርጓል።

ቀደም ሲል በት/ቤቱ ይሰጥ የነበረው ሥርዓተ ትምህርት

 • የቤተ ከርስቲያን ታሪክ
 • የመጽሐፍ ቅዱስ
 • የኃይማኖት ትርጓሜ
 • ቅኔና ዜማ

ከዘመናዊ ሥርዓተ ትምህርቶች ጋር ይሰጥ ስለነበረ ት/ቤቱ ታዋቂነትና ዝና ያገኘው በጣም በፈጠነ ሁኔታ ነበር፡፡ ለዚህም በዋነኝነት ሲጠቀስ የሚችለው ተማሪዎች በትምህርት ችሎታቸው በትህትናቸውና በሥርዓት አክባሪነታቸው ተለይተው ስለሚታወቁና ይኸም የህብረተሰቡን ትኩረት መቆጣጠር በመቻሉ ነበር፡፡

የተማሪዎች ቁጥር ሲጨምርና ት/ቤቱም ሲያድግ ተማሪዎች መጠነኛ ክፍያ እንዲከፍሉና የተሻለ የትምህርት አገለግሎት እንዲያገኙ ከህብረተሰቡ ጥያቄው በመቅረቡ በ1962 ዓ.ም. መጠነኛ ክፍያ-አምስት ብር-እንዲከፈል ተወስኖ ከዚያ ጀምሮ ትምህርት በክፍያ ሆነ፡፡
ት/ቤቱን ፈላጊው ሕብረተሰብ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥሩ እየጨመረ በመሄዱና ማስተናገድ ከሚችለው በላይ በመሆኑ የተማሪ ቅበላ የሚከናወነው በየዓመቱ ኮሚቴ እየተቋቋመ ኮሚቴው በሚያወጣው የመቀበያ መስፈርት አማካይነት ነበረ፡፡

ት/ቤቱ መጀመሪያ ሲቆረቆር ይዞት የነበረው ቦታ አሁን የካቴድራሉ ጽ/ቤት ጀርባ በነበሩ ክፍሎተ ነበር፡፡ የተማሪ ቁጥር እያደገ ሲሄድ ደግሞ አሁን 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ያለበትን ቦታ ይዞ እስከ 1968 ዓ.ም. ድረስ 12ኛ ክፍል ደረጃ አድርሶና 12ኛ ክፍል በዚሁ ት/ቤት አንድ ጊዜ የብሔራዊ ፈተና አስፈትኖ በወቅቱ በተደረገበት ተጽዕኖ ደረጃው ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ባለው ደረጃ በቻ እንዲሆን ተደረገ፡፡

የ1966 ዓ.ም. አብዮትን ተከትሎ የመጣው ሥርዓት በት/ቤቱ ዕድገት ላይ ተጽዕኖ ቢኖረውም በእርሾነት እንዲቆይና ለዛሬው ደረጃ እንዲደርስ የካቴድራሉ አስተዳዳሪዎችና ሠራተኞች ከፍተኛ ጥረትና መስዋዕትነት መክፈላቸው የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ይኸም በመሆኑ ዛሬ የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ት/ቤት በሦስት የትምህርት ዕርከኖች ወይም ደረጃዎች ተደራጅቶ በርካታ ወጣቶችን እያስተማረ ይገኛል፡፡ እነዚህም ት/ቤቶች፡-

 • 1.    አፀደ ህፃናት
 • 2.    የ1ኛ ደጃ ት/ቤት
 • 3.    የ2ኛ ደረጃ እና መሰናዶ ት/ቤቶች ናቸው፡፡

በ2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎችን እንደገና ማስተናገድ የጀመረው በ1ኛ ደረጃው ት/ቤት በ1996 ዓ.ም 9ኛ ክፍል በመክፈት ነበር፡፡
በ1997 ዓ.ም. አዲስ ያሰራውን ህንፃ ለ2ኛ ደረጃና ኮሌጅ መሰናዶ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተናገደ ይገኛል፡፡

በመሆኑም ት/ቤቱ በአሁኑ ጊዜ ከመዋዕለ ሕጻናት እስከ ኮሌጅ መሰናዶ ድረስ ከ2,000 ያላነሱ ተማሪዎችን እየተቀበለ ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት በመስጠት ላይገኛል፡፡ከትምህርቱ ጥራትም የተነሳ ተማሪዎች በሁሉም ብሔራዊ ፈተናዎች ከፍተኛ ውጤት እያመጡ ከደረጃ ወደ ደረጃ እያለፉ ስለመጡ የመንበረ ጸበዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ት/ቤት በተገልጋዩ ህብረተሰብ ዘንድ በአዲሰ አበባ ከሚገኙ እውቅ ት/ቤቶች አንዱ ለመሆን በቅቷል፡፡በዚህም ምክንያት ት/ቤቱ በአሁኑ ጊዜ ለህብረተሰቡ እየሰጠ ያለው ት/ት ካቴድራሉን ብቻ ሳይሆን የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክርስቲያንም የሚያኮራና የሚያስመሰግን ት/ቤት ሆኗል፡፡

 

 

የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተ መዘክር (ሙዚየም)

አደረጃጀትና ይዘት በአጭሩ

ቀደም ባሉት ጊዜያት ካቴድራሉ በሙዚየምነት ሲጠቀምበት የነበረው ከካቴድራሉ ቤተ መቅደስ አንደር ግራውንድ (ምድር ቤት) የሚገኘውን የዕቃ ግምጃቤት እንደ ነበረ ቀደምት ታሪኩን እናስታውሳለን፡፡ ይህ ደግሞ ከምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን መጠበቅና ሥርዓት አንፃር ቦታው ለጉብኝቱ ሂደት አመች አልነበረም፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ባላቸው ፅኑዕ እምነት፣ ለቱሪዝም ዕድገትና መስፋፋት በነበራቸው ከፍ ያለ ራዕይና ከውጭው ዓለም ተሞክሮ በመነሣት ባደረባቸው መንፈሳዊ ቅንዓት በመነሳሳት በተከበሩ በከCረ ምዕመናን ከበደ ተካልኝ በግል ገንዘባቸው ተሠርቶ በበጎ አድራጎት ለሥላሴ ከተሰጠው ዘመናዊ የሙዚየም ሕንፃ ቅርሶቹ ተዛውረው ከተደራጁ በኋላ ጥር 6 ቀን 1998 ዓ.ም. በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም፣ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚዳንትና የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዚዳንት ቡራኬ ተመርቆ ከተከፈተበት ጊዜ ጀምሮ ከቱሪዝም መዳረሻዎችና መስህቦች አንዱ ክፍል ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡

በዚህም ደረጃውን በጠበቀ ዘመናዊ ሙዚየም ውስጥ በጥሩ አደረጃጀትና ጥበቃ ተይዘው በመጎብኘት ላይ ያሉ በርካታ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ቅርሶች ይገኛሉ፡፡ እነዚህም ውድና ማራኪ የሆኑ ቅርሶች በዋጋ ሊተመኑና በምንም ሁኔታ ሊተኩ የማይችሉ ናቸው የተሰጡትም ከቀድሞ ነገሥታት፣ ከእቴጌዎቹ፣ ከብፁዓን አባቶች፣ ከቤተ መንግሥት ልዑላንና ልዕልቶች፣ ከቀድሞ ከመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ከበጎ አድራጊ ክርስቲያኖችና ከ5ቱ አኅት ዐቢያተ ክርስቲያናትም ጭምር ሲሆን ደኅንነታቸውም ለረጅም ዘመናት በሚባ ተጠብቆላቸው ከዚህ ትውልድ ደርሰዋል፡፡

የተሠሩትም ከወርቅ፣ ከብር፣ ከነሐስና ከመሳሰሉት ማዕድናት ሲሆን የወርቅና የብር ቅቦችንም ያጠቃልላል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ከጥልፍ (ሙካሽ) ሥራ የተዘጋጁ የቤተ መቅደስ አልባሳት፣ ድባብ ጥላዎችና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ይልቁንም በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ በተለያዩ ጸሐፍትና አርእስት በግእዝ ቋንቋ የተጻፉ በርካታ ሃይማኖታዊ የብራና ቅዱሳት መጻሕፍትም የዚሁ ሙዚየም ታዳሚዎች ናቸው፡፡

ከእነዚህም ቅዱሳት መጻሕፍት መካከል በ6ኛው መ/ክፍለ ዘመን በቅ/ያሬድ በ8 የዜማ ምልክቶችና በ3 የዜማ ቅኝቶች ከተደረሱት አምስቱ የዜማ መጻሕፍት ውስጥ አንዱና ከ5ዐዐ ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆረጠው ድጓ ተብሎ የሚታወቀው መጽሐፍ በይዘቱም ሆነ በጣዕመ ዜማው በእጅጉ ከሚመስጡትና ከሚያስደንቁት ዋነኛው ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንም ከእነዚህ ከ3ቱ ቅኝቶች ውጭ የሆኑ የዜማ ስልቶች የሏትም አትጠቀምም፡፡ ቅኝቶቹም ዘመን የማይሽራቸው ጊዜ የማይገድባቸውና የማይሰለቹ ሰማያዊ ስጦታዎች ናቸው፡፡

በተጨማሪም ሀገራችን ኢትዮጵያ ከመንፈሳዊው ምንጭ የተቀዳ የራሷ የሆነ ፊደል፣ አኃዝ (ቁጥር)፣ ቀናትና አዝማናት መቁጠሪያ (ካላንደር) ያላት በመሆኗ ከሌላው የዓለም ክፍል ይልቅ በዚህ መንፈሳዊና ሥጋዊ ጥበቧ የተለየች ያደርጋታል፡፡

የሙዚየሙ ዋና ዓላማ

 • 1.    ሃይማኖታዊና ታሪካዊ የሆኑትን የቤተክርስቲያን ቅርሶች በሙዚየም ውስጥ በማደራጀት በልዩ ጥበቃና እንክብካቤ ይዞ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር ጐብኝዎች በማስጐብኘት የቤተክርስቲያኒቱን ታሪካዊ ገጽታ በዓለም ደረጃ እንዲታወቅ ማድረግ፣

እነዚህኑ አስደናቂ ታሪኮችንና ሃይማኖታዊ ቅርሶችን በጥንቃቄ ጠብቆ በመያዝ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ነው፡፡

ከእነዚህም መካከል ለአብነት ያህል በየክፍላቸው መድበን እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡

1ኛ. ከታሪካዊ ቅርሶች

 • የነገሠታቱ የቤተ ክርስቲያን ውስጥ የክብር ዙፋኖች፣
 • የነገሥታቱ የአርበኝነት አልባሳት፣
 • በሞዛይክ ቅርፅ የተዘጋጀ የአፄ ኃይለ ሥላሴ ምስል (ፖርትሬት) እና ሌሎችም፣

2ኛ. ከሃይማኖታዊ ቅርሶች

 • በተለያየ ዲዛይን የተሠሩ መስቀሎች፣
 • ልዩ ልዩ ጽዋዎችና ጻሕሎች ከነእርፈ መስቀሎታቸው፣
 • የተለያዩ ወርቀ ዘቦና የብር ጥልፍ (ሙካሽ) ሥራ ካባዎችና ድባብ ጥላዎች፣
 • የተለያዩ የብራና ቅዱሳት መጻሕፍት ገበታቸው በወርቅና በብር የተለበጡ ጭምር፣
 • ከዕንቀ፣ ከብርና ከሞዛይክ የተሠሩ ቅዱሳት ሥዕላት፣ ሥነ-ስቅለትና የመሳሰሉት ይገኛሉ፣

የሰጭዎቹም ዘርዝር

 • ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና ከሌሎችም አባቶች፣
 • ከዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ፣
 • ከቀ አፄ ኃይለ ሥላሴ፣
 • ከንግሥት ዘውዲቱ፣
 • ከእቴጌ ጣይቱ፣
 • ከእቴጌ መነን፣
 • ከልዑላትና ከልዕልቶቹ፣
 • ከቀድሞ ቤተ መነግሥት ባለሥልጣናት፣
 • ከበጎ አድራጊ ክርስቲያኖች፣
 • ከአኀት አብያተ ክርስቲያናትና ከሌላም

እነዚህም ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ቅርሶች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ይልቁንም ባለሀብቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚገባ ጠብቆና ተንከባክቦ ለቱሪዝም ሴክተሩ እንቅስቃሴ ቢጠቀምባቸው በብዙ መልኩ ከፍ ያለ ሀገራዊ ፋይዳ ይኖራቸዋል እንላለን፡፡ሙሉውን መረጃ ለማግኘት መጥታችሁ ትጐበኙ ዘንድ ቤተ ክርስቲያናችን በአክብሮት ትጋብዛችኋለች፡፡

 

 

 

 

የልማት እንቅስቃሴዎች

ካቴድራሉ በልማት በኩል የተከተለው አቅጣጫ

የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በሁሉም አቅጣጫ መሪ እንደመሆኑ መጠንና አስተዳደራዊ ይዘቱም ሰፊ በመሆኑ ገቢው ያኑ ያህል በቂ መሆን ስለሚገባው ከመንግሥት ከተሰጠው ጋሻ መሬት በተጨማሪ ት/ቤት፣ የሙካሽ ሥራ፣ የሥጋጃ ሥራ፣ የአልባሳት ማዘጋጃ፣ የመጻህፍት ማዘጋጃ እና በነዚህ ክፍሎች የተዘጋጁትን የምርት ውጤቶች ለሕዝብ በማቅረብ የሚከፋፈሉባቸው ሱቆች ከአዲስ አበባ እስከ ክ/ሀገር አቋቁሞ ነበር፡፡

ከነዚህ በተጨማሪ ዘመኑ እየሰለጠነ በሄደ መጠን ካቴድራሉ ከህብረተሰቡ የዕድገት ደረጃ ጋር አብሮ እንዲራመድ ከአካባቢው በጣም ዘመናዊና ጠንካራ የሆኑ ሕንፃዎችን አስገንብቶ ከኪራይ በሚያገኘው ገቢ አስተዳደራዊ ዘርፉን ለማስፋፋት ችሎ ነበር፡፡ ፍልውሃ ያለውን ዘመናዊ ሆቴል የራሱ በማድረግ ከቅድስት ሥላሴ ማየ ሕይወትና ከሆቴሉ ከፍ ያለ ገቢ ያገኝ ነበር፡፡ይህ ሁሉ ገቢ በ1966 ዓ.ም. በተደረገው የመንግሥት ለውጥ ካቴድራሉ በማንኛውም የሀገሪቱ ክፍል እንደደረሰው ሁሉ ሀብቱ ሲወረስ ብዙ ገቢ የሚያስገኝለት ት/ቤትም ደረጃው ከ12ኛ ወደ 8ኛ ክፍል ዝቅ እንዲል በመደረጉ የነበረው ፈጣን እንቅስቃሴ ተገታ፡፡
የካቴድራሉ አስተዳደር ጊዜውን ተከትሎ በዘዴ እየተራመደ ት/ቤቱን በወቅቱ አስተዳዳሪ በነበሩት ሊቀሥልጣናት አባ ሀብተ ሥላሴ (ዶ/ር በአቡነ ጢሞቴዎስ) ጥረት ሳይወሰዱ በቀሩት ቦታዎች ምእመናኑን በማደራጀት ሥራው ሳይቋረጥ ሲያዘግም ቆይቶ ቀስ በቀስ የካቴድራሉን ገቢ ሊያዳብሩ የሚችሉ ቋሚ ተግባራትን ሲያከናውኑ እንደነበር ይነገራል፡፡

 • 1.    ሁለገብ አዳራሽ

ይህ አዳራሽ በሊቀ ሥልጣናት አባ ገብረ ማርያም አጽብሐ የተሠራ ሲሆን እጅግ ዘመናዊ እቅድን ተከትሎ የተሠራ ሆኖ ለሠርግ፣ ለስብሰባ፣ ለሙት ዓመት፣ መታሰቢያና ለመሳሰሉት አገልግሎቶች፣ ለአገልጋዮች በነፃ አገልግሎት ሲሰጥ ለውጭ ሰዎች ደግሞ በገንዘብ ይከራያል፡፡ ከአዳራሹ ጋር ተያይዞ የተሠራው የፉካ መቃብርም ለ7 ዓመታት ውል እየተከራየ የካቴድራሉን ገቢ በማሳደግ ላይ ከመሆኑም ሌላ አብሮ የተገነባው ፎቅም ለልዩ ልዩ ድርጅቶች ተከራይቶ ቋሚ ገቢ በማስገኘት ላይ ነው፡፡

 • 2.    ከፍተኛ ክሊኒክ

ይህ ሕንፃ በአንዲት የተከበሩ የቤተክርስቲያን ልጅ ከሆኑት ከወ/ሮ እስከዳር ገ/ሕይወት አስተዋጽኦ ጭምር የተገነባ ዘመናዊ ክሊኒክ ሲሆን ሥራው ተጠናቆና ተመርቆ ካቴድራሉ ለባለሙያዎች አከራይቶት ሥራውን እያካሄደ ይገኛል፡፡

 • 3. ት/ቤት

ሥላሴ ት/ቤት በአንዲት ክፍል በ1955 ዓ.ም. ለካህናት ማሰልጠኛ ተብሎ በማታው ትምህርት ክፍል የተጀመረው ት/ቤት አድጎና ተስፋፍቶ ከላይ እንደተገለጸው ተቋርጦ የነበረው  የ2ኛ ደረጃ ትምህርት በወቅቱ የካቴድራሉ አስተዳዳሪ በነበሩት ሊቀ ሥልጣናት አባ ሐረገወይን ገብረ ሥላሴ /አቡነ ሠላማ/ አስተባባሪነት በማኅበረ ካህናትና በመላው ሠራተኛ ጥረት እጅግ ባማረ እና በተዋበ የተገነባው ሕንፃ ጥቅምት 2ዐ ቀን 1997 ዓ.ም. ተመርቆ ሥራ ላይ ውሏል፡፡ ይህም የሚያሳየው ካቴድራሉ ርእሰ አድባራትና ገዳማት እንደመሆኑ መጠን ሌሎች አብያተክርስቲያናት ፈለጉን ተከትለው ብዙ ሥራዎችን እያከናወኑ በመሆናቸው አሁንም የመሪነቱን ሥፍራ አለመልቀቁን ያሳያል፡፡ ካቴድራሉ በነባሩ ት/ቤት ባለው ሰፊ ቦታ በቅርብ ጊዜ ዘመናዊ ሕንፃ ገንብቶ ኮሌጅ ለመክፍት እቅድ ይዟል፡፡ ይህ ኮሌጅ ሲከፈትም ካቴደራሉ በሁለገብ መልኩ ተጠቃሚ ከመሆኑም ሌላ በውስጡ ያሉ ካህናት፣ መምህራንና ሠራተኞች እውቀታቸውን ይበልጥ እንደሚያሳድጉበት ይጠበቃል፡፡

 • 4. በአሁኑ ወቅትም  በ22 ማዞሪያ ባለ 4 ፎቅ ህንፃ በመሠራት ላይ ይገኛል.

የቤተክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎት

ይህ ክፍል ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን፣እንደ አጽዋማት፣ ታላላቅ በዓላት እና የመሳሰሉትን መርሐግብሮች ጊዜውን ጠብቆ ፕሮግራም በማውጣት ሕዝቡን የሚያገለግል ሆኖ በተጨማሪም ልዩ ልዩ መንፈሳዊ አገልግሎቶች ዕለቱንና ሰዓቱን  ጠብቀው እንዲፈጽሙ መዘምራኑን፣ ልዑካኑንና ተጓዳኝ አገልጋዮችን የሚመራና የሚቆጣጠር የመንፈሳዊ አገልግሎት ክፍል ነው፡፡

የቤተክርስቲያኑ ሥዩማን

የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሕዝቡን በሠለጠነ መንገድ ለማገልገል እንዲቻል የሚከተሉት የቤት ክርስቲያን ሥዩማን አሉት፡፡ ሥራቸውም የቤተ እግዚአብሔር አገልግሎት እንዳይታጎል ካህናትን ሠርተው የሚያሠሩ ናቸው፡፡
እነርሱም፡-

 • 1.    ሊቀጠበብት
 • 2.    ቄሰ ገበዝ
 • 3.    ርዕሰ ደብር
 • 4.    ቀኝ ጌታ ፣ግራ ጌታ ፣ አጋፋሪና
 • 5.    ሊቀ ዲያቆናት እየተባለ በየማዕረጋቸው ይጠራሉ፡፡

ከአጋፋሪና ከሊቀ ዲያቆናት በታች ያሉት ደግሞ መጨኔዎች ሲባሉ የሥርዓተ ማሕሌቱን ዕቃዎች በኃላፊነት ከመጠበቅ ሌላ የምርፋቁ ሥርዓት በአግባቡ እንዲከናወን ተግተው ይሠራሉ (ያሠራሉ)፡፡የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በ  365.5 ቀናት (በ13 ወራት)፣ በ4 ሳምንታትና ከሰኞ እስከ እሁድ ባሉት የሳምንት ቀናት በዓመታዊ በዓላት፣ በአጽዋማት፣ እና በመሳሰሉት ካህናቱን፣ ዲያቆናቱን፣ መዘምራኑንና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችን በማስተባበር በሰዓታት፣ በማህሌትና በቅዳሴ ሰፊ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ከቅዳሴ መሀል ከቅዳሴ ውጭና በቀኑ የጸሎት ሰዓት በተጓዳኝ ሰፊ የወንጌል ስርጭት በመስጠት የስብከት ሥራን በሰፊው ያካሂዳል፡፡

ይህ መንፈሳዊ አገልግሎት ክፍል በባዕዳን እምነት ወጣቱ እንዳይነጠቅ እና ተተኪ የቤተክርስቲያን ተከታዮችን ለማፍራት እንዲቻል የተለያዩ ኮርሶችን በማዘጋጀት ወጣቶችን በእምነት ያንፃል፡፡

አስተዳደራዊ መዋቅር

እንደዘመናዊነቱ ሁሉ አስተዳደሩም በዚሁ እቅድ እንዲመራ የካቴድራሉ አመራር በሚከተለው መልክ ተደራጅቷል፡፡

 

 

  • 1. ሰበካ ጉባዔ፡- ይህ ክፍል ሌሎች ክፍሎችን የሚቆጣጠር ሆኖ የሁሉም ራስ የሆነው የካቴድራሉ ዋና ጽ/ቤት ነው፡፡
  • 2. የቤተክርስቲያን አገልግሎት፡- ይህ ክፍል ሥርዓተ ቤተክርስቲያን እንደ አጽዋማት፣ ታላላቅ በዓላት እና የመሳሰሉትን ጊዜውን ጠብቆ ፕሮግራም በማውጣት ሕዝቡን የሚያገለግል ሆኖ በተጨማሪም ልዩ ልዩ መንፈሳዊ አገልግሎቶች ሰዓቱን ዕለቱን ጠብቀው እንዲፈጸሙ መዘምራኑን፣ ልዑካኑንና ተጓዳኝ አገልጋዮችን የሚመራና የሚቆጣጠር መንፈሳዊ አገልሎት ክፍል ነው፡፡
  • 3. ንብረት ክፍል፡- ይህ ክፍል በስጦታ የሚገኘውን በፊትም የነበረውን ንብረት የሚጠብቅ፣ ለወደፊትም የገንዘብ ምንጭ የሚገኝበትን መንገድ በሰፊው የሚያጠናና የተገኘውንም ንብረት በአግባቡ የሚጠብቅና የሚቆጣጠር ክፍል ነው፡፡
  • 4. ሙዚየም፡- ይህ ክፍል ጥንታውያን የሆኑ ንዋያተ ቅድሳትን፣ አልባሳትን፣ መጻሕፍትንና የመሳሰሉትን የሚጠብቅ ሌሎችንም ጥንታውያን የሆኑ ዕቃዎችን እየገዛ የሚያጠራቅም ለጐብኝዎችም ሰዓቱን፣ ዕለቱን ለይቶ የሚያሳውቅና የሚያስጐበኝ ክፍል ነው፡፡ ካቴድራሉ በዚህ ክፍል ውስጥ የተለያዩ የመስቀል ዓይነቶችን ያሳተማቸውን አያሌ መጻህፍትንና በስጦታ የተገኙ ንዋያተ ቅድሳትን አስቀምጦ ለአያሌ ጐብኝዎች በማስጐብኘት ላይ ይገኛል፡፡
  • 5. ቁጥጥር ክፍል ፡- ይህ ክፍል ካቴድራሉ እንደ ዕድገት ደረጃው ቀስ በቀስ ያቋቋማቸው አገልግሎት መስጫ ክፍሎች ቁጥጥር ክፍል ይህ ክፍል ከተለያዩ አቅጣጫ የተሰበሰበ ገንዘብና ልዩ ልዩ ንዋያተ ቅድሳት በአግባቡ ተመዝግቦ ገቢና ወጪ መሆኑን የሚከታተል ክፍል ነው፡፡
  • 6. ሒሳብ ክፍል፡- ይህ ክፍል በልዩ ልዩ መንገድ የተሰበሰበውን ገንዘብ በዘመናዊ ቀመር አስልቶና መዝግቦ ያመቱን ገቢና ወጪ ለይቶ በማሳየት የሒሳብ ሥራው ሥርዓት ባለው መንገድ እንዲከናወን የሚያደርግ ሲሆን ለሰራተኞች በየወሩ የደመወዛቸውን መጠን እያሰላ እንዲከፈላቸው ለገንዘብ ቤት የሚያስተላልፍ ክፍል ነው፡፡
  • 7. ገንዘብ ቤት፡- ይህ ክፍል ከልዩ ልዩ ገቢዎች የተገኘውን ገንዘብ ከሒሳብ ክፍል በሚሰጠው ሰነድ መሠረት አገናዝቦ ገንዘቡን ባንክ በማስገባት የሚጠብቅና የሠራተኛ ደመወዝን የሚከፍል ክፍል ነው፡፡
  • 8. ሕግ ክፍል፡- ይህ ክፍል ካቴድራሉ ሕጋዊ ሰውነት ያለው ክፍል በመሆኑ የመከሰስም ሆነ የመክሰስ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ካቴድራሉን ወክሎ ሕጋዊ ሥራዎችን የሚያከናውን ክፍል ነው፡፡
  • 9. ምግባረ ሠናይ ክፍል፡-ይህ ክፍል የተለያዩ በጎ አድራጊ ግለሰዎችንና ድርጅቶችን ኢያስተባበረ ችግረኞችን የሚረዳ ክፍል ነው፡፡
  • 10. የቱሪስት አስጐብኚ ክፍል፡- ይህ ክፍል የተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ ጐብኚዎችን በመቀበልና ካቴድራሉ ያሉትን ቅርሳቅርሶች በማስረዳት የማስተናገድ ሥራን ያከናውናል፡፡
  • 11. የተክሊል እና የክርስትና ክፍል፡- ይህ ክፍል በሥርዓተ ተክሊልና ቅዱስ ቁርባን ጋብቻቸውን ለመፈፀም የሚመጡትን ተጋቢዎች፣ እንዲሁም ጥምቀተ ክርስትናን ለመቀበል የሚመጡትን ምዕመናን ተቀብሎ የሚያስተናግድና ማስረጃ አዘጋጅቶ የሚሰጥ ክፍል ነው፡፡
  • 12. መዝብ ቤትና እስታስቲክስም ይገኙበታል፡፡

 

ቅ/ሥ/ካቴድራል

ቤተክርስቲያን

የቤተክርስቲያን ቅድመ ታሪክ በአጭሩ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በርካታ ቋሚና ተንቀሳቃሽ የሆኑ ሃይማኖታዊ ትውፊትና ታሪካዊ ቅርሶችን ጠብቃ የያዘች ናት፡፡ ይህም ማለት በሕንጻ ግንባታና ከድንጋይ ተፈልፍለው የታነፁ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፡ ገዳማትና ታሪካዊ ሐውልቶች፣ የሥነ ጽሑፍ፣ የዕደ ጥበብ፣ የተለያዩ ንዋየ ቅዱሳትና የሌሎችም ቅርሶች ባለቤት መሆኗ ግልጽ ነው፡፡እነዚህ ደግሞ በዓለም አስደናቂ ከሆኑት ነገሮች መካከል በታሪካዊነታቸው ተመዝግበው የሚገኙ ናቸው፡፡

የቅድስት ሥላሴ ካቴድራልም ከእነዚሁ አስደናቂ ታሪኮች አንዱ አካል ነው፡፡ ካቴድራሉም በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ዓለም ዓቀፋዊ ይዘት ያለውና አንጋፋ ካቴድራል ነው፡፡

ከታሪካዊነቱም በተጨማሪ፡-

 • ዓለም አቀፋዊ የኃይማኖት ስብሰባዎች ይካሄድበታል፣
 • የፓትርያሪኮችና ጳጳሳት በዓለ ሲመት ይከናወንበታል፣
 • ብሔራዊ የመታሰቢያ በዓላትና ሥርዓተ ፀሎት ይካሄድበታል፡፡

የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ታሪክ

የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አመሠራረት

የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የተመሠረተው ታኅሣሥ 15 ቀን 1924 ዓ.ም. እንደሆነ ታሪካዊ ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ፡፡ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ የክርስትናው እምነት እንዲስፋፋና እንዲጠናከር የሀገራቸውም ዕድገትና ሥልጣኔ ከፍ ካለ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ከነበራቸው ቀና አመለካከትና ፅኑዕ ፍላጎት በመነሳትና የውጭውንም ዓለም ሥልጣኔ መልካም አርአያነት አብነት በማድረግ ይህን ዓለም አቀፍ ይዘት ያለውን ካቴድራል ለመመሥረት/ለመሥራት በቅተዋል፡፡

በዚህም ጊዜ አያሌ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና መኳንንት በዚሁ የመሠረት ድንጋይ የማኖር ከፍተኛ ሥነ ሥርዓት ላይ የታደሙ ከመሆኑም በላይ 113ኛው የእስክንድርያ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ዮሐንስ 19ኛ የሥነ ሥርዓቱ ተሳታፊ በመሆን ቡራኬ ሰጥተው የመሠረት ድንጋዩም በግርማልነታቸው ተጥሏል፡፡

የሕንፃ ግንባታው ስለመጀመሩ፡-

የሕንፃ ሥራው በንጉሠ ነገሥቱ ከፍ ያለ አጽንዖት ተሰጥቶበት እየተፋጠነ የበርና የመስኮት መግጠም ሥራ ብቻ ሲቀር የፋሽሽት ኢጣሊያ የግፍ ወረራ በመከሠቱ ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም. ድረስ ለአምስት ዓመታት የሕንፃ ግንባታው ተቋርጦ ቆይቷል፡፡ ቢሆንም በሥላሴ ኃይልና ቸርነት ግርማዊ ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ በድል አድራጊነት ወደ ውድ ሀገራቸው በተመለሱ በ2ኛው ዓመት በ1935 ዓ.ም. ሥራው እንደገና ቀጥሎ ተፋጥኖ በመሠራቱና ፍጻሜ በማግኘቱ ጥር 7 ቀን 1936 ዓ.ም. ሥራው እንደገና ቀጥሎ ተፋጥኖ በመሠራቱና ፍጻሜ በማግኘቱ ጥር 7 ቀን 1936 ዓ.ም. ቅዳሴ ቤቱ ከፍ ባለ ሥነ ሥርዓትና በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል፡፡

የቤተክርስቲያኑ ስም ለውጥ

በ1939 ዓ.ም. መካነ ሥላሴ መባሉ ቀርቶ ሥራው የተራቀቀ አስገራሚ ሆኖ በመኘቱ በሰማያዊት ኢየሩሳሌም አምሳል መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ተብሎ ሲሰየም አስተዳዳሪውም ሊቀ ሥልጣናት እንዲባል ተወሰነ፡፡

የመጀመሪያውም ተሻሚ መምህር መልእክቱ በኋላ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ናቸው፡፡ ይህ ዘመናዊ ካቴድራል ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት የተሻለ በመሆኑ ሕዝቡ በብዛት መጉረፍ ጀመረ፡፡ በዚህም ምክንያት በጣም ሰፊ ነው የተባለው ቤተክርስቲያን በድጋሚ ሊጠብ ቻለ፡፡ የሕዝቡ ቅሬታ ከመሰማቱ በፊት የቤተክርስቲያኑ አስተዳደር የንጉሠ ነገሥቱን ትዕዛዝ በመቀበል የሕንፃው ቁመትና ስፋት እንዲጨመር፣ ጌጣጌጡም የተሻለ ዘመናዊ እንዲሆን በዩኒዬን ኢንጂነሪንግ አጥኝነት በሥራ ሚኒስቴር ተቆጣጣሪነት በ1957 ዓ.ም. ሥራው ለሁለተኛ ጊዜ ተጀመረ፡፡
ሥራው ከልዩ ልዩ ዓለማት በመጡ የሕንፃ ጠበብትና በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ተቆጣጣሪነት 36 ሜትር በ12ዐዐ ካሬ ሜትር የወለሉ ስፋት፣ ከምሥራት ወደ ምዕራብ 36 ሜትር ከሰሜን ወደደቡብ 26 ሜትር፣ ቁመቱ 35 ሜትር ሆኖ ለ3 ዓመታት ያህል በጥራት ሲሰራ ከቆየ በኋላ በ196ዐ ዓ.ም. ተጠናቆ ጥር 7 ቀን በደማቅ ሥነ ሥርዓት ቅዳሴ ቤቱ ተከበረ፡፡

አዲሱ ሥራ ብዙ ውስጣዊ መሻሻሎችን ያካተተ ሆኖ ተገንብቷል፡፡ ይኸውም የንዋየ ቅድሳት፣ የአልባሳት፣ የመጻሕፍት አና ልዩ ልዩ ቅርሶች ማስቀመጫ በምሥራቅ በኩል ባለው ምድር ቤት የተዘጋጀ ሲሆን በምዕራብ አቅጣጫ ባለው ምድር ቤት ደግሞ የዕቃ ግምጃ ቤት፣ የማጥመቂያ ክፍሎች በዘመናዊ መልክ ተዘጋጅቶውለታል፡፡

ወደ ላይ ሲወጣ ደግሞ በፎቕ መልክ የተሠራው ቅኔ ማኅሌት የሕንፃውን ጠበብት በሚያስመሰግን ሁኔታ ተሰርቷል፡፡ በዚህ ድርብ ሥር የቤተክርስቲያኑ መሥራች ታላቁ ንጉሠ ነገሥት ግርማዊ ቀዳማዊ ዓፄ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ለልዩ ልዩ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ቋሚ መታሰቢያ እንዲሆን በጦር ሜዳ ለወደቁና ለሕያዋኑ ጦር ውለታቸውን ለመግለጥና በሕገ መንግሥቱ በ15ኛው ክፍል የተመለከተውን አይተው ይህንኑ ለመፈጸም፡፡

 • 1ኛ. ከ1927-1933 ዓ.ም. ያለውን የጦር ሠራዊት ሰንደቅ ዓላማ፣
 • 2ኛ. የክብር ዘበኛ ሰንደቅ ዓለማ፣
 • 3ኛ. ከ1927-1933 ዓ.ም. በጦር ሜዳ ለወደቁ ጀግኖች ሰንደቅ ዓላማ ሲሆኑ በኋላ በሀገሪቱ የተመሠረተውን ጠንካራ የአየር ሃይል፣ የባህር ኃይልና የምድር ጦር ሠራዊትን ለማክበር የተሰቀለውን ሰንደቅ ዓላማ በ4ቱም ባንዲራዎች ላይ የሥላሴ ኒሻን ያለው ተተክሎ እንዲውለበለብ በመፍቀዳቸው ሰንደቅ ዓላማዎቹ በመዘክርነት ይኖራሉ፡፡

በዚህ ካቴድራል ውስጥ አያሌ ሥዕሎች ስለነፃነት የተደረጉ ታሪካዊ ሂደቶችን በማመላከት በተለያዩ ክፍሎች ተሥለው ለትውልድ የታሪክ አሻራነታቸውን በማስተላለፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ ቅኔ ማኅሌቱ ለዘወትር ግልጋሎት የሚሰጥ ሲሆን በዓላት በሚከበሩበት ጊዜ ስለሚጠብ ከሕንፃው ሰሜን አቅጣጫ ባለው ሰፊ ክፍል በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ሊቃውንት ከተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ስለሚመጡ ሥርዓተ ማህሌቱ በተጠቀሰው ቦታ ሲካሄድ ያድራል፡፡

ከቅኔ ማህሌቱ ታች ያለው ቦታ በብዙ ሺህ የሚቆጠር ሕዝብ ይይዛል፡፡ ከቅድስቱ መግቢያ በስተቀኝ የንጉሠ ነገሥቱ ዙፋን በግራ በኩል የእቴጌ መነን ዙፋን በከበረ እንጨትና በአማረ ጌጣጌጥ ተሰርተው በታሪክነት ተቀምጠዋል፡፡ በግራ በኩል ሰሜን አቅጣጫ የንጉሡና የእቴጌይቱ መቃብር በከበረ ድንጋይ ተገንብቷል፡፡ ቃላቱ ንጉሠ ነገሥት እንደቀደምት አባቶቻቸው ነገሥታት አንድነትንና ሦስትነትን ለማስተማር በሥላሴ ስም ይህን ካቴድራል ሲያሰሩ ከራሳቸው ጀምሮ ንጉሣውያን ቤተሰብ ሁሉ ማረፊያው በዚሁ ቅዱስ ቦታ እንዲሆን በመመኘትም ጭምር መሆኑ አይካድም፡፡ መቅደሱ ሦስት መንበሮች ያሉት ሲሆን መካከለኛው በአጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ ስም የተሰየመ ሆኖ ከወርቅ፣ ከብር፣ ከዝሆን ጥርስና ከወይራ እንጨት የተሠራ ነው፡፡
በመንበሩ ላይ ልዩ ልዩ ስዕሎች፣ ንጉሣዊ ዘውድ፣ መላእክት፣ ምሴተ ሐሙስ፣ የሰሎሞን ኒሻን፣ የንግሥት ሳባ ኒሻንና የጰራቅሊጦስ ሥዕል እንዲሁም የጌታችንና የመድነኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የወርቅ ሥዕል የወይን፣ የስንዴ ቅርፅን አካቶ በመያዝ የቤተክርስቲያናችንን እምነትንና ታሪካዊነት በሰፊው ይገልጻል፡፡ የአርባዕቱ እንስሳ ቅርጽም በ4ቱ ማዕዘን አለ፡፡

ከዋናው ቤተመቅደስ በስተቀኝ በቅድስት ማርያም የተሰየመው መንበር በስተደቡብ ይገኛል፡፡ ስያሜውም የሥላሴን ሦስትነት ለማወቅ ነው፡፡
ከዋናው መቅደስ በስተግራ በቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ የተሰየመው መንበር በስተሰሜን ይገኛል፡፡ በቅዱስ ዮሐንስ የተሰየመበት ምክንያት አንድነት ሦስትነት የታወቀው ከጥምቀት በኋላ መሆኑን ለማዘከር ነው፡፡

አገር ጐብኝዎች

በካቴድራሉ ግራና ቀኝ የማስታወቂያ ግድግዳዎች ላይ እጅግ ማራኪ የሆኑ ስለ ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን ታሪክ የሚያስረዱ ሥዕላት ይገኛሉ፡፡ እንዲሁም በግድግዳ ላየ የተሳሉ ታሪካዊ መንፈሳዊ ሥዕሎችም ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ሥዕሎች በኢትዮጵያዊ ታዋቂ ሠዓሊ በአገኘሁ እንግዳ የተሣሉ ናቸው፡፡

መቃብሮች

የጃንሆይና የባለቤታቸው የእቴጌ መነን መቃብሮች በካቴድራሉ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ መቃብሮቹ ሦስት ታሪካዊ ነገሮችን ያንፀባርቃሉ እነርሱም፡-

 • የአክሱም ሀውልትን፣
 • አንድ የላሊበላ ውቅር ቤተክርስቲያን፣
 • የይሁዳ አንበሳ፣

ዙፋኖች

 • በካቴድራሉ ቅድስት ውስጥ የጀንሆይና የእቴጌ መነን ዙፋኖች ይገኛሉ፡፡

እስከ አሁን የተሾሙ የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አስተዳዳሪዎች (ከ1935 -2004)

 1. ሊቀ ሥልጣናት አባ መልእክቱ /ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ/1935-1938/
 2. ሊቀ ሥልጣናት አባ ቄርሎስ ተስፋዬ /አቡነ ቄርሎስ/ /1949-1954/
 3. ሊቀ ሥልጣናት አባ ሀ/ማርያም ወርቅነህ /አቡነ መልከፄዲቅ/1954-1966/
 4. ሊቀ ሥልጣናት አባ መዓዛ ቅዱሳን /1966-1967/
 5. ሊቀ ሥልጣናት ዶ/ር አባ ሀ/ሥላሴ ተስፋ /አቡነ ጤሞቲዎስ//1968-1969/
 6. ሊቀ ሥልጣናት አባ ኤልያስ አበበ /አቡነ ኒቆዲሞስ/ /1969-1971/
 7. ሊቀ ሥልጣናት ገብረማርያም ፈለቀ /አቡነ ፊሊጶስ/ /1971-1973/
 8. ሊቀ ሥልጣናት አባ ገ/ሥላሴ ኃ/ማርያም /አቡነ አረጋዊ/1973-1979/
 9. ሊቀ ሥልጣናት ተክለሚካኤል ዓባይ /አቡነ ሚካኤል/ከ1979-1980/
 10. ሊቀ ሥልጣናት አባ ዳንኤል ባሳዝነው/1980-1984/
 11. ሊቀ ሥልጣናት አባ ገብረ ማርያም አጽብሐ /ቆሞስ/1986-1989/
 12. ሊቀ ሥልጣናት አባ አምኃሥላሴ አሳየኸኝ / አቡነ ኢጲፋንዮስ/1989-1990/
 13. ሊቀ ሥልጣናት አባ ሐረገወይን ገብረ ሥላሴ /አቡነ ሠላማ/1991-1996/
 14. ሊቀ ሥልጣናት አባ ገብረ ክርስቶስ ስብሐት /ቆሞስ/1996-1998/
 15. ሊቀ ሥልጣናት አባ ጥዑመ ልሳን ኪዳነማርያም /ቆሞስ/1998-2004/
 16. ሊቀ ሥልጣናት አባ ገ/ሥላሴ በላይ/ቆሞስ/ ከ2004-2006 ዓ.ም
 17. ሊቀ ሥልጣናት አባ ኪሮስ ፀጋዬ /ቆሞስ/ ከ2006-2008 ዓ.ም
 18. ሊቀ ሥልጣናት አባ ገ/ዋህድ ገ/ኪዳን 2010 ዓ.ም ጀምሮ

ዓ.ም ጀምሮ